Saturday, 11 September 2021 00:00

በክረምቱ ከ6 መቶ ሺህ በላይ ዜጎች በጎርፍ አደጋ ተጎድተዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 28 ሰዎች በጎርፍ ህይወታቸው አልፏል
- ከ23  ሺህ በላይ ከብቶች  ሞተዋል

እየተገባደደ ባለው የክረምት ወራት በሃገሪቱ እስካሁን ከ6 መቶ ሺህ በላይ ዜጎቹ ጉዳት ሲደርስባቸው፤ ከ2 መቶ በላይ የሚሆኑት  ከቀዬአቸው  መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ  ድጋፍ ማስተባበሪያ  ጽ/ቤት ሪፖርት ያመለክታል።
በ2012 ክረምት ወቅት በአፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልል ባጋጠሙ የጎርፍ አደጋዎች  616 ሺህ 714 ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ 214 ሺህ 127 የሚሆኑት ተፈናቅለዋል እንዲሁም የ28 ሰዎች ህይወት አልፏል።
የክረምቱ የጎርፍ አደጋ እንስሳትና ሰብል ምርቶች ላይም ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በአጠቃላይ 23 ሺህ 788 የቤት እንስሳት በጎርፍ ተወስደዋል፣ በ18 ሺህ 97 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ወድሟል። እንዲሁም  464 መኖሪያ ቤቶች እና 6 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ  ወድመዋል።
በጎርፍ አደጋው በእጅጉ ከተጠቁት አካባቢዎች መካከልም በሶማሌ ክልል የሸበሌ  ዶሎ፣ ጃራር፣ አፍዴር፣ ፋፈን፣ ቆራሄ፣ በደቡብ ክልል ደግሞ በወላይታ፣ ሃላባ፣ ጎፋ እና ከፋ ዞኖች ጉዳቱ ያጋጠመ ሲሆን በአፋር ክልል ዞን 2፣3 እና 4 ፤ በኦሮሚያ ክልል አርሲ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምዕራብ ሃረርጌ፣  የምዕራብ ሸዋ ዞን፤ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ እና መካከለኛው ጎንደር ዞኖች ፣ በሃረር ክልል ሶፊያ ዞን እንዲሁም በጋምቤላ ክልል ላሬ  ወረዳ  የጎርፍ  አደጋዎቹን ያስተናገዱ ናቸው።
የክረምቱ ወቅት አሁንም ቀጣይነት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቀጣይም የጎርፍ አደጋዎቹ በእነዚህና በሌሎች አካባቢዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ የተባለ ሲሆን ህብረተሰቡ አሁንም ጥንቃቄ አይለየው ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ከሶስት ሳምንታት በፊት ባጋጠመው ጎርፍ አደጋ የ8 ሰዎች ህይወት ማለፉ አይዘነጋም።
አስቀድሞ በተሰራው የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ ቅድመ ግምት፤ በክረምቱ እስከ 2 ሚሊዮን ዜጎች የጎርፍ ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብሎ ነበር።

Read 9357 times