Saturday, 14 August 2021 11:50

መልካም ተመሪ ከመሆን መልካም መሪ ለመሆን ተጣጣር

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ ሶስት ጠቢባን አማካሪዎቻቸውን ይጠሩና ጥያቄ ይጠይቋቸዋል።
መሠረታዊ ጥያቄው፡-
አንድ ሰፊ እልፍኝ ዘንድ ወሰዷቸውና፤
“በጣም በርካሽ ዋጋ የሚገዛ፣ ሆኖም ይህንን እልፍኝ ከአዳራሽ የሚሞላ ነገር አምጡልኝ” አሏቸው።
የመጀመሪያው ጠቢብ፤
“ንጉሥ ሆይ! ይህን እልፍኝ የሚሞላ አምጥቻለሁ”
ንጉሡም፤
“መልካም፣ አሳየና?” አሉና ጠየቁት።
ጠቢቡም ያንን እልፍኝ የሚሞላ ጥጥ አቀረበና እልፍኙን ሞልቶ ለማሳየት ሞከረ። ንጉሡ ነጥብ ይዘው ተቀምጠዋል። ቀጥለው ንጉሡ ሁለተኛውን ጠቢብ ጠሩና፤
“ያንተን መወዳደሪያ አቅርብልና?” አሉት።
ተወዳዳሪው ጠቢብም፤
“ንጉሥ ሆይ፤ እነዚህን ጆንያዎች አምጥቻለሁ” አለና በብዙ ጆንያዎች የተሞላ አሸዋ ይዞ ቀረበ። አሸዋው ግን ከነጆንያው ሙሉ ሆኖ ቀረበ እንጂ ብቻውን እንዲወጣ ሲደረግ እልፍኙን ሊሞላ አልቻለም።
በመጨረሻው ንጉሡ ሦስተኛውን ጠቢብ ጠሩና፤
“አንተስ እልፍኙን የሚሞላ ምን ነገር ታቀርብልናለህ?” ሲሉ ጠየቁት።
ጠቢቡም የሚያስገርም ጥበብ ይዞ ቀረበ።
ይኸውም አንዲት ሻማና ክብሪት ነው።
ክብሪቱ ተጫረ። ተለኮሰና ሻማው በራ። እልፍኙ በብርሃን ሞላ።
ሶስተኛው ጠቢብ አሸናፊ ሆኖ ሽልማቱን ተቀበለ።
ንጉሡም እንዲህ ያለ ጠቢብ ስለሰጣቸው አምላካቸውን አመሰገኑ።
*   *   *
በጥበበኞች የታደለች አገር ከአገሮች ሁሉ ለብልፅግና የቀረበች ናት። መታደሏን ግን ህዝቧ ካላወቀ እርባና ላለው ሥልጣኔ አትመቻችም። ለዚህ ኃላፊነት ወጣቷን፣ ሴቶቿን፣ ምሁራኗን፣ ሊቃውንቷን ማበረታታት፣ የዕድገት መንገዶቿን ሁሉ መጥረግ ዋና ትኩረቷ ሊሆን ይገባዋል። ይህን ለማድረግ ግን አስቀድሞ ህዝቧን በአካልም በመንፈስም ማዘጋጀት ዋና ጉዳይዋ መሆን አለበት። የልጆቿ ያዋቂዎቿና የአዛውንቶቿ ጤና፣ ትምህርት፣ መልካም አስተዳደር ሊጤን ይገባዋል። ሥልጣኔ የሚታይ እንጂ የማይበላ ፍሬ ሆኖ ከቆየ  ሰነባብቷል። የማይበላውን ፍሬ አብስሎ የሚበላ ፍሬ ለማድረግ ታታሪነት፣ ልዩ ጥረት፣ ወቅታዊነትና ወቅት አልባነት (Timeliness and Timelessness) ሊኖር ይገባል።
አንድም ደግሞ በዕቅድ ላይ የተመሰረተ የሥራና የኑሮ ሂደትን ሳይታክቱ በማበረታታት ዕድገትን የማጎልበትን ክህሎት ማፍካት የህዝባችን በመላ ልዩ ኩራት እንዲሆን መታገል ልዩ ዒላማና ዓላማ ይሆን ዘንድ ዐይናችንን ሙሉ በሙሉ ከፍተን መንገዳችንን በንቃት ፀዳል እናብራ።
በፀጋዬ ገ/መድህን (ሎሬት) ትርጓሜ የሼክስፒርን ማክቤዝ የመጨረሻ ሰዓት እንዲህ ብሎ እንዳቀረበው እንይ። ሁለቱንም የሎሬት ፀጋዬን የትርጉም ብቃትም ለማሳየት ስንል አቅርበነዋል።
“--Tomorrow and tomorrow and tomorrow
 creeps in this Pety  Pace to the last syllables
Of the recorded times
And all our yesterdays have lighted fools the way to dusty death.
Out! Out! Brief Candle,
life is but a walking shadow
 a poor player, that struts and frets
His our upon the stage and is heard no more.
It is a tale told by an idiot
 full of sound and fury signifying nothing!”
“የነገ ውሎ፣ የነገ ውሎ፣ የነገ ውሎ”
ከቀን ወደ ቀን ይሳባል፣ በዕድሜ ንፉግ ጀርባ ታዝሎ
ትላንትናም ከትላንት በስቲያም፣ ለጅሎች ጥርጊያ አሳምሮ
ዛሬ ፈጥሮ ነገ ቀብሮ
እፍ አንቺ ብርሃን ጨልሚ አንቺ የህይወት ጭላንጭል
 የምትንቀሳቀሺው ጥላ የሰው ህይወት የሰው ዕድል
እንደ አልባሌ ተዋናይ
ተታትሮ ተፍጨርጭሮ ተውተርትሮ መድረኩ ላይ
 ለብልጭታ ብቻ እሚታይ
ጅል የሞኞች ተረት ነሽ
ቋሚ ትርጉም የሌለብሽ።”
ኑሯችን ለብልጭታ ብቻ የምንኖረው መሆን የለበትም። ቋሚና ዘላቂ ትርጉም ያለው እንጂ፡፡ ያ እንዲሆን ደግሞ ሥር-ነቀል አካሄድ፣ ደርዝ ያለው ለውጥ እና ያልተሸራረፈ ጉዞን መራመድ ያስፈልጋል።
ሀገራችን የመሪና የተመሪ ስብጥርና ልኬት እንዲኖራት አስፈላጊ ከሆኑት ግብዓቶች አንዱ የበሰለና አስተዋይ መሪ ለመሆን የሚጣጣሩ ልጆች ማፍራትዋ ነው። ለመሪነት በሚጣጣሩ ጊዜ ተመሪነትን ማወቅ አይቀሬ ነውና! ለዚህም ነው “መልካም  ተመሪ ከመሆን መልካም መሪ ለመሆን ተጣጣር” የሚባለው።

Read 14319 times