Monday, 30 August 2021 00:00

እውን ኢትዮጵያ ስልጡን ሀገር ነበረችን?

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(2 votes)

     (የኢትዮጵያን ስልጣኔ ቀለማት ፍለጋ)
                                
                 Nicolas Joly (እ.ኤ.አ 1812 - 1885) ‹Man before metals› በተሰኘ መጽሐፉ፤ የሰው ልጅ ከድንጋይ ዘመን ወጥቶ የተረጋጋ የሕይወት እንዲመሰረትና ቋሚ መኖሪያ እንዲገነባ ምክንያት የሆኑት ከእሳት በተጨማሪ የምድጃ (hearth)፣ ብረት ማቅለጫ (forge)፣ እና መሰዊያ (altar) የመሳሰሉትን መፈልሰፉ ነበር ይላል። ድሩሲላ ዱንጂ በበኩሏ፤ wonderful Ethiopians and ancient Cushitic Empire በተሰኘ መጽሐፏ፤ ምድጃንና መሰል መገልገያዎችን ለተቀረው ዓለም ያስተዋወቁት ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን ናቸው የሚል የታሪክ ቅኝት አንስታለች፡፡ ድሩሲላ ትቀጥላለች፤ ‹‹ጥንታዊ ኢትዮጵያን አዝዕርትና እንስሳትን በማላመድ ጥበብ መሰል አልነበራቸውም፡፡ ጥንታዊ የኩሽ ኢትዮጵያዊያን የአባይን ወንዝ ተከትለው እስኪሰፍሩባቸው ድረስ ታችኛው የአባይ ተፋሰስ የዛሬይቱ ግብጽ አካባቢዎች ጠፍ መሬቶች ነበሩ፡፡ … በኋለኛው ዘመን ለነበሩ ስልጡን ጥቁር ግብጻዊያን ፑንት እንደ ቅድስት ሀገር ነበረች፡፡›› ዮቫል ኖህ ሐራሬ በበኩሉ ‹ሳፒያንስ› በተሰኘ መጽሐፉ፤ ለዘመናዊው ሰው አባት የሆነው የሆሞ ሳፒያንስ ዝርያ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት የምሥራቅ አፍሪካ ክልል ተነስቶ ወደ ተቀረው ዓለም መሰራጨቱን አብራርቷል፡፡
በሰው ልጅ ታሪክ እንደ ጥቁር ገጽ የሚወሰደውን የሰውን ልጅ ለመስዕዋዕት ማቅረብ (human sacrifice) በማስቀረት ረገድ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን ቀዳሚ ነበሩ። ምናልባትም ከነጭራሹ የሰውን ልጅ ለመስዋዕት ማቅረብን አልፈጸሙትም። በቅርቡ የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች በጀርመን፣ በፈረንሳይ እንዲሁም በሌላው የአውሮፓ አንዳንድ አካባቢዎች፣ በቻይና፣ በህንድና በሌሎችም ሀገሮች ለመስዕዋዕት የቀረቡ የሰው ልጅ ቅሪተ አካላትን አግኝተዋል፡፡
ብዙ የተወራላቸው ሥልጡን አዜቲኮችና ኢንካዎች እንኳን እ.ኤ.አ በ1509 እስፓኞች ላቲን አሜሪካ እስኪደርሱ በየዕለቱ በርካታ ሺህ ህጻናትን ለመስዋዕት ያቀርቡ ነበር፡፡ ቫን ዶሬን ቻርለስ፤ ‹history of knowledge past, present future› በተሰኘ መጽሐፉ፤ አዜቲክና ኢንካዎች በቀላሉ ለእስፓኝ ወራሪዎች እጅ የሰጡት በየዕለቱ ለመስዋዕት በሚጣሉ ሺህ ህጻናት ምክንያት የህዝባቸው መጠን በሚያስደነግጥ መጠን በመመናመኑ ነው ይላል፡፡ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ በቅርቡ ለሕትመት ባበቁት መጽሐፋቸው ‹ወረርሽኝ› እንደዘገቡት፤ የነዋሪው ቁጥር የተመናመነው ከእስፓኝ ሠራዊት ጋር በተዛመተበት መጤ በሽታ ነበር ከሚለው ይልቅ ከላይ የቀረበውን የመስዋዕት መቅሰፍት የሚያጠናክሩ ብዙ መረጃዎች አሉ፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያዊያን የሰው መስዋዕት(human sacrifice) ያስቀረን ቀደምት ህዝቦች ነን ብለን ስንደነፋ፣ዛሬም በኦሞ ሸለቆ የሚኖሩ የእኛው ወገኖች፣ ‹ሚንጊ› በሚል የገረጀፈ ብሒል፣ የሰውን ልጅ እስከ ሕይወቱ ለመስዋዕት እንደሚጥሉ መዘንጋት አይኖርብንም፡፡
ፈረንሳያዊው ደራሲ ኤሚል ዞላ እንዲህ ይላል። ‹‹civilization will not attain its perfection until the last stone from the last church falls on the last priest.›› ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሰሞን በአክሱም ስልጣኔ ላይ ያደረሰውን መጠን የለሽ ውድመት ያነበበ ሰው፤ ዞላ ስህተተኛ ነው ለማለት አይደፍርም፡፡ ዶክተር ነጋ ጌጡ የተባሉ ጸሐፊ ‹የቅማንት ሕዝብ ታሪክ› በተሰኘ መጽሐፋቸው በዝርዝር እንደገለጹት፤ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሰሞን በአክሱም የሆነው የቻይናን የባህል አብዮት (Cultural Revolution) ዓመታት የሚያስንቅ ነበር፡፡
መጀመሪያ አክሱማውያን ለጣዖታቱ ክብር የተሰሩ በርካታ ሐውልቶችና መቅደሶችን አፈራረሱ፡፡ ዛሬ በአክሱም አደባባዮች ቆመው የሚታዩት ሀውልቶች በጊዜው ለማፍረስ አስቸጋሪ የሆኑባቸው ብቻ እንደሆኑ ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? ከክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በኋላ የማዕድን ጉድጓዶች ተረሱ፤ የመስኖ ቦዮች አስታዋሽ አጡ፡፡ ገዥው ሀሳብ ምኑንም የማያውቁት ድግምት ሲነበነብ እየተከተሉ ‹አሜን› ማለት ብቻ ሆነ፡፡ ምናብ ለሺህ ዓመታት ኮሰመነ። የእስልምና እምነት በኃይል መስፋፋትን ታክሎበት አክሱም ተሽመደመደች። እንዳለ ገብረሕይወት ወልዱ የተሰኙ ጸሐፊ ‹ሥነ-መለኮቶች ከጥንታዊያን ሥነ ተረቶች ስለመመስረታቸው› በተሰኘ ያላለቀ የሚመስል መፅሐፋቸው፤ ሐይማኖቶች ከእነሱ ቀድመው ከነበሩ ከጥንታዊያን (Pagans) ሥነ-ተረቶች (mythologies) የተገኙ ናቸው ይሉናል፡፡ እነሱም ተራቸው ደርሶ በሌሎች ሥነ ተረቶች እስኪደመሰሱ እኛ ጉዞአችንን አናቆምም፡፡  
ክርስትና ግን በፍጥነት ተንሰራፍቶ አብዛኛውን አውሮፓ አዳርሶ፣ በዓለም ታሪክ ውስጥ ጭፍን ወደሆነው የጨለማው ዘመን ሰዎችን አንደረደረ፡፡ በኋላም የአብርሆቱ ዘመን ሲጀመር የአውሮፓ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መስቀል ላይ የሞተውን እያመለከች፣ እንደ ጆርዳኖ ብሩኖ ያሉትን የጨለማው ዘመን አብሪ ትሎች የጧፍ ቀሚስ አያለበሰች ማንደዷን ቀጠለች፡፡
አያን ራንድ The Fountainhead በተሰኘ መጽሐፏ፤ ‹‹civilization is the process of setting man free from men.›› ትላለች፡፡ ይሄ ቀንዲል የሆነ ሰውን ከሰዎች ነጻ የማውጣት ሀሳብ እንኳን በዚያ የጨለማ ዘመን ዛሬም በገቢር የሚሰራ አይመስልም። ተነጥሎ መቆም፣ ተነጥሎ ማሰብ ያለመቻል ይሄው እስከ ዛሬም አምልኮ ያሸከመን ዕዳችን ይመስላል፡፡
እኔ ግን ከመልሶች ይልቅ ጥያቄዎች ይመስጡኛል፡፡ የጥያቄዎች አድናቂ ነኝ። ከየትኞቹም አስደናቂ እሳቦቶች፣ ግኝቶች በፊት ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ግኝቶች፣ እሳቤዎች የጥያቄዎች ከፊል መልሶች ይመስሉኛል፡፡ እናም መመለስ ባንችል እንኳን እንዲህ ብለን እንጠይቅ እስቲ… ይህ ሁሉ ሆኖ እውን ኢትዮጵያ ስልጡን ሀገር ነበረችን? ነበረች?
የዘርፉ ባለሙያዎች አንድ ጥንታዊ ስልጣኔ የተሟላ ስልጣኔ ነው ለመሰኘት ቢያንስ ከተሞች፣ የማህበረሰብ አወቃቀር፣ ሐይማኖት፣ የተደራጀ መንግስት፣ የጽሕፈት ቋንቋ፣ ባህልና ሳይንሳዊ ፈጠራን ያካተተ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ በእርግጥ ከናፓታም ተነሳን ከዬሐ ኢትዮጵያ እንደ አክሱም፣ አዱሊስ፣ ሐረር፣ ጎንደር የመሳሰሉ ታላላቅ ከተሞች ነበሯት፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው አውሮፓዊ እንደ ዘላን በዋሻዎች መካከል እየኖረ የበቆሎ ገንፎ በሚበላበት ዘመን ኢትዮጵያዊያን ግን በራሳቸው ፊደል ይጻጻፉ ነበር፡፡ ሞዛርትና ቪትሆቨን ከመወለዳቸው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ዓመታት በፊት፣ አሜሪካ እንደ ሀገር ከመቆርቆሯ ሺህ ዘመናት አስቀድሞ ኢትዮጵያዊው ያሬድ ግን ሙዚቃን በኖታ እየጻፈ ይራቀቅ ነበር፡፡
ታሪክ የመዘገበውን ብቻ እንኳን ብንጠቅስ ከክርስቶስ ልደት 1000 ዓመታት በፊት ጀምሮ ኢትዮጵያ ንጉሳዊ መንግስታት ነበሯት፡፡ ነገስታቶቿ ትልልቅ መርከቦችንና የመስኖ ቦዮችን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ በዚህ አግባብ ካየነው በእርግጥ ኢትዮጵያ ስልጡን ሀገር ነበረች! ወሰኑ በየጊዜው ሊሰፋ ሊጠብ ቢችልም ቅሉ ከህንድና ከቻይናም በላይ የኢትዮጵያ ሥነ መንግስታዊ ሥርዓት ከቅድመ አክሱም ዘመን ጀምሮ ሳይከስም መቀጠሉን ሪቻርድ ፓንክረስትና መሰል የዘርፉ ጠበብት ደጋግመው መስክረዋል፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ከተሞች ቢኖሯቸውም ቅሉ ነገሥታቱ ዘላኖች (nomads) ሆነው አልፈዋል፡፡ የነገሥታቱ አጀብ ለሺህ ዓመታት እንደ አንበጣ መንጋ የሚያልፍባቸውን አካባቢዎች ሁሉ ጠራርጎ የሚበላ ገና በሩቅ ሲጠራ ለነዋሪዎቹ ሽብርን የሚነዛ ወራሪ ተሰሪ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብቸኛው የፊደል ገበታ ባለቤት ብትሆንም ቅሉ የሚራቀቁበት ጥቂት የሰከሩ ደብተሮች ብቻ እንደነበሩ መናገር ለቀባሪ ማርዳት አይሆንብኝ ይሆን? ሌላው ሕዝብ እና አንዳንድ ጊዜ ነገስታቱም ሳይቀር ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ‹ጨዋዎች› ሆነው አልፈዋል፡፡
ላሊበላን ከሚያህል አስደናቂ የውቅር አብያተክርስቲያናት ስብስብ ጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ዛሬም ድረስ የሰዎች መኖሪያ የሆኑ ያዘመሙ ጎጆች ይታያሉ፡፡ ከእነዚያ መከረኛ ቤቶች በባዶ እግር እየተረማመዱ የሚወጡ ጉስቁል ፍጡራን  በምናቤ ይታዩኛል፡፡ ዛሬም ድረስ በየመንገዱ የሚጸዳዳ ሰዎች አሉ፡፡ ከተማዋ በምሽት ለሚመለከታት በመብራት እጦት ከፊል በድን ሆና በኩራዝ ብቻ የምትስለመለም የሙታን ከተማ ትመስላለች፡፡ ከፋሲል ግንብ ጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት እንኮዬ መስክ (የጎንደሩ ጨርቆስ) የመሸገውን የዘቀጠ ሕይወት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ ዘወትር በምሽት ስንሸራሸር ፋሲል ግንብ ከሕዝቡ የአኗኗር ስልት ጋር መጣጣም ተስኖት ለብቻው ጎንቁሎ፣ እንግዳነት የተሰማው መስሎ ሳየው አድጌያለሁ። የአክሱማዊያኑም እውነት ከዚህ የተለየ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ እነዚህ ህዝቦች እኒህን እጹብ ድንቅ ሀውልቶችና ኪነ ሕንጻዎች ከሰሩ በኋላ የት ሄዱ? ስልጣኔውስ እንዴት በኑሯቸው ሳይገለጽ ቀረ? የምርስ ስልጣኔ ነበረን? ለመሆኑ ላሊበላ ለላስቴው ምኑ ነው?
ለምሳሌ በ16ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ ስፔኖች ደቡብ አሜሪካ ሲደርሱ በእርሻ ልማትና በኪነ ሕንጻ ጥበባት የተራቀቁት ኢንካዎችና አዜቲኮች የፊደል ዘር መኖሩን እንኳን የማያውቁ መሀይማን ሆነው አግኝተዋቸዋል፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያዊ ስልጣኔ ብሎ ነገር ነበር! ግን ምን ዓይነት ስልጣኔ? የኦሮሞዎችን የገዳ ስርዓት ጨምሮ ወደ ሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ሲኬድ የሚታየው የሀገረሰብ ጥበብና ዕውቀት ገና ያልተጠናና በቅጡ የማይታወቅ ቱባ ነው፡፡ በቅርቡ Korra Gorra የተሰኘ ጣሊያናዊ የጻፈውን ‹konso water and gods› የተሰኘ መጽሐፍ አንብቤ፣ በኮንሶዎቹ ረቂቅ እሳቤዎችና የአኗኗር ጥበባት በግርምት አፌን ይዣለሁ፡፡ እንቀጥል...
የአሜሪካ ቀደምት ህዝቦች፣ ቀይ ህንዶች ‹‹ምድርን ከልጅ ልጆቻችን ተዋስናት እንጂ ከአያቶቻችን አልወረስናትም፡፡›› ይላሉ። ይሄ አባባል ለታሪክም ግጥም አድርጎ ይሰራል፡፡ ወደዳችሁም ጠላችሁም አድዋን የወረስነው ከንጉሥ ምንይልክ፣ ከራስ አሉላ ወይም ከደጃዝማች ባልቻን ከመሳሰሉት አይደለም። አድዋ የልጅ ልጆቻችን የትውስት ጌጥ ነች። አያቶቻችን በአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ተረተር በዚያች ቀውጢ የሰንበት ማለዳ ከሞት ጋር የተናነቁት ለአያቶቻቸው ዝና አልነበረም፤ ምናልባት ለራሳቸው ክብርና ሞገስም ነበር ለማለት አልደፍርም፡፡ የዚያ ሁሉ አሰቃቂ ትንቅንቅ ምክንያት ለልጅ ልጆቻቸው የሚተርፍ ባርነትን ላለመሸከም የተደረገ መራር ተጋድሎ ይመስለኛል፡፡ ላሊበላንም ሆነ አክሱምና ፋሲል እንዲሁም የጀጎል ግንብ ለልጅ ልጆቻችን የተተው ውድ ሀብቶች ናቸው፡፡ እናም የወረሱትን እንጂ የተዋሱትን ነገር መሸጥም ሆነ ማውደ በእውነቱ የተገባ አይደለም፡፡ እንዲያውም በቅጡ ማጥናትና አጉልቶ ማስረከብ የትውልድ ግዴታችን ይመስለኛል፡፡
ታሪክ እና ስልጣኔ ግን በጊዜ ቅደም ተከተል የተሰደሩ የሁነቶች ጥርቅም ብቻ አይደሉም። ከዚያም ይረቃሉ፡፡ ፈረንሳያዊው ፈላስፋ ቮልቴር ‹‹History should be written as philosophy.›› ይላል፡፡ በቅርቡ እንደ ሀገር ከተመሰረተች በቅጡ 300 ዓመት እንኳን ባልሞላት አሜሪካ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሸክላ ሰሪዎች  በሸክላዎቻቸው ላይ ያስተላለፏቸውን መልዕክቶች የሚያጠና ‹Tales and traditions›የተሰኘ መጽሐፍ አንብቤ በቅናት ተትከንክኛለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊያን እደጥበበኞች ከአክሱም ዘመን በፊት ጀምሮ ሸክላን በመሳሰሉት ጥበባት ላይ ሲራቀቁ ቢያሳልፉም ማንም ምንም ብሎላቸው አያውቅም፡፡ በዓለም ታሪክ ውስጥ ከነበሩ ቀደምት ስልጣኔዎች ሁሉ በቅጡ ያልጠና፣ የተረሳ፣ በየታሪክ መጻሕፍቱ ሁሉ ኩርማን ገጽ ብቻ የሚሰጠው፣ ይህ ነው የሚባል ስም ያልወጣለት ስልጣኔ ቢኖር ኢትጵያዊ ስልጣኔ ብቻ ነው፡፡ ከእኛው ስልጣኔ ጋር የመወራረስ ዝንባሌ ያለው የግብፅ ጥንታዊ ስልጣኔ የተሰጠውን አለም አቀፍ ትኩረት መመልከት ይበቃል።
የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ቀለማት ከአክሱምና ድኅረ አክሱም ዘመን ጀምረን ለመመርመር ከመከርን ግን ነገሩ ሌላ ገጽ ይላበሳል፡፡ ግርማ ሞገስ የተሰኙ ጸሐፊ ‹‹ሰላማዊ ትግል›› በሚል ርዕስ በ2006 ዓ.ም ለንባብ ባበቁት መጽሐፋቸው ከአክሱም ወርቃማ ዘመናት ጀምሮ ኢትዮጵያ በድምሩ ከ500 ዓመታት በላይ በእርስ በእርስ ጦርነት ስትናጥ አሳልፋለች ይሉናል፡፡ ታሪካችን ሙሉ ለሙሉ የጦርነትና የሁከት እንደመሆኑ ነገሩን እንደገና በቅርበት ለሚያጠናው በብጥብጥ የባከነው ጊዜ ከ800 አስከ አንድ ሺህ ዘመናት ከፍ ሊል እንደሚችልም እገምታለሁ፡፡ ዛሬም ከዚያ አዙሪት አልወጣንም፡፡
የሆነስ ሆነና ራሱ ‹ሥልጣኔ ምንድን ነው?› ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ ‹‹Modernity: Its title to the uniqueness and its advent in Ethiopia›› በተሰኘ መጣጥፋቸው ‹‹pluralism is the deep fact of Modernity›› የሚል ሀሳብ አንስተዋል። ዝመና እና ስልጠና(ጠ ጠብቆ ይነበብ) የቅርብ ርቀት ልዩነት ሊኖራቸው ቢችልም ቅሉ… ዶክተር እጓለ ገብረዮሐንስ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› በሚል ርዕስ በሰየሙት መጽሐፋቸው ስልጣኔን በቅጡ ለመረዳት ካልቸር(የነፍስ የመንፈስ ወይም ውስጣዊ ሥልጣኔ) እና ሲቪሊዜሽን (አካላዊ ወይም አፋዊ ስልጣኔ) የሚሉ ሁለት ቃላት ጠቃሚ መሆናቸውን በአጽዕኖት አብራርተዋል። ዶ/ር እጓለ ይቀጥሉና ‹የአውሮፓ የስልጣኔ ጉዞ አንድ አቅጣጫ ብቻ የተከተለ አልነበረም። የአውሮፓ የህዳሴ ጉዞ ሁሉንም ሰብዓዊ፣ ኪናዊ፣ ፖለቲካዊና ሳይንሳዊ ዘርፎች ማሻገር የቻለ ሁሉን አቀፍ የለውጥ ሂደት ነበር፡፡› ይላሉ፡፡
በእርግጥ ዶ/ር እጓለ ካልቸር ሲሉ የጠቀሱት የዳበረ ሁለተናዊ ባህል ኢትዮጵያ ነበራት፡፡ ሆኖም ከሁከት በተራረፉት ሽርፍራፊ የስክነት ዘመናት ውስጥ ሲስለመለም ሥልጣኔው ከአክሱም ዘመን ጀመሮ በኃይል በተጫነው ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ምክንያት መወድሳዊ ገጽታን ተላብሷል፡፡ ብዝሃነትን ማክበር(pluralism) እንኳን ያኔ ዛሬም ልንቀበለው የተቸገርነው ዝመና ይመስላል፡፡ የሀሳብ፣ የሐይማኖት፣ የኪነት፣ የፈጠራ ብዝሃነትንና መራቀቅን መቀበል ለሺህ ዓመታት አቀበት ሆኖብናል፡፡ በደቂቀ እስጢፋዎች፣ በተቀባትና ተዋሃዳት ጉንጭ አልፋ ክርክሮች ሰበብ በአንድ ክርስቶስ ስም በተመዘዙ ሁለት መንታ ሠይፎች የተቀሉ እልፍ አንገቶችን ማን ይረሳል? ለቁጥር የሚታክቱ አድባራትን መሳጅዶችን ገንብተናል፡፡ ግን ምንም መንገድ! ግን አንድ ወይም ሁለት ድልድዮች ብቻ! ዛሬም ድረስ በእግርና በበቅሎ ብቻ የሚደረስባቸው ጠረፍ አካባቢዎች ስትሄዱ በየአካባቢው ቅንጡ አብያተክርስቲያናትን ታገኛላችሁ፡፡ የትምህርት ቤቶችን ደወል እንኳን ለመስማት ግን ብዙ ኪሎሜትሮችን ማቋረጥ የግድ ይሆንባችኋል፡፡
በእርግጥም የኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት የስልጣኔ ሂደት እንደ አውሮፓው ህዳሴ ሁሉንም የሕይወት ዘርፎች የሚዳስስ አልነበረም፡፡ ሥልጣኔው በተለይ እጓለ ‹ሲቪሊዜሽን› ብለው የጠቀሱት ቁሳዊና ኪነጥበባዊ መራቀቆች ጭራሽ አልነበሩትም ለማለት ይቻላል፡፡ ከክርስትና በፊት የተደነቁት የሀውልት እና የመስኖ ቦዮች መሀንዲሶች ምናልባትም በዘመኑ መጤ ቅኝት ተገፋፍተው በታቦት ቀራጭነት ብቻ ተወስነዋል፡፡ መርከቦች ተረስተዋል፡፡ የማዕድን ጉድጓዶች ተመልካች አጥተዋል። ነገስታት ሳይቀር ድንገት እየተነሱ መናኝ ወጣቸው፡፡
ብሩህ ዓለምነህ ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና› በሚል ርዕስ በ2010 ዓ.ም ባሳተመው በእኔ እምነት የግድ ሊነበብ በሚገባውና ለዚህ መጣጥፍ በብዙ መንገድ ግብዓት በሆነልኝ መጽሐፉ እንዲህ ይላል… ‹‹በ1500 ዓመታት የብሕትውና ዘመናችን ውስጥ ተቃርኖን አጥፍተን በአንድ ዓይነት የአንብሮ ሐሳብ ላይ ብቻ ተቸንክረን ስለቀረን አስተራረሳችን፣ የቤት ቁሳቁሶቻችን፣ የስራና የመጓጓዣ መሳሪያዎቻችን፣ የቤት አሰራራችን፣ አመጋገባችን፣ አስተሳሰባችን….ሁሉ ለውጥ አልታየበትም፡፡ ሙያችን ሁሉ የምንኩስና ክርስትናን መተንተን ሆነ፡፡ ለ1500 ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ስንጠቅስ እና ስናብራራ፣ ከራሳችን አንድ ሙያ እንኳን ሳናፈልቅ ዘመናችንን በላነው፡፡ ዕውቀትም - ስነምግባርም፣ ሕይወትም - እስትንፋስም፣ ርዕይም - ሕልምም ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወት ብቻ ሆነ፡፡ መንፈሳዊ ሕይወት የማናቸውም ነገር መጨረሻና መደምደሚያ ሆነ፡፡›› ገጽ 240
ብሩህ በዘርዓያዕቆብ ሀተታ መነሻነት የኢትዮጵያን ሥልጣኔ በበየበት በዚህ መጽሐፉ ምንኩስና የሥልጣኔውን የዕድገት ሂደት ያቀጨጨ ዋነኛ አስተምሮ ነበር የሚል መደምደሚያ አቅርቧል፡፡ ለዚህም ማሳይ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ አባ ጴንጤለዎን አጼ ካሌብን ጨምሮ 1500 ሰዎችን ማመንኮሳቸውን ይጠቅሳል። ነገሩ ግን መች በዚህ ብቻ የሚገደብ ሆነ። የምንኩስናው መንፈስ እንደ ሰደድ እሳት በሁሉም አማኝ ልብ ተዘርቶ በጥቂቱ የሚረካ፣ የማይጠይቅ፣ አሜን ለማለት ብቻ የሚጣደፍ ህዝብ ፈጠረ፡፡ ለሺህ ዓመታት የቀጠለው ይሄው ነው፡፡
‹‹Man is the measure of everything.›› የሚለው የግሪካዊው ፕሮታጎራስ (Protagoras 490- 420 ቅ.ል.ክ) አስተሳሰብ በድህረ ክርስትና ለተፈጠረው ትውልድ ትርጉም የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ዕጣፋንታውን በራሱ እጅ ለመወሰን ከመታተር ይልቅ ለእያንዳንዷ ጥቃቅን ግቡ መከናወን ቁጭ ብሎ አምላኩን የሚወተውት ጥገኛ ህዝባዊ አስተሳሰብ ተገነባ፡፡ (እሱንም መንጋው ከጠጅ ያለፈ ግብ ከነበረው እኮ ነው፡፡) ዛሬም ድረስ ይሄው አስተሳሰብ እየፋፋ ቀጥሏል፡፡
በቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቤትን ለማሳመር፣ ሰንጋ አርዶ ለመብላት፣ ጠጅ ጥሎ ለመጠጣት ሹም መሆን ወይም የሹም ፈቃድ ማግኘት የግድ እንደነበር ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? ከአጼ ምንይልክ ቤተ መንግስት በላይ ቤቱን በመገንባቱ ብቻ ስለተገረፈው ሹምስ? አለቃ ለማ ኃይሉ በተረኩልን በቤቱ ጠጅ ጥሎ ለኪዳነምሕረት ንግስ ወዳጆቹን በመጋዙ ተከሶ አጼ ዮሐንስ ችሎት ፊት የቀረበውን ገበሬ ታሪክ መነሻ በማድረግ ዓለማየሁ ገላጋይ ሲጽፍ ‹‹ብዙዎቹ የሀገራችን ገዥዎች የግዛት ዘመናቸውን ያጠቃለሉት በህዝቡ ላይ ‹‹ስራ የሚጠላ›› ዛር ሆነው ነው ማለት ይቻላል፡፡ የተሻለ የሚመኝ፣ ሀብት የሚያካብት፣ ለለውጥ የሚነሳሳ ‹‹ሽፍታ›› ቅጥያ ይወጣለታል፡፡ በመጠኑም ቢሆን መጠለያውን ከማሳመር፣ የሚበላውን ከማጣፈጥና የሚጠጣውን ከመምረጥ በፊት ሥልጣን ግድ ይለዋል። ቀሚስ ያልበሰ (ሥልጣን ያላገኘ) ድሃ ‹‹አጉል መነፋፋቱ ለመፈንዳቱ›› ይሆናል፡፡›› ኢህአዴግን እከስሳለሁ- የድሃ መንታ ድንበር ገጽ 157
ብሩህ ዓለምነህም ሆኑ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም (መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ) የሚያስረግጡት ይህኑ ነበር፡፡ እስከ አጼ ኃይለስላሴ ዘመን መገባደጃ ድረስ ለሺህ ዓመታት በኢትዮጵያችን ሰርቶ ነግዶ ከማትረፍ ይልቅ መሾም ወይም ሥልጣንን በኃይል መንጠቅ ለመክበር ብቸኛው አማራጭ ነበር፡፡ እስከ አጼ ኃይለስላሴ ዘመን መገባደጃ ድረስ በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ንግዱን ይቆጣጠሩ የነበሩት ግሪካዊያን፣ አርመኖች እና አረቦች ነበሩ፡፡ ለዝርዝሩ የብርሃኑ ሰሙን ‹ከእንጦጦ እስከ ሐሙስ ገበያ መርካቶን› ማንበብ ነው፡፡
ከአክሱም ዘመን በኋላ ስንፍና አለቅጥ ተስፋፋ፡፡ የእጅ ሙያ ያላቸውን ሰዎች ማንቋሸሽ በሽሙጥ ስም መጥራት ባህል ሆነ፡፡ ባህሩ ዘውዴ ‹pioneers of change in Ethiopia› በተሰኘው መጽሐፋቸው አጼ ምንይልክ ቢጨንቃቸው ይህን የተሳሳተ ልማድ ለመስበር በ1903 ዓ.ም የመቀጮ አዋጅ ማውጣታቸውን ያስነብቡናል፡፡
ተመልከቱ በሺህ ዓመታት ሂደት በአባይ፣ ርብ እና አንገረብ ወንዞች ላይ ከተሰሩት ድልድዮች በስተቀር በኢትዮጵያ ሥልጣኔ ታሪክ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የተሰራ አንድስ ነገር እንኳን አልነበረም፡፡ የሆነ መንገድ፣ የሆነ ቤተ ተውኔት፣ … ብቻ አንድ የሆነ ነገር እንኳን!? ላሊበላን ጨምሮ የፋሲል ግንብ የመሳሰሉ ‹‹ገልቱ ሕንጻዎች›› አንድም ለነገስታቱ ክብር አሊያም ለአምልኳቸው አጅ መንሻ የተሰሩ ናቸው፡፡ የነገሥታቱ ዋነኛ ቁምነገር ማስገበርና ደብር መስራት ብቻ ይመስላል፡፡ ለዚህስ ይሆን ለእነዚያ የአጼ ፋሲለደስ የርብና አባይ ድልድዮች ያ ሁሉ መወድሳዊ ቅኔ መዥጎድጎዱ?
ሌላም ነገር እነሆ… የጥበብ (ቅኔ) ነገር ተነሳም አይደል፡፡ በእርግጥ ቅኔው፣ ዝማሬው፣ ዝማሜው፣ የስዕልና የጽህፈት ጥበቡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምናልባት ከሺህ ለሚልቁ ዘመናት ሲከወን፣ ሲከናወን ነበር፡፡ ሆኖም ክዋኔው ሁሉ ከሀይማኖታዊ ተግባራት ውጭ የሆነውን የሕይወት ፈርጅ ለመዳሰስ የማይችል ስንኩል ሆኖ አልፏል፡፡ኪናዊ ክዋኔው በሐይማኖት አስተምህሮው ብቻ የተቀነበበ በመሆኑ መምህር ኮንፊሸስ እንዳለው ‹Learning without thought, labor lost› ዓይነት ነበር፡፡
ኃይሌ ወልደ ሚካኤል የተባሉ ጸሐፊ በነሐሴ 1961 ዓ.ም በወጣችው ‹ውይይት› መጽሔት ‹ባህልና የመምህርነት ሙያ› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ በ15ኛው ክፍለዘመን ወደ ኢትዮጵያ ስለመጣ አንድ ሰዓሊ ይጠቅሳሉ፡፡ ሠዓሊው ራንካሊዎኒ ይባላል፡፡ በዚሁ የኢትዮጵያ ቆይታው ድንግል ማርያም ኢየሱስን በግራ እጇ ታቅፋው የሚያሳይ ምስል በመሳሉ ብቻ የግድያ ሙከራ ተሰንዝሮበታል፡፡ በግራ እጇ እንድትታቀፈው በማድረጉ ብቻ! ይህኛው ታሪክ የአፈወርቅ ገብረኢየሱስ ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ ባሰሩት ቤተክርስቲያን እቴጌይቱ ወደ ግራ ዞረው ከፊል የፊት ገጻቸውን(አንደኛው ዓይናቸው) ብቻ የሚታይበት ስዕል በመሳላቸው ከእቴጌይቱ የመረረ ጥላቻ አትርፈዋል፡፡ ከተለመደው ውጭ የሆነ አሳሳል በመሆኑ ሰይጣናዊ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡
ጥበቡ ቅኔው፣ ዘፈኑ፣ ሥዕል ቅርጻቅርጹ በእርግጥ ነበር፡፡ ሆኖም ጥበቡን የሚጋልበው የሐይማኖት ቀንበር ዝንፍ የማይል ጥብቅ በመሆኑ ክዋኔውን በምህረት የለሽ ክንድ አጉብጦታል፡፡ የመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያዊያን ሰዓሊዎች እንደኮፒ ማሽን የተለመዱ ምስሎችን በማባዛት ሲታክቱ በአውሮፓ እነ ሚካኤል አንጀሎ፣ እነ ራፈኤል፣ እነ ዳቪንቼ በነጻነት ይራቀቁ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ስዕልና ኪነጥበብ እንደገና ከሐያኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደገና ዳዴ ለማለት የተገደደውስ ለዚህ ይሆን?
አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ጥበቡን ስለተጫነው ጥብቅ ሐይማኖታዊ ቀንበር በ‹አልቦ ዘመድ› መጽሐፋቸው አለሳልሰው ሲያነሱ ‹‹ያለፈው የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሥርዓት በእንግሊዝ ሀገር Victorian age እየተባለ ከሚጠራው የበለጠ ጠንቃቃ ነበር ማለት እንችላለን፡፡›› ይላሉ፡፡ ይቀጥሉናም፡፡ ‹‹ግዕዛዊያን አባቶች ተፋቅሮ ነክ(romance) የሚያሳይ ፈጠራ ያላቀረቡበት ምክንያት ምናልባት የቤተ ማኅበሩን ሥርዓት ለማክበር ሳይሆን አይቀርም እላለሁ፡፡ ተፋቅሮ ነክ (romance) ያለው ስነጽሁፍ ለማንበብ የሚፈልጉ ግዕዛዊያን አባቶች ፍላጎታቸውን ለማስደሰት የቻሉት ምናልባት መኅልየ መኅልየ ዘሰሎሞን በተባለው መጽሐፍ መሆን አለበት፡፡›› ይላሉ፡  ዛሬስ ቢሆን ጥበቡን፣ ማኅበራዊ ኑሮአችን ከሐይማኖቱ ጥብቅ እቅፍና መንጋጋ ፈልቅቆ ነጻ ማውጣት ተሳክቶልናል እንዴ?
ሌላም ከኢትዮጵያ ስልጣኔ የተነቀሰ ስንኩል ገጽ እነሆ… ፖርቹጋላዊው ቄስ ሪካርዶ አልቫሬዥ በ1520ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ  ያየውን የጉዞውን ዝርዝር ሁኔታ ጽፎ ነበር፡፡ መጽሐፉም ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት ‹‹ኢትዮጵያ ፖርቹጊዞች እንዳዩአት› ተብሎ ተተርጉሞ አንብቤያለሁ፡፡ አልቫሬዥ በዚሁ መጽሐፉ ላይ እንዲህ የሚል ትዝብት ከትቧል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊያን ርቀትም ሆነ ጊዜ መለኪያ የላቸውም፡፡ ከዚህ እስከዚያ ምን ያህል ይርቃል ሲባሉ በእግር ከሄድክ ጸሐይ ስትጠልቅ በበቅሎ ከሄድክ ጸሐይ ስታቆለቁል ትደርሳለህ ይላሉ እንጂ እንዲህ (ኪሎሜትር) ይሆናል አይሉም፡፡››
በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፉት ኩባዊው ኮለኔል አልኸንድሮ ዴል ባዬም(ቀይ አንበሳ) ሆነ ቼካዊው አዶልፍ ፓርለሳክ (የሀበሻ ጀብዱ)  ይሄን መሰል ትዝብት አጋርተውናል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ምንም ሳይጠረጠሩ የጠላትን ጦር በመሰለል የተካኑ ቢሆኑም የጦሩን ሁኔታ ብዛቱንና አደረጃጀቱን ሲጠየቁ ግን ‹‹ብዙ በጣም ብዙ›› ከማለት ውጭ የተጠጋጋ ግምታዊ የቁጥር ትንተና ማቅረብ አይችሉም፡፡ ከአጼ ልብነድንግል ዘመን እስከ ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ድረስ ለ400 ዓመታት ያችኑ ዳዊትና ጦር ብቻ ታቅፈን ተንከርፍፈን ሳንሻሻል ስንጠብቅ ተገኝተን በነ ጊበን ቢዘበትብን የሚገርም ነውን? ለነገሩስ ቁጥሩም ፊደሉም ነበረን እኮ… ለዚያም ለአፍሪካ ብቸኛና ብርቅ!  
አዎ የኢትዮጵያ ስልጣኔ የሰጡትን ለምን ሳይል የሚያቅፍ፣ ያጎረሱትን ሳያላምጥ የሚውጥ ነበር፡፡ የእኛ ስልጣኔ ከመጠየቅ ጋር አይተዋወቅም፡፡ ከማድነቅ ጋር ኩርፍ፣ ከመመርመር ጋር ሆድ እና ጀርባ ነው፡፡ ቀለሙ ዝንቅ፣ የሆነ ድቅል መልክ ነበረው፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያ ስልጡን ሀገር ነበረች! ነገርግን ስልጣኔው የሚቆራረጥ ገጽታ ነበረው፡፡ እናስ እስከ የክሽፈት መልኩ ኢትዮጵያዊ ስልጣኔ ምን ይመስል ነበር? ክርስትናስ ኢትዮጵያዊ ስልጣኔን ከማሰናከል ባለፈ ለኢትዮጵያዊ ስልጣኔ ያዋጣው ቀለም ምን ድረስ ነው? የኢትዮጵያን ታሪክ የምትጽፍ አንተ ግን እዚህና እዚያ የተወነጋገሩ ሕንጻዎችን ብቻ እያሳየህ በደፈናው ኢትዮጵያ ስልጡን ሀገር ነበረች አትበለኝ፡፡ የማይዳሰሰውንም አሳየኝ! ግብሩ ከቀረጡ፣ ቁንዳላው ሹሩባው፣ ሸማው ከድሪያው፣ ሸክላው ከሸክላው፣ ፉከራው ከሽለላው፣ ሙሾው ከእንጉርጉሮው፣ አዝማሪው ከዘማሪው፣ ቅኔው ከብሂሉ፣ አፈታሪኩ ከልቦና ውቅሩ፣ ጉራጌው ከሀደሬው፣ ሌላው ከሌላው የወረሰውን፣ የነጠቀውን፣ የተዋዋሰውን፣ የተመሳሰለበትን እንደ ሕብረቀለም የደመቀ ምስል አሳየኝ፡፡ አንላቀቅም!
( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ጸሐፊውን በዚህ የኢሜል አድራሻቸው ማግኘት ይችላሉ)Read 9181 times