Tuesday, 17 August 2021 00:00

የጠላትን ማንነት አብጠርጥሮ ማወቅ ያስፈልጋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ኢትዮጵያ እስከ 1966 ዓ.ም ማብቂያ ድረስ ባላባታዊ ስርዓት የምትከተል፣ በንጉሠ ነገሥት የምትመራ አገር ነበረች። በዘውዱ አገዛዝ ስር የምትገኘውን ኢትዮጵያ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረው ዋለልኝ መኮንን “የብሔረሰቦች ጥያቄ” በሚል ርዕስ ባቀረበው ጽሑፍ፤ “የብሔረሰቦች እስር ቤት” ሲል ፈረጃት። ከዚህ ፍረጃ በመነሳትም በብሔረሰባችን ላይ ጭቆና ደርሶበታል ያሉ አንዳንድ ወጣቶች፣ የየብሔረሰባቸውን የነጻነት ንቅናቄ ወይም ግንባር መሰረቱ። የሁሉም ንቅናቄዎች ወይም ግንባሮች አላማና ግብ፣ አለብን የሚሉትን ጭቆና ማስወገድና ኢትዮጵያን የእኩልነት አገር አድርጎ ማስቀጠል ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን በማፍረስ የየራሳቸውን ነፃ አገር መመሥረት እንዲሆን ተደርጎ ተቀረፀ።
ነፃነቱን የነፈጋቸው ፊውዳላዊውና ዘውዳዊው መንግሥት ነው ብለው በተቀበሉበት መጠን፣ ዘውዳዊውን መንግሥት፣ የአማራ መንግሥት አድርገው በመውሰዳቸው፣ አማራ ነፃነት ሰጪ እነሱ ነጻነት ተቀባይ ሆኑ። አማርኛ ቋንቋው ለአገር አቀፍ መግባቢያ በመሆን ከማገልገሉ በቀር የተለየ ልማትና እድገት ያላገኘው አማራ፣ በሌላው ሃብት እንደለማ ተደርጎ እስከ መታሰብም ተደረሰ።
የአጼ ኃይለስላሴ መንግስት ወድቆ የደርግ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ የፊውዳላዊው መንግስት የኢኮኖሚ መሰረት የነበረው መሬት፣ በየካቲት 1967 ዓ.ም “የመሬት ላራሹ” አዋጁ ከታወጀና  መሬት የሕዝብ ከሆነ፣ ጭሰኝነት ከቀረ፣ ፊውዳሊዝም እንደ ሥርዓት ከፈረሰ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በግልጽ መለወጡ የማይታይ ቢሆንም፣ የነጻነት ንቅናቄዎቹ ግን ከተለወጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር የተለወጠ የፖለቲካ አላማና ግብ መስራት አልቻሉም። የደርግ 17 ዓመት፣ የኢሕአዴግ 27 ዓመት፣ በድምሩ 44 ዓመት ያህል ጊዜ የነጎደ ቢሆንም፣ ነጻ አውጪ ነን ብለው እራሳቸውን የሰየሙ ወገኖች ዘንድ ግን ዛሬም በኢትዮጵያ መንግስታዊ ስልጣን ላይ ያለው “የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት” ሆኖ ነው የሚታያቸው። ስለዚህም ነው ዛሬም ድረስ ከአርባ ዓመት በፊት ባነሱት ጥያቄ ላይ እንደቆሙ የቀሩት። ለዚህም ነው አማራ በኢትዮጵያ መንግስታዊ ሥልጣን ላይ ባይኖርም፣ በነገራቸው  ሁሉ ፀረ አማራ ሆነው የቀጠሉት። በዚህ በኩል ደግሞ አሸባሪውን ትህነግን የሚያህልና  የሚወዳደር ድርጅት የለም።
ትህሕነግ ለአማራ ነፍጠኛ የሚል ስም በመስጠት በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔረሰቦች ጠላት አድርገው እንዲቆጥሩት አድርጎት እንደነበርም አይዘነጋም። ከክልሉ ወጪ ያለው አማራ ነፍጠኛ፣ በክልሉ ውስጥ የሚገኘው ደግሞ ትምክህተኛ እየተባለ በትሕነግ/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን፣ በአማራው ላይ የደረሰው በደል እጅግ ብዙ ነው። እሱን ከመዘርዘር ለታሪክ መተዉ የተሻለ ነው። ለዚያም ቢሆን ለማወቅ እንጂ ቂም ለመቋጠር እንዳይሆን አጥብቆ ማሳሰብ ያስፈልጋል። በቀል በበቀል አይሻርም፣ በይቅርታ እንጂ።
ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም መጋቢት ድረስ በዘለቀው የሕዝብ አመጻ ወንበሩ የተነቀነቀው ትህነግ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር  ዐቢይ አሕመድ መንግስት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ጓዙን ጠቅልሎ መቀሌ ለመግባት ተገድዷል። ወደ መቀሌ የሄደው ክልሉን ለማልማት ሳይሆን ለጦርነት ዝግጅት ለማድረግ ነበር፡፡
የአገሪቱ የመከላከያ ሰባ በመቶ የሚሆነውን ኃይል በትግራይ ክልል ውስጥ እንዲሰፍር መደረጉ፣ የደህንነቱንና መገናኛውን ወዘተ ማዕከል ወደ መቀሌ መሻገሩ፣ ይኸና ይህን የመሰለው ተግባሩ ሁሉ ሲታይ፣ ትሕነግ ለአንድ ዓይት ፍልሚያ እራሱን ሲያዘጋጅ የነበረው ከአዲስ አበባ እግሩን ከመንቀሉ ብዙ ዓመታት ቀደም ብሎ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ላይ ጥቃት የከፈተውና ጦርነቱን የጀመረውም ከእጄ የሚወጣ ወይም የሚያመልጥ ነገር የለም ከሚል እምነት ተነስቶ እንደሆነም እርግጥ ነው።
በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ያለ የሌለ ትጥቁ ወድሟል፤ ከሞትና ከምርኮ የተረፈው አመራሩም  በተምቤን በረሃ እንደ ዝንጀሮ ገደል ለገደል እየተንከራተተ ነው የተባለው ትሕነግ፤ ከስምንት ወር በኋላ እንዴትና እንደምን ወደ አጥቂነት ተሻጋገረ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
የአማራና አፋር ክልሎች የትግራይ ተጎራባች በመሆናቸው የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡ ትሕነግ ከትግራይ ድንበር ብዙ ርቀት ተጉዞ  አፋርና አማራ ክልል እስኪገባ ድረስ ምን እየተጠበቀ ነበር? ማለትም ግድ ይሆናል።  
ወደ ኋላ እንመለስ፡፡ ደርግ መቀሌን ለቆ ከወጣ በኋላ የትሕነግ ሰራዊት፣ “የትግራይ ድንበር አልውኃ ነው ብላችሁናል። ከዚህ በኋላ አንዋጋም። ሌላው ብሔር ብሔረሰብ ነፃነቱን ከፈለገው ራሱ ተዋግቶ ነፃነቱን በራሱ ያምጣ” በማለት አቋም ወስዶ እንደነበር ይታወቃል። ወደ አማራ ክልልና ወደ ሌላው አካባቢም የተንቀሳቀሰው ከብዙ ጊዜ  የፖለቲካ ሥራ በኋላ ነው። አማራ ክልል ከገባ በኋላ ደግሞ የተዋጋው ደርግን ይጠላ የነበረውንም ያልነበረውንም አማራ፣ በውድም በግድም  በፊት መስመር በማሰለፍ ነው።
ደርግ ትግራይን ለቆ ለትህነግ የመደራጃ ጊዜ መስጠቱና ትህነግ አማራ ክልል መግባቱ በአማራ ጉልበትና ህይወት ደርግን ለመውጋት ተጠቅሞበታል። ዛሬም ተመሳሳይ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ትህነግ በገባበት የአማራ ክልል የሚገኘውን ወጣትና  መሳሪያ ለመሸከም አቅም ያለውን የከበበውን ሰው እያስገደደ፣ ወደ ጦርነት የሚማግድበት ሁኔታ እየተፈጠረለት ነው።
የመጀመሪያው እርምጃ የትህነግን እንቅስቃሴ ወደ ኋላ መመለስ፣ እሱም ካልተቻለ ባለበት እንዲቆም ማድረግ ነው። ወደ ማሰልጠኛ እየገባ ያለውን የሰው ኃይል የእግረኛ ሰልፍ ማስተማሩ ቀርቶ ግዳጁን ለመፈጸም የሚያስችለው ስልጠና መስጠት ነው።
ሁለተኛው ልዩ ልዩ በራሪ ወረቀቶች በማዘጋጀት የትህነግ ጦር እጁን ለመከላከያ እንዲሰጥ ማግባባት ነው። በዚህ መንገድ የአንድ ሰው ልብ ማሸነፍ ከተቻለ እንደ ትልቅ ግብ መታየትም ይኖርበታል። ከሁሉ በላይ ግን የፌደራል መንግስትም ሆነ የክልል መንግሥታት እየተፋለሙት ያለውን ጠላት ማለትም፣ ትሕነግን አበጥረው አንጠርጥረው ማወቃቸው ወሳኝ ነው፡፡ ትሕነግን ድል ለመምታት አስፈላጊና ቀዳሚ ግብዓት ነውና።


Read 9087 times