Print this page
Saturday, 04 September 2021 16:51

በቀዶ ሕክምና ማዋለድ የመሳሪያ ልምምድ ይፈልጋል፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ዶ/ር ራሔል ደምሰው የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት ሲሆኑ የሚሰሩት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ESOG የቦርድ አባል በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር መቀመጫውን ኖርዌይ ካደረገ ላርዴል ከሚባል ድርጅት ጋር በመተባበር ነሐሴ 24/2013 ዓም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለህክምና ባለሙያዎች አውደ ጥናት አካሂዶአል። ላርዴል የተሰኘው ድርጅት በእናቶችና ሕጻናት ጤና ላይ የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡ ላርዴል በአብዛኛው የአዋላጅ ሐኪሞችን ወይንም በአጠቃላይ ጤና ባለሙያ ዎችን በልምምድ ለማገዝ የሚያስችሉ መሳሪያዎችን በማምረት የሚታወቅ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት ከESOG ጋርም ከዚህ በፊት በተለያዩ ስራዎች የሚገናኝና የሚሰራ ድርጅት ሲሆን ከአሁን ቀደምም Emergency obstetric care በሚባለው ፕሮጀክት ሲሳተፍ የነበረና ለማዋለድም ሆነ ለማስተማር እንዲሁም ለስልጠና የሚጠቅሙ እቃዎችን ሲያመጣና ከማህበሩ ጋር በመሆን ስልጠና ሲያካሂድ የነበረ ድርጅት ነው፡፡   
ዶ/ር ራሔል እንደገለጹት ለዚሀ አውደጥናት መነሻ የሆነው ሀሳብ የተጀመረው አምና በየካቲት ወር አካባቢ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከዚሁ ድርጅት ጋር በመተባበር ልጅን ለማ ዋለድ የሚደረግ ቀዶ ጥገናን ቀላል በሆነ መሳሪያ ለማጆችን ለማሰልጠን እንዲቻል የስልጠና መመሪያ ወይንም ጋይድ እየተዘጋጀ ስለሆነ የዚህ አውደጥናት አላማም ይህን መመሪያ ለማደርጀት ያሰበ ነው፡፡
እናቶች በቀዶ ሕክምና እንዲወልዱ ሲደረግ በምን መንገድ እንደሆነ ሰልጣኞች ሊማሩበት የሚችሉት ይህ መሳሪያ ቀለል ያለና ዋጋውም ተመጣጣኝ የሆነ በዚህ ላርዴል በተባለው ድርጅት የተሰራ ስለሆነ ያንን መሳሪያ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ በጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻላይዝድ ለሚያደርጉ ሰልጣኞች ለልምምድ ለማዋል እንዲረዳ የስልጠናው መመሪያ Guide የመጀመሪያው ደረጃ በመጠናቀቁ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ሐኪሞች እና ባለሙያዎች እንዲመክሩበት ተደርጎአል። ይህን መመሪያ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር እንዲዘጋጅ በማድረጉ ማህበሩም ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላትና ግለሰቦች ጋር በመተባበር አዘጋጅቶታል፡፡ ይህ መመሪያ ወይንም ጋይድ ወደሚመለከታቸው አካባቢዎች ከመሰራጨቱ በፊት ግን መታየት እና በሃሳብ መዳበር ስላለበት የሰኞው እለት አውደ ጥናት ይህን ያከናወነ ነበር ብለዋል ዶ/ር ራሔል፡፡
ይህ መሳሪያ ለማንኛውም በቀዶ ሕክምና መሰልጠን ላለበት ወይንም ወደፊት አገልግሎቱን ለሚሰጥ የህክምና ባለሙያ የተዘጋጀ እንጂ ለዚህኛው ሐኪም ወይንም ለዚያኛው ሐኪም በሚል የተለየ አይደለም፡፡ ስለዚህ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በሚሳተፍ ባለሙያ እይታ ይህ መመሪያ እና መሳሪያ ምን ያህል የተገናኘ ነው ወይንም ምን ያህል ትክክል ነው ምን ያህልስ ይጣጣማል የሚለውን ለማየት ስለተዘጋጀ ወደ 18/የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች፤ የኦፕራሲዮን ክፍል ነርሶች፤ የሰመመን ሰጪ ሐኪሞች፤ አዋላጅ ነርሶች፤ የማህጸንና ጽንስ ሐኪም ለመሆን ትምርት ላይ ያሉ ሐኪሞች ባጠቃላይም ከተለያየ አቅጣጫ እይታ እንዲኖረው ስለተፈለገ ከተሳታፊዎች ምላሽ እንዲሰጥ ተደርጎአል፡፡
ዶ/ር ራሔል ደምሰው በተከታይነት ያብራሩት የቀዶ ሕክምና አገልግሎቱ እስከአሁን ሲሰጥ ከነበረው በምን እንዲለይ ታስቦ ነው ይህ መሳሪያና ያጠቃቀም መመሪያ እንዲቀረጽ ያስፈለገው የሚለውን ነው፡፡
ዶ/ር ራሔል  እንዳሉት   እስከአሁን ድረስ ብዙ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ስልጠና በኢትዮጵያ ወይንም በአፍሪካ በመሰልጠኛ መሳሪያዎች የታገዘ አይደለም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ለአቅምም ፈታኝ ስለሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው አውሮፕላን ላይ ለመስራት ከመውጣቱ በፊት በልምምድ መሳሪያ ተለማምዶ ጨርሶ መሆን እንዳለበት ሁሉ በሕክምናም ወደ ታካሚዎቻችን ከመሄዳችን በፊት መጀመሪያ ስልጠናዎች ይደረጋሉ፡፡ ሰልጣኙ በስልጠና መሳሪያው ላይ እጁን ፈትቶ በደንብ ተለማምዶና በከፍተኛ ሐኪም እየተረዳ አተገባበሩን በደንብ ሲያውቅ ከዚያ በሁዋላ እራሱን ችሎ ቀዶ ሕክምና እንዲያደርግ ይፈቀዳል፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ልምምድ የሚያደርግ ሐኪም በመሳሪያዎች ታግዞ ይህንን ቅድመ ዝግጅት ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡
በአለማችን ላይ እያንዳንዱን የቀዶ ሕክምና አተገባበሮችን የሚያስተምሩ በጣም የሚገርሙ ዘመናዊ እና ኮምፒተራይዝድ የሆኑ ብዙ መሳሪያዎች አሉ። እነዚህ መሳሪያዎች በዋጋ አንጻርም ውድ ስለሆኑ፤ በአገልግት ዘመናቸውም ብልሽት ሊገጥማቸው የሚችል በመሆኑ እና በቀላሉ የመለዋወጫ እቃዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን በተለይም በአፍሪካ ውስጥ እን ዲኖሩ ለማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ከምንም በላይ የአገልግሎት ዘመናቸውም የሚያልፍ ሊሆኑ ስለሚችሉ በቀላሉ እየለዋወጡ አዲስ በተሰሩ መሳሪያዎች እየተኩ መጠቀም አስቸጋሪ ስለሚሆን እነርሱን ወደሀገር ለማስገባት እስከአሁን ሙከራ አልተደረገም፡፡  ከዚህ አንጻር ብዙ ጊዜ የሚመከረው በአካባቢ በሚገኙ ወይንም በቀላሉ መተካት በሚችሉ፤ በቀላል ዘዴ በሚሰሩ እቃዎች መለማመድ ነው።
በቀዶ ሕክምና የማዋለድ አገልግሎት ለሚሰጡ የህክምና ባለሙያዎች ለስልጠና የተዘጋጀው መሳሪያ በጣም ቀላል ዋጋ ያለው፤ ለሁሉም አገራት በማይከብድ ሁኔታ ማቅረብ የሚቻል በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል። አንዳንድ በእርዳታም ይሁን ገንዘብ ተከፍሎባቸው የሚገቡ መሳሪያዎች ቢኖሩንም ለጥቂት ጊዜያት አገልግለው ብልሽት ሲገጥማቸው ወይንም ጊዜ ሲያልፍ ባቸው በቀላሉ መተካት ስለማይችሉ አይቀጥሉም፡፡ አሁን ለስልጠናው እንዲያግዙ የተፈለጉት መሳሪያዎች ግን በቀላሉ የባለሙያን ትኩረት በሳበ መንገድ የተሰሩ እና ለአጠቃቀም የማይከብዱ በዋጋም ደረጃ ብዙ የማይጠይቁ ናቸው፡፡ ስለዚህም በአብዛኛው በጨርቃ ጨርቅ እና በላስቲክ ታግዘው የተሰሩ ባለሙያ የተጠበባቸው መሳሪያዎች ስለሆኑ እና ኮምፒተራ ይዝድ ከሆነው በብዙ መንገድ ስለሚለዩ እንደኢትዮጵያ ላሉ ሐገራት ጠቃሚ ናቸው፡፡
ይህች ለማዋለድ የቀዶ ሕክምና ስልጠና የተዘጋጀች መሳሪያ የሴትን አካል የምትተካ ናት፡፡ ማህጸን አላት፤ ማህጸን ውስጥ አብሮ የሚቀመጥ ልጅ አላት፤ እንዲሁም የእናት ሆድ የመሰለ ነገር አላት፡፡ ስለዚህ ተማሪዎች ወይንም ሰልጣኞች በቀዶ ሕክምና የማዋለድን ጥበብ መጀመሪያ በዚህ መሳሪያ እንዲለ ማመዱ ይደረጋል ማለት ነው።
ሰልጣኞች በከፍተና ሐኪሞች ታግዘውም ቢሆን በቀጥታ የቀዶ ሕክምና አገልግሎትን ለመስ ጠት ወደ እናቶች መሄድ የለባቸውም፡፡ ይህንን የቀዶ ሕክምናን በሰዎች ላይ እንዲለማመዱ ማድረግ  የሙያው ስነምግባርም አይፈቅድም፡፡ ከዚህ ቀደምም የአቅም ጉዳይ ይዞን እንጂ ይህ መደረግ ያልነበረበት በመሆኑ ከዚህ በሁዋላ ግን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው ብለዋል ዶ/ር ራሔል፡፡ በወደፊቱ አሰራር ይህ Guide (መመሪያ) አልቆ ሲጸድቅ እንደከዚህ ቀደሙ በከፍተኛ ሐኪሞች እየታገዙ የቀዶ ህክምና ልምምድን በቀጥታ በሰዎች ላይ መተግበር አይፈቀድም፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ቀለል ያሉ መሳሪያዎች ሲመጡ የአጠቃቀም መመሪያዎችን በማውጣት ወደሚመለከታቸው ሁሉ በማሰራጨት እና ስራ ላይ ማዋል ጊዜ የማይሰጠው አስቸኳይ ነገር መሆኑን የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበርም አምኖ ከላርዴል ጋር በመስማማት ስራው እየተጠናቀቀ ነው፡፡
የቀዶ ሕክምና እንደማንኛውም ሙያ በቂ የሆነ ልምምድን የሚጠይቅ ሙያ ነው፡፡ ስለዚህ ወደስራው ከመገባቱ በፊት ሰው ባልሆነ ግን ሰው በመሰለ መሳሪያ በቂ ልምምድ ማድረግ አማራጭ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡ ሰውን የሚያክል ፍጡር ለመክፈት መጀመሪያ እጅን በሚገባ ሰው በመሰለ ነገር ማሰልጠን ይገባል። ሕክምና የሰው ልጅ ሕይወት ስለሆነ በከፍተኛ ደረጃ ዝግጅት ማድረግን እውቀትን ማዳበርን ይጠይቃል። ቀደም ሲል በነበረው አሰራርም ወደስራው የሚሰማሩ ሰልጣኞች በከፍተኛ ሐኪሞች እይታ ውስጥ እንዲሆኑ እና አብረው እየሰሩ እንዲለማመዱ መደረጉ ተፈልጎ ሳይሆን ለመለማመድ የሚረዱ ቀላል መሳሪያዎች በበቂ ባለመኖራቸው የተነሳ ወይንም ቢኖሩም እንኩዋን ከኢኮኖሚው አንጻር የሚደፈሩ ባለ መሆናቸው ነበር። አሁን ግን ዘመኑ ተቀይሮአል። በአለም ላይ ውድ ያልሆኑ፤ ለመግዛት ከባድ ያልሆኑ፤ በእርዳታም ቢገኙ በቀላሉ የማይበላሹ፤ መተኪያ የላቸውም የማይባሉ መሳሪያ ዎች ስለተዘጋጁ የቀዶ ሕክምናን አገልግሎት አሰጣጥ ለመለማመድ በደንብ እጅን የሚፈቱ እውቀትን የሚያዳብሩ በመሆኑ መመሪያው በቅርብ ጊዜ ሲጠናቀቅ የህክምና ትምህርት ቤቶች እንዲያገኙዋቸውና ስራ ላይ እንዲያውሉአቸው ይደረጋል የሚል እምነት አለ ብለዋል ዶ/ር ራሔል ደምሰው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ እና የ ESOG ቦርድ አባል፡፡

Read 16757 times