Saturday, 28 August 2021 12:50

“በወለጋ በተፈፀመ ዘር የለየ ጥቃት ከ340 በላይ ሰዎች ተገድለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  በተለያዩ ክልሎች እየተፈፀሙ ያሉ የሠብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ አስቸኳይ የማሳሰቢያ መግለጫ ያወጣው ኢሰመጉ ነሀሴ 12 ቀን 2013 በአንድ ቀን ብቻ በወለጋ ከ340 በላይ ዜጎች ዘር የለየ ግድያ እንደተፈፀመባቸው አስታውቋል፡፡
“ሠብአዊ መብት ማክበር የሁሉም ግዴታ ነው” በሚል ከትናንት በስቲያ አስቸኳይ  ጋዜጣዊ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ ኢሰመጉ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣አፋር፣ ትግራይ እና ሶማሌ ክልል እየተፈፀሙ ነው ስላላቸው የሰዎች ግድያና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አትቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን በቂልጡ አቦ ቀበሌ ነዋሪ የበሩት 7 ሰዎች ሐምሌ 29 ቀን 2013 በሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸውንና ከእነዚህም 5ቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
እነዚሁ ታጣቂዎች ነሀሴ 12 ቀን 2013 ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ አጋሳ አበሆ እና ትንቢያ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያናትን መንደር እና የአማራ ብሔር ተወላጆችን ገድለው ከብቶቻቸውን እየነዱ ወደ አሌልቱ ወንዝ አካባቢ መውሰዳቸውን፣በተመሳሳይ መረጋ ጅሬኛ ሲደሮ ቀበሌ በመግባት በአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት በመፈፀም 41 ሰዎችን መግደላቸውን እንዲሁም በሶስት ሰዎች ላይ አካል ጉዳት ማድረሳቸውን ሪፖርቱ አትቷል፡፡
በተጨማሪም በዚያው ቀን ነሀሴ  12 ቀን 2013 ዓ.ም በምስራቅ ወለጋ ዞን ከረ፣ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ከሶስት መቶ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ከአንድ መቶ በላይ መቁሰላቸውን፣ የበርካቶች ቤት መዘረፉን፣ መቃጠሉን እንዲሁም ከተለያዩ ቀበሌዎች ከዘጠና ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የክልሉ መንግስት በበኩሉ ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ በሸኔ ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ኢሰመጉ በዚህ መግለጫው በአማራ ክልል ደግሞ በህወኃት ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈፀመው ጥቃቶች ሳቢያ የበርካታ ሰዎች ህይወት እየጠፋ መሆኑንና በርካቶች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አመልክቶ በዚህ ጥቃት ህጻናትና አዛውንት በእጅጉ እየተጎዱ ነው ብሏል፡፡
ነሀሴ 13 ቀን 2013 በደብረ ታቦር ከተማ በከባድ መሳሪያ የሰዎች ህይወት ማለፉን በሌላ በኩል ነሐሴ 12 ቀን 2013 በዚያው ከተማ ለህወኃት መረጃ ታቀብላላችሁ በሚል ከፍርድ ውጪ በተፈፀሙ ጥቃቶች የሰዎች ህይወት ማለፉን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
 በአፋር ክልል በህወኃት ጥቃት በስደተኞች ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ሰዎች ላይ አሰቃቂ ጥቃት መፈፀሙን በዚህም በዋናነት ህጻናትና አቅመ ደካሞች ተጎጂ እንደነበሩ ሪፖርቱ ያትታል፡፡
በትግራይ ክልል ደግሞ አሁንም ህጻናትን ለውጊያ የመመልመሉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን፣በትግራይ ማንኛውም መገናኛ ዘዴ መቋረጡን ሪፖርቱ አመልክቷል፡
በሶማሌ ክልል ከገርባ ሰኤ ወይም ከገዳማይቱ ከተማ በደረሰባቸው ጥቃት  ምክንያት ተፈናቅለው በሶማሌ ክልል ሙሉ ከተማ፣ሙሉ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ተጠልለው ከሚገቡ ሰዎች 188 የሚሆኑ መገደላቸውን 88 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን 692 አባወራዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
መንግስት በማንኛውም ቦታ የሚደርስን የሰብአዊ መብት ጥሰት መከታተል እና ጥበቃ የማደረግ ሃላፊነት እንዳለበት ያመለከተው ኢሠመጉ ይሄን ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጉዳት የደረሰባቸውን በሙሉ አቅሙ እንዲደግፍ፣የተፈፀሙ ጥቃቶቸን በአግባቡ አጣርቶ እርምት እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል፡፡
በተመሳሳይ በተለይ በኦሮሚያ በወለጋ ከረሙ ወረዳ የተፈፀመውን ዘር ተኮር ጥቃት አስመልክቶ የደረሰበትን መረጃ ይፋ ያደረገው መንግስታዊ የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በምስራቅ ወለጋ ጊዳ ከራሙ ወረዳ ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ሃይሎች ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ነሀሴ12 ቀን 2013 ዓ.ም “የኦነግ ሸኔ” አባላት ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች በአከባቢው ነዋሪዎች ላይ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት መፈፀሙንና በዚህም ከ150 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢውን ነዋሪዎች መረጃ ዋቢ አድርጎ አስታውቋል፡፡
በቀጣይም የአካባቢውን የነዋሪዎች ደህንነት ለማረጋጋት የአካባቢው የፀጥታ ሃይል ሊጠናከር እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ያቀረበው ኮሚሽኑ የንጹሀን ግድያዎች መበራከት በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን አመልክቷል፡፡


Read 11540 times