Print this page
Tuesday, 31 August 2021 00:00

ቴክኖሎጂ፣ እንደባለቤቱ ነው - ያለማልም፣ ያጠፋልም።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)


             ከፅሁፍ ሕትመት ጀምሮ፣ እስከ ሬዲዮና ቲቪ፣ እስከ ኢንተርኔትና ሞባይል፣ ፌስቡክና ዩቱብ ድረስ ሁሉንም “የሃሳብ ቴክኖሎጂዎች” ተመልከቱ።
የውሸት መረጃና የሐሰት ውንጀላ ለማናፈስ ያገለግላሉ። እውነተኛ መረጃ ለማግኘትና መልካም ግንኙነት ለመፈጠርም ይረዳሉ። እንደ አያያዛችን ናቸው- ለክፉም ለደጉም፡፡
የሰው ታሪክ፣ የ200 ሺ ዓመት ታሪክ ነው ይባላል። በአእምሮና በአካል፣ ከምር የሰው ቅርፅ የተፈጠረው በዚያ ዘመን እንደሆነ፣ ጠቢባኑ ይገልፃሉ። ቦታውም፣ ምስራቅ አፍሪቃ ነው ይላሉ። በተለይም ኢትዮጵያን፣ በተለይም የአዋሽ ሸለቆን ይጠቅሳሉ - የሰው ልጅ መገኛ በማለት።
“አይ፤ የሰው፣ ታሪክ ከ50 ሺ ዓመት ብዙም አይበልጥም” ብለው የሚያስተምሩም አልጠፉም። ታሪክ ማለት፣ “መውለድና መወለድ” ማለት ሳይሆን፣ “የተግባርና የኑሮ ለውጥ” ማለት ነዋ። የሰው ልጆች፣ ከኢትዮጵያ “አገራቸው” ተነስተው፣ አለምን በየአቅጣጫው እያዳረሱ ነበር - የዛሬ 50 ሺ ዓመት። ይሄ፣ የተግባርና የኑሮ ለውጥ ነው - ታሪክ።
ግን፣ ከቦታ ቦታ መዘዋወር ብቻውን፣ እንደ ታሪክ ሊቆጠር ይችላል?
በእርግጥ፣ ከቦታ ቦታ መንከራተት፣ አቀበት ቁልቁለቱን መውጣትና መውረድ፣ ተራራና ባሕሩን መሻገር፣ ቀላል “ተግባር” አይደለም።
ቢሆንም ግን፤ ለምልክት ያህል፣ ይህ ነው የሚባል ጥሪት ትቶ የማያልፍ ተግባር፣ምን ተብሎ ይተረካል? ለብዙ ትውልድ ይቅርና፣ ለልጅ ልጅ የሚተርፍና የሚተላለፍ  ቅንጣት ቅርስ የማይወጣው ጉዞ፣ እንዴት እንደ ታሪክ ይቆጠራል? ከሌሎች እንስሳት ያልተለየ ልፋትና ድካም ነው- የያኔው የሰው ልጅ የኑሮ ውጣ ውረድ።
የሰው ልጅ ኑሮ፣ከዘመን ዘመን፣ከትውልድ ትውልድ ብዙም ለውጥ አልታየበትም። ያው ነው፡፡ እንደ ጦጣ፣ ፍራፍሬውን ቅጠላቅጠሉን ይሸመጥጣል።
እንደ ቀበሮ ለአደን ይወጣል፤ አድፍጦ ያጠምዳል። ዋሻ ውስጥ ይዋለዳል። ውሃ ለመጠጣት ወደ ወንዝ ይወርዳል።
የሚሸመጠጥ ፍራፍሬና የሚታደን ጥንቸል ከጠፋ፤ ድርቅ ወይም ጎርፍ ከበረታ፤ ጥቃትና አደጋ ከበዛ፣ ወደ ሌላ ቦታ ይሰደዳል። ይሄ፣ የሰው ልጅ ልዩ ታሪክ አይደለም። የሌሎች እንስሳት ኑሮ፣ ከዚህ በምን ይለያል? ይልቅስ፣ የሰው ልጅ ታሪክ የሚጀምረው፣ የዛሬ 7ሺ ዓመት ገደማ ነው በማለት የሚያስተምሩ፣ ከአዳም ትረካ ጋርም የሚያዛምዱት ምሁራን አልጠፋም።
ታሪኩ፣ወደ 10ሺ ዓመት ሊደርስ ይችላል። እርሻና የከብት እርባታ የተጀመረበትን ዘመን ለመግለፅ።
 አጠር ስናደርገው ደግሞ፣ወደ 5ሺ ዓመት ሊጠጋ ይችላል-  በፅሁፍ “ሀ” ተብሎ ታሪክ የተመዘገበበትን ጊዜ፣ እንደ ታሪክ መነሻ ይዘን፣ ዘመኑን ከቆጠርን ማለት ነው፡፡ የፅሁፍ ፈጠራ፣ “የመረጃና የሃሳብ ቴክኖሎጂ” ልንለው እንችላለን።
ለነገ፣ሩ ዋና የተግባር የቴክኖሎጂ ታሪክ የተከሰተውም ከዚያ ዘመን ነው- ጋሪ የተፈጠረበት ዘመን። የመጀመሪያው መንኮራኩር በሉት። የሚሽከረከሩ ነገሮችን፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች ማዋል! ይሄ ቀላል የሚመስል የተግባር ቴክኖሎጂ፣ የሰውን ታሪክ ምን ያህል እንደቀየረ፣ ዓለም ይቁጠረው- ተቆጥሮ ካለቀ።
ገና ከመነሻው፤ ለሰው ምንም ግንኙነት ያልነበራቸው ቃላት፣ ማለትም ሽክርክሪትንና ጉዞን እስከማቆራኘት የደረሰ ነው- የቴክኖሎጂው ሃያልነት። መንኮራኩር እና መርከብ የሚሉት ቃላት፣ ጉዞን የሚያመለክቱ ናቸው፤… መነሻቸው ግን ሽክርክሪትን የሚገልጽ ቃል እንደሆነ የደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት ይዘረዝራል።
ከጋሪ እስከ ብስክሌት፣ከጎራዴ እስክ ቀስት፣ ከመኪና እስከ አውሮፕላን፤ከታንክ እስከ ሚሳዬል፣መቆጣጠሪያ ከዚያም በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ተርባይንና የህንፃ አሳንሰር፣ የፂም መላጫና የፀጉር ማድረቂያ፣ የልብ ስፌትና የየፋብሪካው ሞተር በሙሉ፣ የሽንኩርት ማሳ ውሃ መሳቢያና የኒዩክሌር ሃይል ንጥረ ነገር ማብለያ…እልፍ የልማትና ጥፋት መሳሪያዎች፣
የሽክርክሪት ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ናቸው- (Wheel technology እንዲሉ።) (“simple machine” ተብለው ከሚታወቁት ከስድስቱ መሰረታዊ የስራ ማስኬጃ መላዎች መካከል አንዱና ትልቁ፣ ይህ ነው (Wheel & axel ወይም wheel & gear)፡፡ ማሽን የተባለ መሳሪያ በሙሉ፣ የስድስቱ ቅንብር ነው፡፡ ዋናው ደግሞ፣ የሽርክሪት ቴክኖሎጂ ነው፡፡
ያላዳረሰው ያልነካው የኑሮ መስክ የለም ማለት ይቻላል። ኑሮን ለማሻሻልና ለማደርጀት፤ ሕይወትን ለማለምለምና ለማሳመር፣… ዘዴና መላ የማያልቅበት የቴክኖሌጂ  ፈጣራ ነው- የሽክርክሪት ቴክኖሎጂ። ታዲያ፣ የሰው ታሪክ የጀመረው፤ ያኔ ተሸከርካሪ ጋሪ የተፈጠረ ጊዜ ነው ቢባል ይገርማል? ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተርፍ የተባረከ ቅርስ ነውና። ካወቁበትማ፣ እየተሻሻለ፣ እየረቀቀ፣ ብዙ ዓይነት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚያፈራ፣የተባረከ መነሻ ሊሆን ይችላል- ከጋሪ ወደ መኪናና አውሮፕላን ለመሸጋገር የሚረዳ።
ይህ ግን ቀላል አይደለም። የጋሪ ቴክኖሎጂና ሙያ፣ አንዴ በአዋቂዎችና በጥበበኞች ከተፈጠረ በኋላ፣… ጋሪው ሳይሰበር ከልጅ ወደ ልጅ ይተላለፋል፤ ሙያውም በዘልማድ ለበርካታ ዓመታት መዝለቅ ይችላል።
እውነተኛ መረጃና የተጣራ እውቀት፣ጠቃሚ ሃሳብና ትክክለኛ የአስተሳሰብ ቅኝት ግን፣ እንደ ጋሪ በቀላሉ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ነገር አይደለም። እንጨት እንደመቁረጥና እንደመጥረብ፣ በዘልማድ የሚሞክሩት አይደለም- ሃሳብና አስተሳሰብ።
ከትውልድ ትውልድ ሊተርፍ ይቅርና፣ ለአዋቂውና ለአሳቢው ሰውዬም ይቸግረዋል - እውቀቱን በቅጥ ለማደርጀትና ሃሳቡን መስመር ለማስያዝ ይከብደዋል።
ሁነኛ መላ የተገኘው፤ የፅሁፍ ቴክኖሎጂ የተፈጠረ ጊዜ ነው።
በአእምሮ ብቃት የመጠቁና ተራቀቁ ሳይንቲስቶችን አስታውሱ-ብእርና ጠመኔ ነው የሙያ መሳሪያቸው፡፡ አርኪሜዲስ፣ ኒውተን፣ አንስታይን፣… የፊዚክስና የሒሳብ ሊቅ የተባለ ሁሉ፣ ዩክሊድ፣ ጋሊሊዮ፣ ኬፕለር ሁሉ አዋቂነታቸውና አሳቢነታቸው በምናብ  ብቻ አይደለም፡፡ የጀግንነት ዝነኛ ሆኑት ያህል፣ የዚያን ያህል፣ ውሏቸው ከፅሁፍ ጋር ነው።
 የተፃፉ ነባርና አዲስ ግኝቶችን እያሰሱ እየተከታተሉ ያነብባሉ። በሌላ አነጋገር፣ እድሜ ለጽሁፍ ቴክኖሎጂ፣ የብዙ ዘመናትን መረጃና የብዙ ሰዎችን እውቀት መማር ችለዋል- ጽሁፎችን በማንበበብ።
አለበለዚያማ፣ የሰው ልጅ ታሪክ፣ ሁልጊዜ የጋሪ ቴክኖሎጂን እንደ አዲስ የመፍጠር አዙሪት  ነበር- Reilnventing the wheel እንዲሉ። በፅሁፍ የሚከማች እውቅና ትምህርት ባይኖር ኖሮ፣የሰው የሳይንስ እውቀት ሁሌም ከዜሮ የሚጀምር የአጭር ዙር ሩጫ በሆነ ነበር፡፡
ደግነቱ፣ ነባሮቹን መረጃዎችና እውቀቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጽሁፍ በመማር፤ ተጨማሪ አዳዲስ መረጃዎችን ወደ ማሰስና ወደ መመርመር፤ ተጨማሪ አዳዲስ ግንዛቤዎችን እያሰላሰሉ ወደ መጨበጥና ወደ ማወቅ መገስገስ ይቻላል።
ታዲያ፣ መረጃዎችን መመርመርና ማሰላሰል፤ ፍሬ ሀሳቦችን ማገናዘብና እየቀመሩ ማስላት፣ እንዲሁ በምናብ ብቻ ወጥነው፣ በምናብ የሚጨርሱት ነገር አይደለም። መረጃዎች ተጣርተው እየተመሳከሩ በወጉ የሚደራጁት በፅሁፍ ከተመገዘቡ ነው። ሃሳቦችና ቀመሮች በውጥን ተቆርጠው ተረስተው የማይቀሩት፣ በፅሁፍ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ነው፡፡ ፅሁፍ ባይኖርስ? ሁሉንም ሸምድዶ አይቻልም። አንዱ ሃሳብ ሌሎች ተዛማጅ ሃሳቦችን እየመዘዘና እየተተበተበ ውሉ ይጠፋል፡፡  የአእምሮ ትኩረት እየዋለለና እየተበታተነ ይባክናል፡፡ አንዱ ቀመር በከፊል ብቻ ተዘንግቶ ሌላኛው ስኬት በጅምር ተወሳስቦ እንደ ጉም እየሳሳ ነገሩ ሁሉ መቅኖ ያጣል። መረጃዎችና ሃሳቦች፣ ቀመሮችና ስሌቶች… ለወግ ለማዕረግ የሚበቁት፣ ወደ እልባትና ወደ እውቀት ግኝት የሚደርሱት፣ በፅሁፍ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ነው።
ለዚህም ነው ለሂሳብና ለፊዚክስ ጠቢባን፣ ወረቀት ላይ በብዕር፣ ሰሌዳ ላይ በጠመኔ  በፅሁፍ መተንተን፣ ቁጥሮችን ማስላት፣ የሙያቸው መለያ ባሕር የሆነው።
ምናለፋችሁ! ሃሳብና ፅሁፍ፣ እንደ አእምሮና አካል ብንቆጥራቸው ይሻላል።
 የአየን ራንድን አባባል ልጠቀምና፣አእምሮ ያለ አካል፣ የማይጨበጥ የማይዳሰስ የጣዕረ ነፍስ ጉም ነው። ብዙ ሃሳቦች ይበታተናሉ፡፡ ብን እያሉ ይጠፋሉ፡፡
 አካል ያለ አእምሮ ደግሞ፣ በእንቅልፍ ልብ እንደሚራመድ ሰው፣ ነፍሱ ከወጣ በኋላ  እንደሚንፈራገጥ እንስሳ፣ እንደ ዞምቢ ነው- በደመነፍስ  የሚደናበር ትርጉም የለሽ ተንቀሳቃሽ ግዑዝ እንደማለት ነው- አእምሮ ቢስ አካል።
ልክ እንደዚያው፤ ግንዛቤ የለሽ ፅሁፍ፣ ትርጉም የለሽ የጭረቶች ግርግር ይሆናል። ፅሁፍ የለሽ ሃሳብ ደግሞ፣ ከዘልማድ ከደመነፍስ አዙሪት የማያድን ህልም ይሆናል- የጋሪ ቴክኖሎጂ ሁሌም እንደ አዲስ የመፍጠር አዙሪት ውስጥ እንደመባዘን ነው።
የፅሁፍ ቴክኖሎጂ ባይኖር ኖሮ፣ የሰው ልጅ ታሪክ፣ ከአዙሪት ድግግሞሽ የማይሻል ይሆን ነበር።
ታዲያ፣ ከጽሁፍ ጋር ነው የሰው ልጅ ታሪክ ሀ ብሎ የሚጀምረው” ቢባል ምን ይደንቃል?።
ታሪኩን ለመመዝገብ አስተማማኙ ዘዴ፣ የጽሁፍ ቴክኖሎጅ መሆኑ፣ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። ታሪክን መስራትና ታሪክን መመዝገብ፣ እርስበርስ የተጣመሩ ክስተቶች ናቸው። አንዱ ያለሌላው አይኖርም፡፡ ነገር ግን፣ የሃሳብ ቴክኖሎጂ እንደተግባር ቴክኖሎጂ፣ ለልማት ብቻ ሳይሆን ለጥፋትም ይሆናል፡፡ ማዕድን መቆፈሪያ፣ቤት መሳሪያ ይሆናል የተግባር ቴክኖሎጂ የመረጃ ወይም የሃሳብ ቴክኖሎጂስ? የውሸት መረጃ፣ የተሳሳተ ሃሳብና ጭፍን አስተሳሰብ ከፅሁፍ ቴክኖሎጂ ጋር ሲገጣጠምስ? ይኸኔ ነው መፍራት፡፡
የዛሬ 550 ዓመት፣ የህትመት ቴክኖሎጂ የተፈጠረ ጊዜ፣ የአውሮፓ ምድር ምነኛ በጥላቻ የፅሁፍ ስብከቶች እንደተናጠ ከዚያም በጦርነት እንደታመሰ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ለዚያውም የአንዳንዶቹ ለ30 ዓመት ባልተቋረጠ የእልቂት ጦርነት ተጫርሰዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ እስከ 80 ዓመት በዘለቀ ጦርነት ተተራምሰዋል፡፡
የዛሬ 220 ዓመት፣ የፈረንሳይ አብዮት የተቀጣጠለው፣ አሰቃቂ የእርስ በርስ ፍጅትና ሽብር የነገሰው፤ በመቶ የሚቆጠሩ ጋዜጦች በተፈለፈሉበት ዘመን ነው፡፡
የ20ኛው ክፍለ ዘመን አምባገነኖችና አመፀኞች፣ ጨካኝ መሪዎችና ነውጠኛ የመፈናቀል መንግስት ሴረኞች ሁሉ፣… ማተሚያ ቤቶችን፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያዎችን ለመቆጣጠር ያደረጉት ሩጫ ማስታወስም ይቻላል፡፡
የዩጎዝላቪያና የሩዋንዳ እልቂቶችም እንዲሁ፣ ከፅሁፍና ከመረጃ ቴክኖሎጂዎች ጋር የተዛመዱ ናቸው፡፡
ዛሬ በሳተላይትና በኢንተርኔት ዘመን፣ በሞባይልና በፌስቡክ በዩቲዩብ ዘመን ደግሞ፣የእስከዛሬዎቹ የመረጃ ቴክኖሎጂዎች ሁሉ ተደራርበው ዘመኑን የጡዘት ዘመን አድርገውታል፡፡
ውጤቱም እንደአያያዛችን ይሆናል፡፡ አያያዛችን ደግሞ አላማረም፡፡ ምን አይነት አደገኛ ዘመን ውስጥ እንደገባን፣ገና በቅጡ አልተረዳንም፡፡Read 7804 times