Monday, 16 August 2021 00:00

ልብ ሰባሪው የልጆች ሰቆቃ

Written by  ብርሃኑ በላቸው አሰፋ
Rate this item
(2 votes)

  ዩኒሴፍ ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ በመላው አለም ከስምንት ልጆች መካከል አንዱ ለፆታዊ ጥቃት ይጋለጣል፡፡ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ክልል ውስጥ ከሚገኙ 20 ሴት ልጆች መካከል አንዷ ደግሞ አስገድዶ መድፈር ይፈጸምባታል።  ምንም እንኳን ጥቃቱ ጾታን የሚለይ ባይሆንም፣ ከሁለት እስከ ሶስት እጥፍ ጥቃት የሚደርሰው በሴቶች ላይ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡  
ማንኛውም ሰው ልጆችን በማታለል ወይንም በማስገደድ ለፍላጎት ማርኪያ ሲጠቀምባቸው ወሲባዊ ጥቃት ይባላል፡፡ ይህ ጥቃት ሃይልን በመጠቀም ያለ ፍላጎት የሚፈጸም ማንኛውንም የወሲብ ድርጊትና ትንኮሳን ያጠቃልላል፡፡ ለምሳሌ፡- አስገድዶ መድፈር፣ የወሲብ ንግድ፣ ፆታዊ ትንኮሳ፣ ግብረሰዶምና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
እጅግ ልብ የሚሰብረው ደግሞ በልጆች ላይ ጾታዊ ጥቃት በአብዛኛው የሚያደርሱት የቅርብ ሰዎች መሆናቸው ነው፡፡ የቤተሰብ አባላት፣ ጎረቤት፣ ጓደኛና ወዳጆች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎች  ብዙውን ጊዜ ያላቸውን እምነትና ቅርበት ተገን በማድረግ ነው፣ የልጆችን ህይወት ገና በማለዳው የሚያጨልሙት፡፡  
በልጆች ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ ጥቃት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ይዞ ይመጣል፡፡ ከእነርሱም  መካከል አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊና የጤና ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ሁኔታውን ይበልጥ የሚያወሳስበው ደግሞ ይህን ከባድ ችግር ልጆች የመከላከልም ሆነ የመቋቋም አቅም የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡  
ጾታዊ ጥቃት አንዱ መገለጫው አካላዊ ጥቃት ሲሆን በማንኛውም መንገድ በአካል ላይ የሚፈፀም የሃይል ጥቃት ነው። ይህም በእጅ መምታትን፣ መገፍተርን፣ በእርግጫ ማለትን፣ በዱላ መምታትን፣ በጥፍር መቧጨርን፣ ጸጉር መንጨትን ያጠቃልላል።
ጥቃቱ አካላዊ ጥንካሬ የሌላቸው ልጆችን፣ በቀላሉ ለመቁሰል ለመድማትና ራሳቸውን እስከ መሳት ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡ ለጤና መታወክም ይዳረጋሉ፡፡ ለተላላፊ በሽታዎች፣ ላልታሰበ እርግዝና፣ እንዲሁም ለተለያዩ የሥነተዋልዶ  ጤና ችግሮችም ይጋለጣሉ፡፡
ጥቃቱ በተጨማሪም፤ ለደም መፍሰስ አደጋ፣ ለኢንፌክሽን፣ ለኤችአይቪ እና ሌሎች ከወሊድ ጋር ለተያያዙና  እስከ ሞት ለሚያደርሱ አደጋዎች ይዳርጋቸዋል። ጥቃት የደረሰባቸው ልጆች በቂ ክትትልና ድጋፍ ካልተደረገላቸው  እንግዳ የሆነ ባህርይ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ከችግራቸው ለመሸሽም በሱስና መጠጥ ውስጥ ሊሸሸጉ ይችላሉ፡፡
ዋናው ጉዳት ሳያንሳቸው ማህበረሰቡ ጥቃት በደረሰባቸው ልጆች ላይ የሚፈጽመው የማግለልና መጠቋቆሚያ የማድረግ ሁኔታ ልጆቹን ለሌላ የሥነልቦና ቀውስ ያጋልጣቸዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ለፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ቅዠት፣ ፀፀት፣ ራስን ማግለል፣ ብቸኝነት፣ ብሶት፣ አለመረጋጋትና በራስ ያለመተማመን ይዳረጋሉ፡፡
እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ አጥቂዎችም ይህንን የማህበረሰብ አመለካከት ስለሚያውቁ  “አጋልጥሻለሁ/ሃለሁ” “ትዋረጃለሽ/ዳለህ” እና ሌሎች ማስፈራሪያዎችን በመሰንዘር፣ ምንም ያላጠፉትን ልጆች ያሸማቅቋቸዋል።  በዚህም ሳቢያ አንገታቸውን ለመድፋት ይገደዳሉ፡፡
በዚህ ክፉ ወቅት ለልጆች በቀዳሚነት ሊደርስ የሚገባው ቤተሰብ ነው፡፡ ምንም እንኳን በወላጆችና በልጆች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ ቢሆንም፣ በፆታዊ ጥቃት ዙሪያ ቀደም ብለው ያደረጉት ውይይት ችግሩን ለመፍታት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል፡፡  
በሌላ በኩል፣ ፆታዊ ጥቃት እንደ ነውር ተቆጥሮ ምንም ውይይት የማይደረግበት ቤተሰብ ከሆነ፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ልጆች ከሚደርስባቸው ጥቃት በላይ ጥቃቱን ለመደበቅ የሚሄዱበት ርቀት ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል። ለአመታት ዋጋ ከፍሎ እያሳደገ ያለው ወላጅ በዚህ ፈታኝ ወቅት ሊደርስላቸው እንዳይችል እንቅፋት ይፈጥራል፡፡ ይህም እጅግ አሳዛኝ ውጤት ያስከትላል፡፡  
በ30 የዓለም አገራት በተደረገ ጥናት፣ አስገድዶ መድፈር ከገጠማቸው ልጆች መካከል ጥቃቱን  ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ያደረጉት አንድ በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየን በበርካታ ሀገራት ጥቃቱን ሪፖርት የማድረግ ባህል አለመዳበሩን ነው፡፡  የልጆች ፆታዊ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀየረና እየተባባሰ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ ጉዳዩን መሸፈንና መደበቅ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ለጆሮ የሚዘገንኑ፣ ልብ የሚሰብሩ የጥቃት ታሪኮች እየሰማን በዝምታ ልናልፍ አይገባም፡፡
በወላጆችና በልጆች መካከል ግልፅ የውይይት ባህል ማዳበር፣ ልጆች ችግር በሚገጥማቸው ወቅት ሁኔታውን ለወላጆቻቸው ለመናገር ያስችላቸዋል። ልጆች ለሚረዳቸው፣ ለሚሰማቸው፣ ጊዜ ለሚሰጣቸውና ፍቅር ለሚያሳያቸው የልባቸውን ያጫውታሉ፡፡
ይህንን ነውረኛ ድርጊት ለመከላከል እንደ ማህበረሰብ የአመለካከት ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ ለዚህም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ለቤተሰብ፣ ለጤና ባለሙያዎች፣ ለትምህርት ቤት ማህበረሰብ ሊዘጋጁ ይገባል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፎ ሊያድግ ይገባል፡፡ በተለይም ልዩ የልጆች ፆታዊ ጥቃት ማገገሚያ ማዕከላት በበቂ ሊገነቡ ይገባል፡፡ በመንግስት በኩል ደግሞ የህግ ማዕቀፉን በማጠናከር ጠንካራ አስፈጻሚ አካላትን ማብቃት ይጠበቃል፡፡ ሰላማችሁ ይብዛ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው ፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ያገኙታል፡፡

Read 4438 times