Saturday, 14 August 2021 11:08

አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛዋን ወደ ኢትዮጵያ ልትልክ ነው

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(6 votes)

   ሁሉም ወገኖች በአስቸኳይ ወደ ድርድር እንዲመጡ ጥሪ ቀርቧል
                            
             የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በማድረግ ከወራት በፊት የሾማቸው ጄፈር ፌልትማን ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው። ነሐሴ 9 ቀን 2013 ዓ.ም የሚጀምረው የልዩ መልዕክተኛው ጉብኝት ኢትዮጵያን፣ ጅቡቲንና የተባበሩት አረብ ኢምሬትን  የሚያካትት ነው ተብሏል።
 ልዩ መልዕክተኛው ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት ያህል ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን ባለፈው ሚያዚያ  ወር ልዩ መልዕከተኛ ሆነው ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያ ጉዞአቸውን ያደረጉት ወደ ኢትዮጵያ ነበር። በግንቦት መጀመሪያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር የተወያዩት መልእክተኛው፤ የተረጋጋና የበለጸገ የአፍሪካ ቀንድ በትብብር መደገፍ በሚቻልበት  መንገድ ላይ ለመወያየት በሚል ሰበብ ሁለተኛውን ዘር ጉብኝታቸውን በማድረግ  ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ የሚወዛገቡበትን የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከነሐሴ 9 ቀን 2013 እስከ ነሃሴ 18 ቀን 2013 ለ10 ቀናት በሚዘልቀው የልዩ መልዕክተኛው ጉብኝት፤ በታጣቂ ቡድኖች መካከል እየተደረገ ስላለው ጦርነትና ሁለቱን ወገኖች ወደ ድርድር ለማምጣት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ ለመነጋገር መልዕክተኛው መላካቸውን የልዩ መልዕክተኛውን ጉብኝት ይፋ ያደረጉት የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ጸጥታ  አማካሪ ካድ ሱሉቫን ገልፀዋል።
አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት ከህውኃት ታጣቂ ቡድኖች ጋር እያካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆምና በትግራይ ክልል ላይ የተጣሉትን እገዳዎች ለማስነሳት በተለያዩ መንገዶች ጫና ለማሳደር ሙከራ እያደረገች ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ አሜሪካ የምታደርገውን ጫና በመቋቋም በፅኑ አቋም ቀጥሏል።

Read 13461 times