Tuesday, 07 September 2021 00:00

መንግሥት ከጠላት በላይ መሆን አለበት!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ከሁለት ዓመት በፊት በወጣ አንድ ሪፖርት፣ በአማራ ክልል ከአንድ ሺህ በላይ የዳስና የዛፍ ስር ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ተገልጧል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ በትግራይም በርካታ የዳስ ትምህርት ቤቶች እንደነበሩ መነገሩን አስታውሳለሁ። ይህ ሪፖርት ካሳሰባቸውና ካሳዘናቸው ሰዎች አንዱ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፣ በራሱ ወጪ አንዱን ትምህርት ቤት ወደ ሕንፃ ለመለወጥ ቃል ገብቶ በተግባር ማሳየቱም ተዘግቧል።
በጦርነት ተወጥሮ ተይዞ የነበረው ደርግ፣ በአንድ እጁ እየተዋጋ በአንድ እጁ የልማት ስራ ለመስራት በነበረው ፍላጎት፣ ለሶስት ገበሬ ማህበራት አንድ ት/ቤት ለመስራት አቅዶ ተግባራዊ እያደረገ እንደነበርም ይታወቃል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ አሸባሪው ትሕነግ በቀሰቀሰው ጦርነት ከሰባት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን፣ በትግራይ ብቻ አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሃያ ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መለየታቸውንና አርባ ስምንት ሺህ  መምህራን ያሉበት እንደማይታወቅ ተናግረዋል። ሚኒስትሩ በአፋር ክልል አራት መቶ ሃምሳ አምስት ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን አመልክተዋል። በተመሳሳይ አሸባሪው ቡድን  የውጊያ ቀጠና ባደረጋቸው በወሎና በጎንደር አካባቢዎች፣ ከሶስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ፣ የቀሪዎቹ ባይታወቅም ከነዚህ  ውስጥ አንድ መቶ አርባ ትምህርት ቤቶችና ሁለት የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች  በጁንታው መውደማቸውን ገልጸዋል።
ጦርነቱ በዚህ የሚያበቃ አይደለም። ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አይታወቅም። አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው። እሱም ምንም እንኳን ወያኔ ጦርነት ለመቀስቀስ የሚያበቃው ምክንያት አለው ብዬ ባላምንም፣ ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን መካከል የሚካሄድ፣ እርስ በእርስ የምንተላለቅበት ጦርነት መሆኑን ነው።
በዚህም የተነሳ ስለ ጦርነቱ የሚኖረን ግንዛቤና ጦርነቱን የምንገልጽበት መንገድ የታሰበበትና ጥንቃቄ የሚፈልግ ሆኖ እናገኘዋለን። በእኔ እምነት ጦርነቱ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ጦርነት አለመሆኑን አስቀድሞ ማመን ያስፈልጋል። በጦርነቱ ላይ የበላይነት ማግኘት አስፈላጊ የመሆኑን ያህል የተገኘውን ድል ላለመነጠቅም ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን አስፈላጊ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ወያኔ ለማጥቃት የተነሳ ኃይል በመሆኑ የሚያጠቃበትን አካባቢ የሚመርጠው እሱ ነው። መንግስት ሊያደርግ የሚችለው ለጥቃት ይጋለጣሉ ብሎ የሚያስባቸውን አካባቢዎች አስቀድሞ መያዝና መጠበቅ ወይም ደግሞ ጥቃቱ በተከሰተ በአጭር ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስ ተወርዋሪ ሀይል ማዘጋጀት ነው። ተወርዋሪ ኃይሉ በቦታው በተጠበቀው ጊዜ መገኘት አለመቻሉ በሕዝብና በመንግስት መካከል ያለውንና ሊኖር የሚገባውን መደጋገፍ እንዳይፈታተንም መታሰብ ይኖርበታል። በአጭር አማርኛ፣ የታጠቀን ኃይል ህዝብ በዱላ እንዲገጥም መጠበቅም የሚገባ አለመሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።
እየተካሄደ ያለው ጦርነት ነው። ጦርነቱን የከፈተው ትሕነግ አስቦ ተደራጅቶ ነው። መንግስት ወደ ጦርነቱ የገባው ድንገት መሆኑም የታወቀ ነው። መላውን ትግራይ በአጭር ጊዜ የተቆጣጠረው መንግሥት፣ ድሉን ማስጠበቅ ያልቻለበት ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ እንዳይደገም አብዝቶ ማሰብ አለበት። እየተከላከለ እያጠቃ በሄደ ቁጥር ይዞታውን በአስተማማኝ ለማስጠበቅ መነሳት ይኖርበታል። ወያኔ ለዘመቻ ፀሐይ ግባት የተከተለውን መንገድ መዳሰስም ብልህነት ነው።
ጦርነቱ በጦር ሜዳ የሚካሄድ ብቻ አይደለም። የመገናኛ ብዙኃኑ መስክም ጠንካራ ተፋላሚ የሚፈልግና የሚጠብቅ የትግል ሜዳ ነው። ከወርና ከ2 ወር በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲታይ ለውጥ እንዳለ ቢታይም፣ አንዳንድ የጦር መሪዎች ወደ አደባባይ እየወጡ መግለጫ እየሰጡ ቢሆንም፣ አሁንም በዚህ በኩል ብዙ መስራት ያስፈልጋል። መንግሥት መረጃውን በመስጠት በኩል  መፍጠን ያለበትን ያህል በልዩ ልዩ መንገድ መረጃ ለህዝብ የሚያደርሱ ክፍሎችም መረጃውን በጥንቃቄ ተቀብለው በትክክለኛ መልኩ ሳያዛቡ ለህዝብ ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል። ጦርነቱን የአንድ ሳምንት ወይም የአንድ ወር ስራ አድርገው ለማሳየት የሚፈልጉ ወገኖች ከዚህ ስራቸው መታረም ይኖርባቸዋል። ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ምን ብላችሁን ነበር የሚል ጥያቄ ማስነሳት እንደሚችልም ማወቅ አለባቸው። ነገሩን በልኩና በመጠኑ መግለጽ፣ ህዝብ ትጥቁን እንዳይፈታ ማስገንዘብ ከነሱ የሚጠበቅ ግዴታ ነው።
መንግስት የሚያዩና የሚያስተውሉ 101 ዓይኖች፣ የሚያዳምጡ እልፍ አእላፍ ጆሮዎች፣ ፈጣንና ቆራጥ ውሳኔ የሚሰጡ አመራሮች በሚያስፈልጉበት ወቅት ላይ መገኘቱን ማወቅ  ይኖርበታል።
እስካሁን እንደነበሩት ሁሉ ዛሬም የወዳጅ ጠላቶች ባጠገቡ መኖራቸውን አምኖ እግር በእግር መከታተል፣ በበቂ መረጃ ላይ ቆሞ ፈጣንና ተገቢ ቅጣት መስጠት ከመንግስት ይጠበቃል። መንግስት ከጠላት በላይ ሆኖ ለማየት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚጓጓ ሊረዳ  ያስፈልጋል።

Read 9580 times