Saturday, 14 August 2021 10:57

አዲሱ የ”ህወኃት” እና የ”ኦነግ ሸኔ” ጥምረት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

   - የሁለቱ ቡድኖች ጥምረት አዲስ ነገር አይደለም - ቢሌኒ ስዩም (የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክረተርያት)
               - የሁለቱን ስምምነት የኦነግ ሸኔ ሠራዊት ታጣቂዎች እንኳን የሚያውቁት አይመስለኝም አቶ ቀጀላ መርዳሳ (የኦነግ ም/ሊቀመንበር)
                     
               የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የፈረጃቸው የህወኃት ኃይሎችና የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድኖች ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ መስማማታቸውንና ጥምረት መፍጠራቸውን  ማስታወቃቸውን ተከትሎ አነጋጋሪ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።  የኦነግ ም/ሊቀመንበር አቶ ቀጀላ መርደሳ፤ ሁለቱ ቡድኖች የፈጠሩት ጥምረት የኦሮሞን ህዝብ ፈፅሞ የማይመጥንና ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
የኦነግ ሸኔው መሪ ኩምሳ ድሪባ ለኦሶሴሽትድ ፕሬስ፣ የህወኃቱ መሪ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ደግሞ ለሮይተርስ በሰጡት መግለጫ፤ ሁለቱ ቡድኖች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መንግስት ለማፈራረስ ትብብር በመፍጠር አብረው ለመስራት መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህንን የሁለቱን ቡድኖች የትብበር ስምምነት የኦነግ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ቀጄላ መርዳሳ፤ “ሊታመን የማይችል፣የኦሮሞ ህዝብን የማይመጥንና ዘላቂነት የሌለው ከንቱ ጥምረት ነው” ብለውታል፡፡
አቶ ቀጄላ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ “ወያኔ በታሪክ እንደሚታወቀው ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር በጣም በተቃራኒ የቆመ፣ የኦሮሞን ወጣትና ህዝብ ሲገድልና ሲያሰቃይ የኖረ ድርጅት ሆኖ እያለ፣ አሁን ምን ተፈጥሮ ነው ለኦሮሞ ህዝብ አሳቢና ወዳጅ ሆኖ በጋራ ለመስራት የተስማማው?” ሲሉ ጠይቀዋል። ይህ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት እያለ የሚጠራውና በተለምዶ ´ኦነግ ሸኔ´ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ድርጅት፣ የኦሮሞ ህዝብ ታሪካዊ ጠላት ከሆነው ቡድን ጋር አብሮ ለመስራት የተስማማበት  አግባብ ምንድን ነው የሚለው ጉዳይ መመለስ የሚገባው ነው፡፡ ኦነግ ሸኔ አሁን ከህወኃት ቡድን ጋር አደረግሁት የሚለውን ስምምነት ሲያደርግ የኦሮሞን ህዝብ ያላማከረ በራሱ ፍላጎትና ውሳኔ ብቻ ያደረገው በመሆኑ የኦሮሞን ህዝብ ፈፅሞ የማይወክልና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል፤ ም/ሊቀመንበሩ።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሪ ኩምሳ ድሪባ ከህወኃት ጋር ጥምረት መፍጠራቸውን በይፋ ሲናገሩ የራሳቸውን ሰራዊት አባላት እንኳን ያማከሩ አይመስለኝም ይላሉ፤ አቶ ቀጀላ። በየሜዳው ያለው ሠራዊታቸውም ስለ ጥምረቱ የሚያውቅ አይመስለኝም ያሉት የኦነግ ም/ሊቀመንበሩ፤ ከዚህ ቀደምም ኩምሳ ድሪባ ከሌሎች አመራሮች ተደብቀው ውስጥ ውስጥ ከህወኃት ጋር በጥምረት መሰራቱ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ሲታሙ ነበር ብለዋል። ሁለቱ ቡድኖች ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በጋራ በድብቅ ሲሰሩ የቆዩትን ነገር አሁን ይፋ ከማድረጋቸው ውጭ ስምምነቱ አዲስ ነገር የለውም ብለዋል አቶ ቀጀላ፡፡
መንግስት በአሸባሪነት የፈረጃቸው ሁለቱ ቡድኖች በጋራ አብሮ ለመስራት መስማማታቸውን ይፋ ባደረጉበት በዚሁ መግለጫቸው፤  የኦነግ ሸኔ ቡድን መሪው ኩምሳ ድሪባ እንደተናገረው፤ “የጥምረቱ ጥያቄ ከህወኃት ቡድኖች መነሳቱንና አሁን ባለው ሁኔታ ብቸኛ መፍትሔው  ጥያቄውን ተቀብሎ ከህወኃት ቡድኖች ጋር በማበር፣ የኢትዮጵያ መንግስት በሚፈልገው ቋንቋ በማናገር በወታደራዊ ኃይል ከስልጣን ማስወገድ ብቻ ነው” ብሏል፡፡ በጋራ ጠላታችን ላይ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ተስማምተናል ያለው ኩምሳ ድሪባ፤ ይህም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንከር ያለ ጫና ያሳድራል የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቤለኔ ስዩም ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤  ሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች በጥምረት መስራታቸው አዲስ ነገር እንዳልሆነ ጠቁመው ቀደም ሲል እኒህ ቡድኖች አገር ለማፍረስ በጋራ እየሰሩ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር እንደነበር አውስተዋል። ሁለቱ ቡድኖች ጥምረታቸውን ይፋ ያደረጉበት ጊዜ ሊመረመር እንደሚገባው የተናገሩት ቢልለኔ፤ መንግስት ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን የህወኃትን አፍራሽ  ተልዕኮ አስፈጻሚ መሆኑን ሲገልጽ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ከህወኃት ቡድን ጋር በጋራ ይሰራል በሚል ከመንግስት በተደጋጋሚ የሚቀርብበትን ክስ ሲያስተባብል የከረመው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን መሪው ኩምሳ ድሪባ፤ ከህወኃት ጋር ቀደም ሲል ከነበረው ጠላትነት አንጻር የሚኖራቸው መተማመን ጥርጣሬ የተሞላው እንደሆነና በጋራ ጠላት ላይ ግን በጋራ ከመስራት የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግሯል።

Read 14074 times