Saturday, 04 September 2021 13:33

ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ በድንገተኛ ህመም አረፈ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አንጋፋው ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ  ባደረበት የልብ ህመም ሳቢያ፣ በ79 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ድምጻዊ አለማየሁ የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን እስከ ሦስት ዓመቱ ድረስ ከእናቱ ጋር ደሴ ነበር ያደገው።  የሦስት ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ ወደ አዲስ አበባ አመጡት። ‘ክርስቲያን ትሬኒንግ ኢንስቲቲዩት’ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ በትምህርት ቤቱ ቆይታውም መንፈሳዊ መዝሙሮችን  በእንግሊዝኛ ጭምር በመዘመር  ይታወቅ ነበር።
በዘመኑ ተወዳጅና እውቅ የነበሩ የምዕራባውያን ድምጻውያንን ሙዚቃ ማንጎራጎር ያዘ። በተለይ የሮክ የሙዚቃ ስልት ለአለማየሁ ነፍሱ ነበር። የአሜሪካውያኑን ድምጻዊያን ፓት ቦን፣ ቢል ሃሊይ እና ኤልቪስ ፕሪስሊን የእንግሊዝኛ ዘፈኖች አብዝቶ ይጫወት ነበር። የኤልቪስ ፕሪስሊን ሙዚቃ አብዝቶ በመጫወቱ፣ በፀጉር አበጣጠሩና ዘመናዊ አለባበሱ ‘ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ’ የሚል ቅፅል ስምም ተሰጥቶት ነበር፡፡  
በዚህ እውቅናን እያተረፈ የመጣው አለማየሁ በጀነራል ዊንጌት፣ በዳግማዊ ምንሊክና በሌሎችም ትምህርት ቤቶች እየተጋበዘ ይዘፍን ነበር። በወቅቱ ለአማርኛ ዘፈን ብዙም ግድ አልነበረውም፡፡
ከአለማየሁ እሸቴ የሙዚቃ ሥራዎች መካከል "ስቀሽ አታስቂኝ"፣ "እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ"፣ "ማን ይሆን ትልቅ ሰው"፣ "ምሽቱ ደመቀ"፣ "አዲስ አበባ ቤቴ"፣ "የወይን ሃረጊቱ"፣ "የሰው ቤት የሰው ነው"፣ "ደንየው ደነባ"፤ "ትማርኪያለሽ"፣ "ወልደሽ ተኪ እናቴ"  እና "ተማር ልጄ" በዋነኝነት ይጠቀሱለታል፡፡
የድምፃዊውን ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ የመንግስት ባለሥልጣናትና አርቲስቶች እንዲሁም አድናቂዎቹ ሀዘናቸውን እየገለፁ ይገኛል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት የሃዘን መልዕክት፤ ሃገራችን ካፈራቻቸው ታላላቅ ድምጻውያን አንዱ በሆነው በአለማየሁ እሸቴ ዜና እረፍት እጅግ አዝኛለሁ ብለዋል፡፡
‘‘የአለማየሁ ዘመን ተሻጋሪና ቁም ነገር አዘል ግጥምና ዜማዎቹ በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ለዘለዓለም ይኖራሉ’’ ሲሉም  አስፍረዋል፤ በመልዕክታቸው። ለድምጻዊው ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።
አዲስ አድማስ ጋዜጣ በድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ  ህልፈት የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ፤ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።


Read 13602 times