Saturday, 04 September 2021 17:20

ከበደች ተክለአብ፤ ታላቋ ባለቅኔ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(8 votes)

የአለንበት ድህረ-ዘመናዊዉ ዓለም የጥበብ ሥራን ሸቀጥ (commodity) አድርጎታል፡፡ የሳይንሱንና ቴክኖሎጂዉን መራቀቅ ተከትሎ ዕውቀት ረክሷል፡፡ የሰው ልጅ ከሞራል ልዕልናው አንሶ አውሬአዊ ባሕርይን ተላብሷል፡፡ ባሕል ዘቅጧል፡፡ ሳይንስ በእጅ አዙር ኪነ-ጥበብን ሊቀብር በብርቱ እየተፍጨረጨረ ይገኛል፡፡ ይህ ሳይንስ ወለዱ ዘርፈ ብዙ ቀውስ በዚህ ዘመን በአዱኛ ኪስን የማትሞላውን ጥበብን ሙጥኝ ብለን የምንኖርን ጸሐፍት ኑሮ እጅግ ፈታኝ አድርጎታል፤ ግን አሁንም ድረስ በጥበብ ምርኮኛነታችን ዘልቀናል፡፡
* * *
ሥነ-ጽሑፍን ሙያ አድርገን የምንኖር የዚህ ዘመን ጸሐፍት (ገጣሚያን)፣ የዛሬውን መክሊታችንን ያሟሸነው የአገራችንን ታላላቅ ባለቅኔዎች (የእነ ሰሎሞን ዴሬሳን፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታን፣ ከበደች ተክለአብን፣ ደበበ ሰይፉን፣ ፀጋዬ ገብረ መድኅንን፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬዉን እና ሙሉጌታ ተስፋዬን) ሥራ በማንበብና በመመርመር ነበር፡፡ የእያንዳንዳችን የእለት ተእለት ኑሮ በእጀጉ ከንባብ ጋር የተቆራኘ ነበር፡፡ ጥበባዊ ዉይይታችን ጥልቅ ነበር፣ ሙግታችን ብርቱ ነበር፡፡
ጥበብ ሸቀጥ መሆኑን ተከትሎ ሥነ-ጽሑፋዊ ሥራ በገፍ አደባባዩን ቢያጥለቀልቀውም በተቃራኒው የአገራችን የንባብ ባህል አሽቆልቁሏል፡፡ እየተመነደገ የነበረዉ የቀድሞዉ የሥነ-ጽሑፍ ውይይትና የሂስ ባህላችን ከስሟል፡፡ ጥበብን ለተፈጠረበት ፋይዳው የሚሠሩ ከያኒያን ጥቂት ናቸዉ፡፡ በተቃራኒዉ፣ ጥበብን ለሌላ ህቡዕ ፍጆታነት የሚያዉሉ ሶፊስቶች እንደ ጉንዳን ፈልተዋል፡፡ እድሜአቸዉን ለጥበብ ሰውተዉ ዘመን አይሽሬ ሥራዎችን ሠርተው ያለፉ ጸሐፍት ግን ሁሌም እየተዘከሩ ይዘልቃሉ፡፡ እኔም በዚህ አጭር ጽሑፌ ታላቋን ባለቅኔ ከበደች ተክለአብን እዘክራለሁ፡፡
የከበደች ታላቅ ሥራ ከአስራ አንድ ዓመታት የእስር ቆይታዋ በኋላ በ1983 ዓ.ም ለህትመት ያበቃችዉ የት ነዉ?  የተሰኘው የግጥም መድበል ነዉ፡፡ በዚህ መድበል የቀረቡ ግጥሞች በአያሌው የገጣሚዋን ግላዊ ስሜቶች የሚያስተጋቡ ኢምፕረሺኒስቲክ ናቸዉ፡፡ ኢምፕረሺኒዝም ፈረንሳይ የተወለደ ሥነ-ጥበባዊና ሥነ-ጽሑፋዊ አስተምህሮ ነው፡፡
ኢምፕረሺኒስት ገጣሚያን ግላዊ ስሜታቸውን በግጥም የማተት አባዜ የተጠናወታቸው ገጣሚያን ናቸው፡፡ አገራችን ያፈራቻቸው ሁለቱ እዉቅ ደራሲያን አዳም ረታ እና ኦ’ታም ፑልቶ (ስንቅነህ እሸቱ) ደንበኛ ኢምፕረሺኒስት ጸሐፍት ናቸው፡፡ ለዋቢነት ከአዳም ሥራዎች መካከል ግራጫ ቃጭሎች የተሰኘውን የደራሲውን የበኩር ረዥም ልብወለድ፣ ማሕሌት ከተሰኘው ሥራው ውስጥ ማሕሌት የተሰኘውን አጭር ልብወድ እና አለንጋና ምስር እና ሊሎች አጫጭር ታሪኮች ከተሰኘው ሥራው ውስጥ ከልጅቷ የተሰኘውን አጭር ልብወለድ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከኦ’ታም ፑልቶ (ስንቅነህ እሸቱ) ሥራዎች መካከል ደግሞ በሁለት ቅጽ የታተሙት ተከታታይ ረዥም ልብወለዶቹ (trilogy novels) የሲሳዬ ልጆች (ኬክሮስ እና ኬንትሮስ) እና ኤላን ፍለጋ (የአዞ ኮሌጅ) ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡ ከታዋቂ የባህር ማዶ ኢምፕረሺኒስት ደራሲያን መካከል ጆሴፍ ኮንራድ፣ ሄነሪ ጀምስ እና ጀምስ ጆይስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ኢምፕረሺኒስት ጸሐፊ የታሪክ ቅደም ተከተልን ተከትሎ አይተርክም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ደራሲው በፈጠራ ሥራው ከሳለው ገፀ-ባሕርይ ሞት ተነስቶ ወደ ውልደቱ ታሪክ ሊዘልቅ ይችላል፡፡ ኢምፕረሺኒስቶች ጥቃቅን ጉዳዮችን በዝርዝር መዘብዘብ የሚወዱ ጸሐፍት ናቸው፡፡
ኢምፕረሺኒስት ገጣሚያን ብዙ ጊዜ በብዕራቸው ውስብስብ ልባዊ ንሸጣቸውን (subjective sensations) ስለሚከትቡ ገለፃቸዉ ለሌሎች ግንዛቤ ሊረቅ ይችላል። ከበደች የነፍሷን ትኩሳት ከገለፀችባቸው ኢምፕረሺኒስቲክ ግጥሞች መካካል አንዱ እንባና ፈገግታ ነው፦
የብሶት ነዲድ አካልን
ገሞራ ሆኖ ሲያግለው
ዐፅሞች ነበልባል ሆነው
ሕዋሳት በረመጥ ፍመው
ዐይኖች በሙቀት ቀልተው
የከርሠ ምድር ቀላጭ
መዉጫ አጥቶ እንደሚታመ
ጉሮሮን ሲቃ ሲተናነቅ
ዐይንም በእንባ ሲጨነቅ
አካል በእልህ ሲጥለቀለቅ
የመከራ ሰማይ ዳምኖ
የመዓት ዝናቡን ሲጥል
በቁጣ ፍሳሽ ጎርፉ፡፡
እና ሕይወት ሊበከል
… በዚህ መሐል
የዚህ ሁሉ ተሸካሚ
በሐዘን የተሰበረው
የሚመካበትንም ህልውናውን ሲማፀነው
አብነቱን፣ ቀኝ እጁን
ድንገት ከጎኑ ያገኝና
የተንጠለጠለው መዓት
የጠቆረውም ዳመና
በመመኪያው ሙቀት ተኖ
ብናኝ ሆኖ ይጠፋና
ያሸለበ ሕሊና
ደግሞ መልሶ ሊቀና!
የጥቁር ሰማይ ነፀብራቅ
ጽልመት ያለበሰው ፊት
ድንገት ባየው አብነት
ባቆጠቆጠው ተስፋ ግፊት
የብርሃን ብልጭታ ፈክቶ
ገጸ-ጽልመት ሲገፈፍ
ንጹሕ ፍሳሽ አካል ላይ
እንደሚንጣለል ሰፈፍ
የታመቀውም ትኩስ እንባ
በቁጭት ቅጽበት ተኮርኩሮ
እንደ ፈጣኑ ገሞራ
የዐይንን አውታር ሰብሮ
ፈገግ ባለው ገጽታ
ዘና ባለው ጉንጭ ላይ
የእንባ እንክብሎች ለመውረድ
ሲሽቀዳደሙ ሲታይ
ሁለት ልዩ ስሜቶች
ተፃራሪ ዳርቻዎች
የደስታ ፈገግታና
የሐዘን መለኪያ እንባዎች
በአንዲት ቅጽበት ተጋጭተው
እንባ ፈገግታን ላይሽር
ፈገግታም እንባን ላይገታው!
(ከበደች፣ 1983፣ ገፅ 19-21)
ብዙ ጊዜ በኢምፕረሺኒስት ገጣሚያን ሥራዎች ውስጥ ግላዊ ሥነ-ልቦናዊ ምልከታዎች በእጀጉ ይንፀባረቃሉ፡፡ ከበደች ባይተዋርነት የከበበውን፣ ቀቢፀ-ተስፋ ያጠለበትን የነፍሷን ሰቀቀን፣ የአካሏን ጉስቁልና የገለፀችበት ሌላኛው ኢምፕረሺኒስቲክ ግጥም መንዴራ ይሰኛል፦
መንዴራ! የእኩይ ገጽታ ጣምራ
መቅሰፍት አንጸባራቂ ጮራ
የሥቃይ መናኸሪያ ጎተራ!
ምን ይሆን ሟርትሽ መንዴራ
በደጅሽ ብርሃን የማይበራ
ምን ይሆን ከቶ ምስጢርሽ
የጨለመበት እንግዳሽን
በጨለማ ቤት መቀበልሽ
በሰናስልት ግጭት ጩኸት
በቁልፍ ቅጭልጭል ማሸበርሽ
ለመግባት እንጂ ለመውጫ
እማይከፈት ይመስል
በሩን በቁጣ መዝጋትሽ
ጸጥ ባለው ጨለማ ቤትሽ
ድምፅ ሥቃያት ማብዛትሽ
ምን ይሆን እኩይ ጥበብሽ
የሲኦል ተቀጽላ ሟርትሽ!
መንዴራ!
አንቀጽሽ ምንኛ ይከፋል
ጨለማሽ ምንኛ ይውጣል
በርሽ ምን ያህል ይጫናል
የሰናሰልትሽ እኩይ ድምፅ
ለስንት ጊዜ ይደውላል?!
(ከበደች፣ 1983፤ ገፅ 40-44)


Read 305 times