Sunday, 22 August 2021 13:21

የጥላቻ ንግግሮች የጋረጡት አደጋ!?

Written by  ሙሼ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)


            የጥላቻ ቃላትና ሀረግ ለዘር ፍጅትና ለዘር ማጥፋት አቀጣጣይ መሳርያ ሆነው ያውቃሉ:: በዚህ ሰበብ በየሀገሩ በሕግ የታገዱና የሚያስጠይቁ ቃላት፣ ሀረግና ምልክቶች አሉ፡፡ የሃገር፣ የዜግነት፣ የሰንደቅ ዓላማን ክብር የሚያዋርዱ፣ በማንነት፣ በቀለም፣ በጾታና በሃይማኖት ላይ ተመስርተው ጥላቻና የዘር ማጥፋት ቅስቀሳ የሚያደርጉትን በሕግ ያገዱ በርካታ ሀገራት አሉ፡፡ ሩዋንዳ፣ ጀርመን፣ ቤልጂየምና ካናዳ ጥቂት ምሳሌ ናቸው፡፡
“እቺ ሀገር” የሚለው ሀረግ ኢትዮጵያ ሀገሬ ወይም ሀገራችን የሚለውን ቃል ተክቶ ወደ መዝገበ ቃላታችን ከገባ 30 ዓመት ሆኖታል፡፡ ቃሉ አግላይ፣ የሀገር ክብርን የሚደፍቅና እራስን ከሀገር የሚነጥል ነው። ሀረጉ በተለይ ኢትዮጵያን ሀገሬ ብሎ መጥራትን የሚጸየፉ ነገር ግን ጥቅሟን የሚፈልጉ ሃይሎች የፈጠሩት ከፋፍለህ ግዛው ነው፡፡ ይህ ጸያፍ ሀረግ ተደጋግሞ ስለተነገረ ዛሬም አዕምሯችን ላይ ታትሞ ከላንቃችን ጋር ተጣብቆ አልላቀቅ ያለን በባለስልጣኑ፣ በአርበኛው፣ በሰራዊቱ አባላት፣ በፖለቲከኛውና በአክቲቪስቱ ዘንድ እንደዘበት የሚነገር ቃል ሆኗል፡፡   
ላላፉት 30 ዓመታት የሀገርን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ፣ ከፋፋይ፣ እርስ በርስ የሚያናቁሩን፣ የክፋትና የመሰሪነት ቃላት እንደ አሸን ተራብተው በጥላቻ እንድንተያይና በደም እንድንፈላለግ አድርገውናል፡፡ እነዚህ ቃላት እስር፣ እንግልትና ስደት ካደረሱብን ጉዳት በላይ እንደ ተተኳሸ ጥይት በመሆን አስጠቅተውናል፣ ለጥላቻና ለግጭት ዳርገውናል፣ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም ከባድ ዋጋ አስከፍለውናል ፡፡
ኢትዮጵያ ሁላችንንም አቅፋና ደግፋ የምትይዝ ለሁላችንም የምትመች የእኩልነት ሀገር እስክትሆን ድረስ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበን በርካታ ተሃድሶዎች ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ አንዱ ተሃድሶ ደግሞ እንዲዚህ ዓይነት ከፋፋይና ለጥፋት በመሳርያነት የሚያገለግሉ ቃላቶችን ከመዝገበ ቃላታችንና ከአንደበታችን የሚያስወገድ የባህል አብዮት ማካሄድ ነው።
እንዲወገዱ የምንሻቸው፣ እነዚህ ቃላት በትውልድ ወስጥ ዳግሞ እንዳያንሰራሩ ከመገናኛ ብዙኅን፣ ከትምህርት ተቋማትና በአስተዳደር ቋንቋነት ጭምር መገልገያ ከመሆን በሕግ እንዲታገዱ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ኢትዮጵያዊነት የትኛውንም ጫናና ተጽእኖ ተቋቁሞ የሚዘልቅ ጽንሰ ሃሳብ እንደሆነ ዛሬም በተግባር እየታየ ነው። የበለጠ እናጠብቀውና መደላድሉን እናጠነክረው ዘንድ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያውያንን የከበበውን ፈርጀ ብዙ እሾህና አሜኬላ በየጊዜው ልናጸዳና ልናጠራ ያገባል፡፡

Read 1551 times