Saturday, 21 August 2021 00:00

ሩሲያ ዓለማቀፉ መገናኛ ብዙኃን ጦርነቱን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ጠየቀች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲያበቃ እንዲሁም ሃላፊነት የማይሰማቸው አለማቀፍ መገናኛ ብዙሀን ጦርነቱን የሚያባብሱ የተዛቡ መረጃዎች ከማቅረብ እንዲታቀቡ የሩሲያ የወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጥሪ አቀረቡ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን በአፋጣን እንዲያቆሙ አሳስበዋል፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ማረያ ዛካሪቫስ አዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በበኩሉ ትናንት ባስተላለፉት መግለጫቸው ሃገራቸው በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በትኩረት እየተከታተለች መሆኑን  አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳ ፌደራል መንግስት የተናጥል የተኩስ አቁም አድርጎ ትግራይን ከወራት በፊት ለቆ የወጣ ቢሆንም የህወኃት ሃይል በውጊያው መቀጠሉን ከትግራይ ውጭ ያሉ የአፋርና የአማራ አካባቢዎችን በሃይል መቆጣጠሩን በዚህም ቀደም ሲል በጦርነቱ ያልተጠበቁ አካባቢዎች የጦርነት ቀጠና እንዲሆኑ ማድረጉን የቃል አቀባዩ መግለጫ ያመለክታል፡፡
ህወኃት ጦርነቱን በቀጠለበት ወቅት የኢትዮጵያ የውጭ  ገቢ ንግድ መስመር የሆነውን ጅቡቲን ከኢትዮጵያ የሚያገኘውን መስመር ለመቆጣጠር ጥረት ማድረጉን ምንም እንኳ ይህ ጥረቱ ባይሳካም በመቶ ሺዎች እንዲፈናቀሉና በርካቶችን ለሞት መዳረጉን በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ በዚህ በሃገሪቱ የሰብአዊ ቀውስ እንዲባባስ የህወኃት እርምጃዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቻቸውም ገልጸዋል፡፡
ይህ እጅግ አስከፊ ግጭት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲቀየርና ተፋላሚ ሃይሎችን ሠከን  ብለው ችግሩን እንዲያጤኑት ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሁኔታውን ከሰብአዊ መብቶች ጋር ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ በማያያዝ ማራገባቸው ሃላፊት የጎደለው ተግባር ነው ያለው መግለጫው ጋዜጠኞች ከዚህ ድርጊታቸው ተቆጥበው ሠላም በሚያመጡ ሁኔታዎች ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቀዋል፡፡
ይህን ደም አፋሳሽ ጦርነት ማቆም ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑንና በሃገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ወሳኝ መሆናቸው በመግላጫቸው ያመለከቱት ቃል አቀባይዋ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ሃይሎች የራሳቸውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ መክረዋል፡፡
አፍሪካውያን የኢትዮጵያን ሠላም በመመለስ ረገድ የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉ በፊት አውራሪነት እንዲያግዙ የሩሲያ ቃል አቀባይ በመግለጫቸው ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አሁን በኢትዮጵያ ባለው ችግር ወታደራዊ ፍልሚያ ምንም አይነት ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል አስገንዝበው ሁሉም ሃይሎች በውይይት ችግሮችን  መፍታት አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

Read 10365 times