Saturday, 04 September 2021 17:14

ኢትዮጵያዊው የጁ-ጂትሱና የጁዶ “ግራንድ ማስተር”ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(7 votes)

 ልዩ ቃለምልልስ ክፍል 1


                 ኢትዮጵያዊው የጁ-ጂትሱና የጁዶ “ግራንድ ማስተር”ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ

    • በፌደራል ጀርመን የክብር መስቀል ኒሻን ተሸልመዋል
    • በጁዶና ጁ-ጂትሱ ስፖርት ከ30 አመታት በላይ ሰርተዋል፤ 6ኛ ዳን ጥቁር ቀበቶ(ነጭ ቀይ) ተቀዳጅተዋል፡፡
    • የጁ-ጂትሱ ማርሻል አርት ፍልስፍናና መሰረታዊ ቴክኒኮች በመፅሃፍ አሳትመዋል፡፡


          ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ጉግሣ ነዋሪነታቸውና ቋሚ ስራቸው በጀርመን በርሊን ነው፡፡ በየዓመቱም የእረፍት ጊዜያቸውን እየተጠቀሙ በተለያዩ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ ይመላለሳሉ፡፡ ዘንድሮ የፌዴራል ጀርመን የክብር መስቀል ኒሻን ተሸላሚ (Bearere of the Fedral Mereit of Cross) ተጎናፅፈዋል፡፡ በአስተዳደር ማኔጅመንት ሁለተኛ ዲግሪ፣ በኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪ የያዙም ናቸው፡፡ በዳይምለር መርሴዲስ ቤንዝ የጀርመን ገበያ ዲቭዥን ውስጥ በሰው ሃይል ዲፓርትመንት የብዝሃነት እና የዘላቂ ልማት (Diversity & Sustainability) ማኔጀር ናቸው፡፡
በጁዶ እና ጁ-ጂትሱ ስፖርት ከ30 አመታት በላይ በመስራት 6ኛ ዳን ጥቁር ቀበቶ (ነጭ ቀይ) የግራንድ ማስተር Grand Master ማዕረግ ተቀዳጅተዋል፡፡ የአፍሪካ ጁ-ጂትሱ ፌዴሬሽን  ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፤ ከ2016 እኤአ ጀምሮ የዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት እና  የዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን የዘላቂ ልማት (Sustainability & sport4climate) የበላይ ኃላፊ ሆነውም እያገለገሉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በእውቀት ለህብርት እና ልደታ ወንዶች ት/ቤት (ካቴደራል) አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ተከታትለዋል፡፡ ከዚያም በእንጦጦ የሙያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (የቀድሞው ተፈሪ መኮንን) ተምረዋል፡፡ በጀርመን እየተማሩ በሁምቦልት ዩኒቨርስቲ የታዳጊ አገሮች የጥናት ማኅበር ሊቀመንበር፣  በቀድሞ አልይንስ የመኖሪያ ሰፈር ውስጥ የቦርድ አባል ነበሩ። በዶክትሬት ጊዜያቸውም በምርምር ረዳትነት በተለያዩ የምርምር ፕሮጄክቶች ውስጥ በመስራት እና ከጨረሱም በኋላ  በፕሮጀክት ማኔጅመንት ዙሪያ በቪስማር ዩኒቨርሲቲ በተጋባዥ መምህርነት እና ሌክቸረርነት ለዓመታት በትግበራ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ለዓለም አቀፍ ተማሪዎች በበርሊኑ ቲክኒካል ዩኒቨርስቲ የክረምት ኮርስ ተጋባዥ ሌክቸረር በመሆን የማኔጅመንት ክህሎቶችን ለጀርመን እና ለውጭ አገር ተማሪዎች ሰጥተዋል።  በAllstate ኢንሹራንስ ካምፓኒ ውስጥ የቢዝነስ ተንታኝነት የመጀመሪያ የስራ ልምዳቸውን ወስደዋል። በኢትዮጵያ ከስፖርቱ በተጨማሪ በተግባራዊ ፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በሥራ ባህልና በውቅረ ሃሳብ፣ በግጭት አፈታት ሴሚናሮች ወርክሾፕና ሴሚናሮችን  ለተከታታይ ዓመታት በበጎፈቃደኝነት ስሰጥ በእውቀት ሽግግር ዙሪያ ጽሁፎችን በማቅረብ፣ በማማከር እና የኢትዮጵያ እና የጀርመን ወዳጅነት ለማጠናከር  እየሰሩም ቆይተዋል።
ትውልዳቸው አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን አባታቸው ሜጀር ጄነራል ደግነህ ጉግሳ እና እናታቸው ወ/ሮ ሊያውሽ መለሰ ይባላሉ፡፡ ሜጀር ጄኔራል ደግነህ በመጀመሪያው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ከነወታደራቸው  ወደ ሶማሊያ ግዛት ዘልቆ በመግባትና ጦርነቱን በመጨረስ ይታወቃሉ፡፡ የገለብ እና ሀመር ባኮ አውራጃ ገዥ የነበሩ ሲሆን፤ በማይጨው ፣ በጎጃም እና በነገሌ በሽምግልና እንዲሁም በበጎ ፈቃደኝነት በተለያዩ ሃላፊነቶች ያገለገሉና ትምህርት ቤት በመገንባት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው፡፡
ዶክተር ፀጋዬ የህክምና ኦዲተር ከሆነችው ጀርመናዊቷ አኔት ጋር ጋብቻ ከመሰረቱ በኋላ ሁለት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ሊያን እና ሳሮን ይባላሉ፡፡ ሳሮን በጀርመን ፊልም መድረክ ወጣት ተዋናይ ስትሆን በቅርቡ ከአፍጋኒስታን የመጣች ስደተኛ ቦክሰኛ ሆና የተወነችበት የቴሌቭዥን ፊልም ጥቅምት 1/2021 በጀርመን ብሔራዊ ቲቪ እየታየ ነው፡፡
*   *   *
የደረሱበትን የግራንድ ማስተር Grand Master  ማዕረግ እንዴት ይገልፁታል?
6ኛው የዳን ዲግሪ ጥቁር ቀበቶ (ቀይ ነጭ) በማርሻል አርት ፒራሚዳዊ ስርዓት ግራንድ ማስተር ተብሎ የሚሰጥ ማዕረግ ነው።  ከጃፓን የቡዶ ስፖርት የምረቃ ሥርዓትም ጋር በጣም የሚመሳል ሲሆን፤ ጀማሪ ተማሪዎች በመጀመሪያው መደብ የሚያገኙት ማዕረግ (ኪዩ kyu) ይባላል። ስፖርተኛው በስልጠናው ሂደት ከአንዱ የቀበቶ ቀለም ወደ ሌላው መመረቅ ይኖርበታል። እያንዳንዱን የቀለም ቀበቶ ለመታጠቅ ከ6 ወር እስከ አንድ ዓመት ይፈጃል።
በሳምንት ሁለት ጊዜ መሰልጠንና  መደበኛ ልምምድ መስራት ዋናው መስፈርት ነው፡፡ ከ5 ዓመት መደበኛ ስልጠና በኋላ በማስተር ማዕረግ ጥቁር ቀበቶ (1st dan) በመታጠቅ በመምህርነት መመረቅ ይቻላል። እኔ ይህን ማዕረግ የደረስኩት በ7 ዓመት ነው ።  ማስተር ዲግሪው 5 ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፤ ከተማሪው ኪዩ ማዕረግ በተለየ መልኩ ብዙ የዝግጅት ዓመታት ማሳለፍን ይጠይቃል ። በእኔ በኩል የመጀመሪያ  ጥቁር ቀበቶን ካሰርኩ በኋላ አሁን ለወሰድኩት 6ኛ ዳን ለመድረስ 22 ዓመታት በላይ ፈጅቶብኛል።
በጀርመን 1ኛ ዳን ለመመረቅ የአሰልጣኝነትና የመጀመሪያ እርዳታ ፈቃዶችን ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ በ4ኛ የዳን ጥቁር ቀበቶ ለመመረቅ ደግሞ ብሔራዊ የብዙሃን ስፖርት አሰልጣኝ ፈቃድ ይጠይቃል፡፡ በፌዴራል የስፖርት ማህበራት በሚዋቀር የስልጠና መርሃግብር 120 ሰዓታትን በትርፍ ጊዜና በማታ ትምህርት ሁሉ መከታተል ግድ ይሆናል፡፡  5ኛ ዳን ማዕረጌን ያገኘሁት በ2014 እአኤአ ፓሪስ ላይ ከተለያዩ ሀገራት የተወከሉ 4 ግራንድ ማስተሮች ፊት በመቅረብ በተሰጠኝ ፈተና ነው፡፡
የGrandmaster ማዕረግ እንደሽልማት የሚበረከት እንጂ በምረቃ በኩል የሚደረስበት አይደለም፡፡ ይህን ማዕረግ መቀዳጀት የሚቻለው ልዩ ስብዕና በመላበስ፤ እንዲሁም ማርሻል አርትና ስፖርትን በአጠቃላይ ለማዳበር በተመዘገበው ስኬት ልክ ነው፡፡
በስፖርት ውስጥ የGrandmaster ማዕረግ መጎናፀፍ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ግራንድ ማስተር መሆን በማርሻል አርት ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረስ ነው። ይህን ማዕረግ ለመቀዳጀት በማርሻል አርት፣ በስፖርትና በምሉዕ ስብዕና የላቀ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚያስፈልግ አንዳንዶች ይገልፃሉ፡፡ በጁዶና በጁ-ጂትሱ ስፖርቶች ለሚሳተፉ ሰዎች ትልቅ ከበሬታ ያሰጣል፡፡ በተጨማሪ የአመራርነትም ማዕረግ ነው። እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ በጣም የተከበረ መሪ መሆን ነው። በጁዶ እና በጁ-ጂትሱ ስፖርት (Judo and Ju-Jitsu ) ፕሬዝዳንት ፑቲንን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። 7ኛ የዳን ግራንድ ማስተር ሲሆኑ የዓለም አቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽን የክብር ፕሬዝዳንት ናቸው።   Grand master መሆን ማለት የስፖርቱን ዘዴዎችና እሴቶች ማወቅ ብቻ አይደለም፤ ከሥነ ምግባር፣ ከተፈጥሮ፣ ከተክለ ሰውነትና ከአእምሮ ጋር ያላቸውን ግንኙነት መገንዘብም ነው። ከድርጅታዊ ኃላፊነት ባሻገር ለማህበረሰቡ ተምሳሌት መሆን ይገባል፡፡
ከ30 ዓመታት በላይ በስፖርቱ ያሳለፉት ልምድ ምን ይመስላል፤ በሥነ-ምግባርና ዘላቂነት ባላቸው ተግባራት በያዟቸው ዓለም አቀፍ ሃላፊነቶች ያበረከቱትን አስተዋፆስ?
ማርሻል አርት በጣም ነው የምወደው፡፡ በጀርመን ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በሥልጠና ውስጥ ቆይቻለሁ። በበርሊን ሀምቦልት ዩኒቨርስቲ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ በትርፍ ጊዜዬ አሰልጣኝ ሆኜ በማገልገል ስኬታማ አትሌቶችን የያዘ የስፖርት ማህበረሰብ መገንባት ችያለሁ፡፡
ጀርመን ውስጥ በተለያዩ የጁ-ጂትሱ እና የስፖርት ኮርሶች እና አገር አቀፍ ኮርሶች ላይ ብሔራዊ ፈተናዎችን በመስጠትና ኢንስትራክተር ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ በተለይ የስፖርቱን አድማስ ለማስፋት፤ እሴቶቹን ለማጎልበትና ውህደት ለመፍጠር ልዩ ትኩረት በማድረግ ችያለሁ፡፡ በ2014 እኤአ ላይ በጀርመን ጁ-ጂትሱ ፌዴሬሽን HIGHEST GOLDEN NEEDLE OF HONOUR ከፍተኛ የወርቅ መርፌ ክብርን ተቀብያለሁ።
የጁ-ጂትሱ ማርሻል አርት ፍልስፍና እና መሰረታዊ ቴክኒኮች “Ju-Jitsu-Martial Art Philosophy and Basic Techniques” በሚል ርዕስ በአማርኛ ቋንቋ መፅሃፍ አሳትሜያለሁ። ይህ መጽሐፍና በአይነቱ ለአፍሪካ  ፈርቀዳጅ ነው። በጀርመን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች መፅሃፉን ለማዘጋጀት በተቀረፀው ፕሮጀክት ተካፍለዋል። በአብዛኛው ከሀምቦልት ዩኒቨርስቲና የተወሰኑት ከኢትዮጵያ በአጠቃላይ 21 ሰዎች ተሳትፈዋል። ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው የፕሮጀክቱ  ሂደት ከ5000 በላይ ፎቶዎች የተወሰዱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 830ዎቹ በመፅሐፉ ተካትተዋል። በዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ተገቢውን እውቅናና አድናቆት ያተረፍኩበት መፅሃፍ ነው፡፡ በ2010 እ.ኤ.አ ላይ የአፍሪካ ጁ-ጂትሱ ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኜ ከተመረጥኩ በኋላ ህብረቱን በሙሉ አደረጃጀት በማዋቀርና ህገ ደንቦችን በማሻሻል ሰርቻለሁ። የአፍሪካ አህጉር በዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች ጠቅላላ ጉባኤዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራት እንዲሁም በሁለትዮሽና በብዙ ወገን በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ በመሳተፍ ሳገለግልም ነበር።
ከ2016 እአኤአጀምሮ ውስጥ የዓለም አቀፉ የጁ ጂትሱ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ባካሄደው ምርጫ የሥነ ምግባር ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኛለሁ፡፡ በአዲሱ የሥነ ምግባር ኮሚሽን አወቃቀር ላይ ከዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ጋር በሚስማማ መልኩ በማደራጀት፤ የአባል አገራትን የሥነ ምግባር ደንብ ለማዳበር እንዲሁም የየአገራቱን ጽኑ አቋም በመገምገም ተሳትፎ አደርጋለሁ። በስፖርቱ የሚነሱ አቤቱታዎች ስርዓትና ታማኝነት ዙርያ፤ ስነምግባርን ከማህበረሰቡ እና ከተፈጥሮው ጋር የሚያያይዙ ሴሚናሮችን አካሂጃለሁ።
በተጨማሪም ከ2020 እአኤ ጀምሮ በዓለም አቀፉ ፌደሬሽን የSport4 የአየር ንብረት ተወካይ / የዘላቂነት ኦፊሰር በመሆን እያገለገልኩ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦቹን በአባል ፌዴሬሽኖች ለመተግበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከአየር ንብረት ለውጥ ዲፓርትመንት ጋር እሰራለሁ። በተሰጠኝ ኃላፊነትም በየአገራቱ የሥራ ቡድኖችን በማቋቋም፣ የኃይል ቁጠባ ውድድሮችን፣ ሥልጠናዎችና ሴሚናሮችን  በዘላቂ ልማት ዙርያ ያላቸውን አፈፃጸም እከታተላለሁ። በዘላቂ ልማት ላይ የሚሰሩ አምባሳደሮችን ብቃትም እገመግማለሁ፡፡ ከፕላስቲክ ነፃ የስፖርት ውድድሮች እንዲካሄዱ፣ ዛፍ መትከል፣ ቆሻሻ መሰብሰብና ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ በመስጠት ስፖርተኞች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም እንቀሳቀሳለሁ፡፡ ዕውቀቴን ወደ ሀገሬ ኢትዮጵያ እና እንደኔ አይነት እድል ላልገጠማቸው ሰዎች ማሸጋገር ሁሌም ፍላጎቴ ነው።  ስለዚህ የጁ-ጂትሱ ስልጠና በኢትዮጵያ የጀመርኩት በ2007 እኤአ ሲሆን ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ የጁዶ እና የጁ ጂትሱ መዋቅር ላይ መስራት ጀምርያለሁ። ከባድ ፈተናዎች ቢያጋጥሙንም አንድ ጊዜ ማቆም በጣም አስቸጋሪ ነው። በየዓመቱ በሚኖረኝ የእረፍት ወቅት ላይ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ   ወጪዬን በራሴ እየሸፈንኩና በበጎፈቃደኝነት ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በመጓዝ ስፖርቱን ለማስፋፋት ጥረት አድርጊያለሁ፡፡
የጁ-ጂትሱን ዘመናዊ ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ካመጣሁ በኋላ ከ2010 እኤአ ወዲህ  ከጁዶ ስፖርት ጋር ውህደት በመፍጠር እያስፋፋሁት ነው፡፡ በዚህም መሰረት ክለቦችና ማህበራት በጁዶና ጁ- ጂትሱ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እንደ በላይ ጠባቂ ሆኜ እየሰራሁ እገኛለሁ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ2011 እኤአ የዓለም የጁዶ ሻምፒዮና እና በ2010 የዓለም የጁ-ጂትሱ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሳተፉም አስችያለሁ።
በ2019 እ.ኤ.አ ሚያዝያ  ላይ ሞሮኮ  ባስተናገደችው የጁ-ጂትሱ የአፍሪካ ሻምፒዮና  ያሬድ ንጉሴ በወንዶች የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም መስከረም አለማየሁ በሴቶች ምድብ የብር ሜዳልያ ለኢትዮጵያ  ተጎናፅፈዋል፡፡ በዓመት እረፍቴ ላይ ወደ ኢትዮጵያ በምመጣበት ወቅት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ተጉዤ በርካታ የማርሻል አርት ሴሚናሮች (የፕሮጀክት አስተዳደርና የሥራ ባሕል ሴሚናሮችን ጨምሮ) ስሰጥም ቆይቻለሁ። ባለፉት ዓመታት ያከናወንኳቸው እነዚህ የስፖርት እንቅስቃሴዎች ከ1000 በላይ ህፃን፤ ወጣት እና አዋቂ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈውባቸዋል፡፡ ብዙ የማርሻል አርት ስፖርተኞችን  የምደግፍ ሲሆን የጁዶ እና ጁ-ጂትሱ እሴቶችን ለመተግበር በኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ውስጥ እንደ ዲሲፕሊን፣ መከባበር፣ የራስ ኃላፊነት እና ሌሎችንም ለማዳበር  በትጋት ሰርቻለሁ፡፡ ከጀርመን የጁዶ ግራንድ ማስተር ጆሃንስ ዳክስባቸር ጋር በመተባበር (ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ቢሮ፣ ከጀርመን ኦሊምፒክ ስፖርት ፌዴሬሽን፣ ከጀርመን ጁ-ጂትሱ ና ጁዶ ፌዴሬሽኖች እና ከአዲስ አበባ የጀርመን ኤምባሲ ጋር በመስራት) ለኢትዮጵያ በርካታ የቁሳቁስ ልገሳዎችን አበርክቻለሁ። በርካታ አሰልጣኞችን ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም አሰማርቺያለሁ።…. ይቀጥላል


Read 12700 times