Print this page
Friday, 27 August 2021 00:00

አባሀዋ ትሬዲንግ አምስት የትራፊክ ሼዶችን ሰርቶ አስረከበ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

   “የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በርትተን እንድንሰራ ያግዘናል” - ም/ኮማንደር ብርሀኑ ቱፋ
                                
               የዋን ውሃ አምራች ኩባንያ የሆነውና በሶስተኛ ትውልድ የሚመራው አባሃዋ ትሬዲንግ ዋና መስሪያ ቤቱ በሚገኝበት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍል ከተማ ለሚገኙና ከፍተኛ የትራፊክ እንቅስቃሴና አደጋ ይከሰትባቸዋል ተብለው በተለዩ አምስት ቦታዎች ላይ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቀ የትራፊክ ፖሊሶች ማረፊያ ሼዶችን ሰርቶ አስረከበ፡፡
ባለፈው ረቡዕ ነሀሴ 19 ቀን 2013 ዓ.ም በተለምዶ ሀይሌ ጋርመንት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡና የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ የትራፊክ ፅ/ቤት ከፍተኛ ሃላፊዎች በተገኙበት ሼዶቹን አስረክቧል፡፡
ከሩብ ሚ.ብር በላይ የወጣባቸው እነዚህ የትራፊክ ፖሊስ ማረፊያ ሼዶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተና በሰውና በንብረት ላይ አደጋና ውድመት እያደረሰ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እንደሚያግዛቸው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ቁጥጥር ዲቪዥን ሀላፊ ም/ኮማንደር ብርሃኑ ቱፋ በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ባደረጉት ንግግር ላለፉት 30 ዓመታት በትራፊክ ደህንነት ሥራ ላይ መቆየታቸውንና ከትራፊክ ፖሊሶች ፈተና እንዱና ዋነኛው ተፈራራቂውን የአየር ንብረት ያለማረፊያ በብዙ ድካምና እንግልት  መስራታቸው እንደሆነ አስታውሰው የዋን ውሃ አምራቹ ኩባንያ አባሀዋ ትሬዲንግ ለዚህ ችግር መቀረፍና ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት የሰራው ተግባር የሚያስመሰግንና ለሌሎችም በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡
የአባሀዋት ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ እንየው ዘለቀ በበኩላቸው ለሚመሩት ድርጅት ከትራፊክ ፅ/ቤቱ በቀረበው ጥያቄ መሰረት አፋጣኝ ምላሽ መስጠታቸውንና ሼዶቹም ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰትና አደጋ ይደርስባቸዋል በተባሉ ቦታዎች ላይ መቀመጣቸውን ጠቅሰው ይህም ለትራፊክ ፖሊሶቹ ስራ መቃናት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ እስካሁን የትራፊክ ቁጥጥርን በማሳለጥና በየዓመቱ  በክፍለ ከተማው በትራፊክ አደጋ 62 ሰዎች ይሞት የነበረውን ወደ 43 ዝቅ በማድረግ ለውጥ በማምጣት ከ10ሩም ክፍለ ከተሞች  በአንደኝነት እየመሩ እንደሚገኙ የገለጹት የትራፊክ ቁጥጥር ዲቪዥኑ ሀላፊ ም/ኮማንድር ብርሃኑ ቱፋ አባሀዋ ትሬዲንግ ሰርቶ ያስረከባቸው ሼዶች ሥራቸውን ያለድካምና መሰላቸት እንዲሰሩና ይበልጥ ውጤት ለማስመዝግብ እንደሚረዳቸው ገልጸው ድርጅቱን አመስግነዋል፡፡
አባሀዋ ትሬዲንግ ከዚህም በፊት በርካታ ማበራዊ ጉዳዮችን በመደገፍና ሃፊነቱን በመወጣት የሚታወቅና ወደፊትም በዚሁ የሚቀጥል መሆኑን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ እንየው ዘለቀ ተናግረዋል።


Read 1412 times