Print this page
Saturday, 14 August 2021 12:06

የሻምበል ምሩፅ ድርብ ድል በቀነኒሳና ጥሩነሽ የተደገመበት

Written by  ግሪም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  29ኛው ኦሎምፒያድ ቤጂንግ 2008 እኤአ ቻይና በዋና ከተማዋ ቤጂንግ ያስተናገደችው 29ኛው ኦሎምፒያድ 40 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ስለሆነበት በታሪክ ውዱ ኦሎምፒክ ነበር፡፡ በወቅቱ 86 አገራት በሜዳልያ ሰንጠረዥ ከመግባታቸውም በላይ በተለያዩ የውድድር መደቦች 43 የዓለም ሪኮርዶች እንዲሁም 132 የኦሎምፒክ ሪከርዶች መመዝገባቸውም ልዩ ታሪክ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡
ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድንም  29ኛው ኦሎምፒያድ  አዲስ ክስተት የተፈጠረበት ነበር፡፡ ምሩፅ ይፍጠር በሞስኮ ኦሎምፒክ ካስመዘገበው ታሪክ 28 ዓመታት በኋላ በ5ሺ እና በ10ሺ ውድድሮች ድርብ ድል በማስመዝገብ ቀነኒሳ እና ጥሩነሽ ክብረወሰኑን ተጋርተዋል፡፡ በሁለቱ አትሌቶች ፍፁም የበላይነት የተገኙት እነዚህ የረጅም ርቀት አራት የወርቅ ሜዳልያዎች ከሲድኒ ኦሎምፒክ በኋላ ትልቁ ውጤት ቤጂንግ ላይ መመዝገቡም የሚጠቀስ ነው፡፡ በ10ሺ ሜትር ወንዶች ስለሺ ስህን እንዲሁም በ5ሺ ሜትር ሴቶች መሰረት ደፋር የብር ሜዳልያዎችን ሲጎናፀፉ፤ ጸጋዬ ከበደ በወንዶች ማራቶን የነሐስ ሜዳልያውን ለማግኘት በቅቷል፡፡
ቤጂንግ ባስተናገደችው 29ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል 27 ኦሎምፒያኖች በአትሌቲክስ ውድድሮች ብቻ ተሳትፈዋል፡፡ የ15ዐዐ ሜትር አሠልጣኝ ሆነው የተጓዙት ዶ/ር ይልማ በርታ ሲሆኑ የ3ዐዐ0 ሜትር መሰናክል አሰልጣኝ ሻምበል ዮሃንስ መሐመድ ተሳትፈዋል፡፡
በ1500 ሜትር ወንዶች ደሜ ዳባ እና ሙሉጌታ ወንድሙ ለግማሽ ፍጻሜ ሲደርሱ ደረሰ መኮንን በመጀመርያው ማጣርያ ተሳትፎው ተወስኗል፡፡ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ሮባ ጋሪ፤ ያቆብ ጃርሶና ናሆም መስፍን በማጣርያ ውድድሮች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በ5ሺ ሜትር ላይ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ ሜዳልያውን ሲጎናፀፍ አብርሃም ጨርቆሴ እና ታሪኩ በቀለ 5 እና 6ኛ ደረጃን አግኝተዋል፡፡ በ10ሺ ሜትር ቀነኒሳ በቀለ ሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያውን ቤጂንግ ላይ የተጎናፀፈው እስካሁን የኦሎምፒክ ሪከርድ ሆኖ የሚገኘውን 27፣01.17 በማስመዝገብ ነበር፡፡ ስለሺ ስህን የብር ሜዳልያውን የወሰደ ሲሆን እንዲሁም ኃይሌ ገብረስላሴ 6ኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ በማራቶን ውድድር ፀጋዬ ከበደ በሶስተኛ ደረጃ የነሐስ ሜዳልያውን ሲጎናፀፍ ድሪባ መርጋ 4ኛ እንዲሁም ጋሻው አስፋው 7ኛ ደረጃን በመያዝ ጨርሰዋል፡፡
በሴቶች 1500 ሜትር ገለቴ ቡርቃና መስከረም አሰፋ በማጣርያ ውድድሮች ላይ ሲሳተፉ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ላይ ዘምዘም አህመድ በፍፃሜው ውድድር 7ኛ ደረጃ ስታገኝ ሶፊያ አሰፋ እና መቅደስ በቀለ ተሳትፏቸው በማጣርያ ተወስኗል፡፡ ከፍተኛ የቡድን ስራ እና የርስ በእርስ ፉክክር በታየበት የሴቶች 5ሺ ሜትር ውድድር ላይ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ ሜዳልያውን ስትወስድ መሰረት ደፋር በሁለተኛ ደረጃ የብር ሜዳልያ እንዲሁም መሰለች መልካሙ 8ኛ ደረጃን ማግኘት ችለዋል፡፡ በ10ሺ ሜትር ደግሞ ጥሩነሽ ዲባባ 29፡54.66 በሆነ ሰዓት የወቅቱን ኦሎምፒክ ሪከርድ አስመዝግባ የወርቅ ሜዳልያውን በመውሰድ በኦሎምፒክ ታሪክ ድርብ የወርቅ ሜዳልያ ያሸነፈች የኢትዮጵያ ኦሎምፒያን ሆናለች፡፡ ታላቅ እህቷ እጅጋየሁ ዲባባ 14ኛ ደረጃን ይዛ ስትጨርስ መስታወት ቱፋ ውድድሯን ማቋረጧ ተመዝግቧል፡፡ በማራቶን ውድድር ላይ ድሬ ቱኔ 15ኛ ደረጃን ስታገኝ ብርሃኔ አደሬ እና ጌጤ ዋሚ ውድድሩን ሳይጨርሱ ቀርተዋል፡፡


Read 1319 times