Saturday, 04 September 2021 13:37

ኮሮና 30 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ለስራ አጥነት ዳርጓል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በመላው አፍሪካ 30 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ከስራ ገበታቸው በማፈናቀል ለስራ አጥነት መዳረጉንና ወረርሽኙ በፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ሳቢያ በ2021 ብቻ 39 ሚሊዮን ያህል አፍሪካውያን ለከፋ ድህነት ሊጋለጡ እንደሚችሉ የአፍሪካ ልማት ባንክ አስታውቋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አዴሲና ባለፈው ሰኞ ለሲኤንቢሲ እንደተናገሩት፤ አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ እስከ 190 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ቅናሽ የገጠማት ሲሆን፣ የበጀት እጥረቷም ከቀውሱ በፊት ከነበረው 60 በመቶ ወደ 70 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
ከ7.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት አፍሪካ ከኮሮና ተጽዕኖ ማገገም የምትችለው በቂ ክትባት ስታገኝ ብቻ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ከአህጉሪቱ ህዝብ ሙሉ ለሙሉ ለመከተብ የቻለው 2.5 በመቶው ብቻ መሆኑንና ይህ መጠን ከእስያ 25 በመቶ፣ ከደቡብ አሜሪካ 27 በመቶ እንዲሁም ከ40 በመቶ በላይ ከደረሰው የአውሮፓና አሜሪካ የክትባት ሽፋን አንጻር ሲታይ እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
በሌላ የአፍሪካ ኮሮና ዜና ደግሞ፣ የደቡብ አፍሪካ ተመራማሪዎች ራሱን በተደጋጋሚ የመቀያየር ባህሪይ ያለውና ሲ.1.2 የሚል ስያሜ ያለው አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ማግኘታቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ የስርጭትና የገዳይነት ደረጃውን ጨምሮ በቫይረሱ የተለያዩ ተፈጥሮዎች ዙሪያ ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ መነገሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሁሉም የአገሪቱ ግዛቶች ታይቷል የተባለው ይህ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓና እስያ ከተሞች ሰዎችን ማጥቃቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2862 times