Wednesday, 25 August 2021 00:00

“ከንባብ የራቁ… በመጻሕፍት ንግድ የተራቀቁ…"

Written by  አብዲ መሀመድ
Rate this item
(1 Vote)

 "፡- 58% የአሜሪካ ጎልማሳ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ በኋላ ፈጽሞ ሌላ መፅሐፍ አላነበበም፡፡ 30% የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ
ትምህርት ያጠናቀቁ መፅሐፍ አላነበቡም፡፡ 42% የሚሆኑ የኮሌጅ ምሩቃን ሌላ መፅሐፍ አላነበቡም፡፡ 80% የሚሆኑ የአሜሪካ
ጎልማሶች ከ2016 በፊት በነበሩት በ5 ዓመታት ወደ መፅሐፍ መሸጫ መደብር አልሄዱም፡፡››
             
          በየዓመቱ ከረምት በመጣ ቁጥር የተማሪ ማረፍን ተከትሎ የንባብ ንቅናቄዎች፣ የመጽሐፍ አውደ-ርዕይ በየአውራ ጎዳናው ይደረጋል፡፡ ከንባብ ጋር “ባላንጣ” በዕውቀትም ቢሆን የነጣ፣ አንብቡ በሚል ቡራኬ በየሚዲያው ብዙሃን እንሰበካለን። በጋውን ሙሉ በድርቀት፣ ክረምትን ብቻ በዕውቀት ጊዜያችንን የምንገፋ ይመስል፡፡ ንባብ ለጥቂት ወራት ፣ለዓመታት ሳይሆን “ንባብ ለሕይወት” መሆኑን የምትፈክር አንድ “መርህ” ነበረች!... በአንድ ወቅት! እሷ መሪ-ቃል በተለይ ለእኔ ትስማማኛለች (ዛሬ የት ደርሳ! ምን ውጧት ይሆን? )
ወደ ዋና ጉዳዬ ከማምራቴ በፊት በንባብና አንባቢ አለመኖር ዙሪያ እንደ መነሻ አድርጌ ልንደርደር፡፡ ምህረቱ ጴጥሮስ የተባለ አጥኚ በአጠቃላይ የንባብ ባህል በሀገራችን ምን እንደሚመስል በቃኘበት ‹‹የንባብ በባልና ቤተክርስቲያን›› በተሰኘ ጥናታዊ መፅሐፉ ውስጥ ንባብ ቋሚ እሴታችን እንዳይሆን ያደረገው ማህበራዊ አኗኗራችን ነው ሲል ተመራማሪው ያስረግጣል፡፡ አጥኚው ሃሳቡን ሲያብራራ!... በከተማም ሆነ በገጠሩ አካባቢ ለማህበራዊ አኗኗር እና ለጋራ ሥራ የምንሰጠው ቦታ ለንባብ አለመለመድ እንደ-ችግር የመጀመሪያው ነው ይለናል። የሀገራችን ባህል አብዛኛውን ጊዜ ሰውን በማስደሰት ላይ እንድናተኩር የሚያደርገን ከመሆኑ የተነሳ ለንባብ የምንሰጠው ዕድል በጣም የተመናመነ ነው፡፡ ባህሉ ራሱ ሰውና ህብረተሰብ -ተኮር በመሆኑ ግለኝነትን ወይም መለየትን አያበረታታም። ንባብ ደግሞ በግል የሚሰራ ሥራ ነው። በሰው ብዛት የተጨናነቀ ሁኔታና ደካማ የቤት ውስጥ ብርሃን ዘወትር መፅሐፍትን ለማንበብ ፍላጎትም ሆነ ችሎታ እንዳይኖር ያግዳል...፡፡ ሲል በዳሰሳዊ ጥናቱ የደረሰበትን ድምዳሜ አስቀምጧል፡፡     
ሁሌም ባይሆን  አንዳንዴ የሚመስሉን ለመሆን ሩብ-ጉዳይ የቀራቸው ሁነቶች በህይወታችን ያጋጥማሉ፡፡ ነው ብለን ለመደምደም የምንቸገርባቸው፤ እርግጥ ነው በዚህ በዘመነ - ካፒታሊዝም ስርአት ውስጥ በመጽሃፍ ንግድ ላይ ተሰማርተው ጥሪት የቋጠሩ ግለሰቦች ጥቂት አይደሉም፤ ሞልተውናል፡፡ ከንግዱ ጎን ለጎን የሚሸጡትን መጽሃፍት ለንባብ የሚያገላብጡ ነጋዴዎች ግን የሉንም፡፡ (የንባብ ባህል እንዳልዳበረባት ሀገር ካሰብን  ይህ በራሱ ትልቅ የእውቀት-ኪሳራ ነው፡፡)
እንበልና አንድ ‹‹እህል ነጋዴ›› ሀብት ቢያፈራበትም፣ ንብረት ቢያካብትበትም እንኳን ዞሮ-ዞሮ እሚሸጠው ምርት ውጤቱ ‹‹እንጀራ›› ወይም ‹‹ዳቦ›› ነውና ይመገበዋል። ወደ መጽሃፍ ነጋዴዎች ስንመጣ ግን እውነታው በተቃራኒው ሆኖ እናገኘዋለን፤ አያነቡትም፣አይመገቡትም፡፡ ለምን?
ቀደም-ባሉት ዘመናት መጽሃፍትን እየነገዱና እያነበቡ ራሳቸውን በገንዘብ ያሳደጉ፣ በንባብ ያበለፀጉ ደራሲያን በታሪክ ውስጥ አልፈዋል፡፡ ብዙም የዘመን-ርቀት ባይኖራቸውም እንኳን ከትናንትናዎቹ…አቤ ጉበኛ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ማሞ ውድነህ.. እስከ-ዛሬዎቹ እንዳለጌታ ከበደ፣ አውጋቸው ተረፈ (ነፍስ ይማር)፣ ለአብነት መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ..እነዚህ ጠቢባን ከመጽሃፍ መሸጥና ማከራየት ጎን-ለጎን የሚሸጡትን እያነበቡ (በአንድ ድንጋይ) ተጠቅመው .. ሀሳቦቻቸውን በመጽሃፍ ሰንደው ለትውልድ ያኖሩ በክብር የትም ስማቸውን የምንጠራላቸው አርአያዎች መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡ በርግጥ የንባብ ፍቅር በነጠፈበት፣ ባለ-ዲግሪ፣ ባለ-ዶክተሬት፣ ባለ-ፒ ኤችዲ.. መጽሃፍት ባለበት ‹‹ዝር›› በማይሉበት ሀገር፣ (አንድ አንጋፋ ጉምቱ የጥበበ ሰው በቅርቡ በአንድ መጽሔት ላይ!…. በደርግ ዘመን ወታደሩ ሳይቀር ትጉህ አንባቢ ነበር። አሁን በየክረምቱ ከዩኒቪርስቲው ‹‹ብዙ ሺህ ተማሪ ተመረቀ›› ሲባል እሰማለሁ፡፡ አንባቢ ግን፣ የለም፡፡ የትምህርት ስርዓቱን እንዴት አድርገው ቢያኮላሹት ይሆን እያልኩ ዘወትር እገረማለሁ፡፡" ሲሉ ለዚህ እንደዋነኛ ችግር የትምህርት ስርዓታችንን ተችተዋል፡፡ (..ታዛ ቅጽ 04.1 ቁጥር 47..) እውቀት እንደ-ዋዛ የትም ባክኖ በሚቀርበት ሀገር.. በመጽሃፍት ንግድ ላይ የተሰማሩ (አዟሪና ነጋዴዎችን) ለምን አያነቡም ብሎ ለመጠየቅ መነሳት በራሱ እኔኑ ሊያስገምት እንደሚችል አላጣሁትም፡፡ ይሁንና ብዙ ሰአታቸውን እሚያጠፉት ከመጽሃፍት ጋር ነውና ቁርኝታቸውንም ከንባብ ጋር ከማጠናከር ውጪ ሌላ አማራጭ ያላቸውም አይመስለኝም፡፡ በስራ-ፈጠራ ዘርፍ ተሰማርቶ አንቱታን ያተረፈውና በጉዳዩ ላይ በርከት ያሉ መጽሃፍትን ያበረከተው ‹‹ወሮታው በዛብህ›› እንደሚያወሳው ከሆነ.. የሰው ልጅ ከተሰጡት ‹‹ሀያ አራት›› ሰዓታት ውስጥ ብዙ ጊዜውን በሚያጠፋበት ቦታ ‹‹ደስተኛ›› ካልሆነ ቀሪ ህይወቱ የስቃይ እንደሚሆን ዶክተሩ ያብራራል፡፡ የንባብ ጥማችንን ከመቁረጥ ባሻገር ደስታ ከሚጨምሩልንና ከሚሰጡን መንፈሳዊ ሀብቶቻችን ውስጥ ከመጽሃፍት ውጪ ሌላ ማሰብ እንዴት ይቻላል፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ካላነበቡ ደስታን ማለም ህልም እንደሚሆንባቸው ማንም አያጣውም፤ ታዲያ ከዚህ የ"ደስታ እጦት" ሳይሆን ይቀራል በዝና የምናውቃቸውን፤ እጃችን ላይ የሌሉ መጽሃፍት ለመግዛት ጎራ ባልን ቁጥር እጅ-እግር በሌለውና በማያላውስ የኑሮ ውድነት ላይ የመጽሃፉን ሶስትና-አራት እጥፍ ዋጋ እየጠየቁ የሚያስደነግጡን! ቆሌያችንን የሚገፉት! ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ብላችሁ? ብቻ እኔን መሰለኝ ..ከመሰለኝ ደግሞ ነው እንዲል ‹‹ሌሊሳ ግርማ›› ፡፡
በዚህ ‹‹ድህነት›› በዚያ ‹‹ድንቁርና››..እንዲሁም የኑሮ ውድነት እንደ-ጉድ በሚፈነጩብን በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ለመኖር ተጨማሪ ምክንያት ከሚሰጡን እድሜ ማራዘሚያዎቻችን፣ መጽናኛዎቻችን መካከል መጽሃፍት ብቸኞቹም፣ ግንባር ቀደሞቹም ናቸው፡፡ በመኖር ጉጉት ውስጣችንን የሚያቀጣጥሉት፤ በተስፋ መቁረጥ እንዳንዋጥ የተሻለ ነገ ከፊታችን እንዳለ አቅጣጫ ጠቋሚ ኮምፓሳችንም ጭምር፡፡ በመጽሃፍ ንግድ ለተሰማራ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ሙያ ላይ ለሚማስን ዋነኛ ‹‹ትጥቁና ስንቁ››መጽሃፍት ሊሆኑ ግድ ነው፤ ከወታደር እስከ ወዛደር፣ ከአውርቶ-አደር እስከ አርብቶ- አደር፤ ከሴተኛ-አዳሪ እስከ ሀገር-አስተዳዳሪ፣ ከወጥ-ሰሪ እስከ ጫማ-አሳማሪ መጽሃፍትን ያንብቡ። ማንበብ አማራጭ ሳይሆን የግዴታ ‹‹ማዕቀብ›› ይጣልበት፡፡ የሚሰጡ ‹‹እጆች›› ብቻ ሳይሆኑ የሚጽፉልንም ‹‹እጆች›› ይባረኩ፡፡ የመጽሃፍ አምራቹ ደራሲና ተርጓሚ ‹‹ማሞ ውድነህ›› በህይወት በነበሩበት ጊዜ.. ለቤት የኑሮ ፍጆታ የሚሆን ‹‹አስቤዛ›› ሸማምተው እቃቸውን ለተሸከመላቸው ወዛደር ወይም ኩሊ የሚሰጡት ገንዘብ አልነበረም፤ መጽሃፍትን እንጂ፡፡.. ‹‹እንካ ያዝ›› ይላሉ፤ ጋሼ ማሞ ውድነህ፣ ከአሁን-አሁን ገንዘቡን ተቀብሎ ለመሄድ አይኑን በጉጉት እያቁለጨለጨ ለሚጠብቃቸው ወዛደር… እንካ ያዝ ገንዘብ አይደለም እምሰጥህ፤ ‹‹ኪሴ›› ምንም ቤሳ-ቤስቲ የለኝም (ቢኖራቸውም)፤ ዘወትር ሆድህን ብቻ አትመግበው፤ አንዳንዴ እስኪ ጭንቅላትህንም መግበው! ብለው ከደረሷቸውና ከተረጎሟቸው አያሌ መጽሃፍት መካከል አንዱን መዘው የመስጠት ልማድ እንደ-ነበራቸው በታሪክ ይነገርላቸዋል፡፡
በነገራችን ላይ በቀድሞ አጠራር ‹‹ወዛደር›› ተብለው የሚጠሩ እቃ በመሸከም ኑሮዋቸውን እሚገፉ፣ አሁን-አሁን የቀን ሰራተኞች በሚል ስያሜ ይጠራሉ፡፡(ወዝ-አደር ሲባል ስያሜው፤ በወዙና በላቡ ሰርቶ የሚያድር ለማለት ይመስለኛል፡፡ ይህንን ቃል ለመፍታትም ሆነ ለማፍታታት የተሰማ ሀብተ-ሚካኤልንም ሆነ የደስታ ተክለ-ወልድን መዝገበ-ቃላት በምንጭነት አልተጠቀምኩም).. ጋሽ ማሞ ውድነህ ለዚያ የቀን-ሰራተኛ መጽሃፉን ሽጦ ይብላበት ወይም መጽሃፉን እያነበበ ይደሰትበት ወይም እውቀት ይሸምትበት ሌላ ጥያቄ ቢሆንም እርሳቸው ሁሉም እንዲያነብ የነበራቸው ምኞት ግን ሊያስመሰግናቸውና ሁሌም በክብር ስማቸውን እንድናነሳቸው የሚያደርግ ምሳሌያቸው ነው፡፡ በርግጥ ሁሉም እንዲያነብ መመኘት ያባት ነው፡፡ ሁሉም እንዲያነብ መጠበቅ ግን ‹‹ቂልነት›› ነው፡፡ ብዙ ከምንጠብቅባቸው እንኳን ከንባብ በመራቅ ‹‹ነቀርሳ›› ምክንያት ተስፋ ቆርጠን የተውነው ነገር ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድ ወቅት ሚዩዚክ ሜይዴይ በተባለ የውይይት መድረክ ላይ ደራሲ ‹ዘነበ ወላ›፤ የንባብ ልምድና ተሞክሮውን ባካፈለበት አንድ መድረክ ላይ እግር ጥሎኝ በአጋጣሚ ተገኝቼ ነበር፡፡ ዘነበ በንዴትና ሀይለ-ቃል በተጫነው ድምፀት የተናገረው አይረሳኝም። እንዲህ ሲል.. ነብሱን ይማረውና ስብሃት ገብረ-እግዚያብሔር አንዴ በጠና ታሞ ሆስፒታል ገባና ላስታምመው አብሬው ነበርኩ፡፡ እሚገርማችሁ ከሚያክሙት ዶክተሮች መካከል ጋሽ ስብሐትን የሚያውቀው አልነበረም፡፡ መቶ በመቶ አላወቁትም፤ እያከሙት እሱ መሆኑን በጭራሽ አያውቁትም ነበር፡፡ ምክንያቱም አያነቡማ.. ምንም ንባቡ የላቸውም፡፡ መጽሃፉ ቢቀር ጋዜጣና-መጽሔት ቢያነቡ እኮ በቀላሉ ሊለዩትና ሊያውቁት ይችሉ ነበር፡፡ እንግዲህ ‹‹እግዜር›› ያሳያችሁ በዶክተርነት ‹‹ደረጃ›› ላይ ያለ ግለሰብ የማያነብበት ሀገር ላይ ነው ያለነው፡፡ አስቡት እስኪ ስብሐትን ያህል ታላቅ ደራሲ በዶክተርነት ደረጃ ላይ ባለ ሰው አለመታወቁ ምን ያህል እንደ-ሚደንቅ፤አይገርምም፡፡ እኔ ዘወትር እንደገረመኝ! ቃል በቃል ባይሆንም የንግግሩ መንፈስ ግን ከሞላ ጎደል ይኸው ነበር፡፡ በእርግጥ እንደ -ሀገር ስናስብ የንባብ ባህል ችግር ገና አብዛኛው ህዝቧ ማንበብና መጻፍ የማይችል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምዕራቡ ዓለም እየተደረጉ ያሉ ለማመን የሚያስቸግሩ የንባብ ባህል መላሸቅን የሚያመለክቱ አሀዛዊ መረጃዎች እጅግ የሚያስደነግጡ ናቸው፡፡ ለአብነት.. በ2020 እ.ኤ.አ በአሜሪካ መፅሐፍት ሻጮች ማህበር በተደረገ አጠቃላይ ዳሰሳዊ ጥናት ከላይ በጠቀስኩት ምርምር ውስጥ እንደሚከተለው ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ … ፡- 58% የአሜሪካ ጎልማሳ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ በኋላ  ፈጽሞ ሌላ መፅሐፍ አላነበበም፡፡  30% የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁ መፅሐፍ አላነበቡም፡፡ 42% የሚሆኑ የኮሌጅ ምሩቃን ሌላ መፅሐፍ አላነበቡም። 80% የሚሆኑ የአሜሪካ ጎልማሶች ከ2016 በፊት በነበሩት በ5 ዓመታት ወደ መፅሐፍ መሸጫ መደብር አልሄዱም፡፡ ›› ገጽ 20   
ቀደም-ሲል ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ ደራሲና ተርጓሚ ‹‹ማሞ ውድነህ›› ለዚያ የቀን ሰራተኛ ‹‹መዘዝ›› አድርገው ሊሰጡት ከሚችሉት ደርዘን ከሚሞሉት፣ ብዙ ከተማርንባቸው ስራዎቻቸው ውስጥ በሰልፍ ተሰድረው በምናቤ መጡ... (የደረስኩበት ወይስ የአለም ጦርነት፣ እድርተኞቹ ወይስ እቁብተኞቹ፣ ማህበርተኞቹ ወይስ ከዳተኞቹ፣ አሉላ አባ-ነጋ ወይስ አፄ-ዮሐንስ፣ ሾተላዩ-ሰላይ ወይስ የክፍለ-ዘመኑ ሰላይ፣ የአለም-ጦር ወይስ የኦዴሳ-ማህደር፣ የካይሮ ጆሮ ጠቢ ወይስ ኬ.ጂ.ቢ) አቤት ስንቶቹን አስታውሼና ቆጥሬ እዘልቀው ይሆን?
እስኪ ተጠየቁ
እነዚህ-ነጋዴዎች.. በመጽሃፍ ንግዱ ርቀዋል፣ ተራቀዋል፤ የሚሸጡለትን ህዝብ ኑሮውን ግን የሚያውቁት አይመስሉም። ከሰሀራ-በታች ሳይፈልግ በተጫነበት የመኖር-ቀንበር ጋር እየተፍገመገመ አንድ መጽሃፍ ገዝቶ ለማንበብ ዋጋው ‹‹ዳገት›› ለሆነበት ህዝብ (ክምር-ዋጋ) ቆልሎ መናገር የወደቀ-እቃ እንደ-ማንሳት ቀልሎዋል..ዋጋ እንደ-ተራራ ተቆልሏል፡፡ ለመግዛት የተከየፍንባቸውን መጽሃፍት በአይናችን ብቻ ለክፈናቸው በሙድ - መቀየስ የዘወትር ተግባራችን ሆኗል፡፡‹ ‹ካፒታሊዝም›› ያመጣው የነፃ-ገበያ ‹‹ስርአት›› ነው በሚል ሁሉም ዝምታን መርጧል፡፡ የመጽሃፍ ገበያው የሞቀላቸውና የደራላቸው ነጋዴዎች በዚህ ‹‹ቁማር›› ከብረዋል፤ ንብረት አካብተዋል፤ የንባብ ፍቅር ያለውን ደሀ አንባቢ አራቁተዋል፡፡ ከወራት በፊት በመጽሃፍ ንግድ ተሰማርቶ የከበረ ‹‹መደብር ያለው ቱጃር›› በአለላ መጽሄት ላይ በእንግድነት ተጋብዞ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ! ..አየህ ከጥቂት አመታት በፊት አንድ መጽሃፍ በ30 ሺህ ብር ሸጬ ነበር..አሁን ያንን መጽሃፍ ባገኘው አትጠራጠር 70 ወይም 80 ሺህ ብር መልሼ እገዛዋለሁ..  ቅጽ (1 ቁ 2) ሲል ማንበቤ (ፈጣሬ ምስክሬ ነው) አስደንግጦኛል፡፡
በእርግጥ ጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የነጋዴ ብቻ ነው ብሎ ለመደምደም አያስደፍርም፡፡ የአንድ መጽሃፍ አማካይ መነሻ ዋጋ 300 ብር እንደሆነ በጠቅላያችን ‹‹መደመር›› በይፋ ታውጇል፡፡
በዚህ ቀዳዳ ገብቶ አዙሪቱ ላይ እንጀራውን ለመጋገር ላሰፈሰፈ ነጋዴ፣ የማስበዝበዝ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ የታሰበበት አይመስልም፡፡ ምንም እንኳን የመደመር መጽሃፍ የዋጋው አላማ ዞሮ-ዞሮ እውቀትን ለማስፋፋት (ለትምህርት መማሪያ ቤት ግንባታ) በሚል ለበጎ ቢሆንም የህዝቡን የመግዛት አቅም ያላገናዘበ፣ ህዝብ ጋ በቀላሉ እንዳይደርስ የተደረገበት ምክንያት ግን በራሱ ጥያቄ ያስነሳል? የመጽሃፉ ሀሳብ ነው እኛ ጋ መድረስ ያለበት ወይስ ሌላ፤ ጥሩ ዜጋ፣ መሪውን ተከታይ፣ ለአገዛዝም ቢሆን ምቹ እንድንሆን ከተፈለገ ቢቻል በነፃ መበተን እንጂ በዋጋ ማስፈራሪያነት እንዳንደርስበት የተደረገው ምን የሚሉት አጉል ፈሊጥ ነው? ለዚህም ይመስላል አጥኚው ምህረቱ እንዲህ የሚሉን …. ሀገራችን ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት እንዷ ናት፤ ይህ ደግሞ ሰዎች መፅሐፍ እንዳይገዙ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡
የመጽሐፍት ዋጋ ካላሽቆለቆለ ቁጥራቸው የማያንስ አያሌ ሰዎች ማንበብ እያጓጓቸው በፈለጉት መጠን ለንባብ ሕይወት ያልታደሉ ይሆናሉ፡፡ የመግዛት አቅምም ስለሚያጥራቸው ከንባብ ጥም ተቆራርጠው ይቀራሉ፡፡ ስለዚህ የመፅሐፍ መሸጫ ዋጋ ካልተቀነስ በርካታ የሀገሬው ህዝብ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት በሚታትርበት ምድር ከመሰረታዊ ፍላጎቶቹ ማሟያ ቀንሶ፣ ከጎሮሮው ገምሶ ገንዘቡን ለዚህ ተግባር ያውላል ማለት ዘበት ነው፡፡ (ገጽ 113)   
ሁሉንም መጽሃፍ በ‹‹ታሪክ ድርሳናት›› ሂሳብ ዋጋ የሚያሰሉ የመጽሃፍ ነጋዴዎች ባሰፈሰፉበት ሀገር እንዴት ገዝቶ ማንበብ ይቻላል? ገዝታችሁ አንብቡ የሚል ‹‹ሞራል›› ያለው አካል ማን ነው? በዚህ ሁኔታ የንባብ-ባህል እንኳን ሊያድግ በምን መሠረት ላይ ሊዳብር ይችላል? ለወደ-ፊት ብዙ እጽፋለሁ ብሎ ዛሬ ላይ በንባብ ለመበርታት ለሚሻ (የኔ ቢጤ) ተስፋው ምንድነው? ነባሩን ተዋውሶ የማንበብ ባህላችንን ከመናፈቅ ውጪ ሌላ ምን? ብዙ መልስ አልባ ጥያቄዎች?፡፡
በዚህ ምጥን ሐተታ ለመውጫነት ጥቁምታዬ የሚሆነው እነዚህ ከንባብ ለራቁ .. ዋጋ በማናር ለተራቀቁ… “ነጋዴዎችና አንዳንድ ህገወጥ አከፋፋዮች!... ለፍርድ ይቅረቡ፣ እስር ይከናነቡ፡፡ በደራሲ ድካም ‹‹በግፍ ዋጋ›› ለመክበር ንባብን ገድለዋል.. ‹‹..አንባቢን ከመጽሃፍ አቆራርጠዋል። እውቀት እንዲቀጭጭ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፤ ከድንቁርና ጋር በማሴር እውቀት ላይ ዶልተዋል፡፡ በርግጥ ይጠይቁልን፡፡… ወይም “እስኪ ተጠየቁ” እንዲል ታላቁ ገጣሚ ዮሐንስ አድማሱ!፡፡

Read 4401 times