Saturday, 28 August 2021 14:04

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

       …..ቤተልሔም ባሏን በመግደል ወንጀል ተጠርጥራ እነሆ ዛሬም ለሰባተኛ ቀን በእስር ላይ ነች፡፡ የታሰረችበት ክፍል ስምንት የሚሆኑ ሴቶች ያሉበት ሲሆን፤ ክፍሉ ከሌሎች ክፍሎች በስፋቱ ትንሽ ሻል ያለ ነው፡፡ አብረዋት ያሉ ታሳሪዎች ከሦስቱ በስተቀር የተማሩና ደህና የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ከቤተልሔም ቀኝ የምትተኛው ቀጭኗ ሴትዮ ሐኪም ናት እየተባለ ይወራል። ከቤተልሔም ቀጥላ የምትተኛው ሴትዮ ደግሞ የመንግስት ባለስልጣን እንደሆነች የተወራው ወሬ አብዛኛው የክፍሉ አባላት ተስማምተውበታል፡፡ ክፍሉ ከንፋስ እጥረት የተነሳ እምክ እምክ እንዳይል፣ ቀን ቀን በደንብ ስለሚከፈት ብዙም የማያጨናንቅ ነው፡፡ ማታ ላይ ግን ብርዱ፣ ጨለማው፣ የቤተልሔም ተደጋጋሚ ቅዥት አንድ ላይ ተዳምሮ ክፍሉ እጅግ እንዲያስጠላ አድርጎታል፡፡
ዛሬም ሴቶች ሲያወሩ ቆዩና ወደ አምስት ሰዓት ገደማ እንተኛ ተባብለው  ሻማቸውን አጠፉ፡፡ ሻማው እንደጠፋ ቤተልሔም ከመቼውም ማንኮራፋት እንደጀመረች ሁሉም ገርሟቸዋል፡፡ ትንሽ ሳትቆይ  ያንን የቅዠት ድምጿን ማሰማት ጀመረች፡፡
“ጥፋቱ የኔ ነው፡፡ አዎ! የኔ ነው፡፡ አንተን አስቀርቼ እኔ ግን ጥዬህ ሔድኩኝ….” እያለች ዛሬም እንደወትሮዋ ትቃዣለች፡፡
ከሳምንት በፊት፣ቤተልሔም ከአባቷ ቤት ቁጭ ብላ ወንድሟ የሚያወራላትን የጅል ወሬ እየሰማች ሳለ ነው የወንድሟ ስልኩ የጠራው፡፡
“አቶ ይሀይስ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገድሏል ቶሎ ድረሱ፡፡” አለ በስልኩ በዚያኛው ወዲያ የሚያወራው ሰው፡፡
የዛሬ ዓመት ጀምራ በስርዓቱ የምታናግረው ወንድሟ፣ ሊያግባባትና ያስቀየማትን ነገር ይቅር እንድትለው ከስሯ በማይጠፋ በዚህ ሰዓት፣ ስልኩ እንዴት ሲጠራ ፈጥኖ አነሳው፡፡ የመርዶ መልዕክቱን ሲቀበል እሷ እንዳትሰማና እንዳትደናገጥ ያደረገው አንዳች ጥንቃቄ አልነበረም። የሚሰማውን ነገር እሷም እንዳትሰማ የማድረጉ አስቀያሚነት ዛሬም ድረስ አልገባውም፡፡
የሰማው ነገር እንዳለ ሲነግራት መጀመሪያ አጥወለወላት፣ እግሮቿ ዛሉና መሬት ሲርቅባት ተሰማት፡፡ አስደንጋጩን መርዶ እንደ ቀልድ ተናግሮ እህቱ በድንጋጤ ስትጮኽ፣ ስትወድቅና አናቷ በጠረጴዛው ጫፍ ሲነረት ሲያይ፤ የሚያደርገው ጠፍቶት ክው ብሎ እንደደነገጠ ቆሞ ቀረ፡፡
“ልጄን…!” ብለው አባቷ ከውጭ ዘለው ሲገቡ፣ እሱ በድንጋጤ ባለበት ደንዝዟል፡፡ የሚለው ሲጠፋ በጅል ድምጹ “ወደቀችና ጠረጴዛው አናቷን መታት፡፡” አለ፡፡
ከሐዘኗ በተጨማሪ፣ ድንጋጤና የተመታው አናቷ፣ ዛሬ ለተከሰተው የአንጎል እጢ መንስኤ ነበር፡፡ ታማ የጣዕር ሆስፒታል እስከገባችበት ጊዜ ድረስ፣ የአንጎል እጢው  በመላው አካላቷ ለተሰራጨው ኢንቬክሽን ዋና ምክንያት ሆነና የሞት ጣዕር ስቃይ ማስተካከል መጀመሩን ማንም አያውቅም ነበር፡፡
የአሜሪካ ዜግነት ያለው አቶ  ይሀይስ ማን እንደገደለው ሣይታወቅ ተግድሎ ሲገኝ ፖሊስ የተጠረጠረውን ሁሉ አፍሶ እስር ቤት አጎረ፡፡ ቤተልሔምም አንድ ሳምንት ያህል ለምን ተለይታው አባቷ ቤት ታድር ነበር የሚል ጥያቄ ተነሳና ተጠርጥራ እሷም ታሰረች፡፡ የዕጢው ህመም አንዳንድ ቀላል ምልክቶች ማሳየት የጀመረው እስር ቤት በገባችበት በአንደኛው ሳምንት አካባቢ ነው።
ህመሙ ማታ ማታ ይብስባትና በእንቅልፍ ልቧ ክፉኛ ያስቃዣታል፡፡ በአብዛኘው የባሏን በድን ወለሉ ላይ ተዘርሮ ያየችበትን ሁኔታ በህልሟ ይመጣባታል፡፡ ይህን አስፈሪ ትዕይንት ሲታያት በድንጋጤ እየጮኸች ከእንቅልፏ ትባንናለች፡፡
እንደምንም ራሷን አረጋግታ እንቅልፍ ሸለብ ያረጋትና ትንሽ እንደቆየች “እኔን ጥለህ ልትሄድ?!” ብላ ከሕይወት ጉዞው ያስቆመችውን ሰው ደግሞ በህልሟ ይመጣባትና በድንጋጤ ትባንናለች። ከእንቅልፏ ባንናም ዓይኖቿን ገልጣ ከሰዎች ጋር ማውራቱ ስለሚያስጠላት ፀጥ ብላ ሰዎች ስለ እርሷ የሚያወሩትን ብቻ ትሰማለች፡፡ ዛሬም ያደረገችው ይህንኑ ነው፡፡
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ለምን እንደሆነ ባይታወቅም፤ የሚሰማው ዜና ሁሉ የቅርብ አጋራቸውን በሞት ያጡ ሰዎች የሞት ወሬ ነው፡፡” ብለው ሴቶች ያወራሉ፡፡ ይህን ስትሰማ ገረማት፡፡
“ይህ ዓመት የፍቅረኛሞችና የትዳር አጋሮች ሞትን ተከትሎ መሞት እየተበራከተ የመጣበት ዓመት ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ግን ማንም አያውቅም፡፡” ትላለች፤ አንዷ ስለ ሟቾቹ  ይሀይስ ከፖሊሶች ሲወራ የሰማች ሴትዮ፡፡ ይህች ሴትዮ እስረኞችን ለመሰለል የታሰረች ሰላይ እንደሆነች ማንም ሰው አያውቅም፡፡
“የሞታቸው ዋና ምክንያት የፍቅር ልብ ስብራት ነው፡፡ በዚህ የሚወራረድ ካለ ሊወራርድ ይችላል፡፡” ብላ ትመልሳለች- የሰው አናት ፈንክታ የገባችው ታሳሪ፡፡
“በፍቅር የተሰበረ ልብ ለሞት ሊዳርግ አይችልም፡፡” በማለት ሴቶቹ ሁሉ የሚያስቡት አስተሳሰብ በመናቅ፤ መመፃደቅ ጀመረች፤ የወንዳወንድ ደምጽ ያላት ሌላኛዋ ጉልቤ ሴት፡፡
“በእውነቱ ግን የተሰበረ የእውነተኛ አፍቃሪ ሰው ልብ ፣ፍቅሩ ለመሞቱ ምክንያት ለምን አይሆንም?” በማለት፤ ቤተልሔም በልቧ ራሷን ጠየቀች፡፡
“ድሮ ድሮ፣በደጉ ዘመን ማንም ቢጠይቀኝ፤ መልሴ “አዎ የፍቅረኛዬ ሞት ልብ ለሞት ይዳርጋ የሚል ነበር፡፡ ፍቅረኛን የማጣት ሐዘን ለሞት መንስኤ ተደርጎ በስፋት ሲወሰድ ኖሯል፡፡ ከሠላሳ ዓመታት ወዲህ የሳይንስ ሊቃውንት እንዲህ ዓይነቱን የሚስኪን አፍቃሪያን  ሀሳብ ነው በማለት፤  ምክንያቱንም ውድቅ አድርገውት ነበር። ዛሬ ግን እንደገና ወደ ቀድሞ አስተሳሰብ በመመለስ፣ አዎ ሐዘን ለሞት ምክንያት ነው የሚለውን የሚቀበሉ ምሁራን አልፎ አልፎም ቢሆን ታይተዋል፡፡” አለች ዘአንዷ የህክምና ባለሙያ እንደሆነች በስፋት የሚወራላት ታሳሪ፡፡ ቀጠለችና፤
“ዛሬ በስፋት በተጠናቀሩ መረጃዎች ማለትም በሰነድ በተዘረዘሩ መጥፎ  የልብ ምት መዛባት ዜናዎች፤በሐዘን ምክንያ የሚከሰቱ ውጤቶችን በሚመለከቱ ጥናቶች ወይም በተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋዎችና እንዲሁም በጭንቀትና በድብርት የሚመጡ የስሜት ቀውሶች በልብ ላይ ምን ያህል ተፅኖ እንደሚያሳድሩ በተሻለ መታወቅ ተችሏል፡፡” ብላ በልበ ሙሉነት ስታብራራ፣ ሴቶች ሁሉ ብዙ የማናውቀው ነገር ይኖራል ብለው ስላሰቡ ፀጥ ብለው ማዳመጣቸውን ቀጠሉ፡፡
“ምንም እንኳን የትዳር አጋር ሞት በቀናት አሊያም በሳምንት ውስጥ በሕይወት የተረፈው ሲሞት የሚተርኩ ታሪኮች ሲነገሩ አፈታሪክ ስለሚመስሉ ባይታመንም፤ታሪኮቹ ግን ብዙውን ጊዜ እውነትነት አላቸው፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች በሕይወት የተረፈው የትዳር አጋር፣ የትዳር አጋሩን የሞት ዜና ሲሰማ፤ በድንጋጤ ብዛት ሲወድቁ ታይተዋል፡፡ በሌሎች አጋጣሚዎች ደግሞ፣ ከሞት የተረፈው ሰው ለሞት የተዘጋጀ ህሊና ሲይዝና ሞትን በፅኑ ሲመኝ  ተሰምቷል፡፡” ብላ ስታብራራ፣ አንዷ ሴት ወደ ወንዳወንዷ ሴት ጆሮ ጠጋ ብላ  “ይህች ሴት እውነትም ሐኪም ነች፡፡” አለቻት፡፡
ምንጭ፡- (ሞት በውክልና የተሰኘ መፅሐፍ  የተቀነጨበ)

Read 1238 times