Sunday, 22 August 2021 12:43

“ሞት በውክልና” አዲስ መፅሐፍ ገበያ ላይ ዋለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

የደራሲ ሀይሉ ወርቁ ሥራ የሆነውና በፍቅር፣ የህክምና በሳይኮሎጂ በህግና በመሰል ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥነው “ሞት በውክልና” አዲስ መፅሐፍ ገበያ ላይ ዋለ።
መፅሐፉ በዋናነት ከህግ፣ ከፍትህና ርትዕ፣ ከህክምና ቴክኖሎጂና ሞራል፣ ከሃይማኖት አስተምህሮቶች፣ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና ስምምነቶች ከማህበረሰብ እድገት አንፃር ደራሲው ስራውን ለጥበብ ዕድገት በሚጠቅም መንገድ ያስቀመጠበት ድንቅ መፅሐፍ ስለመሆኑ በመፅሐፉ ጀርባ ማስታወሻ ያሰፈሩ ምሁራንና የህግ ባለሙያዎች መስክረውለታል። ደራሲው በሙያው ሲቪል መሃንዲስ ሲሆን፣ በዚህ መፅሐፍ ፍቅርን በጥላቻ፣ እምነትን በክህደት፣ ቸርነትን በሌብነት እየቀየሩ ለሚኖሩ እኩይ ሰዎች በቻሉት መጠን ከተበዳይና ከህግ ቢያመልጡም ሞት ግን የማይቻል ጣዕረ-ሞትም ከባድ ስለመሆኑ ደራሲው ሀይሉ ወርቁ በማስረጃ የሞገተበት ነውም ተብሏል።
“ሞት በውክልና” መፅሐፍ በታዋቂ ገጣሚያን ግጥም የተገጠመለት፣ በድንቅ ዘሜኛ ዘፈን የተዘፈነለት ልዩ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተፃፈ እጅግ አዝናኝና አስተማሪ ነው የተባለለት ሲሆን፣ በግራፊክ ማተሚያ ቤት በጥራት ታትሞና በ256 ገፅ ተቀንብቦ በ250 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መፅሀፉ  በዋናነት በጦቢያ መፅሐፍ መደብር አከፋፋይነትና በሁሉም አዟሪዎች እጅ የሚገኝ ሲሆን በውጭ ለሚኖሩም በአማዞን የመገበያያ ኔትወርክ ላይ ለሽያጭ መቅረቡም ታውቋል።
ደራሲው ሀይሉ ወርቁ ከዚህ ቀደም “የወታደሩ ሚስት” “የነፍስ እናት እና ልጇ”፣ “የዴልታው ልዕልት”፣ “ዕፀ ሀበቅና ጭራ አልባዎች” “ዲ ሳንግ ዌ”፣ “ፓቶጵያ ወደ ዮቶጵያ መድረሻ መንገድ” የተሰኙና ሌሎች መፅሐፎች ለንባብ ያበቃ ሲሆን ለመታተም የተዘጋጁ በርካታ መፅሐፎች በእጁ ላይ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል።

Read 2184 times