Sunday, 12 September 2021 20:36

በዓመቱ ያጣናቸው ታላላቅ ሰዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

https://youtu.be/GonjDf73WXY

የተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም ለአገራችን እጅግ ፈታኝ ዘመን ነበር። ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት ያልቻሉበት፣ በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን በሞት የተነጠቅንበት፣ በተፈጥሮአዊ አደጋዎች፣ በጎርፍ፣ በመሬት መንሸራተትና መሰል አደጋዎች በርካቶች ለእልፈት ህይወታቸውን ያጡበት ጊዜም ነበር። በዓመቱ በኮቪድ ወረርሽኝና በተለያዩ ህመሞች በሞት ካጣናቸው ታዋቂ ኢትዮጵያውያን መካከል ጥቂቶቹን እናስታውሳቸው።
የኮሮና ወረርሽኝ በ2013 ዓ.ም ካሳጣን ታላላቅ ሰዎች መካከል ቀዳሚው ታዋቂው ምሁር፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛው ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ናቸው። ፕሮፌሰር መስፍን በኮሮና ሳቢያ ሕክምናቸውን ሲከታተሉበት በነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ በ90 ዓመታቸው ህይወታቸው ያለፈው መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር። ሌላው ኮቪድ-19 ያሳጣን ታላቅ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰን ነው። እኚህ ታላቅ ምሁር፣ የቲአትርና የፊልም ተዋናይ፣ ደራሲና ተርጓሚ ተስፋዬ ገሰሰ፤ በኮሮና ሳቢያ በ84 ዓመታቸው በሞት የተለዩን ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር።
ይህ ክፉ ወረርሽኝ ባሳለፍነው ዓመት ያሳጣን ሌላው ዕውቅ ምሁር የዓለም ሎሬት ዶ/ር ጥበበ የማነብርሃን ናቸው።
በህክምና ሙያ፣ በዕርዳታ  አስተባባሪነት፣ በእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባልነትና በአገር ሽማግሌነት አገራቸውን ያገለገሉት እኚህ ታላቅ ባለሙያ በኮሮና ሳቢያ በሞት የተለዩን በያዝነው ዓመት፣ የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር። ኮቪድ በተጠናቀቀው ዓመት በበጎ ተግባር ላይ ተሰማርተው ሺዎችን የታደጉ የበጎ ተግባር አርአያዎቻችንንም አሳጥቶናል።
በኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት (ኦቲዝም) ያለባቸውን ህጻናት ህይወት በመለወጥ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከቱትና የጆይ ኦቲዝም ማዕከል ሴንተር መስራቿ ወ/ሮ ዘሚ የኑስም ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ህይወታቸው ያለፈው በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ነበር።
ኢትዮጵያዊቷ “ማዘር” ትሬዛ የሚል ስያሜ የሚታወቁት የተሰጣቸውና የሺዎች እናትና አሳዳጊ የነበሩት የክቡር ዶ/ር አበበች ጎበናም ኮቪድ-19 ለህልፈት ዳርጓቸዋል። ልጆቻቸው እዳዬ በሚል  የፍቅር ስም የሚጠሩትና በ10ሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መጠጊያ በመሆን ሺዎችን ያሳደጉት ወ/ሮ አበበች፤  ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም  በሞት ተለይተውናል።
ኮቪድ ወደ ኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ጎራ ብሎም ተወዳጁን የፊልም ደራሲ፣ ተዋናይና አዘጋጅ አርቲስት መስፍን ጌታቸውንም ለሞት ዳርጎታል። “ሰው ለሰው” የተሰኘው የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ ደራሲና ተዋናይ የነበረው መስፍን ጌታቸው፤ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም  በቫይረሱ ሳቢያ ህይወቱ አልፏል።
ዘመኑ የኪነ-ጥበቡን ዘር በሞት ደጋግሞ የጎበኘበትም ነበር። አንጋፋው ሰዓሊ ለማጉያ፣  ተወዳጅ ተዋናይት አልማዝ ኃይሌ (ማሚ)፣ አንጋፋው የማንዶሊን ንጉስ አየለ ማሞ፣ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ቀደምት ከሚባሉት የሙዚቃ አሳታሚዎች፣ አንዱ የነበረው አሊ አብደላ ኬያፍ (አሊታንጎ) በሞት የተለዩን በዚሁ በተጠናቀቀው ዓመት ነበር።
በደርግ ስርዓት ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩት ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስን ነበር። የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ኮሚሽነር አበረ አዳሙም በሞት የተለዩት በተጠናቀቀው ዓመት ነበር። የመጀመሪያዋ ሴት የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሕሌኒ መኩሪያም በሞት የተለየችን በዚሁ በ2013 ዓ.ም ነው።
ዓመቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ሲቀረው በድንገተኛ የልብ ህመም በሞት ያጣነው ደግሞ ተወዳጁና አንጋፋው ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ ነው። ድምጻዊው ቀብር  ስነ-ስርዓቱ የተፈጸመው ባለፈው ማክሰኞ ጳጉሜ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር። ለሁሉም ፈጣሪ ነፍሳቸውን በመንግስተ ሰማያት ያኑርልን!!


Read 10411 times