Print this page
Saturday, 28 August 2021 13:57

“ያልተነገረ እልቂት ታሪክ” መፅሐፍ ነገ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

በአንጋፋዋ  ደራሲ ውደላት ገዳሙ የተፃፈውና ከ46 ዓመት በፊት በአማራ ክልል በአንድ አካባቢ የደረሰን የማህበረሰብ ጭፍጨፋና እልቂት የሚዳስሰው “ያልተነገረ እልቂት ታሪክ መፅሐፍ ነገ ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ይመረቃል።
በ252 ገፅ የተቀነበበውና  በ199 ብር ለገበያ ቀረበው ይሄው መፅሐፍ ከ46 ዓመታት በፊት በቦታው ዘግናኝ የሆነ ጭፍጨፋ ቢካሄድም እስከዛሬ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎችና በጭፍጨፋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ወገኖች ምንም አይነት ድጋፍና እርዳታ ካለማግኘታቸውም በላይ በቦታው ሀውልትም፣ ት/ቤትም ሆነ ሌላ የታሪክ ማስታወሻ ባለመቀመጡ በዚህ ቁጭት መፅሀፉ መዘጋጀቱን አንጋፋዋ ደራሲ ገልፃለች። በርካታ  መረጃ በማሰባሰብ ተጎጂዎችን በማነጋገርና በብዙ ጥናትና ምርምር የተዘጋጀው መፅሐፉ እንዲህ አይነት እልቂቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ለመማሪያነትና ለታሪክነት መሰነዱንም ነው የገለጸችው።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን በመፅሀፉ ላይ ግምገማ የሚያቀርቡ ሲሆን በጭፍጨፋው አካላቸው የጎደለ እናትና አባት፣ ወንድምና እህቶቻቸውን ያጡ ሰዎች ከቦታው ድረስ መጥተው  በምረቃው ላይ እንደሚታደሙና በዕለቱም በቦታው አንድ ማስታወሻ ለማቆም ቃል እንደሚገባ ደራሲዋ ገልፃ መድረኩም የመማማሪያ ይሆናል ብላለች ደራሲ ውዳላት ገዳሙ 6 የህፃነት መፅሀፍትን ሶስት ሌሎች መፅሐፍትንና ከሌሎች ደራሲዎች ጋር በጋራ አራት መፅሐፍትን ለንባብ ማብቃቷ አይዘነጋም።

Read 11521 times