Saturday, 28 August 2021 12:42

ልዩ ጣዕም ያላቸው ቡናዎችን ያቀረቡ 39 አምራቾች ተሸለሙ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    ኢትዮጵያ ዘንድሮ በታሪክ ከፍተኛውን የውጪ ምንዛሬ አግኝታለች
                     
             በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በተካገሄደው የባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ውድድር (Cup of Excellence) 39 ቡናዎች አሸናፊ ሆነው ተሸለሙ። ሽልማቱ ሀሙስ አመሻሽ ላይ በስካይላይት ሆቴል የግብርና  ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በተገኙበት ተካሂዷል። በሽልማት ስነ-ስርዓቱም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘቷ የተገለጸ ሲሆን ለዚህ ውጤት እንደ “ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ” አይነት ልዩ ጣዕም ያላቸው ቡናዎች ውድድር ትልቁን ሚና ሳይጫዎት እንዳልቀረ ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር፣ የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት ዩኤስ አይ አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ኢትዮጵያ” ከኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ የባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ውድድር፤ 1849 የቡና ናሙናዎች  ለውድድር መቅረባቸው የታወቀ ሲሆን በሶስት  ዙር በተካሄደ ቅምሻ 40 ያህል ቡናዎች  ከ85 በላይ ውጤት በማስመዝገብ ወደ መጨረሻው አለም አቀፍ ውድድር ማለፋቸውም በዕለቱ ተገልጿል።
በአሜሪካ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ በአውስትራሊያ፣ ኖርዌይና በጃፓን የቡና ላብራቶሪዎች በተከናወኑ የቡና የቅምሻ ክንውኖች ከ40ዎቹ አንዱ ከውድድር ሲወጣ 30 የቡና ናሙናዎች ከ87 በላይ ነጥብ በማምጣት የ2021 የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አሸናፊዎች ሆነዋል።
ከ30 ቡናዎች አምስቱ ደግሞ ከ90 በላይ ነጥብ በማግኘት ፕሬዚዳንሽያል አዋርድ የሚባለውን ሽልማት የተጎናፀፉ ሲሆን፣ ከ85-87 ነጥብ ያስመዘገቡ ዘጠኝ ቡናዎች ደግሞ ብሔራዊ አሸናፊ መሆናቸው ተገልጿል።
“ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ”  የተባለው ውድድር አዳዲስ የቡና ዝርያዎች እንዲታወቁ ከማድረጉም በተጨማሪ የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ተናረዋል።
በዚህ ዕለት ልዩ ተሸላሚ የሆነው የሲዳማው ቡና አምራች አቶ ታምሩ ታደሰ ያቀረበው አንድ ኪሎ ቡና በግልጽ ጨረታ በ330 ዶላር ወይም በ14 ሺህ 533 ብር  በመሸጥ 1ኛ ከመውጣቱም በላይ እስከዛሬ የነበረውን ከፍተኛ የቡና መሸጫ ዋጋ ሪከርድ መስበሩም ታውቋል።
አቶ ታምሩ ታደሰ 19 ከረጢት ቡና በ346 ሺህ 643 ዶላር በመሸጥ መደመምን መፍጠሩ የተነገረ ሲሆን ይህ አይነቱ ውድድር እስከዛሬ ከምርታቸው ብዙ ተጠቃሚ ያልነበሩ አርሶ አደሮችን ህይወት ለውጦ ማየት በእጅጉ እንደሚስደስት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ገልጸዋል። ውድድርና ሽልማቱም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይባላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት አመቱ በታሪኳ 248 ሺህ ቶን ቡና ለአለም አቀፍ ገበያ አቅርባ 927 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷም በዕለቱ ተገልጿል።
በሁለተኛው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር ስነ-ስርዓት ላይ ከግብርና ሚኒስትሩ በተጨማሪ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴና የብሄራዊ ባንክ ገዥው ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ፣ለአሸናፊዎቹ ሽልማት አበርክተዋል።



Read 750 times