Saturday, 08 September 2012 12:30

ወላጅ አልባነት ከዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ራስን ከመለወጥ አያግድም!

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

“የራሳችንን ሰብዕና የምንፈጥረው ራሳችን ነን”

ሰባት ናቸው፡፡ በየሄዱበት “ተረጂ ናቸው፤ ወላጅ አጥ ናቸው፣ …” መባል ሰልችቷቸዋል፡ ወላጅ አልባ መሆናቸውን ሲያውቁ “አይዟችሁ፤ አለንላችሁ፡፡ በእርግጥ በሕፃንነትና በልጅነት ወላጅ ማጣት ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን የኅብረተሰቡ አካል ስለሆናችሁ ብቻችሁን አይደላችሁም፤ ልጆቻችን እንደሚያድጉት ታድጋላችሁ…” በማለት የሚያበረታቷቸው፣ ሞራልና ድጋፍ የሚሰጧቸው ሰዎች ጥቂት ናቸው፡፡ በተቃራኒው አብዛኞቹ የአዞ እንባ አንጓቾች፣ እነዚያ ሕፃናትና ልጆች የኅብረተሰቡ አካል መሆናቸውን፣ ተስፋና አለኝታቸው እነሱ መሆናቸውን፣ ካቀረቧቸውና ፍቅር ከሰጧቸው፣ ድጋፍና እንክብካቤ ካደረጉላቸው፣ … ነገ፣ ጥሩ ደረጃ እንደሚደርሱ አይረዱም፡ “እናቷ’ በእንትን ነው የሞተችው፤  አባቱን አያውቀውም፤ ሳይወለድ ነው የሞተው፤ … በማለት እያወሩና ከንፈር እየመጠጡ በነገር ጅራፍ ይለበልቧቸዋል፡፡

ይህ ድርጊት የችግሩ ሰለባ የሆኑትን ሕፃናትና ወጣቶች ሞራል፣ ክብርና ሰብዕና ይነካል፣ ሥነ ልቦናዊ ጫናና ቀውስ፣ … ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ፣ ተረጂና ወላጅ አጥ የሚሉት ቃላት አስጠሏቸው፣ አንገፈገፏቸው፡፡ “በእርግጥ በሕፃንነትና በልጅነት ወቅት ወላጅ ማጣት፣ ድጋፍ እንደሌለው የሐረግ ተክል ቢሆንም፣ መለያችን (ታፔላችን) ሆነው መቀጠል የለባቸውም፡፡ “ስለዚህ የጋራ ችግራችንን በጋራ እንቅረፍ” በማለት ሰባት የሀዋሳ ከተማ ወላጅ አጥ ህፃናትና ወጣቶች፣ ወላጅ አልባ ሕፃናትን የሚረዳና የሚያቋቁም “ፍቅር በሕይወት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትና ወጣቶች ማኅበር” መሠረቱ፤ በ1998 ዓ.ም፡፡ ማኅበሩ ታዲያ በአሁኑ ወቅት እንዳሰቡት ወላጅ አልባ ሕፃናትና ወጣቶችን እንደ ወላጅ ሆኖ እያበላ፣ እያጠጣ፣ እያለበሰ፣ እያስተማረ … ነው? ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ … ሕይወታቸውስ ምን ይመስላል? የተመሠረተበትን ዓላማ እያሳካ ነው? የወደፊት ዕቅዱስ ምንድነው? … በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አንድ የማኅበሩን ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ ጋር ቆይታ አድረጋል፡፡

ስምህ ማነው? ኃላፊነትህስ ምንድነው?

አብርሃም መሃሪ እባላለሁ፡፡ ኃላፊነቴ ደግሞ በደቡብ ክልል “ፍቅር በሕይወት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትና ወጣቶች ማኅበር” መሥራችና ኤግዚኩቲቭ ዳይሬክተር ነኝ፡፡

ማኅበራችሁ በአሁኑ ወቅት ምን እየሠራ ነው?

እኛ በዋናነት በልጆች ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን ነው የምንሠራው፡፡ የልጆቹን አዕምሮ ለማዳበርና አቅም ለማጐልበት የሚረዱ የተለያዩ የሕይወት ክህሎት፣ የሥነ ልቡና፣ የገቢ ማስገኛ፣ የአመራር ብቃት (ሊደርሺፕ) … የመሳሰሉ በርካታ ሥልጠናዎች እንሰጣቸዋለን፡፡

ሌላውና ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለው የከተማ ግብርና ነው፡፡ የዚህ ፕሮግራም ዓላማ ለልጆቹ የገቢ ምንጭ መፍጠር ነው፡፡ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር መሃል ከተማ ውስጥ የሰጠን 400 ካ.ሜ መሬት አለን፡፡ “ዓሣ አጥምደህ አትስጠው፤ እንዴት እንደሚጠመድ አስተምረው” እንደሚባለው ሁሉ፣ እኛም አምርተን እንኩ ተመገቡ ሳይሆን ቦታ ከፋፍለን ሰጥተን ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ እስከ ምርት መሰብሰብ ድረስ የክህሎት (የሙያ) ሥልጠና እየሰጠንና እየተከታተልን አምርተው ለራሳቸው እንዲጠቀሙ እያደረግን ነው፡፡

ይህ ማለት መረዳት (ተረጂነት) ብቻ ሳይሆን ቆፍሮና ጉልበት አፍስሶ በመሥራት ራስን በመርዳት ከችግር መላቀቅ እንደሚቻል ለማስተማር የምንጠቀምበት ዘዴ ነው፡፡ እርሻው ውጤታማ ነው፡፡ መንግሥትም፣ ልጆቹ የገበያ ችግር እንዳይገጥማቸው ከማምረቻው ቦታ በተጨማሪ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሸጫ ቦታ ሰጥቷቸው እዚያ እየሸጡ ገቢያቸውን እያሻሻሉ ነው፡፡

ሁለተኛው ተግባራችን ድጋፍና ክብካቤ ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ሁሉም ልጆች ድጋፍ አይደረግላቸውም፡፡ ከአባላቶቻችን መካከል ድጋፍ ማግኘት የሚገባቸውን መርጠን ነው የምንሰጠው፡፡

በዚህ ረገድ ከምንሰጠው አገልግሎት አንዱ የሥነ-ልቡና ምክር ነው፡፡ ለምሳሌ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ባለመስማማትና በመጋጨት የማያስፈልግ ችግር ውስጥ የሚገቡ ልጆች ካሉ ከተሞክሮአችን በመነሳት እንመክራለን፣ እናስተምራለን፡፡ በዚህ መንገድ የማይሳካ ከሆነ፣ በማኅበሩ አማካሪ (ካውንስለር) እንዲመከሩ ይደረጋል፡፡ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ የሥነ-ልቡና ባለሙያዎች ጋብዘን ልጆቹ አመለካከታቸውን እንዲለውጡ እንጥራለን፡፡

የሥነ-ልቡና ችግር አለባቸው ብለን የምናስባቸውን ልጆች ደግሞ እየለየን የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች እያዘጋጀን ዘና እንዲሉና እርስ-በርስ ልምድ እንዲለዋወጡና እንዲማማሩ እናደርጋለን፡፡

ትምህርት ቅርሳቸው መሆኑን እንዲያውቁ ማድረግም ሌላው የማኅበሩ ተግባር ነው፡፡ እነዚህ ልጆች ራዕይ ኖሯቸው ራሳቸውን ለውጠው ሀገር የሚጠቅሙ ዜጐች የሚሆኑት በትምህርት ነው፡፡ ስለ ትምህርት ጥቅም ከማስተማር በተጨማሪ ጎበዝ ተማሪ እንዲሆኑ የትምህርት መርጃ ድጋፎች እናደርግላቸዋለን፡፡ ከተለያዩ ኮሌጆች ጋር በመነጋገር ትምህርት ያቋረጡ ልጆች ነፃ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡ እንዲሁም ዓመቱን ሙሉ በሳምንት ሁለት ቀን የማጠናከሪያ ትምህርት (ቱቶሪያል) ይሰጣል፡፡ በበዓል ጊዜም ከኅብረተሰቡ ገንዘብ አሰባስበን ከብት አርደን በቅርጫ መልክ እናከፋፍላለን፡፡

ለትምህርት ድጋፍ በማድረጋችሁ የተገኘ ውጤት አለ?

አዎ! ከመካከላችን 35 አባሎቻችን ዩኒቨርሲቲ ገብተው እየተማሩ ነው፡፡ ወላጅ ማጣት፣ ተምሮና ተመርቆ፣ ሥራ ይዞ መኖር እንዳይችል የሚያደርግ ተስፋ መቁረጥና ጨለምተኝነትን ያስከትላል፡፡ “ለካንስ ዩኒቨርሲቲ መግባት ይቻላል፤ ቅርሳችን ትምህርት ነው” ማለት የሚያስችል አስተሳሰብ መፍጠራችን ለእኛ ትልቅ ውጤት ነው፡፡

ሐሮማያ፣ ሀዋሳ፣ ዲላ፣ አርባ ምንጭ … ዩኒቨርሲቲ መግባታቸው ትልቅ እርካታ ፈጥሮልናል፡፡

በተፈተናቸው ትምህርቶች በሙሉ “A” አምጥቶ ሕክምና የሚማር ልጅ አለ፡፡

በርካታ ልጆች ደግሞ ጐበዝ ናቸው፡ በዚህ ዓመት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል ዋንጫ ያገኘችው ትዝታ አስራት የእኛ አባል ናት፡፡

ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ ለአንዳንድ ወጪዎች ገንዘብ ያስፈልጋል፡ ማኅበሩ ያን ድጋፍ ያደርጋል?

ይህን ያህል ጐልቶ የሚጠቀስ አይደለም እንጂ አለ፡፡ ለሁሉም ልጆች ያሰብነውን ማድረግ ባንችልም የፎቶ ኮፒ ማድረጊያ ችግራቸውን ለመቅረፍ መቶ ብር ያገኛሉ፡፡

የእኛ አባላት የሆኑ ልጆች ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የሀዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ ለ3 ዓመት የኪስ ገንዘብ እየሰጠ ሸኝቷቸዋል፡፡ ማኅበሩ ደግሞ ልጆቹ ሲመረቁ ሱፍ ልብስ አሰፍቶላቸዋል፡፡

አንተ ወላጆችህን ያጣኸው ስንት ዓመት ሲሆንህ ነው?

አባቴ የሞተው በሕፃንነቴ ስለሆነ ምን ዓይነት አባት እንደነበረኝ አላውቅም፡፡

እናቴ 12 ዓመት ሲሆነኝ ነው የሞተችው፡፡ ያ ወቅት ለእኔ የጨለማ ጊዜ ነበር፡፡ ነገ የሆነ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ የሚል የተስፋ ጭላንጭል እንኳ አይታየኝም ነበር፡፡ የጨለምተኝነት ስሜት ውጦኝ ነበር፡፡

የዚያን ጊዜ ስሜትህ ምን ነበር?

ያኔ ባዶነት ብቻ ነበር የሚሰማኝ፡፡ ባዶነት ብዙ ነገርን ይገልፃል፡፡ የሚረዳህ ሰው ከጐንህ ስታጣ ብዙ የሚሰሙህ ነገሮች አሉ፡፡ አክስቴ ዝቅተኛ ገቢ ቢኖራትም በተወሰነ ደረጃ ትረዳኝ ነበር፡፡ ወላጆችህን ስታጣ በራስ መተማመን አይኖርህም፡፡

ራስህን ለማጥፋት የምትመኝበት ጊዜም አለ፡፡

ያንን ጊዜ እንዴት አሳለፍክ? ዕድገትህ ምን ይመስላል?

አነስተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ የሚወለዱ ልጆች እንደሚያደርጉት ሁሉ እኔም ያልሠራሁት ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ ጋዜጣ አዙሬአለሁ፣ ሸንኮራ ሸጫለሁ፣ የታክሲ ረዳት ሆኛለሁ፣ ሎሚና ብርቱካን ሸጫለሁ፣ ዕንቁላል፣ ሲጋራ፣ ቆሎ፣ …. አዙሬአለሁ፡፡ በአጠቃላይ ራሴን ለመለወጥ ብዙ እጥር ነበር፡፡ ግማሽ ቀን እየተማርኩ በቀሪው ጊዜ እሠራለሁ፡፡ እንደዚያ መሥራቴ ገንዘብ የማገኝበት ዕድል ፈጥሮልኛል፡፡ ወላጆቼ ወደዚች ምድር ለመምጣት ምክንያት ሆኑኝ እንጂ ማንነቴ የሚወሰነው በግሌ በማደርገው ጥረት ነው የሚል መርህ ይዤ ነው እዚህ የደረስኩት፡፡

ትምህርትህስ ምን ደረሰ?

ራሴን ለመለወጥ በማደርገው ጥረት አትክልት ቤት ከፍቼ ነበር፡፡ ነገር ግን ቦታው ሕገ-ወጥ ስለነበር ፈረሰ፡፡ ይኼኔ አማራጭ ጠፋ፡፡ የ10ኛ ክፍል ፈተና ወስጄ ውጤት አልመጣልኝም፡፡ ችግሮች ተደራረቡብኝ፡፡ እናቴ ከመሞቷ በፊት በሀዋሳ በኦሳ ትረዳ ነበር፡፡ በዚያ የተነሳ አስመዝግባኝ ስለነበር ስሜ እዚያ አለ፡፡ በትምህርት መቀጠል እፈልግ ስለነበር፣ የሙያ ትምህርት ለመማር እንዲረዱኝ ጠየቅኳቸው፡፡

ኦሳ እየረዳኝ ኤሌክትሪክሲቲ ተማርኩ፡፡ በሜታልወርክም ተመርቄአለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በኮሙኒቲ ዴቬሎፕመንት (በማኅበረሰብ ልማት) ዲፕሎማ አግኝቻለሁ፡፡

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሶስዮሎጂ (የማኅበረሰብ ጥናት) የ1ኛ ዓመት ተማሪ ነኝ፡፡

ይህን ማኅበር ለማቋቋም ምን አነሳሳህ?

ኦሳ እየረዳኝ ስማር ከወላጅ ማጣት ጋር በተያያዘ በውስጤ ልጆችን መርዳት፣ በሰብአዊ ተግባራት ላይ መሰማራት፣ … የሚል ሐሳብና ፍላጐት ነበረኝ፡፡ እኔ ባለፍኩበት መንገድ ሌሎች ወላጅ አልባ ሕፃናት እንዳያልፉ የማድረግ ፍላጐት ነው ይህን ማኅበር ለመመስረትና እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ምክንያት የሆነኝ፡፡

የማኅበሩ አባላት ቁጥር ምን ያህል ነው?

በአሁኑ ወቅት 842 ሕፃናት ወጣቶች አሉ፡፡ እነዚህ ልጆች በአቅም ግንባታ፣ በድጋፍና እንክብካቤ፣ በከተማ ግብርና፣ በአይቲና በተለያዩ ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች የሚሳተፉ ናቸው፡፡

ከትምህርት በተጨማሪ ያገኛችሁት ስኬት አለ?

ከትምህርትም በላይ ዋናው ስኬታችን የኅብረተሰቡን አመለካከት መቀየራችን ነው፡፡ በፊት ይባል የነበረው ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች በተለያዩ ድርጅቶች ተደግፈው ይረዳሉ የሚል ነበር፡፡ ዛሬ ግን ማኅበር መሥርተን የሠራናቸውን ተግባራት ሲያዩ “ለካንስ ወላጅ ያጡ ልጆች ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን መርዳትና ማስተማር ይችላሉ” የሚል አመለካከት በኅብረተሰቡ ውስጥ ፈጥረናል፡፡ ይኼ በመንግሥት፣ መንግሥታዊ  ባልሆኑ ድርጅቶችና በማኅበረሰቡ ውስጥ የፈጠርነው የአመለካከት ለውጥ ትልቁ ስኬታችን ነው፡፡

ሌላው ስኬት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሥራችንን አይቶ 400 ካ.ሜ በነፃ ሰጥቶናል፡፡ በዚያ ስፍራ የቢሮ ችግሮቻችንን የምንቀፍርበት መለስተኛ የሕፃናትና ወጣቶች መዋያ ማዕከል ሠርተናል፡፡ ማዕከሉ፣ ቤተ-መጻሕፍት፣ አይሲቲ የማኅበረሰብ መረጃ ያለውና ሌሎችም አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡

ይህን ማዕከል የሠራልን መንግሥት ወይም የዕርዳታ ድርጅት አይደለም፡፡ በየክልል ቢሮዎች የሚገኙ አሮጌ ዕቃዎች እየሰበሰብን በሐራጅ በመሸጥ ባገኘነው ገንዘብ ነው፡፡

የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?

ከክልሉ ሴቶች ሕፃናት ወጣቶች ቢሮ ጋር በመተባበር በጌዴኦ ዞን በዲላ፣ በወላይታ ዞን በሶዶ፣ በጋሙጐፋ ዞን በአርባ ምንጭ፣ በሐዲያ ዞን - በሆሳዕና ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ለመክፈት አንዳንድ ጥናቶች አድርገናል፡፡

በአማራ ክልል የተቋቋመ ተመሳሳይ ድርጅት አለ፡፡  ከዚያ ማኅበር ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ዕቅድ ይዘናል፡፡ ወደፊት ደግሞ ሀገር አቀፍ የወላጅ አጥ ብሔራዊ ማኅበር የመገንባት ራዕይ አለን፡፡ ይህን ተቋም በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ለማድረግ እንጥራለን፡፡

ወላጅ ያጣ ልጅ የተለያዩ ችግሮች ማለትም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ-ልቡናዊ፣ … ችግሮች እንደሚያጋጥሙት የታወቀ ነው፡፡ በእርግጥ ወላጆቻችን ወደዚች ምድር ለመምጣት (ለመወለዳችን) ምክንያት ናቸው፡፡ ነገር ግን የራሳችንን ሰብዕና የምንፈጥረው ራሳችን ነን፡፡ ሰው ይወለዳል፣ ይኖራል፣ ይሞታል፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ሕግ ነው፡፡  ወላጆቻችን ስለሞቱ እኛም ራሳችንን መጉዳትና መሞት የለብንም፡፡

በዓለም ላይ ተፅዕኖ የፈጠሩ ወላጅ አጥ ሰዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኔልሰን ማንዴላ፣ ነብዩ መሐመድ፣ … ወላጅ አጥ ናቸው፡፡ እንደነዚህ ሰዎች ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ትችላላችሁ፡፡ ስለዚህ ወላጅ በማጣታችሁ የሥነ-ልቡና ችግር ውስጥ እንዳትገቡ፣ ጠንካራ ሁኑ፡፡

መንግሥትም ወላጅ ላጡ ልጆች በተበጣጠሰ መልክ ድጋፍ ከሚያደርግ በተደራጀ መንገድ ድጋፍ ቢሰጥ ለልጆቹ ጥሩ ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡

ብዙ የውጭ አገር ሰዎች ወላጅ አጥ ልጆችን በጉዲፈቻ እየወሰዱ ነው፡፡ አሳዳጊ ሰዎች ከውጭ እየመጡ ከሚወስዱ ይልቅ ሕፃናቱን ኢትዮጵያውያን በጉዲፈቻ እየወሰዱ ከአብራካቸው እንደተገኙ ልጆች ቢያሳድጉ፣ ሕፃናቱ ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ ውስጥ አይገቡም፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ መበረታታት አለበት እላለሁ፡፡

 

 

Read 3439 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:36