Saturday, 04 September 2021 16:57

“ኦፌኮ የሽግግር መንግስት አላቋቋመም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


         የተወለዱት በቀድሞ  ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ጅባትና ሜጫ አውራጃ ደንዲ ወረዳ፣ ሹኔ በሚባል  ስፍራ ነው። ከቀድሞ የኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ኢንስትቲዩት በ1ኛ ደረጃ መምህርነት በዲፕሎማ፣ በዚያው በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በሁለተኛ ደረጃ መምህርነት (በባዮሎጂና ኬሚስትሪ) ሁለተኛ ዲፕሎማ፣ ከቀድሞ የካቲት 66 ፖለቲካ ት/ቤት በፖለቲካ ትምህርት ዲፕሎማ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፒኤስአይአር የመጀመሪያ ድግሪ፣ ከዚያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በህዝብ አስተዳደርና ልማት ማኔጅመንት ሁለተኛ ድግሪ  ያላቸው ሲሆን ከኢሰፓ እስከ ኦብኮ፤ ኋላም ኦህኮ  ቀጥሎም ኦፌኮ የደረሰ የረጅም ዘመናት የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ ያላቸው አንጋፋ መምህር  ፖለቲከኛ ናቸው።
የቀድሞ የኢፌዴሪና የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባል፣ የአሁኑ የኦፌኮ ም/ሊቀ መንበር የሆኑት  እኚህ አንጋፋ ፖለቲከኛ አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

                ለረጅም ጊዜ ከሚዲያ አካባቢ ጠፍተዋል፤ ፖለቲካዊ አስተያየቶች ከመስጠትም ተቆጥበዋል ከርመዋል ለምን ይሆን?
እንደተባለው ጠፍቻለሁ። በሁለት ምክንያቶች ነው ይህ የሆነው።  አንደኛ፤ ሚዲያውም እኛ ከህዝባችን መሃል ሆነን ስንታገል የነበረውን  ሰዎች ብዙ የፈለገን አልመሰለኝም። ሌላው እኔም በራሴ የተቆጠብኩባቸው ሁኔታዎች አሉ። አንዳንዶች የት ከርመው እንደመጡ ሳይታወቅ ዛሬ መጥተው እኔ ካልተናገርኩ፣ እኔ ካልሆንኩ የፖለቲካ ወሳኙ የሚሉ ሰዎችን ስመለከት ትንሽ ገለል ማለቱን ነው የመረጥኩት። እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ በፖለቲካ ውስጥ ስለነበርኩ “አንዲት ኢትዮጵያ ወይም ሞት” እያልኩ የታገልኩ ነኝ። ዛሬም ያንን ሃሳቤን፣ ያንን ወኔዬን የገፈፈኝ የለም፤ የትም ቦታ ይህቺ ሀገር ስትጠቃ አልወድም። ነገር ግን ተናጋሪው በበዛበት ገብቶ መዘላበድን አልመረጥኩም። በተለይ በዚህ ዘመን ከኢሠፓአኮ እስከ ኢሰፓ ገብተን እንዳላገለገልን ሁሉ፣ በተለይ አሁን ስማቸውን መጥራት ባያስፈልግም፣ የሽግግር መንግስት እናቋቁማለን ምናምን የሚሉ ሰዎችን በሚገባ ስለምንተዋወቅ እታዘባቸዋለሁ። አንዳንዶቹ ደግሞ በቅርብ ጊዜ ከፍተኛ ቦታ የተቀመጡና ወያኔን ይዘው የመጡ፣ በራሳቸው ጥፋት ይሁን በሌላ እስር ቤት የከረሙና ከዚያ ወጥተው አሜሪካ ገብተው “ጸሎተኛ ሆኛለሁ፣ ጳጳስ፣ ፓስተር ሆኛለሁ” ሲሉ ከርመው አሁን ደግሞ በአቋራጭ ምኒልክ ቤተ-መንግስት ለመግባት የሚቋምጡ ሰዎች ያልሆነ ወሬ ሲያወሩ ዳር ላይ ሆኜ እየሰማሁ እገረማለሁ።
የዘንድሮ ጅብ ደግሞ የሚውቁት ሃገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ማለት ጀመረ እንዴ እላለሁ። እኔ በሃገሬ ጉዳይ ምንም ችግርና ብዥታ የሌለብኝ ሰው ነኝ።
ፓርላማ በነበረኝ ቆይታም ለኢትዮጵያ  ከኛ በላይ የተሟገተ የታገለ የለም። መድረክን በመመስረት፣ በም/ሊቀመንበርነት በዋና ፀሃፊነት በማገልገል የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀኛል። አሁን የጠፋሁት ያሉትን ነገሮች በሚገባ በእርጋታ ለመታዘብ እንዲሁም ሚዲያው እኛን ብዙም ባለመፈለጉ ነው።
በዚህ መሃል ግን ብዙ የታገልኩበት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ስም በአንዳንድ ሰዎች ባልተገባ መልኩ ሲነሳ ሳይ እውነታውን ማስገንዘብ ያለብኝ መስሎ ይሰማኛል። ኦፌኮ ግልጽ እምነቱ ሰዎች እንደሚጠረጥሩት ሳይሆን የኦሮሞ ችግር በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ሊፈታ ይችላል የሚል ነው። ዛሬም የተለወጠ ነገር የለም። አንዳንዶች በጣም በተሳሳተ ሁኔታ ከኦነግ ጋር ቆማችሁ፣ የሽግግር መንግስት እንመስርት አላችሁ ይላሉ። ይሄ ፈጽሞ የድርጅቱ አቋም አይደለም።  ግለሰቦች እንደ ግለሰብ አስተያየት ሰጥተው ሊሆን ይችላል።
አሁን እርስዎ ካነሱት ጉዳይ አንፃር ኦፌኮ ከኢትዮጵያዊነት እሳቤዎች ወርዶ የብሔር ፅንፈኝነትን እያራመደ ነው፣ በተለይ የብሔር ፅንፈኝነት አራማጅ ናቸው ተብለው በብዙዎች የሚታሰቡት አቶ ጃዋር ፓርቲውን መቀላቀላቸውን ተከትሎ በሊቀ መንበሩ ጭምር የአስተሳሰብ ለውጦች ታይተዋል ይባላል። በእርግጥ የእነ ጃዋር እንቅስቃሴ የኦፌኮ ፕሮግራሞችና አላማዎች ላይ ጫና አላሳረፈም?
ፕ/ር መረራ የሚሰጧቸውን ቃለ-ምልልሶች ተከትሎ ብዙ ኢትዮጵያውያን እንደሚከፉ እሰማለሁ። ነገር ግን አስቀድሜ እንዳልኩት ፓርቲው ይዞት የተነሳውን መሰረታዊ የሆነ ወይም ሰነድ ላይ የተቀመጡትን መርሆዎች የጣሰ ነገር የለም። ደጋግመን እንደምንለው የኦሮሞ ችግር  በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ችግር ጋር ሊፈታ ይችላል በሚል አበክረን የትግል መስመራችን አድርገን ስንታገልበት የነበረ ነው። አሁንም ከዚህ መስመር አልወጣንም። አንወጣምም። እኔ ይህ መርህ ከተጣሰ ፓርቲው ውስጥ መቆየት አልችልም። ዛሬም ከነገ ወዲያም የኦፌኮ መርህ ይሄ ብቻ ነው። ፕ/ር መረራም ቢሆን  ምናልባት ከአነጋገሩ ተሳስቶ አለያም ሰዎች ባልሆነ መንገድ ተረድተውት ሊሆን ይችላል እንጂ የፒኤችዲ ጽሁፉ ውስጥ እኮ ያስቀመጠው ይሄንኑ የኦፌኮን አቋም ነው።
ለዚሁ አቋምም ብዙ መከራ አይቶ ሲታገል የኖረው እሱ ነው። ነገር ግን እሱ ስለተናገረው ነገር ራሱ ማብራሪያ ቢሰጥ፣ ፓርቲው ግን ከመሰረታዊ መርሆና የትግል መንገዶቹ እንዳልተዛነፈ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን። ይህቺ ሃገር አንድነቷ ተጠብቆ የኦሮሞ ችግሮች ከሌላው ብሄር ብሄረሰብ ጋር ተፈትተው በኢኮኖሚዋ የዳበረች፣ በማህበራዊ ፍትህ በኩል ለሁሉም ዜጎቿ እኩል ፍትህን  የምትሰጥ የበለጸገችና የዳበረች ኢትዮጵያን ማየት ነው የምንፈልገው።
ይሄ የሚሆነው ሁሉም በመከባበር፣ በመግባባት ላይ የተመሰረተ አካሄድን ሲከተል ነው። አንዳንዶች ተነስተው የኢትዮጵያዊነት ሰርተፍኬት ሰጪ ለመሆን ሲሞክሩ ያስቀኛል። ኢትዮጵያዊነትን ለገብሩ ገ/ማርያም ኡቱራ ማንም አይሰጠውም። እኔ ነኝ ኢትዮጵያዊነቴን የማውቀው።
የጃዋር ወደ ፓርቲያችሁ መምጣት የፓርቲውን አካሄድ ለውጦታል፤ ምናልባትም ወደ ጽንፍ ብሄርተኝነት ወስዶታል የሚሉ ወገኖች አሉ?
የጃዋር ጉዳይን በተመለከተ እኔ እሱ የኛን ፓርቲ ስለመቀላቀሉ የሰማሁት ውጪ ሃገር ሆኜ ነው።  እንዴት ወደ ፓርቲያችን እንደገባ ለኔም  ግልጽ ያልሆነ ነገር አለ። ስራ አስፈጻሚ አካባቢ ጠይቄም ምላሽ አላገኘሁም። ሊቀመንበሩን ግን አልጠየኩም፤ ምክንያቱም ልጁ በወቅቱ ወደ ፓርቲው ገብቶ ስራውን ጀምሯል። ነገር ግን በመርህ ደረጃ ማንም ግለሰብ ወደ ፓርቲው ልግባ ቢል የፓርቲውን ፕሮግራም ሳይሸራርፍ፣ ሳይቀናንስ ተቀብሎ ነው የሚሆነው። ጃዋርም በዚህ መንገድ ነው ሊገባ የሚችለው። ስለዚህ ጃዋር ስለገባ ኦፌኮ ተለውጧል ተብሎ የሚወራው የተሳሳተ ነው። ልጁ ላይ ያለን ጥላቻ ድርጅቱም ላይ ለማላከክ የሚፈልጉ ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች ተሳስተዋልና አቋማቸውን ቢያስተካክሉ ጥሩ ነው። ጃዋር በፓርቲው ፕሮግራምና መመሪያ ሊገዛ ነው ወዶ የገባው።
ኦፌኮ ከምርጫ ውጪ ከሆነ በኋላ አሁን በምን ቁመናና እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል?
ከምርጫ ውጪ ሆነን ሳይሆን ተደርገን ነው። ኦፌኮ አሁን በምን ቁመና ላይ ነው ለተባለው፣ ኦፌኮ አሁን ተዳክሟል። ይሄን በግልጽ መናገር እችላለሁ።
በምን ምክንያት ነው የተዳከመው?
ቢያንስ ሶስት ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል። አንደኛ ገዥው ፓርቲ  በየዞኑ በየወረዳው ጽ/ቤቶቻችንን በመዝጋት አመራሮቻችንን በማሰር እንድንዳከም አድርጓል። ሁለተኛው የራሳችን የውስጥ ችግር ነው። ለምሳሌ ስብሰባዎችን በህገ ደንባችን መሰረት ማካሄድ አልቻልንም። ስብሰባ በየ15 ቀኑ ግዴታ ያስቀምጣል። ይሄንን ማድረግ አልቻልንም። ይሄ መሆኑ የኦፌኮን እንቅስቃሴ አዳክሞታል። ሌላው ይሄ ጦርነት የፈጠረው ነባራዊ ሁኔታ ነው። ሙሉ ለሙሉ የሃገሪቱ ትኩረት ኮቪድ 19 እና ጦርነቱ ላይ ስለሆነ ብዙ መንቀሳቀስ አልቻልንም። ጦርነቱ ሃገሪቷን የማዳን ወይም ያለማዳን ስለሆነ ኦፌኮ በዚህ ሰዓት ሌላ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ከመግባት ተቆጥቧል። ይሄ ነገር እልባት እስከሚያገኝ ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ተቆጥበናል። በእነዚህ ምክንያቶች የኦፌኮ እንቅስቃሴ ተዳክሟል።
ከኦፌኮ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የመድረክ ጉዳይ ነው፤ እርስዎ የመድረክን ምስረታ ሃሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ እስከ ምስረታው ድርሻ  አለዎት አሁን መድረክ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው?
ስለ መድረክ ሲነሳ በእውነቱ በእጅጉ አዝናለሁ። ልቤ ይደማል። የመድረክን ምስረታ ሃሳብ ያመጣሁት እኔ ነበርኩ። ዶ/ር ነጋሶ ነፍሳቸውን ይማርና ፓርላማ ውስጥ አብረን ነበርን። በወቅቱ ከሳቸው ጋር በዚያ አጋጣሚ ጥሩ ቅርርብ ነበረን። የሃገሪቷን ችግር እንወያይ ነበር። በዚህ መሃል “እንደው ምን ይሻላል? መፍትሄው ምን ይሆን?” እያልን ስንወያይ አንድ የጋራ ትግል እንደሚያስፈልግ ተነጋገርን። የኔን ሃሳብ ነገርኳቸው፤ ጥሩ ሃሳብ ነው አሉኝ። በዚያው በሌላ ጊዜ ስንገኛኝ እሳቸው ሃሳቡን አዳብረው አነሱልኝና ተወያየን። እውነቱን ለመናገር ትልቁ ድርሻ የሳቸው ነበር ማለት ይቻላል። በኋላም በህብረቱ ደረጃ ውይይት መደረግ ጀመረ። እነ ስዬ እነ ገብሩ አስራትም እንዲገቡ ተደረገ። በዚህ ሃሳቡ እየዳበረ መጥቶ የመድረክ ምክክር ተመሰረተ። በወቅቱም የምክክር መድረኩ ህዝብ ግንኙነት ሆኜ ተመርጬ  ነበር። በዚህ አጋጣሚ አንድ የማልረሳው ነገር አለ። ዛሬ በአሜሪካ የህውሃት ተወካይ እየሆነ ያለው ስዬ አብርሃ ያለውን ነገር ለኢትዮጵያ ህዝብ ብናገር ደስ ይለኛል። በወቅቱ አቶ ገብሩ እኔ ቢሮ መጥተው አንድ መግለጫ ጻፍ ተብዬ እሱን ጽፌ አነበብኩላቸው። መግለጫውን ካነበብነው በኋላ አቶ ገብሩ ምንም ሳይል የመግለጫውን ሃሳብ ተቀበለ። በሌላ ቀን አቶ ስዬ ባለበት ደግሞ መግለጫውን ለመገምገም አነበብኩላቸው። በዚህ መግለጫ ላይ ለገሰ (መለስ) ዜናዊ የኢትዮጵያን ህዝብ በቀን ሶስቴ ትበላለህ ብሎ አንዴም እንዳይበላ አደረገ የሚል ነገር ነበረ።  ይሄን ገብሩ ተቀብሎታል። ስዬ ግን ለመከራከር ተነሳ። የለም እሱ እንደዚህ አላለም አለኝ። ገብሩ ያን ጊዜ ብሏል ብሎ መለሰለት። ተከራከርን። ያኔ ነበር እኔ ስዬን መጠራጠር የጀመርኩት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አቋሙን በጥርጣሬ ነበር የምመለከተው። በእርግጥም ይኸው ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ የኢትዮጵያ ህዝብ እየታዘበ ነው።
ወደ ቁምነገሩ ስመለስ፣ ብዙ ተስፋ የተጣለበትና የተለፋበት መድረክ ዛሬ አለ ለማለት አያስደፍርም። በነገራችን ላይ በሂደቱ ሁሉ ደግፎት ተሸክሞት ብዙ መንገድ ያመጣው ኦፌኮ ነው።
ኦፌኮ እና ኦነግስ አብረው ለመስራት የነበራቸው ስምምነት አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
አስቀድሜ እንዳልኩት ኦፌኮ የኦሮሞ ችግር በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ይፈታል ብሎ የሚያምን፣ በትግሉ ሁሉ ከሃገር ያልወጣ፣ እዚሁ ሆኖ አባሎቹ እየታሰሩ እየተፈቱ እየተገደሉ፣ የታገሉበት ድርጅት ነው። መሪው ፕ/ር መረራ ጉዲና ታስሮበት እንኳ ሃገር ውስጥ ሆኖ ትግሉን ያፋፋመ ድርጅት ነው። የኦሮሞን ወጣቶች ትግል ሲያታግል የነበረ ነው። ነገር ግን ለውጡ መጥቶ ውጪ የነበሩ ድርጅቶች ወደ ሃገር ውስጥ ይግቡ ሲባል ከገቡት  አንዱ ኦነግ ነው። ኦነግ ሲገባ እስቲ አብረን የምንሰራ ከሆነ “እንኳን ደህና መጣችሁ እንበላቸው” ብለን ኮሚቴ አቋቁመን አቀባበል አድርገንላቸዋል። በኋላም በጋራ አንድ መግለጫ አውጥተናል። ይሄ ጥሩ የግንኙነት ሂደት ነበር። ድሮ አንዱ አንዱ ፊት እንኳን መቆም አይችልም ነበር። ነገር ግን ያቺ መግለጫ ከመውጣቷ በስተቀር ከኦነግ ጋር በትብብር የሰራንበትን ጊዜ  እንደ ኦፌኮ ም/ሊቀመንበርነቴ የማውቀው ነገር የለም።
በቅርቡ ኦፌኮና ኦነግ የሽግግር መንግስት በኦሮሚያ መስርተዋል ተብሎ የወጣው መግለጫስ?
መቼም በማህበራዊ ሚዲያ ሁሉም ነገር እውነት ሆኗል ተብሎ አይታሰብም። እኔ እስከማውቀው ድረስ ድርጅቴ የሽግግር መንግስት እንመሰርታለን ብሎ ከኦነግ ጋር ያደረገው አንዳችም ስምምነት የለም። ለወደፊትም እንዲህ ያለ ሃሳብ የለውም። ይሄን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲገነዘብ እንፈልጋለን።
በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ አንዱ የትግል ጥያቄ ማዕከል የኦሮሞ ህዝብ ነፃነት የሚል ነው። አሁን ላይ የኦሮሞ ህዝብ የሚፈልገውን ነጻነት አግኝቷል?
ያገኘባቸውም ያላገኘባቸውም አሉ፡፤ ነፃ የወጣባቸወም ያልወጣባቸውም አሉ። ነፃ ከወጣባቸው መካከል ለምሳሌ በሞግዚት አስተዳደር መመራቱ ቀርቷል። እነ አባዱላን በገመድ ይጎትቱ የነበሩ ተነስተዋል። አፋን ኦሮሞ ሁለተኛ ብሄራዊ ቋንቋ እንዲሆን አቅጣጫ መቀመጡ መልካም ጅምር ነው። ግን አሁንም መተግበር አለባቸው። ያልተመለሱት ብዙ ናቸው፤ ዝርዝር ውስጥ መግባት አንፈልግም።
ይሄን ጥያቄ ያቀረብኩልዎ ዛሬም በነፍጥ ጭምር ለነጻነት እንዋጋለን የሚሉ ስላሉ ነው። እርስዎ እነዚህን እንቅስቃሴዎች እንዴት ነው የሚመለከቷው?
ምንም የኦሮሞ ህዝብ ነጻ አልወጣም ብሎ የሚዘፍነውን አልቀበልም። ነጻ የወጣባቸው አሉ የሚቀሩም አሉ። እነዚህ  የሚቀሩ ነገሮችም ማሳካት የሚቻለው በሃይል ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ነው። ጉልበት የሚፈልጉ አይደሉም። ምንም አልተሰራም አይኔን ግንባር ያድርገው ማለት የሚያስኬድ አይደለም። የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደርም ቁጭ ብሎ በመነጋገር ነገሮችን ለመፍታት ለምን እንደሚፈራ አይገባኝም። ይህ ሁኔታም ብዙ ችግር ፈጥሯል። እስቲ መነጋገሩ ምን ይጎዳል? እስቲ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠኝ።
የተደበቀው ሁሉ አደባባይ ወጥቶ መታየቱ ምንድን ነው ጉዳቱ? ይህ የቆየው የኢህአዴግ በሽታ ይመስለኛል። አሁንም እኮ እኛን ለማናገር ይሽሻሉ። የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት እኮ እኛን ለማናገር ይሸሻሉ። ብቸኛው ያጋገረን ሰው ለማ መገርሳ ነበር። ያውም ራሱ አንድ ስብሰባ ላይ  አግኝቶ ከኋላዬ መጥቶ  “ኦቦ ገብሩ  አንዴ ይቆዩ የማነጋግሮት ነገር አለኝ” ብሎ ለ15 ደቂቃ አነጋገረኝ። እሱ ብቻ ነበር። በጣም በቅንነት ነው ያነጋገረኝ፤ በጣም ነው የማደንቀው።፡
አሁን ከገባንበት የጦርነትና የቀውስ አዙሪት እንዴት ባለ መንገድ ነው የምንወጣው?
 በእውነቱ አሁን ባለው ጦርነት ህይወታቸውን ለሚያጡ፣ ልጆቻቸውን ለሚያጡ እናቶችና ኢትዮጵያውያን ወገኖች ሁሉ በጣም ነው የማዝነው። ልቤ በእጅጉ ይደማል። በመቀጠል ይህ ጦርነት ከመነሳቱ በፊት በአንድ ቴሌቪዥን ያስተላለፍኩት መልዕክት አለ። በወቅቱ ያልኩት፡- “ጋሽ ስብሃት ነጋ አከብርሃለሁ፣ አቶ መስፍን ስዩም አከብርሃለሁ፤ እባካችሁ ቆም ብላችሁ አስቡ” ብዬ ነበር። እነሱም ቆም ብለው አላሰቡም፤ ባከማቹት ሃብትና ጦር ሰከሩ። ይሄ ስካር ደግሞ የሌላውን ሰው ቋንቋ እንዳይሰሙ አደረጋቸው። በዚያው ልክ ከውስጣቸው የወጡትን ልጆችም ናቁ። በህወሃት አፈና ተደብቀው ያንን ሚስጥራዊ ስራ ሰርተው ያባረሯቸውን ልጆች ነው ለመግጠም የተነሱት። እነዚህ ልጆች እኮ ጠንካራ ስራ ነው የሰሩት። አሁንም ቢሆን ጦርነቱ የትም አያደርስም። ፉከራው  ምንም ያህል አያራምደንም። መጨረሻውም የሚሆነው  መነጋገር ነው። ታዲያ ብዙ ሳንከስር ለምን አይወያዩም? ትክክለኛ ፖለቲካ የሚፈልገው ይሄንን ነው። መከላከያው ለሃገሩ አንድነትና ሉአላዊነት ለሰራው ስራ ሙሉ አክብሮት አለኝ፤ ግን ጦርነቱ ይብቃን። በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ጦርነቱ የወያኔ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች እጆችም ያሉበት ነው። ስለዚህ ይሄን ጦርነት ማስቆሙ በብዙ መልኩ ጠቃሚ ነው።
በመጨረሻ ለሁሉም አካል የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
እኔ ለኢትዮጵያ ህዝብ የማስተላልፈው መልእክት፡- ይህቺ ሃገር ትልቅ ሃገር ነች፤ ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች የሚኖሩባት ሃገር ናት። አንዱ የሚጠግብባት ሌላው የሚራብባት፤ አንዱ የበላይነቱን የሚያሳይባት ሌላው በዝቅተኝነት ስሜት እንዲኖርባት የምትፈልግ ሳይሆን በእኩልነት ተከባብረን ተፈቃቅረን፣ ተረዳድተን ክብሯንና ታላቅነቷን ጠብቀን አብረን ልንኖርባት ይገባል። ዛሬ የተፈጠረው ሁኔታ ጊዜያዊ ነው፤ ነገር ግን በፉከራና  ግፋ በለው ሳይሆን በመነጋገር፣ በመወያየት፣ በተማመናቸው ጉዳይ ላይ አብረን በመስራት የሃገር  ህልውናውን በማስቀደም የደጀን ጦሩን ተግባር እያበረታን፣ በሌላ በኩል በወዲያኛው ወገን የሚዋጉትንም የሚያዋጉትንም “ቆም ብላችሁ አስቡ፤ ልቦና ግዙ፤ ይሄ 21ኛው ክፍለ ዘመን ነው፣ በየቀኑ የሚቀጠፈው የሰው ህይወት ሊያሳስባችሁ ይገባል። ይህቺን ሃገር ወዴት እየወሰድናት ነው” ብላችሁ ሰክናችሁ አስቡ ልል እወዳለሁ።
ጦርነቱን መንግስት ለማስቆም የወሰደውን እርምጃ ያለማክበር፣ ህጻናን ለጦርነት የመማገድ ተግባር እባካችሁ አቁሙ የሚል ጥሪ ላቀርብላቸው እወዳለሁ። ለዚህች ሃገር ቁጭ ብሎ መነጋገር ብቻ መፍትሄ  መሆኑን ላስረግጥ እወዳለሁ።
በሌላ በኩል፤ መንግስት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ጠንካራ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሃላፊነት መዋቅሮች ጀምሮ በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች ሙሉ በሙሉ በብቃታቸው ብቻ የተመደቡ መሆን አለባቸው። እውቀትን እንጂ ፖለቲካ ውግንናን መሰረት ያደረገ ምደባን ማስቀረትና ለቦታው ብቁ ባለሙያዎች መመደብ ይገባል።


Read 3152 times