Monday, 16 August 2021 00:00

ከኃይሌና ደራርቱ በኋላ አዲስ የኦሎምፒክ ትውልድ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   28ኛው ኦሎምፒያድ አቴንስ 2004 እኤአ በ1896 እኤአ ላይ 1ኛውን ኦሎምፒያድ ያስተናገደችው ግሪክ በ2004 እኤአ ላይ በአቴንስ ከተማ 28ኛውን ኦሎምፒያድ አዘጋጅታለች፡፡  የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን  በሁለት የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ እና በቦክስ  26 ኦሎምፒያኖች የነበነሩበት ነው፡፡
በረጅም ርቀት የኢትዮጵያ የበላይነት የተስተዋለበት እንዲሁም ከኃይሌ እና ከደራርቱ በኋላ አዲስ የኦሎምፒክ ትውልድ የተፈጠረበት ነው፡፡ በዚህ ኦሎምፒክ በአዳዲስ የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ጀግኖች 2 የወርቅ ፤3 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች ለኢትዮጵያ ተገኝተዋል፡፡ በወንዶች 10ሺ ሜትር ቀነኒሳ በቀለ እንዲሁም በሴቶች 5ሺ ሜትር መሰረት ደፋር ሁለቱን የወርቅ ሜዳልያዎች ተጎናፅፈዋል፡፡  3 የብር ሜዳልያዎች የተገኙት በወንዶች 5ሺ ሜትር በቀነኒሳ በቀለ ፤ በወንዶች 10ሺ ሜትር በስለሺ ስህን እና በሴቶች 10ሺ ሜትር በእጅጋየሁ ዲባባ  ሲሆን፤ በ5ሺ ሴቶች ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ እና በ10ሺ ሜትር ሴቶች ደራርቱ ቱሉ የነሐስ ሜዳልያዎችን አሸንፈዋል፡፡
በወንዶች የመካከለኛ ርቀት የኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ በ1500 ሜትር  ሙሉጌታ ወንድሙ ለፍፃሜው በመድረስ 10ኛ ደረጃ ሲያገኝ በ800 ሜትር ብርሃኑ አለሙ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ተወዳድሯል፡፡ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ቴዎድሮስ ሽፈራውና ሉልሰገድ ዋለ ተሳትፏቸው እስከ ግማሽ ፍፃሜ ሆኗል፡፡ በወንዶች 5ሺ ሜትር ላይ የመጀመርያውን የኦሎምፒክ ተሳትፎ ያደረገው ቀነኒሳ በቀለ የብር ሜዳልያውን በተጎናፀፈበት ውድድር አስገራሚ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የቡድን ታክቲክ ተዋውቋል፡፡ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም 4ኛ ደረጃን ደጀኔ ብርሃኑ 5ኛ ደረጃን ሊያገኙም ችለዋል፡፡ በ10ሺ ሜትር ወንዶች ላይ የኢትዮጵያ ሯጮች ልዩ የቡድን ስራን ዓለም በገሃድ የተመለከተበት ነው፡፡ ቀነኒሳ፤ ስለሺ እና ኃይሌ በኦሎምፒክ ትራክ ላይ አረንጓዴው ጎርፍ የተባለውን የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተከታትሎ እና ተያይዞ የመግባት ብቃት በማይረሳ ትእይንት ሊፈፅሙ በቅተዋል፡፡ ቀነኒሳ በቀለ 25፡05.10 በሆነ ሰዓት አዲስ የኦሎምፒክ ሪከርድ አስመዝግቦ የ10ሺ ሜትርን ክብር ከኃይሌ ሲረከብ፤ ስለሺ ስህን በሁለተኛ ደረጃ የብር ሜዳልያንውን ሊወስድ በቅቷል፡፡ በሁለት ተከታታይ ኦሎምፒኮች ባስመገባቸው ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ከፍተኛ ስም ያተረፈው  ኃይሌ ገብረስላሴ በ5ኛ ደረጃ ለመጨረስ ችሏል፡፡ በወንዶች ማራቶን ከተሳተፉት ኦሎምፒያኖች አምበሴ ቶሎሳ 15ኛ እና ደረጄ ወዳጆ 46ኛ ደረጃን ሲያስመዘግቡ ሃይሉ ንጉሴ ውድድሩን ሳይጨርስ ቀርቷል፡፡
በሴቶች 1500 ሜትር የተሳተፉት መስታወት ታደሰ እና መስከረም ለገሰ በማጣርያው የመጀመርያው ዙር  ከውድድሩ ሲወጡ ከባርሴሎና ኦሎምፒክ ጀምሮ  ልምድ ያላት ቁጥሬ ዱለቻ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ተሳትፋለች፡፡ በሴቶች 5ሺ ሜትር ላይ ከጌጤ ዋሚ ፈርቀዳጅ ውጤቶች በኋላ ለኢትዮጵያ አዲስና ከፍተኛ ውጤት የወርቅ ሜዳልያውን በመውሰድ ያስመዘገበችው መሰረት ደፋር ናት፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ የነሐስ ሜዳልያውን ስታገኝ ስንታየሁ እጅጉ 10ኛ ደረጃ ላይ ጨርሳለች፡፡ በ10ሺ ሜትር ደግሞ እጅጋየሁ ዲባባ በሁለተኛ ደረጃ ደራርቱ ቱሉ በሶስተኛ ደረጃ የብርና የነሐስ ሜዳልያቸውን ሲወስዱ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ4ኛ ደረጃ ዲፕሎማዋን ተቀዳጅታለች፡፡ በሴቶች ማራቶን ውድድር ላይ እልፍነሽ አለሙ በ4ኛ ደረጃ የዲፕሎማ ክብሯን ስትወስድ አይሻ ጊጊ እና ወርቅነሽ ቶላ ውድድራቸውን ሳይጨርሱ ቀርተዋል፡፡ በ2004 የአቴንስ ኦሎምፒክ ከአትሌቲክስ ባሻገር በቦክስ ውድድሮችም ኢትዮጵያ ተሳትፋለች፡፡ እንዳልካቸው ከበደ በቀላል ሚዛን በመጀመርያ ዙር ማጣርያው ላይ የጃፓኑን ኢጋራሺ በማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ካለፈ በኋላ በቻይናው ዞው ሴም ተሸንፎ ከውድድር ውጭ ሲሆን አቤል አፈረልኝ ደግሞ በባንተም ዌይት በመጀመርያ ዙር በቡልጋርያው ዳላኪሌቭ ተሸንፏል፡፡

Read 1235 times