Print this page
Saturday, 21 August 2021 00:00

በጦርነቱ ሳቢያ የተራዘመ የሰብአዊ ቀውስ ይፈጠራል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በትግራይ  የተፈጠረው ጦርነት ያስከተላቸው ሰብአዊ ቀውሶች የተራዘመ ጊዜ ችግር ሆነው ሊቆዩ እንደሚችሉ ያስገነዘበው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ጦርነቱ በአማራና አፋር ክልልም በመቶ ሺዎችን አፈናቅሎ ለእርዳታ ጠባቂነት ዳርጓል ብሏል።
በትግራይ ክልል ካሉ አጠቃላይ 5.2 ሚሊዮን ያህል ተረጅዎች ውስጥ 4 መቶ ሺህ ያህሉ  ለእርዛት መዳረጋቸውን ያመለከተው የተቋሙ ሪፖርት፤ 75 በመቶ ለሚሆኑ አጠቃላይ ተረጂዎች የህውኃት ታጣቂ ሃይል በፈጠረው ጦርነት ምክንያት መተላለፊያ ኮሪደር ባለመገኘቱ  እርዳታ ማድረስ እንዳልተቻለ ጠቁሟል።
በአሁን ወቅት የምግብ አቅርቦት ወደ ትግራይ እየገባ ያለው በአፋር በኩል በአባኦላ መሸጋገሪያ ብቻ መሆኑንና በዚያም በኩል ቢሆን መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ በነበረበት ወቅት ህውኃት ጦርነቱን በመቀጠሉ መተላለፊያውን አስቸጋሪ አድርጎታል ብሏል- የተቋሙ ሪፖርት።
በአሁን ወቅት ወደ ትግራይ በቂ እርዳታ እየገባ ካለመሆኑም ባሻገር በቀጠለው ጦርነት ምክንያት አርሶ አደሮች የእርሻ ተግባራቸውን ማከናወን እንዳልቻሉና  ሪፖርቱ አመልክቶ ይህም ችግሩን እንዲራዘም ያደርገዋል ብሏል።
በበርካቶቹ የትግራይ አካባቢዎች አርሶ አደሮች የእርሻ ጊዜውን መጠቀም ሳይችሉ መቅረታቸውንና አጠቃላይ ሊመረት ከሚገባው የሰብል ምርት ከ25 እስከ 50 በመቶ ያህሉ ብቻ መከናወኑን ሪፖርቱ አመልክቷል።
በዚህም ትግራይ ያለው ችግር እስከ ጥቅምት 2015 ሊቆይ እንደሚችል ከወዲሁ የተገመተ ሲሆን በዚህም ዜጎች በእጅጉ ተጎጂ እንደሚሆኑ ተመልክቷል።
በትግራይ አሁንም ጦርነቱ መቀጠሉን ተከትሎ የምግብና የጤና አቅርቦት እጥረት የትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ እየፈተነ ከአመት በላይ እንደሚዘልቅ ሪፖርቱ ያመለክታል።
የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የየብስና አየር ትራንስፖርት ግንኙነት መቋረጡም የክልል ነዋሪዎች ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ያላቸው ግንኙነት ተቋርጦ እንዲቆይ ከማድረጉም ባሻገር፣ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለሰው ልጅ አስፈላጊና መሰረታዊ ከሆኑ መካከል አንዱ የመረጃ ልውውጥ ግንኙነት እንደመሆኑ የትግራይ ህዝብ ከመረጃ ርቆ በአፈና ውስጥ እንዲቆይ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች በተዛመተው ጦርነት ከሁለቱም ክልሎች ከ8 መቶ ሺህ ያላነሱ ዜጎች መፈናቀላቸውን፣ የክረምት የእርሻ ተግባር መስተጓጎሉን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ይህም ሃገሪቱን በተራዘመ ሁኔታ ለሚፈትን የሰብአዊ ቀውስ እንደሚያጋልጣት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ሪፖርት አመልክቷል።

Read 10038 times
Administrator

Latest from Administrator