Saturday, 04 September 2021 13:36

አዲስ መንግስት ምስረታውና ተፎካካሪ ፓርቲዎች

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(8 votes)

   - አዲስ መንግስት ምስረታው የኢትዮጵያን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ነው - ኢዜማ
      - አዲስ መንግስት ምስረታው አገሪቷን የማፈራረስ ጉዞን ያፋጥናል - ባልደራስ
      - የመንግስት ምስረታው አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን - እናት ፓርቲ
     - መንግስት ምስረታው ቀርቶ ሰላም ቢወርድ መልካም ነው - ኦፌኮ
                 
            የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ መንግስት ተገድዶ በገባበት ጦርነት ሳቢያ ፓርላማው ወደ ስራ አይገባም እየተባለ የሚነገረው ከእውነት የራቀ መሆኑንና ምክር ቤቱ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ተሰይሞ አዲሱን መንግስት እንደሚመሰርት ሰሞኑን ይፋ አድርገዋል። የሚመሰረተው አዲስ መንግስት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ በነቂስ ወጥቶ የመረጠውን ህዝብ በታማኝነት የሚያገለግል ይሆናልም ብለዋል።
የአዲሱ ምክር ቤት አባላት የህዝብ ውክልናቸውን ለማረጋገጥ ወደ መረጣቸው ህዝብ እያቀረቡ ውይይት በማድረግ የሚሰሩበት ሁኔታ እንደሚፈጠር የገለጹት አፈጉባኤው፤ በአዲሱ መንግስት ምስረታ ውስጥ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከ7 እስ 13 ሆኖ ይደራጃል ብለዋል።
ስድስተኛው ዙር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እውነተኛ የህዝብ ውክልና ያለው ምክር ቤት ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።
የአዲስ መንግስት ምስረታውን በተመለከተ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተለያዩ አቋሞችን አንጸባርቀዋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ  (ኢዜማ)፤ የመንግስት ምስረታው በወቅቱ መከናወን ያለበትና የኢትዮጵያ ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ይገልጻል። የኢዜማው ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ። “ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጪ የሚደርሱባትን ከፍተኛ ተቃውሞና ጫና ለመቋቋምና እንደ አገር ለመቀጠል ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ያስፈልጋታል። ምንም አይነት ቅሬታ ቢኖረን ምንም ያህል ችግር አለ ብለን ብናምን በአገር መቆምና መቀጠል ጉዳይ ላይ ልንደራደር አንችልም።
ምንም አይነት ማሻሻያ ማድረግ የሚቻለው በቆመ ነገር ላይ ነው፤ በወደቀና በፈራረሰ ነገር ላይ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም፤ ስለዚህም አገሪቱ እንደ አገር መቀጠል ይኖርባታል። ለዚህም የመንግስት ምስረታው ምንም ጊዜ የማይሰጠውና ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ኢዜማ ያሉትን ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች ለአገርና ለህዝብ ሲል በማቆየት ለአዲስ መንግስት ምስረታው ድጋፉን ያደርጋል ያሉት አቶ የሺዋስ፤ ምርጫ ቦርድ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለው ድምጽ አግኝቷል ያለው ፓርቲ መንግስት በመመስረት ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስትን ማቋቋም ይኖርበታል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢዜማ ሊቀመንበርን ሃሳብ የሚጋሩት የእናት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ፤ ምንም እንኳን በምርጫው ሂደት ላይ በርካታ ቅሬታዎች ቢኖሩንም ዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት የሚረጋገጥበትና አገር እንደ አገር የምትቀጥልበት መንግስት መቋቋም አለበት ብለን እናምናለን ብለዋል።
ምርጫው ከህውኃት በባሰ አፈና የተከናወነ ምርጫ ነበር ያሉት አቶ ጌትነት፤ ገዥው ፓርቲ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምጽ በማግኘቱ ቀሪውን መስከረም 20 ይደረጋል የተባለውን ምርጫ እንኳን ነፃና ፍትሃዊ ቢያደርገው ጥሩ ነው ብሏል።
አዲሱ መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ስለሚገባቸው ጉዳዮች ሃሳብ መስጠታቸውን የተናሩት አቶ ጌትነት፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ ዓይን ያወጣውን የሙስና ተግባር መግታትና ወጣቱን ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ መንግስት የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ተግባራት ናቸው ብለዋል።
የአዲሱ መንግስት ምስረታው አገሪቷን የማፈራረስ ጉዞን የሚያፋጥን ነው የሚሉት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት አቶ ወግደረስ የመንግስት ምስረታው ስርዓትን ያልጠበቀ አምባገነናዊነት ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል። “በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ምርጫ ባልተደረገበት፣ በርካታ ተፎካካሪ  ፓርቲዎች በምርጫው ላይ ቅሬታ አቅርበው ገና ምላሽ ባላገኙበት ሁኔታ የትህነግን የአውራ ፓርቲ አካሄድ ተግባራዊ በማድረግ መንግስት ለመመስረት መሞከር ታላቅ ቧልት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ብሔራዊ እርቅ በማድረግ ያለ ጥፋታቸው የታሰሩ ንፁሃን የባልደራስ አመራሮችና ጋዜጠኞች  ከእስር እንዲፈቱ በማድረግ ለሰላና ለእርቅ መቀመጥ በሚያስፈልግበት በዚህ ጊዜ በአምባገነንነት እኛ ብቻ ነን ለዚህች አገር መሲህ የሚለው አካሄድ ፈጽሞ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም ያሉት አቶ ወግደረስ ባልደራስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም በቅርቡ ይፋ ያደርጋል ብለዋል።
ምርጫው የምርጫን ዝቅተኛ መስፈርት እንኳን የማያሟላ በመሆኑ ውጤቱን የማንቀበል መሆኑንም አሳውቀናል ሲሉም ተናግረዋል።
የኦፌኮው ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በሰጡት አስተያየት፤ “አሁን በድፍን አገሪቱ ጦርነትና ስደት ባለበት፣ በርካቶች በሚሞቱበትና  በሚሰደዱበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ይህንን ችግር ለማስቀረት ከመሞከር ይልቅ ህብረተሰቡ በዚህ  አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ሰዓት የህዝቡን ትኩረት ወደ ሌላ አቅጣጫ አዙሮ መንግስት ለመመስረት መሯሯጡ ተገቢ አይደለም።” ይላሉ።
ለህዝቡ የሚያስቡ ከሆነ መንግስት ምስረታውን ትተው  ሁሉም ሰው በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ ችግሩን የሚፈታበትንና ሰላም የሚወርድበትን መንገድ መፈለግ ይሻል ብዬ አምናለሁ። መንግስት ምስረታው ግን ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።
መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም የሚሰየመው አዲሱ ምክር ቤት በየወሩ ሙሉ ሳምንት አባላቱ ተሰብስበው የአስፈጻሚ አካላትን ሪፖርት የሚያዳምጡበትና ህግ የሚያወጡበት አዲስ አሰራር ተግባራዊ ያደርጋል ተብሏል።


Read 14052 times