Sunday, 22 August 2021 11:31

“ሆዱን ያየ ሆዱን ተወጋ”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ እመት ጦጣ እሰው ማሳ ገብታ፣ እሸት ስትቦጠቡጥ፣ የማሳው ባለቤት ይደርስባትና ይይዛታል። ከዚያም እግቢው ውስጥ ካለው ትልቅ ግንድ ላይ ጥፍር አድርጎ ያስራትና ወደ ቤቱ ይገባል።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አያ ዝንጀሮ እየተጎማለለ ሊጠይቃት ይመጣል።
አያ ዝንጀሮ፡
“እመት ጦጢት እንዴት አረፈድሽ?”
ጦጢትም፤ “ደህና አርፍጃለሁ። አንተስ  ደህና ነህ?”
አያ ዝንጀሮ፤ “በጣም ደህና ነኝ። ወደ ሰፈርሽ ብቅ ብዬ ለዐይኔ ሳጣሽ፣ የት ሄዳ ይሆን እያልኩ ስጨነቅ ነበር “
ጦጢትም፤ “ቆየሁ´ኮ! ብታይ ጌታዬ፣ ሰብሉ ውስጥ ከያዘኝ ጀምሮ ብዙ አሰረኝ።”
“ምን አጠፋሽ ብሎ ነው?”
“ምን እባክህ እኔ ለራሴ ሆድ የለኝ። የአገር ምግብ አምጥቶ፣ ይሄን የመሰለ ምግብ እኔ ቤት እያለልሽ ምን ልሁን ብለሽ ማሳዬ ውስጥ ገባሽ ብሎ ነው!”
“አንቺ ለምን እምቢ አልሽ?”
“ይገርምሃል! በጣም ጥግብ ብያለሁ። ከዚህ በኋላ ማር አልልስም!”አለች።
አያ ዝንጀሮም፤ “ወይኔ! እኔ ባገኘሁት ጥርግ አድርጌ ነበር የምበላው” አለ።
ጦጢትም፤ “እኔ በጣም ስለመረረኝ ማን ይተካኛል?” እያልኩ ስጨነቅ ነበር።”
ዝንጀሮ ተስገብግቦ፤
“እንዴ! እኔ ልተካሽ ታዲያ?”
“አርገኸው ነው አያ ዝንጀሮ!”
“መልካም፤ በይ ልፍታሽና አንቺ እሰሪኝ።”
“እሺ የእኔ ቆንጆ!” ብላ ተፈታች።
ከዚያም ዝንጀሮን ከግንዱ ጋር ጥፍር አድርጋ አሰረችውና፤
“በል የሚበላ ነገር ልፈልግ”፣ ብላው ሄደች።
ቆየት ብሎ የሰብሉ ባለቤት መጣ።
ከዚያም በጦጣዋ ቦታ ዝንጀሮን ታስሮ አገኘውና፤
“ምን ልታደርግ እዚህ ተገኘህ!?” አለው።
“ጦጢትን ተክቼ አንተ የምታቀርበውን ምግብ እየጠብኩኝ ነው።”
ባለ ሰብሉም ወደ ቤት ገብቶ ጉማሬ አለንጋውን ይዞ መጥቶ፣ የውስጥ ቆዳው ውጪ እስኪታይ ሙልጭ አድርጎ ገረፈና ለቀቀው።
ዝንጆሮም፤
“አይለመደኝም!” ብሎ ምሎ ተገዝቶ ተለቀቀ።
*   *   *
ብልጦች እንዳያሞኙንና መጫወቻ እንዳያደርጉን እንጠንቀቅ።
ከሁሉ በፊት፤
“ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል” የሚለውን ተረት አንዘንጋ።
አያ ዝንጀሮ፤ “ጦጢት ለምን ታሰረች” የሚለውን ጥያቄ ባለመጠየቁ፤ በጦሷ ገብቶ፤ ያስጠይቀኛል ሳይል ቀለጠ። እንደተስገበገበ የአለንጋ ዋጋውን ቀመሰ።
የሌሎችን ንብረት፣ የሌሎችን ፈንታ መውሰድ ቀርቶ መመኘትም ትክክል አይደለም። ያልለፋንበትን፣ ያልደከምንበትን ገንዘብ አንፈልግ፣ ንብረትም ላግኝ አንበል። ይሄ ልማድ እያደረ ያልተመቸን ጊዜ ወደ መስረቅ ወደ መመዝበር ይሄዳል። አለመታመን የረባ የኃላፊነት ቦታ ላይ አለመሾምን ያመጣል። በላብ ዋጋ አለመክበር የሚከሰተው፣ በአግባቡ የመበልፀግን ጉዳይ፣ ሂሳብ ውስጥ ካለማስገባት ነው።  ውርደት ከሌብነት የሚመጣ  አባዜ ነው። ሁሉንም ነገር ስናደርግ ጥንቃቄንና አለመጣደፍን ሥራዬ ብሎ ማጤን ይገባል። ጥንቃቄ ወደ ፍርሃት እንዳያደርሰንም ከመሰረቱ ብልህነትንና ዘዴ ማወቅን እንደሚጠይቅ ልብ እንበል። አለመጣደፍ ዋና ጉዳይ ነው ስንል፤
“ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ”
…የሚለውን የትናንት ግጥም ሳንረሳ ነው። ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም ዋና ነገር ነው። ናፖሊዮን ቦናፓርት እንዳለው፤
“የተወሰደብንን ቦታ ማስመለስ እንችላለን።
ያጣነውን/ያጠፋነውን ጊዜ ግን ማስመለስ አይቻለንም።”
አንድም ደግሞ እያጎ እንዳለው (በሼክስፒር ልሳን)፤
“አንዴ የሆነን ነገር ለምን ሆነ ማለት
ለማለት ብቻ ማለት…”
አንዴ ሆኗልና ወይ ለማረም፣ ወይ ከናካቴው ስለ ነገሩ እርግፍ አድርጎ ለመርሳት ዝግጁ መሆን  መለኛነት ነው። ይህ እሳቤ አዲስ ዘዴ ወደ መቀየስ ሊወስደን ስለሚችል፣ ለህይወታችን ሂደት ዓይተኛ ግብዓት ይሆነናል። ከዕድል ሁሉ መልካም ችግርን በትክክል የመፍታት ፀጋን መጎናፀፍ ነው። ወደተነሳንበት ሀሳብ ተመልሰን በለሆሳስ ስናስቀምጠው፤ ለኔ ብቻ ማለትን፣  ሁሉን ልብላው ማለትን፣ መስገብገብን እናስወግድ ዘንድ የህይወት ተመክሮ ይመራናል። አለበለዚያ ብዝበዛ፣ ምዝበራ፣ ዘረፋ ደረጃ የሚያደርሰን የራስ ወዳድነት አባዜ ነው!
“ሆዱን ያየ ሆዱን ተወጋ” ከላይ ያነሳናቸውን መዘራዝሮች ሁሉ የሚያካትትልን ለዚህ ነው!!


Read 11501 times