Saturday, 04 September 2021 16:53

ለተመራቂዎች መነቃቃትን የፈጠረው የቢዝነስ አቅድ ውድድር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 ብዙ ወጣቶች ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ያለ ስራ ቁጭ የሚሉት ሀሳብ ስለማያፈልቁ፣ እውቀት ስለሌላቸው ወይም የስራ ፍላጎት ማጣትም አይደለም ይላሉ አንጋፋ የቢዝነስ ባለሙያዎች። ይልቁንም የእነዚህ ወጣቶች ትልቁ ፈተና ሀሳባቸውን እውን የሚያደርጉበት የመነሻ ካፒታል፣ የመስሪያ ቦታና የሚያማክራቸው ባለሙያ ማጣት እንጂ። ይህን በእጅጉ የተረዳው ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ለሚያስመርቃቸው ተማሪዎቼ ምን አይነት የቢዝነስ ፍኖት ላስቀምጥ ብሎ ሲነሳ በተለይ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎችን ተስፋ የሚያለመልም፣ ከላይ የተገለጹትን ተግዳሮቶች የሚቀርፍ መላ ዘየደ። ይህን እውን ለማድረግም የመጀመሪያውን የተማሪዎች  የቢዝነስ እቅድ ውድድር አካሄደ። ባለፈው ቅዳሜ  ነሀሴ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በጎልደን ፑሊፕ ሆቴል ለመጨረሻ  ዙር ያለፉ አምስት ተወዳዳሪዎች የተፋለሙበት ትልቅ ውድድርም ተካሂዶ ነበር።
ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ከተመሰረተ ሁለት ዓመቱ ሲሆን በሶስት የማስተርስና በሁለት የዲግሪ ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል። የኮሌጁ መስራችና ባለቶች ለረጅም ጊዜያት በቢዝነሱ አለም ያለፉና ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ በመሆናቸው “ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅን” ሲመሰርቱም “የማናስቀጥረውን ተማሪ አናስመርቅም” በሚል መሪ ቃል መሆኑን የሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ እውነቱ ይገልጻሉ።
ኮሌጁ መስራት ከሚጠበቅበት የመማር ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት በተጨማሪ ቢዝነስን መፍጠርና ማሳደግ አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ነው ረዳት ፕሮፌሰሩ የሚናገሩት። ስለሆነም ተማሪዎቹ ቢዝነስ እንዲፈጥሩ በማነሳሳትና በመደገፍ ባለፈው የካቲት ወር ተማሪዎች በቢዝነስ እቅድ እንዲወዳደሩ ተደርጎ ለውድድሩ 23 ፕሮጀክቶች መቅረባቸውንና እነዚህ የቢዝነስ እቅዶች በየደረጃው እየተወዳደሩ በተለያዩ ዳኞች እየተዳኙ በዚሁ ዕለት ለመጨረሻው ዙር አምስት የቢዝነስ እቅዶች ማለፋቸውን ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ አብራርተዋል።
በዚሁ እለት የቀረቡት አምስት የቢዝነስ እቅዶች “ቆረሶ የአሳ ምርት” አንዱ ሲሆን እቅዱን ያቀረበው ተማሪ ኤርሚያስ ነዋይ ነው። ሁለተኛውና በጌታ ያውቃል ዘካሪያስ የቀረበው የቢዝነስ እቅድ “የሰላም እንጀራ” የተሰኘ ከባዕድ ነገር ቅልቅል ነፃ የሆነ ጥራት ያለው እንጀራ ለገበያ ማቅረብ ሲሆን ሶስተኛው የቢዝነስ እቅድ በመልካሙ ጉደታ የቀረበው “ዮዮ የቾክ ማምረቻ” ነው። አራተኛውና በአዳራሹ የታደሙትን ቀልብ ስቦ የነበረው በዘመዳማሞቹ ተማሪዎች ዮሃና ጂዮቫኒና እፀ ህይወት ታደሰ የቀረበው “ኢሴ ኪድስ ካፌ” ሲሆን እነዚህ ወጣት ተማሪዎች በተለይ በሀገራችን ለህጻናት ተብሎ ራሱን የቻለ ካፌና ሬስቶራንት አለመኖሩን ገልጸው በሌላው ዓለም ያለውን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ የቢዝነስ እቅዳቸውን ያቀረቡ ሲሆን በውድድሩ ሶስተኛ በመውጣት የእውቅና  የምስክር ወረቀትና 10 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል። በእለቱ 1ኛ በመውጣት የ50 ሺህ ብር አሸናፊ የሆነው የቢዝነስ ዕቅድ የ29 ዓመቷ ወጣት የሀመረኖህ ዘውዱ “Paper Bag Manufacturing Company” ሲሆን ወጣቷ ከቢዝነስ ትንታኔና፣ ከመረጃ አወቃቀር ጀምሮ ያቀረበችበት መንገድ ዳኞችን ከማስደነቁም በላይ የወረቀት ከረጢት በመስራት አገርን እየበከለና እያስጨነቀ ያለውን የፕላስቲክ ምርት ከአገር ለማስወገድ ያቀደችበት፣ ጉዳዩን ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር የቃኘችበት ሁኔታ የታዳሚውን ቀልብ ስቦ ነበር።
በዕለቱ በውድድሩ 2ኛ በመውጣት የ25 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነው የኤርሚያስ ነዋይ የቆሮሶ አሳ ማምረቻ (Qoroso-Fish Farm Inc) ነበር።
ታዲያ እነዚህ ወጣቶች ይህንን ውድድር ካሸነፉ በኋላ ህልማቸውን እውን ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን የመነሻ ካፒታል፣ የመስሪያ ቦታና ሙያዊ ድጋፍ ከየት ያገኛሉ? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ይዞ ነው ይህንን ውድድር ያስጀመረው። ለምሳሌ የሀመረኖህ ዘውዱ የወረቀት ከረጢት ማምረቻ ኩባንያ እውን እንዲሆን ኮሌጁ የግማሽ ሚሊዮን (500 ሺህ) ብር የመነሻ ካፒታል፣ የመስሪያ ቦታና ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ይህ የማምረቻ ፋብሪካ ራሱን ችሎ ሲያድግና ሲስፋፋ ኮሌጁ ካዘጋጀው ቦታ ይወጣና ወደ ሌላ የራሱ ሰፊ ቦታ በመዛወር፣ ቦታው ለሌሎች አዲስ ለሚመጡ ተወዳዳሪዎች ጥቅም ላይ  እንደሚውል ነው ረዳት ፕሮፌሰሩ የተናገሩት።
ኮሌጁም ይህንን ለመስራት መንግስትን የመስሪያ ቦታ ስጡኝ አትስጡኝ ከማለት ተፅዕኖ ተላቅቆ ሁሉንም ራሱ ባሰራቸው ህንጻዎች ላይ እንደሚያከናውን ተገልጿል። በውድድሩ ከ1-3ኛ የወጡት የቢዝነስ እቅዶች ተመርጠው ኮሌጁ ከኢንቨስተሮች ጋር ባለው ግንኙነት መሰረት በኮሌጁ ቢዝነስ ኢንኪዩቤሽን ሴንተር ገብተው የመነሻ ካፒታል፣ የሙያ ድጋፍ፣ የሴልስና ማርኬቲንግ ስልጠና፣ የሎጂስቲክስ  ድጋፍና የማምረቻ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ለ6 ወራት ከኮሌጆች ጋር አብረው ከሰሩ በኋላ ራሳቸውን ችለው ይወጣሉ ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰሩ።


Read 1968 times