Monday, 30 August 2021 00:00

ስለ ራሴ የተፃፈ ወግ

Written by  ረድኤት አሰፋ
Rate this item
(1 Vote)

እድሜዬ እየገፋ ነው። አገፋፉ ግን እንደ ፅንስ አይደለም። ጽንስ የሚጠበቅ ውጤት አለው። ከእድሜዬ መግፋት ግን የምጠብቀው ምንም የለም። እግዚያብሔር ይመስገን ከመጠበቅ ነፃ ነኝ። ስለዚህ የሆንኩትን እቀበላለሁ። የሆንኩትን መግለፅ እንጂ ያልሆንኩትን ለመሆን አልፍጨረጨርም። እና በገዛ ልኬና መልኬ እገለጣለሁ። ... ስለዚህ እድሜዬ እየገፋ ነው የሚለውን አሰልቺ አባባል ላሻሽለው።
እድሜዬ እየሳበ ነው። የሆነውን ሁሉ ወደ ራሱ እየሳበ ነው።..
ስበት አንድ
እጥላለሁ።
የማልጥለው ጉድ የለኝም። ኪሴ ነፍሱ ቀዳዳ ነው። በተዘጋ ዚፕ በተቆለፈ አዝራር ሾልኮ የማይጠፋብኝ ነገር የለም። የያዝኩትን አንድ የደረስኩበት ቦታ አስቀምጬው ተነስቼ እብስ ነው። መጣሌን እንኳ አላስታውሰውም። የጣልኩት ድንገት ሲያስፈልገኝ እጆቼን ገልመጥ... ኪሶቼን ገልበጥ ቆዳዬን ሁሉ ለጠጥ አድርጌ ነው መጣሌን የማውቀው። ያልጣልኩትና የማልጥለው ነገር የለም።
ጥሬ ብር በየታጠፍኩበት ስዘራ ነው የኖርኩት። ከኪሴ የተሻለ የተራመድኩበት ጎዳና የታጠፍኩበት ኩርባ ገንዘብ አላቸው። በእጄ የያዝኩት... ኪሴ የከተትኩት ድፍኑም፡ ከፊል ዝርዝሩም፡ ደቃቅ ዝርዝሩም ባለፍኩበት በቆምኩበት በተቀመጥኩበት ይዘራል። የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የጣልኩት ገንዘብ ከእቁብ ተቆጥሮልኝ አንድ ቀን የሚወጣበትን ቀን በእምነት የምጠብቅ ተስፈኛ ነኝ። የመንገድ የድልድይና የጎዳና እቁብተኛ ነኝ። ከግዑዛን ጋር እቁብተኛ ነኝ። አምናለሁ ይደርሰኛል።
ስሜን ረድኤት አሉኝ። አይኖረኝም... አላከማችም... አልከምርም... ግን ጎድሎብኝ አያውቅም። ቢጎድልብኝም ከፍቶኝ አያውቅም... ቢከፋኝም... መፅናኛ አላጣም። «አባ ዝራው»ነቴ ከስሜ ሳይጀምር አይቀርም። እግዚአብሔር አዝኖልኝ እጅና እግሬን አጣብቆ ፈጠረልኝ እንጂ ይሄኔ ብልቶቼ በየእጥፋቱ ወድቀው ቀርተው ነበር። ያልጣልኩት ያልጠፋብኝ ነገር የለማ! ንብረቶቼን እንደ አስራ ሁለቱ ኅዋርያት እና ሰባ ሁለቱ አርድእት በየአቅጣጫው ተበትነው ስለኔ ይሰብኩ ይሆን? አዲስ ባለንብረት አፍርተው ይሆን? ፈርሰው በስብሰው ቀርተው ይሆን? አንዳንዴ አስባቸውና የደረሱበትንና የደረሰባቸውን ለማወቅ እጓጓለሁ! ግን ይከብደኛል።
ከልጅነቴ ጀምሮ ስጥል ነው የኖርኩት።ጋዝ ግዛ ተብዬ የጋዙን ጀሪካን ቤት ጥዬው... ረዥም ሰልፍ ተሰልፌ... ቀጂው «የታል ያንተ?» ሲለኝ ድንግጥ... ቅጥቅጥ... ።
እርሳስ፡ እስኪብርቶ፡ ላጲስ፡ መቅረጫ፡ ማስመሪያ፡ ኮምፓስ፡ ደብተር፡ መፅሐፍ፡ ወርሃዊ ክፍያ፣ ምሳ እቃ... ዩኒፎርም (ሹራብም ሰደርያም) የፈተና ወረቀት፡ የውጤት ካርድ... ያልጣልኩት የለም። አምስተኛ ክፍል እያለሁ ሙሉ ቦርሳ ጥዬ ቤተሰቦቼንና ጓደኞቼን ሰርፕራይዝ አደረግኳቸው። ግቢ ስገባም አመሌ አብሮኝ አደገ። የግቢ መታወቂያዬ ሶስት ወር ከእኔ ጋር መክረሙን አላስታውስም። ድጋሚ መታወቂያ የማውጫዋ መስኮት ቤቴ ትመስለኝ ነበር። ምግብ መመገቢያ ካርዴን ደጋግሜ ጥዬ... ከጓደኞቼ ጋር በጀርባ በር እየገባሁ መመገብ ስራዬ ነበር። መታወቂያዬንም ሚልካርዴንም ደርቤ ጥዬ እንደ እስረኛ ከግቢ ሳልወጣ በቆሎና በበሶ የከረምኩባቸው ቀናት ቀላል አይደሉም። ቤተሰቦቼ የላኩልኝን ገንዘብ እዛው ባንኩ በር ላይ ጥዬ ወደ ግቢ መመለሻ ሳንቲም አጥቼ.. በችግር የተቆራመድኩባቸው ቀናት ጥቂት አልነበሩም። የተመዘግብኩባቸው ስሊፖችና ውጤት የተቀበልኩባቸው ወረቀቶች ለታሪክ እንኳን አሁን ያኔም አንዳቸውም የሉም።
ስራ አለም ላይ ፋይል ያከማቸሁባቸው ፍላሾች፡ ሲዲዎችና ሀርድ ዲስኮች ጠፍተውብኛል። ዶክመንቶች ከቀላል እስከ ውስብስብ ኮንፊደንሻል የት እንደገቡ አላውቅም። ሙሉ ደሞዜን ጥዬው የደሞዝ ማግስት በመበደር የሰራተኛውን መደብ ሪከርድ አሻሽያለሁ። ከወር እስከ ወር በብድር የዘለቅኩባቸው ቀናት ቀላል አይደሉም። ብሬን ጥዬ ታክሲ ውስጥ ሰቀቀን እንደ ምስጥ ውስጤን ሲያፈርሰኝ... ላብ አንዲቷን ጥምቀቴን ሲከልስብኝ ነው የኖርኩት። የመስሪያ ቤትና የቀበሌ መታወቂያዎቼ ይሄኔ በየመስኮቱ ተንጠልጥለው ቀርተዋል። የኛን ቤት የቀበሌ ፋይል የሞላው እኔ መታወቂያ በጣልኩ ቁጥር ከፖሊስ እያመጣሁ ያከማቸኋቸው ወረቀቶች ክምር ነው። መታወቂያ ሳሳድስ ትዝ አይለኝም። ለአቅመ መታደስ ከመድረሳቸው በፊት ጠፍተዋል።
ሞባይል ስልኮቼን የሜክሲኮ፡ የመሿለኪያና የመገናኛ መንገዶች ይቁጠሯቸው። ከተዘረፍኳቸው እኔ ጥያቸው በየታክሲው፡ በየታክሲ መጋፊያው፡ በየካፌው በየላይብረሪው የረሳኋቸው ይበልጣሉ። የደሞዜን ግማሽ እያደር የምጥላቸውን ቻርጀሮች፡ ኬብሎችና ኢርፎኖች በመግዛት እፈጃለሁ ብል ማን ያምነኛል? የቤትና የቢሮ ቁልፎች እየጣልኩ በየጓደኞቼ ቤትና በየሆቴሉ አድሬ... ቢሮ ደግሞ ሌላ ሰው እስኪመጣ መጠበቅ ግዴታዬ ነው።
በየክፍለሀገሩ ለስራ በሄድኩ ቁጥር መታወቂያ ስለማይኖረኝ ከየሪሴፕሽኒስቱ ጋ መግባባትና ማስተዛዝን ግዴታዬ ነው። በየኬላው ፖሊስ ባየሁ ቁጥር መታወቂያ ይጠይቀኛል እያልኩ አጥንቴን ይበርደኛል። በስራ ምክንያት እጅግ አደገኛ በሆኑ አካባቢዎች መታወቂያ ሳይዙ የመጓዝን ስጋት ከኔ በላይ የሚያውቀው የለም። ከግቢ ጀምሮ እስከ ስራ ከየጥበቃዎቹ ጋር የምቀላለደውና ወዳጅነት የምፈጥረው መታወቂያ እንደማይኖረኝ ስለማውቅ የትውውቅ ቀብድ ለመክፈል ነው። ባንክ ቡክና ኢቲኤም በየጊዜው ይጠፋብኛል። በየባንኩ ከቴለር ጋ «ቡክ የለኝም.. መታወቂያም የለኝ... ተባበሩኝ... በምትል ለልመና ዋሽንት ብቻ በሚቀራት ዜማዬ እስክታወቅ ድረስ ነው የምሰቃየው። ብዙ ማህበራዊ ግንኙነቶቼ በዚህ ፍርሃት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ማንኛውም ህጋዊ ዶክመንት እፈራለሁ እጠላለሁ። እንደማጣውና እንደምቸገር ስለማውቅ... ስቀበለውም በስጋት ነው።
ግጥም የፃፍኩባቸው ወረቀቶች ድራሻቸው የለም። ኧረ የልጅነቶቼ የግጥምና የፅሁፍ አጀንዳዎች ደብዛቸውም የለም። በየመድረኩ ግጥም ላነብ የሄድኩበት መድረክ ላይ ወረቀቶቼን እያጣኋቸው ባለቀ ሰዓት ፕሪንት አድርጌ ... ወይ በቃሌ የማውቀውን ሌላ አቅርቤ አውቃለሁ። በወሬ በወሬ የጥንት ወዳጆቼ «ያቺ ግጥምስ?» ሲሉኝ... የማስታውሳቸው ነፍስያም ስራዎች ነበሩኝ። ባሉበት እግዜር ይጠብቃቸው።  የዲጅታሉ ዘመን አከረማቸው እንጂ አንድም ፅሁፍ ላይኖረኝ ይችል ሁሉ ነበር።
 ችግሩን ከመቀበል ይልቅ ማሻሻል ይቀላል በሚል ብዙ ሞክሬያለሁ። ለማንበብ፡ ለማማከር... ለመጠየቅ። አንድ ያማከረኝ ሰው «ትንሽዬ ማስታወሻ ደብተር ያዝና... የያዝከውን... የሄድክበትንና የምትሄድበትን መዝግብ... ስትንቀሳቀስ እንደ ቼክ ሊስት ትጠቀመዋለህ» ብሎኝ ... ሞከርኳት ዘዴዋን። በነጋታው ማስታወሻ ደብተሯን ጣልኳት። ሌላዋ ወዳጄ... ምእራብ ጎጃም አንድ ፀበል አለ... እንዳንተ ለሚዘነጋ ሰው ፍቱን ነው ብላ መርታኝ... አራት መቶ ኪሎ ሜትር በመኪና፣  ሁለት ሰዓት በእግር የሄድኩበት ቅዱስ ስፍራ... በንጽሕና ምክንያት መጸበል አልቻልኩምና... አምስት ሊትር ጠበሌን አስቀድቼ ተመልሼ መኪና ውስጥ ጀሪካኑን ጥዬው ወረድኩ።
«በሙሉ ልብህ ስለማትኖር ነው የያዝከው የጨበጥከው የሚጠፋብህ... ቁሳቁስ ጣልኩ ትላለህ እንጂ አንተ ራስህ የታለህ? » አለችኝ! ልክ መሰለችኝ...
በእርግጥ ራሴን ፈልጌው ስለማላውቅ መጥፋቱን አላውቅም ነበር። ወትሮም ስፈልጋቸው ነው የጠፉኝን ሁሉ የማውቃቸው። ራሴን አሁን ፈለግሁት... ይሄኔ ጠፍቷል... እድሜዬ እየሄደ አይደል? መንገድ ላይ ሊያገኘው ይችላልና መሄዱን ይቀጥል...
አምላከ እስራዔል ይመስገን!
 (ወደ ክፍለሀገር የሚሄድ ባስ ማቆሚያ ላይ... ትኬቱን መጣሌን ሳውቅ የተፃፈ)


Read 233 times