Print this page
Saturday, 04 September 2021 17:25

ስለ ሂስ እማልዳለሁ!

Written by  በዮናስ ታምሩ
Rate this item
(1 Vote)


               የቃለ እሳት ነበልባሉ፣
አልባከነምና ውሉ፣
የዘር-ንድፉ የፊደሉ፣
ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ፤…
        (ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን)
ፈረንሳዋዮች አንድ አባባል አለቻቸው፤ በእንግሊዝ አፍ ስትባል እንዲህ ነች፣ ‹‹There is no free lunch›› የምትል፤ ይኼም ‹‹ፋሲካን ያሉ ሕማማትን ተቀበሉ›› የሚል አገራዊ አቻ ትርጓሜን ይመስላል። ታዲያ፣ ጸጋዬ ገ/መድኅን ከተጠቀሰው ብሒል ጋር እሰጣ-ገባ ውስጥ መግባቱ ዕሙን ነው ባይ ነኝ - በ‹‹የብዕር አሟሟት ሌላ›› ግጥሙ። በእኔ ዕምነት፣ አንድ የሥነ-ጽሑፍ ሥራ በደራሲው፣ በድርሰቱና በተደራሲው በኩል ለሂስ ተጋልጦ (በእርግጥ ማሟያ ማለፍ ወይም መውደቅ የሚባል አቃቂር በሂስ ዓለም ሊኖር አይገባም፤ የለምም) ሲያበቃ ድክመትና ጥንካሬው በሃቲት እንዲቀርብ ውል አለ። ቢሞት ‹‹ሞተ›› ቢባል ነውር የለውም።    
የማነበው ድርሰት እንደ እግር-ኳስ ሊያወናብደኝ ግድ ይለዋል። የእኔን ዕውነት በሌላ፣ በራሱ ዕውነት፣ አለያም ቀንድ ባወጣ ቅጥፈት በርዞና መርዞ ሊያወራክበኝ የቤት ሥራ አለበት። አጀማመሩን እንጂ ምን ብዬ እንደምጨርስ ፍንጭ ሊጠቁመኝ ቢዳዳው በተሃ ይሆንብኛል። በእግር-ኳስ ዓለም ሃያ ሁለት ሰዎች እሜዳ ዘልቀው አንዷን ኳስ ለመነረት ሲራኮቱ ብሎም ለቡድናቸው አቸናፊነት ሲተጉ ያለው የልብ መናጥ አጃዒብ ነው። ኳስ አጀማመሩ ላይ ያማረ ነው፤ እስኪያልቅ ደግሞ ያጓጓል። ብሎም፣ ከተጠናቀቀ በኋላ መልሶ ይናፍቃል። ‹የእግር-ኳስ ልክፍት› ቢባል ያግባባኛል። እንዲህ ዓይነቱ ልክፍት ድርሰትን ሊጣባ ይገባዋል። ከተነበበ በኋላ የሚረሳ፣ ወይም መደርደሪያ የሚያሞቅ መሆን የለበትም።
አንድ መጽሐፍ ካነበብኩ በኋላ እንዲሰማኝ የምሻው ስሜት የሕጻን ጡት እጦት፣ ወይም ጣዕር ሲያንገላታት፣ ዓይን-ዓይኗን እያዩዋት፣ ቤሳቤስቲን ቢያጡ፣ እናት እንደ ማጣት ዓይነት መብከንከንን እና መፋጨርን ነው። ነፍሲያዬ ቁስሏ ጠግጎ፣ ዕውነትን ለማጤን ያጎነቆለ ጥያቄዋ ጠውልጎ ድርሰቱን ላገባድደው አልፈቅድም - ክንፌ ረግቦ ኩምሽሽ እላለኋ! የዚህ ዓይነቱ ጽሑፍ ከድርሰትነት ይልቅ ነፍሳችንን ኩም አድርጎ ከዓላማችን የሚያናጥበን አፈ-ታሪክ፣ ወይም ተረት-ተረት መባል ይቀለዋል።
ብሎም፣ ለሚቆፍነኝ ብርድ ቡልኮ የሚያከናንበኝ ጽሑፍ ቃባዥዋ ነፍሴን አሞኝቶ እንቅልፍ ከመልቀቅ ውጭ ሌላ ፋይዳ አይፈይድላትም። ይልቅ ቡልኮዬን ገፍፎ ለብርድ የሚያጋልጠኝን፣ የአሳሽነት ስሜት የሚጥልብኝ ቢሆን ምኞቴ ነው።
ወደ አሁኔ ስመለስ፣ በእኛ አገር፣ በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ ሂስ መስጠት ወጥ እንደ መርገጥ ነው፤ ነውረኛና ጥቁር ምላስ ያስብላል። ቢኖር እንኳን፣ በመልኩ አቆለጳጳሽና አሞጋጋሽ ይሉት ሂስ የተጠናወተው ነው። ለማሳመን ዕልፍ መቧቸር፣ ከንቱ ውዳሴና ተራ ቁልምጫ ይበዛዋል። ደራሲና ድርሰቱ በ‹‹አፍህን ያዝ›› ባይ እልፍኝ አስከልካዮችና በ‹‹በዓይናችን መጡ›› በሚሉ ጋሻ-ጃግሬዎች የታጠሩ ናቸው።
ሂስ ብትሰጥ በአፉ ጤፍ የሚቆላ ወራፊ እንደ ንብ ከብቦ ያዋክብሃል። በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ፣ ‹‹ዕውነትን ታውቃላችሁ፤ ዕውነትም ነጻ ያወጣችኋል›› የሚል የሐዋሪያው ጳውሎስ መልዕክት ውኃ እንደተቸለሰበት አምናለሁ። በግብታዊነት መመዘንና በአጀብ ማሞካሸት ጥላ አጥልተዋል። የሥነ-ጽሑፍ ዓለማችን፣ ጥዋ እንደ መጠጣት የማሕበር ጉዳይ ሆኖ አርፏል። በሆታ የሚያቧችር ‹‹አንቆራባጭ››፣ አለያም በአጀብ በሚያብጠለጥል ‹‹ነኹላላ›› አንባቢ መሃል ተቸንክሯል። ይኼ በሥነ-ጽሑፍ ላይ የተቃጣ ውንብድና ነው።
አስታክኬ የማነሳው፣ አልፍሬድ በሚባል ደራሲ የተሰናዳቸው ‹‹ሕይወት ላንተ ምን ማለት ናት?›› የምትል መጽሐፍ ያቀፈችውን ጥዑም ሃቲት ነው። ‹‹ከግለሰባዊነት ይልቅ፣ በማሕበር መሥራትና ማሰብ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ ጥላ በማጥላቱ ሰው የሕይወት ትርጉም ጠፍቶታል›› ይላል። አዎ! ሰው እንደ ስንዴ ዱቄት በአንድነት ተፈጭቶና ተቦክቶ ወደ ሊጥነት ተሸጋግሯል፤ ቀጥሎ ወደ ዳቦነት። ‹‹ማሃረነ!›› ማለት ይኼኔ ነው። ይኼ ድክመት በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ በጉልህ ይስተዋላል። ሰው፣ በገባው ልክ ሳይሆን የወዳጁን ቃላት በመቃረምና አገባብ በመንጠቅ ሂደት ውስጥ ዕውነቱን ያበጃጃል። ዕውቀቱን፣ ዕውነቱን፣ እንዲሁም ድጋፍና ነቀፌታውን የሚያሸግነው በግለሰባዊነት ልክ ሳይሆን በማሕበር ሥም ነው። በሕብረት ይሸልማል፣ በማሕበር ይረግማል።          
ብሎም፣ ድርሰት እንደ ታቦት ዕቃ ‹‹ካለ ቀሳውስት››፣ ‹‹ጀሌዎች›› በቀር አይነካም። በውስጣችን ለድርሰት የሚውል ግብርና የአምልኮ ስፍራ አበጅተናል። ሌላው ቢቀር አንድ ሰው ስላነበበው መጽሐፍ ሲጠርቀን እንደ ዮጋ አምላኪ ዓይኖቹን ጨፋፍኖ፣ አለያም በግማሽ ከድኖና ድምጹን ዝግ አድርጎ ነው - ኧዲያ! እኔ ግን ድርሰትን ከማምለክ ይልቅ መዳሰስ ይቀናኛል፡፡
በዓሉ ግርማ ‹‹ኦሮማይ›› በተሰኘ ድርሰቱ አንድ ድንቅ ነገር ያወሳል፤ ‹‹አገር የመጠበቅ ኃላፊነት የደኅንነቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሕዝብ ፈንታ ነው›› በማለት። እኔ ደግሞ እንዲህ እላለሁ፣ ሂስ መስጠት የሃያሲው ብቻ ሳይሆን ተደራሲ በተሰማው ልክ ለውይይት ሊዘጋጅ ይገባዋል ባይ ነኝ።    
ባይልልን እንጂ ‹‹ዘራፍ›› የምንሰኘው ሥነ-ጽሑፋዊ ሂስ ዓላማው ማቆለጻጸስ፣ ተራ ሽንገላ፣ ወይም ማንቋሸሽና መወረፍ አይደለም። ሂስ በበኩሉ የሥነ-ጽሑፍ ማሟሻ ነው። ያልተሟሸ ምጣድ ወይም ጀበና እንደማያጣፍጥ እርግጥ ነው። በመሆኑም፣ ሥነ-ጽሑፋዊ ሂስ ለሥነ-ጽሑፍ ሕልውና ጉልህ ሚና አለው።    
ባነሳሁት ሀሳብ ዛቢያ፣ ዓለማየሁ ገላጋይ የሚላት አንድ ነገር አለችው፡- ‹‹ ‹‹የሀዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር ተረታማ ነው›› ከተባለ ቱግ የሚሉ ‹‹አንቆራባጮች›› አሉ፡፡ ‹‹በዓሉ ግርማ ልብወለድ ያድፋፋል፤ አጨራረሱ መሰላቸት የሚታይበት የተካለበ ነው›› ከተባለ የሥራው ‹‹ተሸላሚዎች››፣ ‹‹ሐይማኖት የግል ነው፣ ለምን ይነካብናል›› በማለት ሕገ-መንግሥት መጥቀስ ይዳዳቸዋል፡፡ ‹‹የመንግሥቱ ለማ ግጥሞች ጥብቀትና ፍላት የሌለባቸው በተሃ ናቸው›› ከተባለስ? ጉዳዩን የቤተሰብ ፖለቲካ አድርገው ‹‹አብዬን?›› የሚሉና የዛገ ጦር ከራስጌ የሚመዙ ሞልተዋል፡፡ ‹‹ከበደ ሚካኤል መከሩ፣ ዘከሩ እንጂ አልተቀኙም›› የሚል ካለ፣ ‹‹ባባቶቻችን ደም›› ይዘፈንበታል፡፡ ‹‹ጸጋዬ ገ/መድኅን ግጥም እንጂ ዝርው ያዳግተዋል›› ብሎ በሕይወት መኖር ያዳግታል›› ›› ይላል - ‹‹መለያየት ሞት ነው›› ላይ፡፡
ያክላል ዓሌክስ፤ እንዲህ ሲል፣ ‹‹የእኛ ሥነ-ጽሑፍ መብላላት ሲገባው የሚደነብሸው ለዚህ ሳይሆን ይቀራል?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ በእኛ ዘንድ ክብርና ቦታ የሰጠነው ሁሉ በሌላው ሰው ሲተች ወይም ሲገመገም ዓይናችን ደም፣ ሰውነታችን ቋያ ይለብሳል፤ ያሳክከናል፡፡   
ተመልከቱልኝ እንግዲህ፣ ስለ አንድ ድርሰት ወይም ደራሲ መተንተንና ማውራት ግለሰቡን እንደ ማማት ሊታይ አይገባውም ባይ ነው፡፡ ይኼንን ሀሳብ ገጣሚና መ/ር ዮሐንስ አድማሱ እንደሚጋራውም ዓለማየሁ አክሎ ይተነትናል፤ አሁንም ‹‹መለያየት ሞት ነው›› ላይ፡፡
በእኛ አገር፣ ኪነ-ጥበብ የማሕበር ድርጓችንን የምንገብርበት ጣኦት ሆኗል። ደራሲያን፣ እንዲሁም የኪነ-ጥበብ ውጤት በእሳት ታጥረውና መስመር ተሰምሮላቸው በውስጣችን ባነጽነው ሙዚዬም ውስጥ ተጎልተው መጎብኘት ብቻ በቂያቸው አይደለም፡፡ ለሂስና ለትንታኔ ቢቀርቡ ንቀትም ድፍረትም አይደለም፡፡ የጥበብ ሰዎችን ከሰዋዊ አካላቸው ፈጥርቀን አውጥተን ወደ ሀሳብነት በመመንዘር በሀሳቦቻቸው ዙሪያ መወያየት ተገቢ ነው ባይ ነኝ፡፡  
አለበለዚያ አምልኮ እንዳይሆንብን፡፡ ጥበብ ከመመከለክ ይልክ መዳሰስ ይቀናታል። ይኼንን ትፈቅድማለችም፡፡ የምን መደመም ነው (በእርግጥ በደፈናው ማብጠልጠልም ሆነ ወላ ማሞካሸት መረገም ነው)፤ መፈትሽ እንጂ። ምክንያቱም፣ ኪነ-ጥበባዊ ሂስ ለኪነ-ጥበብ ዕድገት ወሳኝ ነውና፡፡  
የሕዝቡ የጋራ ተፋልሶ ኪነ-ጥበብን ማምለኩ ነው፡፡ ጥበብን የሚያመልክ ደራሲ ወይም አንባቢ ከጥበባዊነት ይልቅ ሰባኪነት ይጠቀልለዋል፡፡ በእኔ ግምት፣ ጥበብን የሚሰብክ ደራሲ ዕውር ነው፡፡ በአጉል ብፁዕነት ታጅሎ ጥበብን ያካልባታል፡፡ ብሎም፣ ጥበብ ‹‹ሕዝቡ ምን ይፈልጋል?›› እያለች ገበያ አታጠናም፡፡ ገበያ ተኮር ጽሑፍ ፍራንክ ለማግበስበስ መማሰንን እንጂ ጥበበኛነትን አያጎናጽፍም፡፡
በዕውነቱ ደራሲ ክብር ይገባዋል። ነገር ግን አምልኮ የሚዳዳው መሆን የለበትም። ምክንያቱም ደራሲ ተዐምረኛ አይደለም፡፡ ዕሳትና ውኃን ፈጥሮ ሲያበቃ ‹‹ጽድቅና ኩነኔውን የመምረጡ ፈንታ ያንተ ነው›› ሊልህ አይችልም። አይገባውምም፡፡ ምክንያቱም፣ የራሱ ዕውነት፣ ዕውቀትና ዓለም የሚባሉ ነገሮች የሉትምና። የደራሲ ዕውነት የሚቀዳው ከማሕበረሰቡ ወራዳ አዋዋልና ባሕሪይ ከተቀደደ የትዝብት ቁራጭ ላይ ነው፡፡ ሽራፊ አዋዋልህን በብዕሩ ሰፍቶ ዝንፉን አኗኗርህን ጠጋግኖ ለራስህ ያቀርባል እንጂ እንደ ፕሮሚቲዬስ ‹‹ከክፉ ልታደግህ ይኼንን ፈጠርኩልህ›› አይልህም፡፡ እናም በደራሲ አትደመም፡፡
ደራሲ ነውርህን ቀባብቶ፣ ግርቢጥ አኗኗርህን ወንፍቶ ወዳንተ እንዲመልስ ጥበብ ታስገድደዋለች፡፡ የዕለት-ተለት ትዝብቱ ዕውቀቱ ነው፤ ብኩንነትህን ይኩለዋል እንጂ እንዳንተ ተፈጣሪ መሆኑን አትዘንጋ። በተቃራኒ ፍላጎትህን አጥንቶ፣ የልብህን መሻት ፈትፍቶ ሲያበቃ ‹‹አለውልህ›› የሚልህ ከሆነ እመነኝ ገንትሮሃል፤ እየተጫወተብህ ነው፡፡
ያው ባይሆንልኝም፣ በአጠቃላይ ሃያሲ የአንድን ጽሑፍ ድክመትና ጥንካሬ ለመተንተን አብዝቶ ከሚማስን ለወደፊቱ የሥነ-ጽሑፍ ዕጣ-ፈንታ ጥቁምታን የሚያበክር ቢሆን ይመረጣል እላለሁ፤ ምክንያቱም፣ ሃያሲ ሸላሚ ወይም ረጋሚ ስላይደለ። እዚህ ላይ ተቻኩላችሁ ‹‹ፋሲካን ያሉ ሕማማትን ተቀበሉ›› ከማለታችሁ በፊት ‹‹ፋሲካን ሊያገኙ ሁዳዴን ይመኙ›› በማለት ለላቀ ሥራ ጥበበኞችን ብታበረታቱ ሸጋ ነው ባይ ነኝ፡፡   
እኔ በበኩሌ፣ ለሥነ-ጽሑፋዊ ሂስ እማልዳለሁ!


Read 1053 times