Saturday, 11 September 2021 00:00

የሳምንቱ ወሬዎች (ከዚህም ከዚያም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የህወሓት አማጺያን በሰሜን ጎንደር ከ120 በላይ  ሰዎች መግደላቸውን ነዋሪዎች  ተናገሩ

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት ወረዳ ጭና በሚባል አካባቢ የህወሓት ታጣቂዎች ከ120 በላይ ንፁሃን ሰዎችን መግደላቸውን ነዋሪዎችና የወረዳው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ግድያው የተፈጸመው አካባቢው በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በቆዩባቸው ቀናት ውስጥ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ በጥቃቱ ሽማግሌዎች፣ ቀሳውስት፣ ሴቶችና ህጻናት መገደላቸውን  ጠቁመዋል፡፡  
የጭና አጎራባች ቀበሌ አብጥራ  ነዋሪ የሆኑት አቶ አስማረ ታፈረ፤ ነሐሴ 12 ቀን 2013 ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ የህወሓት ኃይሎች ወደ  አካባቢው  በመግባት ተኩስ መክፈታቸውንና ውጊያ መካሄዱን ይናገራሉ፡፡  ጦርነቱም እስከ ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ መካሄዱን የሚገልፁት አቶ አስማረ፤ እስካሁን ድረስ ተገድለው የተገኙ 119 ሰዎች በጦርነቱ ያልተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ነዋሪው ይናገራሉ። ከአንድ ቤተሰብ አምስትና ስድስት ሰዎች የሞቱ መኖራቸውንም አቶ አስማረ ገልጸዋል።
ሮይተርስና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎችም፤ በዳባት አካባቢ በምትገኘው ስፍራ በተፈጸመው ጥቃት ከ120 ሰዎች በላይ መገደላቸውን የአካባቢውን ምንጮች ጠቅሰው ዘግበዋል፡፡ የትግራይ የውጭ ግንኙነት ጽህፈት ቤት የተባለው አካል ግን ረቡዕ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ በህወሓት ኃይሎች ተፈጸመ የተባለውን የጅምላ ግድያ ክስን  አስተባብሏል።
የህወሓት ታጣቂዎች ወደ ጭና ሲገቡ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳልደረሰባቸው የገለጹት ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሞላ ውቤ፤ “ጦርነቱ ሲፋፋምና አማጺያኑ መሸነፋቸውን ሲያውቁ አዛውንት፣ ሕጻናት፣ ሴቶች እንዲሁም እንስሳትን እየገደሉ ሄደዋል” ብለዋል።  ከአንድ ቤተሰብ አራት ሰዎችን፣ ቀሳውስትን እንዲሁም ወንድማማቾችንና ነፍሰ ጡር ሴትን  መግደላቸውን አቶ ሞላ  ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አካባቢውን እንደተቆጣጠሩ “እኛ ችግር ያለብን ከመንግሥት ጋር ነው፤ ከእናንተ ጋር አይደለም” በማለት ለነዋሪው ይናገሩ እነደነበር የገለጹት አቶ አስማረ፣ በኋላ ግን ጦርነቱ እየተጧጧፈ ሲመጣ ንፁሃንን ገድለዋል ብለዋል።
የህወሓት ታጣቂዎች ወደ ዳባት ጭና ከመድረሳቸው በፊት፣ አዳርቃይ እንዲሁም ደባርቅ ወረዳ ላይ ከፍተኛ ጥቃት መፈፀማቸውን አስተዳዳሪው ጨምረው ገልፀዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ከህወሓት ኃይሎች ነጻ ከወጣ ከቀናት በኋላ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ንጹሃን የተቀበሩበት የጅምላ መቃብር ማግኘቱን ያስታወቀው የዞኑ አስተዳደር ነው።
በዚህም የህወሓት ኃይሎች በወረዳው ውስጥ “ጭና ተክለ ሐይማኖት በተባለ ቀበሌ ቀሳውስትን ጨምሮ በንጹሃን ሰዎች ላይ ነሐሴ 26 እና 27 የጅምላ ግድያ ፈጽመዋል” በማለት በአንድ መቃብር ብቻ 47 አስከሬኖች እንደተገኙ ገልጿል።
(ቢቢሲ)


==================================================

 ‹የትግራይ ሕዝብ የእኛ ሕዝብ ነው ብለን በፅኑ እናምናለን››


የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለውን ጉዳይ ማወቅ ባይቻልም፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ የእኛ ሕዝብ ነው ብለን እናምናለን›› ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሯ ሰኞ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክተው በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች እየተከናወነ ስላለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ አቅርቦት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ምንም ዓይነት የፌዴራል መንግሥት መዋቅር ባለመኖሩ ፈቃድ የተሰጣቸው ዕርዳታ የሚያቀርቡ መንግሥታዊ ያልሆኑ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለምን ያህሉ ሕዝብ፣ ምን ያህል ዕርዳታ፣ በምን አግባብ እንዳስተላለፉ ሪፖርት እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጎ ከትግራይ ክልል ሲወጣ ለአንድ ወር የሚሆን የዕለት ደራሽ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን፣ በተመሳሳይ የዕርዳታ ድርጅቶችም ለአንድ ወር የሚሆን ተመሳሳይ አቅርቦቶችን ጥለው መውጣታቸውን ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።  
በተጨማሪም ከመንግሥት የተናጠል ተኩስ ማቆም በኋላም እሑድ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የተንቀሳቀሱ 152 የጭነት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 500 ያህል ተሽከርካሪዎች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ፣ እንዲሁም የዕርዳታ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሕወሓት ኃይሎች በተደጋጋሚ በአፋርና በአማራ ክልሎች ላይ ባደረጉት ወረራና በንፁኃን ዜጎች ላይ እያደረሱ ባለው ጥቃት ምክንያት፣ እንዲሁም በዕርዳታ መተላለፊያ መስመሮች ላይ በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ተጨማሪ ዕርዳታ የማድረስ ሒደቱን ውስብስብ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የዕለት ደራሽ የዕርዳታ ምግብ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል የገቡ ተሽከርካሪዎች መመለስ ሲኖርባቸው፣ 72 በመቶ የሚሆኑት አለመመለሳቸውን ወ/ሮ ሙፈሪያት አስታውቀዋል፡፡
‹‹ተሽከርካሪዎች ለተፈቀደላቸው ሥራ ብቻ መዋላቸውን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጎ ከወጣ በኋላ የክልሉ ሕዝብ በመጪዎቹ ዓመታት በተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንዳይገባ በማሰብ፣ የግብርና ግብዓት ሲያደርስ መቆየቱን በመጥቀስ፣ የመንግሥት ፍላጎትና ጥረት ሕዝቡ እንዳይጎዳ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
‹‹በመሆኑም አምርቶ የሚመገብ ማኅበረሰብ መኖር እንዳለበት ስለምናምንና ሥራችን እሱን መሠረት ካላደረገ፣ ችግሩ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊትም በክልሉ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የምግብ ዋስትና ችግር እንደነበረበት በመጥቀስ፣ ‹‹ከአንበጣ ወረርሽኝ ጋር ተዳምሮ ሕወሓት በራሱ ጊዜ ፈልጎ በከፈተው ጦርነት ለሕዝቡ ያተረፈው ቀውስ እንዳይቀጥል ስለምንፈልግ፣ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰድን ነው፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከክልሉ ሲወጣ በመጋዘኖች ያከማቻቸውን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና አሁን እየተላከ ያለውን አቅርቦት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ፣ አሁን በአንዳንዶች የሚወሳው ረሃብና ሞት የማስከተል ዕድሉ ትንሽ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ነገር ግን በትግራይ ክልል ረሃብ ወይም ሞት ተከሰተ ቢባል እንኳ በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከሰሞኑ እየተሰማ ያለው ሰፊ የሆነ ለጦርነት የሚሆን የስንቅ ዝግጅት፣ ከሚባለው እውነት ጋር የተራራቀ ነው ሲሉ ወ/ሮ ሙፈሪያት አስረድተዋል፡፡
በሕወሓት ወረራ ምክንያት በአማራና በአፋር ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 500 ሺሕ የደረሰ መሆኑን፣ በአማራ ክልል ለ150 ሺሕ ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ  መቻሉን ሚኒስትሯ አክለው ተናግረዋል፡፡
በአፋርና በአማራ ክልሎች ሕወሓት በፈጸመው ጥቃት 4.5 ሚሊዮን ዜጎች ለጉዳት መዳረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡
(ሪፖርተር)

============================================

“ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታል ማውደም በጦር ወንጀልኝነት መታየት አለበት”

  የህወሓት ቡድን “ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ላይ እያደረሰ ያለው ውድመት እጅግ አስነዋሪና በጦር ወንጀለኝነት መታየት ያለበት ድርጊት ነው” ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ተናገረ፡፡
 “ማን ከማን ጋር እንኳ እንደተጋጨ የማያውቁ ህጻናትን ትምህርት ቤት ማውደም በምን ይገለጻል?” በማለት በምሬት ጠይቋል፤አትሌት ሃይሌ፡፡
 አትሌቱ በአማራ ክልል በዋግ ኸምራ ዞን ፃግብጂ ወረዳ በዳስ ጥላ ለሚማሩ ህጻናት ያስገነባው ትምህርት ቤት በመውደሙ እጅግ እንዳዘነም ነው የገለጸው፡፡  ትምህርት ቤቱን ለመገንባት ከገንዘብ ወጪ በላይ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈ የገለጸው አትሌቱ፤ የትምህርት ቤቱ መውደም በአካባቢው ማህበረሰብ ቁስል ላይ እንጨት እንደ መስደድ ይቆጠራል ብሏል፡፡
 አትሌቱ ያስገነባውን ጨምሮ በአካባቢው በርካታ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች መውደማቸውን ጠቅሶ፤ ይህም የቡድኑን “የክፋት ጥግ ያሳያል” በማለት አስረድቷል፡፡
 በየትኛውም ዓለም በሚካሄዱ ጦርነቶች ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎችን ዒላማ ማድረግ በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ መሆኑንም አትሌት ሻለቃ ሃይለ ገብረስላሴ መናገሩን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 ትምህርት ቤቱም ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ህጻናት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ (ኤፍቢሲ)


=============================================

ሳዑዲ አረቢያ ማቆያዎች ውስጥ ያሉ 60 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ እስከ 3 ወራት ጊዜ ያስፈልጋል ተባለ


በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ማቆያዎች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ 60 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከሁለት እስከ ሶስት ወራት እንደሚወስድ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ። ስደተኞቹን በአጠረ ጊዜ ወደ ሀገር ቤት መመለስ ያልተቻለው፤ ለተመላሾች የተዘጋጁት ጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች ባላቸው “ውስን አቅም ምክንያት ነው” ተብሏል።
በሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አምባዬ ወልዴ፤ በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ በሚገኙ የማቆያ ካምፖች ውስጥ 60 ሺህ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ወደ ስፍራው በተጓዘ አጣሪ ቡድን ጭምር መረጋገጡን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የአጣሪ ቡድኑ አባላት ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና ከኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የተውጣጡ ናቸው ብለዋል።  
 “[ይህ ቁጥር] በእኛ በኩል በተላከው አጣሪ ቡድን የተረጋገጠ ነው። ከዚያም በላይ ዜጎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል” የሚሉት አቶ አምባዬ፤ ቡድኑ የለያቸውን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ስራ በመከናወን ላይ እንዳለ ጠቁመዋል። ነሐሴ 12 ቀን 2013 በተጀመረው ሁለተኛ ዙር የስደተኞች የመጓጓዝ ሂደት፤ እስካሁን ድረስ አራት ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን መመለሳቸውን አስታውቀዋል። ስደተኞችን ወደ አገር ውስጥ በመመለሱ ሂደት ውስጥም ለሴቶችና ህጸናት ቅድሚያ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በሳምንት ሶስት ጊዜ በሚደረጉ በረራዎች፤ በእያንዳንዱ ጊዜ ከ250 እስከ 400 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ቢሆንም፤ አጠቃላይ ሂደቱ ከሁለት እስከ ሶስት ወራት እንደሚወስድ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መመለስ የማይቻለው፤ ለእነርሱ የተዘጋጁት ጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች ያላቸው የማስተናገድ አቅም ውስን በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ አቶ አምባዬ አብራርተዋል።
ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያንን እያስተናገዱ የሚገኙ ጊዜያዊ ማቆያዎች በቁጥር ዘጠኝ ሲሆኑ፤ ሁሉም የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ወደ እነዚህ ማቆያ ቦታዎች ውስጥ የሚገቡ ስደተኞች ለአንድ ቀን እንዲቆዩ ከተደረጉ በኋላ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እንደሚሸኙ አቶ አምባዬ ገልጸዋል።
 ረቡዕ ጳጉሜ 3፤ 137 ህጻናትን ጨምሮ 454 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በትግራይ ክልል ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ከሁለት ሺህ በላይ የክልሉ ተወላጅ ስደተኞች በጊዜያዊ ማቆያዎች ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉንም አመልክተዋል። ተመላሾቹ በማቆያዎቹ ውስጥ እንዲሰነብቱ የተደረገው ወደ ክልሉ ለመሄድ የሚያስችል ትራንስፖርት ባለመኖሩ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ። ህወሓት “ወጣቱን እያስገደደ፣ እያፈሰ ወደ ጦርነት እየማገደ ነው” ሲሉ የሚወነጅሉት ኃላፊው፤ ይህ ሁኔታም ከስደት ተመላሾቹ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እንዳይሄዱ ተጨማሪ ምክንያት ነው ይላሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሰላም ሚኒስቴር በሐምሌ ወር በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ከሳዑዲ አረቢያ ከተመለሱ ከ40 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንድ ሶስተኛ ገደማ የሚሆኑት የትግራይ ክልል ተወላጆች መሆናቸውን አስታውቀው ነበር። ከእነርሱ ውስጥ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከጊዜያዊ ማቆያ መውጣታቸው በወቅቱ ተገልጿል።
 (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


Read 9985 times