Saturday, 14 August 2021 11:38

ዓለም ፊቱን ያዞረባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ጥቅምት 24 ቀን 2013 በትግራይ በተቀሰቀሰውና ላለፉት 10 ወራት በዘለቀው ጦርነት፣ እስካሁን በተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት ጭምር በተረጋገጡ መረጃዎች፣ 2 ሺ ያህል ንጹኃን ዜጎች በህወኃት ሃይል ተገድለዋል፡፡
የአማራ ማንነት ጥያቄ ለዘመናት ሲነሳበት በነበረው ወልቃይት ጠገዴ በኩል በማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ሳምሪ በተባለው ቡድን ተፈጽሟል በተባለው የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ከ1 ሺህ 2 መቶ በላይ ሰዎች ስለመገደላቸው  የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን፤ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ጥናት ያደረገው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በተፈፀመው ዘር ተኮር የጅምላ ጥቃት 1600 ያህል ንጹኃን መገደላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
የፌደራል መንግስት የክረምት ጊዜ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አርሶ አደሩ ወደ እርሻ ተግባሩ እንዲገባ በማሰብ የተናጥል ተኩስ አቁም እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ ደግሞ ህወኃት መቀሌና ሌሎች የትግራይ አካባቢዎችን በተቆጣጠረበት አጋጣሚ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹኃንን “ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር አብራችኋል; በሚል እንደገደላቸው በትግራይ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ካወጧቸው መግለጫዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከሌሎች ገለልተኛ ወይም በሰብአዊ መብት ጥበቃና ክትትል ላይ ከሚሰሩ ተቋማት ማረጋገጫ ባይገኝም፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በመቀሌ ብቻ “ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ወግናችኋል” በሚል በህወኃት የተገደሉት ሰዎች 53 ያህል መሆናቸውን በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡
የፌደራል መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም እርምጃን ወደ ጎን በማለት ጦርነቱን የቀጠለው በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወኃት፤ በአፋር በኩል በከፈተው ጦርነት ደግሞ ጦርነቱን ሽሽት በአንድ ማዕከል በተጠለሉ 108 ያህል ህጻናትን ጨምሮ ከ240 በላይ ንፁሃን ላይ የጅምላ ግድያ መፈፀሙን አለማቀፍ ተቋማት ጭምር አረጋግጠዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫው፤ ግድያው እጅግ አሳዛኝና ሌሎች ተመሳሳይ ጥቃቶች ሊፈፀሙ እንደሚችሉም አመላካች መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በአጠቃላይ ህወኃት በራሱ መንገድ በጀመረው ጦርነት ባለፉት 10 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ2 ሺህ በላይ የንጹኃን ህይወት ጠፍቷል።
ከዚያ ቀደም  የፌደራል መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ ማጣሪያ መረጃ ማዕከል ባወጣው ሪፖርት፤ በምዕራብ ወለጋና በሌሎች አካባቢዎች በህወኃት አቀነባባሪነት 1500 ያህል ዜጎች በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መገደላቸውን ይፋ ማድረጉም አይዘነጋም፡፡
በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወኃት እነዚህን ሁሉ ድርጊቶች መፈጸሙን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና አለማቀፍ ተቋማት በየጊዜው ይፋ እያደረጉ ቢሆንም፣ አሁን ባለው ጦርነት የህወኃትን በደል አይቶ እንዳላየ በማለፍ ምዕራባውያን የጦርነቱን ሁሉ ሃጢያት በፌደራል መንግስቱ ላይ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የፌደራል መንግስቱም እውነታውን በተደጋጋሚ እያስረዳ ቢሆንም፣ እስካሁን ምዕራባውያን ሃገራት ጆሮ የሰጡት አይመስሉም።
በህወኃት ተንኳሽነት በተቀሰቀሰውና 10 ወራት ባስቆጠረው የትግራይ ጦርነት፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ይፋ ባደረገው ወቅታዊ መረጃው፤ በትግራይ ብቻ 2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ለእርዳታ ተዳርገዋል፤ ከ68 ሺህ የሚልቁት ደግሞ ድንበር አቋርጠው ወደ ሱዳን ተሰደዋል፡፡
በአጠቃላይ በህወኃት ቆስቋሽነት በተጀመረው ጦርነት፣ የትግራይ ህዝብ በእጅጉ ተጎሳቁላል። 5.2 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ በቀጥታ የሰው እጅ ጠባቂ እንዲሆን ተፈርዶበታል፡፡ አሁንም አርሶ አደሮች ተረጋግተው የእርሻ ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ ጦርነቱ እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ በርካቶቹ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች ቀጥተኛ የጦርነቱ ተሳታፊ መሆናቸውን ምርኮኞች ከሚሰጡት ቃል መረዳት ይቻላል፡፡
በትግራይ በአሁኑ ወቅት ወደ ትምህርት ቤት የሚላክ ህፃን የለም፡፡ ት/ቤቶች ተዘግተዋል፣ ዩኒቨርሲቲዎች ተከርችመዋል። የትግራይ አዲስ ትውልድ እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ራሱን በእውቀት እንዳያበቃ የተፈረደበት ይመስላል፡፡ በዚህ ትርጉም አልባ ጦርነት የትግራይ ህጻናትና ታዳጊዎች ተስፋ መክኗል፡፡ የትውልዱ ስነ ልቦና እንዲላሽቅ ተደርጓል።
የዚህ ጦርነት ዳፋ በትግራይ ብቻ አያበቃም፡፡ እንደ ሃገር በኢኮኖሚው ላይ  እያሳደረ ያለው ተጽዕኖም ቀላል አይደለም። መንግስት በ8 ወራት ጊዜ  ውስጥ የጦርነት ወጪውን ሳይጨምር በሰብአዊ ድጋፍና ትግራይን መልሶ ለመገንባት ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ፈሰስ ማድረጉን መግለፁ አይዘነጋም፡፡
መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም ባደረገበት ሁኔታ ጦርነቱን የቀጠለው ህወኃት፤ በአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች በፈጸመው ወረራም  በመቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል፡፡ እንደ ክልል መንግስታቱ ሪፖርት ከሆነ፤ በአፋር ከ3 መቶ ሺህ በላይ ዜጎች የህወኃትን ጥቃት ሽሽት ሲፈናቀሉ፤ በአማራ ክልል በተመሳሳይ ከ250 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቅለዋል፡፡
ትግራይን ጨምሮ በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወኃት ተቆጣጥሯቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች የመብራት፣ የስልክና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንደ ልብ እየተሟላላቸው አለመሆኑም የበርካቶችን ህይወት አናግቷል፤ የሚሊዮኖችን ተስፋ ነጥቋል፡፡
ህወኃት እንደ አዲስ ጦርነት ከፍቶ በተቆጣጠራቸው የራያና የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ዜጎች ቀለብ አስፈጭተው እንዳይበሉ እንኳን የኤሌክትሪክ ሃይል አለመኖሩ እንቅፋት እንደሆነባቸውና በርካቶች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ከየአካባቢዎቹ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ህወኃት ሁሉንም ነገር ለጦርነት በሚል አባዜው፣ ከገበሬው ጎሮሮ እየነጠቀ ጦሩንም እያጠናከረበት እንደሆነ ይነገራል፡፡
መንግስት እንኳን ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በ8 ወራት ውስጥ 100 ቢሊዮን ብር ወጪ ከማድረጉ ባለፈ፣ የተናጥል ተኩስ አቁሙን ከማድረጉ በፊት 4 መቶ ሺህ ኩንታል የእርዳታ እህል፣ 2.5 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ፣ 536 ሺህ 979 ኩንታል ማዳበሪያ፣ 37 ሺህ 599 ኩንታል ምርጥ ዘር ለህዝቡ ደህንነት ሲባል አስቀምጦ መውጣቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም 1079 ሜትሪክ ቶን ምግብ፣664 ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች፣ 47 ሺህ 740 ሊትር ነዳጅ በአለማቀፍ ተቋማት በኩል  ከተኩስ አቁሙ በኋላ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
እነዚህ ሁሉ ለህዝቡ የቀረቡ የነፍስ ማቆያ ግብአቶች አሁን ላይ ለምን አላማ እየዋሉ ነው? የእርዳታ እህል በረሃብ አደጋ ላይ ላለው የትግራይ ህዝብ በትክክል እየደረሰ ነው? በክልሉ የሰብአዊ መብት አያያዝ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ለዚህ ሁሉ ምላሽ የሚገኘው ጦርነቱ ሲቆም ብቻ ነው፡፡
ይህ ፈርጀ ብዙ የሰብአዊ ውድመት እያደረሰ የሚገኘው ጦርነት መቼ እንደሚቋጭ ደግሞ ለጊዜው ማንም የሚያውቅ አይመስልም፡፡Read 3149 times