Monday, 23 August 2021 00:00

የውሃ እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ውሃን በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል ቻርተር የፊታችን ሐሙስ ይፈረማል
                      
            ውሃን እንደቀደመው ጊዜ ቆፈር ቆፈር አድርጎ ማግኘትና ወደ ምርትነት መቀየር ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጋች እየሆነ መምጣቱ አሳሳቢ ስለመሆኑ ውሃን በጥሬ እቃነት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ስጋታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ። ለዚህም ምክንያቱ የትኛውም አካል ቢሆን ውሃን በየዕለቱ ከመጠቀም ባለፈ ውሃን በዘላቂነት ማልማት ላይ አለመስራቱ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህንኑ አሳሳቢ ጉዳይና መፍትሔውን አስመልክተው ውሃን በጥሬ ግብአትነት የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች  ማህበር መስራች አባላት ድርጅቶች ሃላፊዎች ባለፈው ሳምንት በአዜማን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በሀገራችን በተለይም በአዲስ አበባና አካባቢዋ ከ150 በላይ ውሃን በጥሬ ግብአትነት የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማለትም የታሸገ ውሃ፣ የለስላሳ መጠጥ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ጭማቂ፣ ቢራና የሌሎች የአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎች በስራ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
እነዚህ ፋብሪካዎች ውሃን በዋና ጥሬ እቃነት እንደመጠቀማቸው የሚፈልጉት የውሃ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠረና ውሃን ቆፍረው ለማግኘት የሚወስድባቸው ጊዜ፣ ገንዘብና የሰው ሃይል ጉልበት በእጅጉ እየጨመረ፣ ፍላጎትና አቅርቦቱ አለመጣጣሙ እያሳሰባቸው መምጣቱን ይገልፃሉ።
ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት የህዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት በከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በዚያው ልክ አምራች ኢንዱስትሪዎችም እየተስፋፉ መምጣታቸውና ውሃን ለመጠቀም ያለውን ፍላጎት  ያህል የውሃን ዘላቂነት የሚያስጠብቅ ልማት አለመሰራቱን ነው።
የእነዚህ ፋብሪካዎች ሃላፊዎች ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ አበው፤ ችግሩና ስጋቱ ሥር ሳይሰድ መፍትሄ መፈለግ አለብን በማለት አሊያንስ መስርተው ቻርተር ተፈራርመው ውሃን በዘላቂነት አልምቶ ለመጠቀም የፊታችን ሃሙስ ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም  በሂልተን ሆቴል ለመገናኘት ጥብቅ ቀጠሮ ይዘዋል።
የዚህ አሊያንስ መስራች ጉባኤ አባላት አባሀዋ ትሬዲንግ (ዋን ውሃ)፣ ሄይንከን ኢትዮጵያና  የኢትዮጵያ የታሸገ ውሃ፣ ለስላሳ መጠጥ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ አምራች ኢንዱስትዎች ማህበር ሲሆኑ ጋዜጣዊ መግለጫውንም የሰጡት የእነዚህ ተቋማት ከፍተኛ ሃላፊዎች ናቸው።
የሞግሌ የታሸገ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካ (የዋን ዋተር) የዋና ስራ አስኪያጅ ረዳትና በአሊያንሱ የመስራች ጉባኤ አባል የሆኑት አቶ ማለሪ ወዳጄነህ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ሲናገሩ፣ “ሰዎች ሞልቶ ለሚፈስ ውሃ የምን ስጋት ነው፣ ምድርን ከሸፈኗት ነገሮች ሁለት ሶስተኛው ውሃ ሆኖ ሳለ ውሃ  እንዴት ሥጋት ይሆናል? የሚሉና መሰል ሀሳቦችን ያነሳሉ ይሁን እንጂ ምድርን ከሸፈናት ሁለት ሶስተኛው ውሃ ቢሆንም ለመጠጥነት  የሚውለው አምስት በመቶው ብቻ ነው ብለዋል” እንደ ሞግሌ የታሸገ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካ (ዋን ዋተር) ያሉ ውሃን በዋና ጥሬ እቃነት የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች በየግላቸው በተበታተነ መንገድ ውሃን ለማልማት ከሚሰሩ አሊያንስ (ማህበር) አቋቁመው በተጠናከረ መልኩ በመስራት ሊከሰት የሚችለውን ችግር ከወዲሁ ተዘጋጅቶ መጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ ማህበሩን ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ይላሉ።
ከመስራች ኮሚቴ አባላት አንዱና የመስራች ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት እንዲሁም ሄይንከን ኢትዮጵያን የወከሉት አቶ ታረቀኝ ጋሮምሳ በበኩላቸው፤ በቀደመው ጊዜ ውሃን በቀላሉ በቁፋሮ ማግኘት ይቻል እንደነበር ገልፀው፤ አሁን ከህዝብ ብዛትና ከከተማ መስፋፋትና ከተጠቃሚ ቁጥር መብዛት ጋር ሁኔታዎች እየተቀየሩ፣ ውሃን በቁፋሮ የማግኘት ሂደቱና ወጪው እየጨመረ፣ የጉድጓድ ጥልቀትም   እየቀጠለ መሄዱን አስታውሰው፣ በዚህ ምክንያት ውሃን ከማስተዳደር አንፃር በአቅርቦት ከመተማመን ይልቅ ፍላጎትን በመቆጣጠር፣ በቁጠባና በሃላፊነት ወደ መጠቀም ያደላ ፖሊሲ መከተል የግድ እንደሚል ሁኔታዎች አመላካች ናቸው ብለዋል።
ውሃን እንደ ወሳኝ  ሀብት በቁጠባ የመጠቀም አስተሳሰብ  በውሃና ውሃ ነክ ምርት ላይ ላተኮረ ኢንዱስትሪ ይበልጥ የቀረበ መሆኑን የተናሩት ደግሞ የመስራች ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ የታሸገ ውሃ የለስላሳ መጠጥ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና  ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ መርዕድ ናቸው። ከዚህ እውነታ በመነሳት በዘርፉ የተሰማሩ ፋብሪካዎች ይህን ማህበር ለማቋቋም ሥራ የተጀመረው ከሶስት ዓመታት በፊት፣  በኔስትሌ ዎተር ኢትዮጵያ 2030 እና ደብሊው ኦርጂ በተባሉ ሁለት ድርጅቶች ግንባር ቀደምትነት እንደሆነ ገልጸው፤ በኋላ ኮካ ኮላን፣ የኢትዮጵያ የታሸገ ውሃና ለስላሳ አምራች ኢንዱስትሪ ማህበርንና ዎተር ኤይድ ኢትዮጵያን ማካተት መቻሉን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል።
የዋን ዋተር የዋና ሥራ አስኪያጁ ረዳት የአምራች ኢንዱስትሪው መስራች ኮሚቴ አባል አቶ ማለሪ ወዳጄነህ በበኩላቸው፤ ውሃ በዓለም ላይ በስጋትነትና በአንገብጋቢ ጉዳይነት ከሚነሱ ጉዳዮች በሶስተኛ ደረጃነት ላይ እንደሚቀመጥ ጠቅሰው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ውሃን መልሶ መጠቀም (Reuse)፣ አዟዙሮ መጠቀም (recycle) እና ቀንሶ መጠቀም (Reduse) ዋነኞቹ ሊሰመርባቸውና  ሊተገበሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው በማለት ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን የውሃ እጥረት ከወዲሁ መፍትሄ በማዘጋጀት፣ ውሃ ላይ ያለንን አመለካከት በመቀየር አካባቢያችንን በመንከባከብና መሰል ዘላቂ የውሃ ልማቶችን ተግብረን በመስራት መጠበቅ ግድ ይለናል ሲሉ አሳስበዋል።
ነሀሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ጠዋት በሂልተን ሆቴል የአሊያንሱ ምስረታ ሲካሄድም እነዚህ አንገብጋቢ ጉዳዮች በዋናነት ተነስተው ውይይት እንደሚደረግባቸውና ከ120 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሃላፊዎች ተገኝተው ቻርተር እንደሚፈርሙ ነው አቶ ማለሪ ወዳጄነህ የገለጹት። የመስራች ኮሚቴው ሰብሳቢና ሄይኒከን ኢትዮጵያን የወከሉት አቶ ታረቀኝ ጋሮምሳ እንደገለጹት፤ በማህበሩ ምስረታ ዕለት፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሽ በቀለ በክብር እንግድነት የሚገኙ ሲሆን ጉዳዩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ የዘርፉ ተዋንያንና የቢስነስ ሰዎች የሚታደሙ ሲሆን ውሃን በዘላቂነት አልምቶ ለመጠቀም የሚታዩ ስጋቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሃሳቦችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።


Read 3315 times