Monday, 30 August 2021 00:00

ቀነኒሳ በ42 ቀናት ልዩነት ሁለት ማራቶኖችን ይሮጣል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   በማራቶን የዓለማችንን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓትና የኢትዮጵያን የማራቶን ሪከርድ 2፡012፡41 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በታላላቆቹ የበርሊንና የኒውዮርክ ማራቶኖች ለመሳተፍ መወሰኑ የዓለምን ትኩረት ስቧል፡፡ በ42 ቀናት ልዩነት የሚሳተፍባቸው ሁለት ውድድሮች ሴፕቴምበር 26 ላይ የሚካሄደው የበርሊን ማራቶንና ኖቬምበር 6 ላይ የሚከናወነው የኒውዮርክ ማራቶን ናቸው፡፡
በቶኪዮ 2020 ላይ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ማራቶን ቡድን ያልተካተተው አትሌት ቀነኒሳ ሁለቱን ማራቶኖች ላይ ሲሳተፍ የዓለም ሪከርድን ለማስመዝገብ ለመጨረሻ ግዜ በማነጣጠር ነው፡፡  ይህን አስመልክቶ ለስፖርት ኢለስትሬትድ ከአዲስ አበባ  በሰጠው ልዩ የስልክ ቃለምልልስ ‹‹በምርጥ አቋም ላይ ነኝ፡፡ ከሌሎች በምሻልበት ደረጃ ላይ እንደምገኝም ይሰማኛል፡፡ ከውድድር በፊት ማንም አትሌትና ሌሎችም እንዲህ ማሰብ አለባቸው›› ብሏል፡፡
እንደስፖርት ኢለስትሬትድ ሀተታ ቀነኒሳ በሁለቱ ትልልቅ ማራቶኖች ሲሳተፍ ከ17 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በ5ሺ እና በ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርዶች ባለቤት መሆኑ ላይጠቀስ ይችላል፡፡ በረጅም ርቀት 3 ጊዜ የኦሎምፒክና 5 ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ያስመዘገበ መሆኑ ግን ከምንግዜም ምርጥ አትሌቶች ተርታ ያሰልፈዋል፡፡ ቶኪዮ ባስተናገደችው 32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ  ኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ በኦሎምፒክ ማራቶን የሻምፒዮንነት ክብሩን ካስጠበቀ በኋላ በበርካታ የዓለም ሚዲያዎች የምንግዜም ምርጥ አትሌት ተብሎ እየተወደሰ ነው፡፡ ለአትሌት ቀነኒሳ ግን ይህ አድናቆት መረጃዎችን ያገናዘበ አይደለም፡፡ ሁለቱ አትሌቶች  ወደ ማራቶን ውድድር ፊታቸውን ከማዞራቸው በፊት ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው ቀነኒሳ ሲሆን በአገር አቋራጭ እና በትራክ ውድድሮች 21 ጊዜ ተገናኝተው 16 ጊዜ ኪፕቾጌን አሸንፎታል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ቀነኒሳ 11 የወርቅ ሜዳልያዎች ሲሰበስብ ኪፕቾጌ ያገኘው አንድ ብቻ ነው፡፡ ከ3ሺ ሜትር እስከ 10ሺ ሜትር ባሉት የረጅም ርቀት ውድድሮች ባስመዘገባቸው ፈጣን ሰዓቶችም ቀነኒሳ የተሻለ ነው፡፡ እነዚህን ታሪካዊ ውጤቶች በዝርዝር ለተመለከተ  በረጅም ርቀት የዓለማችን የምንግዜም  ምርጥ አትሌት  ማን እንደሆነ ለመዳኘት አይቸገርም፡፡
ኤሊውድ ኪፕቾጌ በሩጫ ዘመኑ ከቀነኒሳ የተሻለ ታሪክ ያስመዘገበው በማራቶን ብቻ ነው፡፡ ከ2014 እኤአ ጀምሮ በ4 ማራቶኖች ተገናኝተው ሁሉንም ኪፕቾጌ አሸንፏል፡፡  ለመጨረሻ ጊዜ በ2018 እኤአ ላይ በለንደን ማራቶን በተገናኙበት ወቅት ኪፕቾጌ በከፍተኛ ብቃት ብልጫ ወስዶ ሲያሸንፍ ቀነኒሳ 6ኛ ሆኖ ነበር የጨረሰው፡፡
በተመሳሳይ ዓመት ኤሊውድ ኪፕቾጌ የበርሊን ማራቶንን ሲያሸንፍ 2፡01፡39 በሆነ ጊዜ የዓለም የማራቶን ሪከርድን አስመዘገበ፡፡ ከዓመት በኋላ በ2019 እኤአ ደግሞ ቀነኒሳ የበርሊን ማራቶንን ሲያሸንፍ የኪፕቾጌን የዓለም ሪከርድ በሁለት ሰከንዶች ቢያመልጠውም በውድድሩ ላይ ያሳየው ብቃት ዛሬም ድረስ የሚደነቅ ነው፡፡ ‹‹ በማራቶን ያስመዘገብኩት ሰዓት ከኪፕቾጌ የዓለም ሪከርድ በሁለት ሰከንዶች የዘገየ ቢሆንም  ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተሟላ ጤንነት እና በእቅዴ መሰረት ከተዘጋጀሁ ከማንም የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደምችል አምናለሁ፡፡ አሁን መቶ በመቶ ከጉዳት ነፃ ነኝ፤ በደንብ እየተዘጋጀሁም ቆይቻለሁ፤  በወቅታዊ ብቃቴም በጣም ደስተኛ ነኝ›› በማለትም ቀነኒሳ ለስፖርት ኢለስትሬትድ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
በአጠቃላይ ቀነኒሳ  በቀለ ከ1500 ሜትር ጀምሮ እስከ ማራቶን ድረስ 20 የሩጫ ዓመታትን እንዳሳለፈ ይታወቃል፡፡ በሩጫ ዘመኑ ያስመዘገባቸው ሪከርዶች፤ የሜዳልያዎች ስብስብ እና ተያያዥ የውጤት ታሪኮች የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ አትሌት መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ ከማራቶን በፊት በሩጫ ዘመኑ ከ21 በላይ የዓለም ሻምፒዮናነት ክብሮችንና የወርቅ ሜዳልዎችን ሰብስቧል፡፡ በኦሎምፒክ፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስና በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ለዓለም ሻምፒዮናነት በመብቃት ብቸኛውና የመጀመርያው አትሌት ነው፡፡ በሩጫ ዘመኑም 6 የዓለም ሪከርዶችን በማስመዝገብ በተለይ ደግሞ በረጅም ርቀት 5ሺ ሜትርና 10ሺ ሜትር ውድድሮች የዓለም ሪከርዶችን ከ15 ዓመታት በላይ ተቆጣጥሮ መቆየቱም ይታወቃል፡፡
አሁን 39ኛ ዓመቱን ለያዘው ቀነኒሳ ስፖርት ኢለስትሬትድ ተጨማሪ ጥያቄውን በመጨረሻ ላይ አቅርቦለታል፡፡ በ2024 እኤአ ላይ ፓሪስ በምታስተናግደው 33ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ትሳትፍ ይሆን? የሚል ነው፡፡ ‹‹በ42 እና በ43 ዓመታቸው ኦሎምፒክን የተሳተፉ አትሌቶች መኖራቸውን አውቃለሁ፡፡በደንብ ከተዘጋጀሁ እና ሙሉ ለሙሉ ጤናማ ከሆንኩ አዎ ይቻላል›› ሲል ምላሹን ሰጥቷል
በኮሮና ሳቢያ ሳይካሄዱ የቆዩት የበርሊንና የኒውዮርክ ማራቶኖች በዓለም የአትሌቲክስ  ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ የበርሊን ማራቶን ከኮሮና በፊት ከ107 አገራት ከ66 ሺ በላይ ተሳታፊዎች የሚያገኝና በዋና ዋና ጎዳናዎች ከ1 ሚሊዮን ተመልካቾች የሚያገኝ ነበር፡፡ 50ኛ ዓመቱን ለማክበር የተዘጋጀው የኒውዮርክ ማራቶን ደግሞ በየዓመቱ ለተሳትፎ ከ99ሺ በላይ አመልካቾች የሚያገኝና ከ33ሺ በላይ የሚሳተፉበት ነበር፡፡

Read 9421 times