Sunday, 05 September 2021 00:00

"የከተማው መናኝ" ሃሳቦች ሲፈተሹ

Written by  ቤኪ
Rate this item
(0 votes)

  እነዚህ ገፆች በመልክሽ አይበልጥሽም አልበም  “ታማሽ በጨረቃ/ጀምበርየ” ስራ ላይ የተመረኮዘ ትንታኔ ሰፍሮባቸዋል። ኤልያስ መልካ ከፊዚክስና ስነ ፈለክ ጋር የገጠመውን ሙግት፣ ሰምና ወርቁን እያነጠረ ይተነትናል። ይነገር ጌታቸውም፣ ኤልያስ መልካ ሃሰትነት ያለባቸውን የሳይንስ የምርምር ውጤቶችን ከሙዚቀኛው ሶስተኛ ብሎ በመደበው የህይወት አጋማሽ ጉዞው፣ ሰማያዊውን ሕግ ከተረዳበት አንፃር ለማረም የሄደበትን ርቀት ያስገነዝባል። በእርግጥ ኤልያስ መልካ ከሳይንስ ጋር ሙሉ ለሙሉ አታካራ ውስጥ አልገባም፤ ለዚህም እንደ ማሳያ የመፅሐፉ ደራሲም በከተማው መናኝ ገፅ 200 እንደ ማጠቃለያ የተጠቀመበትን በቺጊ አልበም ሃይሌ ሩትስ እና እዮብ መኮንን የተጫወቱት ስራ እንደ ማሳያ አቅርቧል።
እውቀት መልካም ነው መመራመር
የሰሪውን እጅ ሳይዳፈር
የሳይንሱን ዛፍ መርጠው ካልበሉ
የሞት ፍሬ አለው በየመኻሉ
ኤልያስ መልካ ስህተት ያለውን ፈጣሪን የካዱ ባላቸው የሰው ልጅ የእውቀት ምርምርን (Human Knowledge) በተደጋጋሚ ከመሞገት አልቦዘነም። ይህ ደግሞ እንደ ማቲው ላውሪትሰን በክርስቲያናዊ ስነ ምግባር (Christian Ethics) ወጥነት እና ርቱዕነትን (Consistency & Rational) ማንፀባረቂያ ተደርጎ ከመቆጠሩም ባሻገር በኮንቴምፖራሪ ክርስትያናዊ የመዝሙር/ሙዚቃ ስራ ላይም በፈጣሪ የሚቀርብን ጥሪ መቀበያ መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል።
ጀምበርየ ኤልያስ መልካ በስራዎቹ በተለያዩ ሃሳባዊ ማጠንጠኛ መንገዶች ሲያንፀባርቃቸው ለነበረው የዘፍጥረት የመፅሐፍ ቅዱስ ሃሳብ ማጠናከሪያ ይሆናል። ከእዮብ መኮንን እስከ ልዑል ኃይሉ፥ ኤልያስ በተሳተፈባቸው የሙዚቃ ስራዎችም ዘፍጥረትን ከመጀመሪያ እስከ ስድስተኛ ዕለት ባሉ የፈጣሪ የፍጥረት (creation) ስራዎቹን አቅርቧል። እነዚህ ስራዎችንም በሁለት መክፈል ያስችለናል፤ ዘፍጥረት ከአራተኛም ዕለት በፊት እና ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ዕለት በማለት።
ይህ ፅሁፍ ዳሰሳ የሚያደርገውም ከከተማው መናኝ ገፅ 194-200 ባለው በመሆኑ የኤልያስ መልካ የመፅሐፍ ቅዱስ ስነ ፈለክ አስተሳሰብ (biblical Cosmology) ምን ይመስላል? ያልተስማማበት ሃሳብ ምንድን ነው? ስህተቱን እነማን በምን ዘርፍ ፈጠሩት የሚለውን ደራሲው ይነገር ጌታቸው ለማብራራት የሞከረበትን መንገድ መፈተሽ ይሆናል።
የመፅሐፉ ደራሲ የጀምበርየ ነጠላ ዜማ በጠቅላላ ዳሰሳዉን በሚገባ ገልፆታል፤ ጨረቃ ከፀሐይ ብርሃኗን አታገኝም ፣ ኤልያስ መልካ የስርዓተ ፀሐይ አስተሳሰብንም (Hileocentric Theory) እንደማይቀበለው፣ ፀሐይና ጨረቃ በየጊዜያቸው ይሰለጥኑ ዘንድ እንጂ የብርሃን ምንጭ እንዳልሆኑ እንዲሁም ከዘፍጥረት አራተኛው ቀን በፊት ብርሃን እንደነበር በአመክንዮ ድርደራው ያስረዳል፤ ሳይንሱ ደግሞ በተፃራሪው ፀሐይ የብርሃን ምንጭ ነች ሲል፥ ጨረቃ መዋቅሯ ከፀሐይ የተለየ በመሆኑ የራሷ ብርሃን ሳይኖራት ከፀሐይ የምትቀበለውን ብርሃን በምሽት ከሶስት እስከ 16 በመቶ ታንፀባርቃለች በሚል ይሞግታል፡፡
እርግጥ ነው ሙዚቃው የBiblical Cosmolgy ጥያቄን ማጠንጠኛ አድርጓል። እርግጥ ነው ስለ ሰማያዊ ፍጥረት ሙዚቃው ያወራል። በዚህ ደረጃም ሙሉ ለሙሉ ስነፈለክን በጥበብ ልዕልና የገለጠ የሙዚቃ ሰውም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ሊገኝ አይችልም (ስንኝ ጣል አድርጎ ከማለፍ ባሻገር)። መነሻችን የተመረጡ ገጾች ከይነገር የማስረጃ መንገድ መመልከት ይሆናል። ይነገር ኤልያስ እንዴት እንደሞገተ ይናገራል። እዚህ ላይ ሁለት ጉዳዮችን መለየት ያስፈልጋል።
ኤልያስ መልካ በጀምበርየ ስራው ይሁን በአጠቃላይ በሶስተኛ የህይወት ምዕራፍ ስራዎቹ፣ እውነት ያለውን በመያዝ ያንኑ እየመነዘረ ፣ ደጋፊ እውነቶችንም በማቅረብ ስለ እውነት እየተናገሩ ስሁትን የማረም መንገድን ይከተላል። በሎጂክና ስትራክቸር አንፃር ስንመለከተው፣ የመከራከሪያና አመክንዮ ማቅረቢያ መንገዱ/ መዋቅሩ Deductive Argument ሆኖ ይገኛል።
ይነገር ጌታቸው (የከተማው መናኝ መፅሐፍ ደራሲ) ኤልያስ መልካ ከሰራቸው ስራዎች በመፅሐፉ የመራረጣቸውን ሲያስረዳም፣ የኤልያስን አቋም በመያዝ ደጋፊ የሆኑ እና ለትንታኔው የመረጣቸው መዛግብቶችን በማጠናቀር እንዲሁም ስሁት የተባሉትንም በማመላከት ነው። ይህ ደግሞ የዳታ /የመረጃ ስብስብ ጥቅም ላይ ሲውል፣ የአመክንዮ ድርደራ መዋቅራዊ ሂደቱ ደግሞ Inductive Argument ይሆናል። ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ደግሞ አመክንዮ የደረደረበት መሰረት ትኩረትና ጥንቃቄ እንዲደረግባቸው ያስገድዳል።
በመሆኑም ፀሐፊው ለአንባቢያን የኤልያስን ሃሳብ ለመረዳት በጥንቃቄ ስራዎቹን ልናዳምጣቸው እንደሚገባ ሲነግረን፣ ጥናታዊ ይዘት ባለው የመፅሐፉ አቀራረብ የፀሐፊው Logic & Structure የምንፈትሽበት አቀራረብን እናገኛለን። ይህ ደግሞ በመስመሮች መሃከል የይነገርን የአገላለፅ መንገድንና የተጠቀመባቸውን ዳታዎች መፈተሽ አስፈልጓል።
• ታማሽ በጨረቃ [ጀምበርየ]
ኤልያስ መልካ በመፅሐፍ ቅዱስ የስነ ፈለክ እውቀትን በጀምበርየ ተቃኝቶበታል። በተለይ ደግሞ በአራተኛው ቀን በእኩል የተፈጠሩት (ፀሐይ እና ጨረቃ ) ስላላቸው ሚና ከሰሙ ቀጥሎ የወርቁ ፍቺ አድርጎታል። ጌቴ አንለይ በተጫወተው ይህ ግዙፍ ሃሳብ፣ ኤልያስ መልካ ሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል። ስነ ፈለክን (Astronomy) እና ፊዚክስን።
ስነ ፈለክን በኒኮላስ ኮፐርኒክስ በፀሐይ መውጣት እና መግባት ሙግቱን ሲያነሳ
ይህም ስንኝ፤
ስትመጪ አይን ያያል መውጣትሽን
ጧት ሲነጋ፣ ሲመሽ መግባትሽ
(From earth perspective) ከመሬት ባለው እይታ/አረዳድ የተፈጠረ የሰው ልጅ ግንዛቤ ሳይንሱ ብሎ ሲጠራው፤
ፊዚክስን እንደ አጠቃላይ በተለይ ደግሞ በክላሲክ ፊዚክስ እና በዘመናዊ ፊዚክስ፣ በፀሐይ የብርሃን እና ሙቀት ምንጭነት ሲደረግ የነበረውን ሳይንስን መሰረት ያደረገ ጥናትና ግኝትን በጀምበርየ ከመፅሐፍ ቅዱስ አንፃር ሆኖ [ኤልያስ መልካ] ሞግቷል፡፡
የሞቀው ወርቃማ ብርሃንሽ
ጨፍኖስ ማን ያጣል ተፈጥሮሽ
(Heat and light) የጉልበት /energy ምንጭ ምን ይሆን በማለት ሳይንሱ የሚያደርገውን ጥናት አመላካች ይሆናል።
የይነገር ማጠናከሪያ ሃሳቦቹን ስንፈትሽ
እዚህ ላይ ይነገር ማጠናከሪያ ያላቸውን ሃሳቦችን ከገፆቹ እየጠቀስን እየተቸናቸው እንሂድ። ፀሐይ የስርዓተ ፀሐይ ማጠንጠኛ ናት የሚለው የኒኮላስ ኮፐርኒከስ ሕግ፣ የዘመናዊ ፊዚክስ መነሻ ተደርጎ ይቆጠራል ይለናል። በእርግጥ የዘመናዊ ፊዚክስ መነሻው የኒኮላስ ኮፐርኒከስ ዘመንና ያመጣው ሃሳብ ነበር ወይ?
የፕቶሎሚ የስርዓተ ምድር ሃሳብ ከአንድ ሺህ አመታት በላይ (1400) ገዥ ሃሳብ ሆኖ ቆይቷል፣ የፈላስፋው አሪስቶትል ማጠናከሪያ ደግሞ እስከ አስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ለቆየው ገዥ ሃሳብ እንደ ዶግማ ይቆጠር ዘንድ አስገድዷል። የግሪክና የሮማ ስልጣኔ ከመውደቁ በፊት ያለው የስነ ፈለክ እውቀት በጊዜ መለኪያ ሲቀመጥ ግን ጥንታዊ (Ancient Astronomy) በሚለው የጊዜ ክፍል ውስጥ ይካለላል። ከሰባተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የታየው የእስልምና መስፋፋት እንዲሁም የአይሁድ ባህልና እውቀት መዳሰስ መጀመሩ በስነ ፈለክ የቆየው አስተሳሰብ ላይ ተግዳሮት ሆነው ቆይተዋል። በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የፕቶሎሚ የስርዓተ ምድር ቀመር ዳግም የማጤን ሙከራዎች ያለውን እውቀት በአርተር ኢዲንግተን አልያም ሃንስ ቤት በኩል በተቀመረ አስተሳሰብ ላይ የተመረኮዘ አድርገውታል።
በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የቴርሞዳይናሚክስ መሰረታዊ ህጎች መተዋወቃቸውን ተከትሎ፣ ፀሐይ ብርሃንና ሙቀት ለመስጠት ጉልበትና ምንጭ የሚሆናትን ለመመርመር አጋዥ ሆኗል። የሃንስ ቤት የስራ ውጤት የሆነው የስቴለር ቴዎሪ (Stellar Theory) ደግሞ ከጥንት ሲንከባለል ለነበረው ጥያቄና ምላሽ አጥጋቢ በሚባል ደረጃ ምላሽ የሰጠ ሆኖ በተለይ ደግሞ ፀሐይ ጉልበት ሳትጨርስ ለምትሰጠው ብርሃንና ሙቀት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ችሏል።
ኤልያስም ሳይንሱን ሲተች በአሉ እና እንገምታለን ግኝቶች፣ የፈጣሪ ስራን በማንኳሰስ ፈጣሪ የሌለበትን አለም እያገነኑ መምጣታቸው ይሆናል። ፀሐፊ ይነገር ጌታቸውም የሙግቱን ጥልቀትን ለማሳየት በሄደበት መንገድ የተሳሳቱ ዳታዎችን በማስረጃነት ማቅረቡ የአመክንዮ ድርደራው የተሳሰተ እንዲሆን ሲጋብዝ፣ በአንባቢው ላይ የሚፈጠረው የድምዳሜ ውጤት ደግሞ በዛው ልክ የተሳሳተ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ በInductive Argument እይታ መሰረት ሲደረግ ውጤቱም ይገኛል።
በእርግጥ የጀምበርየ ውስጠ ወይራ ሃሳቦች ከበርካታ አውታሮች እየተቃኘ በሳይንሱ የምርምርና ግኝት እንዲሁም በኃይማኖቱ በኩል ያለውንና ኤልያስ በመፅሐፍ ቅዱስ አረዳዱ ላይ ትክክል ብሎ ያመነበትን መሞገቻ ሃሳብ እያነሱ መከራከር ይቻላል። ይነገርም ይህንን በፅሑፉ ላይ በክርስትና አስተምህሮ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን አቡነ ሽኖዳን ያነሱትን ጥያቄ ማካተትና የኤልያስ መከራከሪያ ሃሳብ የሆነውን ዛብያ ለማመላከት( ለማጠናከርም) ሞክሯል። ከዘፍጥረት አራተኛ ቀን በፊት በአንደኛ ቀን ጀምሮ የነበረው ብርሃን ምንድን ነው በማለት ሰፊ ትንታኔ የሚያሰጠውን የነገረ መለኮት ሃሳብን ያነሳል።
ጥያቄው ለሁለት ሚልዮን አመታት ሲብላላም የቆየ ያደርገዋል። በእርግጥ ፀሐፊው ይነገር የአቡነ ሽኖዳ ጥያቄን ከነ ምላሹ ቢያቀርብልን የኤልያስንም ሞጋች ሃሳቦች መረዳት ያስችል ነበር፤ ነገር ግን ሰፊ ትንታኔ የሚያሰጥ ነው በማለት ምላሽ ሳይሰጥበት ወይንም ምላሽ የተሰጠባቸውን ድርሳናት ሳያጣቅስ አልፏል። የነገረ መለኮት ምላሹን ከማየታችን በፊት ግን ይነገር ምላሽ ይሆናል ያለውን ሃሳብ እንተች። ኒኮላስ ኮፐርኒከስ በትንሽ ብርሃን የተመሰለው ጨረቃ የራሱ ህላዌ እንደሌለው ይነግረናል። ጨረቃ ቀን የሰበሰበውን ብርሃን ማታ ይረጫል ይላል። እርግጥ ነው በሳይንሱ ዘርፍ ጨረቃ መዋቅራዊ አፈጣጠሩ ከፀሐይ ስለሚለይና የራሱ ብርሃን ስለማይኖረው ከፀሐይ የተሰበሰበው ብርሃን በምሽት ከ3-16 በመቶ መልሶ ያንፀባርቃል።
ነገር ግን ስለ ጨረቃ የራስ ህላዌ አለመኖር ኮፐርኒከስን መጥቀሱ አሳማኝ ትንታኔ አያደርገውም። በ499 ቅ.ል.ክ ህንዳዊው አርያብሃታ የተባለ የስነ ፈለክ አዋቂ የጨረቃ ብርሃንን በተመለከተ ባደረገው የምልከታ ጥናት፤ ጨረቃ የፀሐይን ብርሃን እንደምታንፀባርቅ ድምዳሜ ላይ በመድረስ ግኝቱን ይፋ አድርጓል። ነገር ግን አውሮፓውያን የራሳቸው የስነ ፈለክ ታሪክ ለማጉላት ሲሉ ብዙውን ጊዜ ስሙ ሲነሳ አይደመጥም። ከዚህም ባሻገር በ11ኛው ክፍለ ዘመን በእስልምና እውቀት የተደገፈው የፊዚክስ የጥናት ውጤት አልሃዘን በተባለ ግለሰብ ሁለት አውታር ያለውን ግኝት ይፋ ማድረግ ችሏል። ይህም ጨረቃ የራሷ ብርሃን እንዳላት እንዲሁም የፀሐይ ብርሃንን በተጨማሪነት በመሰብሰብ እንደምታበራ ይናገራል። የተሻለ ግኝት ተብሎ በታሪክ የሰፈረው ግን የጋሊሊዮ ጋሊሊ ምልከታ ነው፡፡
ወደ ነገር መለኮታዊው ምላሽ እንመለስ። ጆን ዋልተር በብሉይ ኪዳን የነገር መለኮት ትንታኔው፣ ከአንድ ሺህ ገፅ በላይ በከተበው መፅሐፉ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ይሰጥበታል። ምላሽ ለማግኘት የጥንት እስራኤላውያን አረዳድን ማወቅ ያስፈልጋል ይላል። በአራተኛ ዕለት በእኩል ቀን የተፈጠሩት ፀሐይና ጨረቃ ቁስ (Object) መሆናቸውን ይናገራል። በመሆኑም ስለ ብርሃን ምንጭነት ለመረዳት የቁሶቹን ሚና ማወቅ ይኖርብናል። በእርግጥ ፀሐይና ጨረቃ በዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ ቁጥር አስራ አራት ላይ ሚናቸው ተለይቷል። በምዕራፍ አስራ አምስት ደግሞ በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ ይላል። እንዲያ ከሆነ ምንጭነታቸው ጥያቄ ያስነሳል። በዚህ የጥንት እስራኤላውያን አረዳድ ብርሃናቶቹ ብርሃን ይሰጡ ዘንድ እንጂ ብርሃን ምንጭ ይሆኑ ዘንድ እንዳልተፈጠሩ ታምኗል። (In the Israelite view the sun was seen as a source of heat and as a source of light, but not as the source of light.) ይህ ደግሞ በProvider እና Producer መሀከል ሰፊ ልዩነት መኖሩ አሳይቷል። የጀምበርየ ነገረ መለኮታዊ ምላሽ ከሰፊው በአጭሩ ይህንን መስሏል።
ታዲያ ብርሃን የሚሰጡን ከሆነ ከአራተኛ ቀን በፊት የነበረው ብርሃን ምንድን ነው ጥያቄው ይሆናል። ይህ ጥያቄ ነው ሰፊ ትንታኔ የሚያስፈልገው፡፡ በእርግጥ በነገረ መለኮት የተሰጡና የመፅሐፍ ቅዱስ (ብሉይና ሐዲስ) ተጓዳኝ ንባቦችን በመጠቀም ምላሽ ማግኘት የሚቻል ሲሆን ከተነሳንበት አውድ እንዳንርቅ ለጊዜው ምላሹን እንግታው።


Read 12251 times