Sunday, 12 September 2021 21:08

ሰው፣ ከሁሉም በላይ፣ መንፈሳዊ ፍጥረት ይሆን እንዴ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 አንዳንዱ ሰው፣ ምንም ትርፍ ላያገኝበት፣ ከሞባይል ጌም ጋር እልህ ይያያዛል። ልላው ደግሞ፣ የስፖርት ሊጎችን እንደሱስ ይከታተላል። በድርሰትና በድራማ መመሰጥስ? ለዓመት በዓል ጠብ እርግፍ ማለትስ? ምን ትርፍ ያመጣለታል?
ሰው በአካልና በእንጀራ ብቻ አይኖርም። መንፈሳዊም ነው - ሰው ማለት። የስፖርት ውድድር፣ ልብወለድ ድርሰት፣ የዓመት በዓል ድግስ፣ … ከዚህ የሰው መንፈሳዊ ተፈጥሮ የሚመነጩ ናቸው።


  አየ ሰው! መቶ ዓመት ላይኖር፣ ለ10 እና ለ15 ዓመት አሻግሮ፣ ከዓመት ዓመት ይማራል።
የሰው ነገር! ዛሬ ይሙት ነገ ሳያረጋግጥ፣ …. ለከርሞው ያርሳል።
ከዛሬ ገቢው ቆጥቦ፣ ከዛሬ ፍጆታውና ከወር አስቤዛው ቀንሶ፣ ለመጪዎቹ ዓመታት ኢንቨስት ያደርጋል። ግንባታው ብቻ፣ 5 እና 10 ዓመት እንደሚወስድበት አይጠፋውም። የኢንቨስትመንት ወጪውን ለመመለስ 15 እና 20 ዓመት እንደሚፈጅበትም ያውቃል። ቢሆንም ይገባበታል።
ወጪውን እስኪመልስ ድረስ በሕይወት ከቆየ፣  ትርፉን ለመዝናኛ፣ ገንዘቡን ለፍጆታ እንደ ልብ እየዘገነ፣ “ዓለሙን የሚቀጭ” ይመስለናል። ሰው “ሞኝ” ነው። ትርፉን ቆጥቦ፣ እንደገና ወደፊት በሌላ የ30 ዓመት ኢንቨስትመንት ላይ ለማዋል ተስፋ ያደርጋል። ዘላለም የሚኖር ነው የሚመስለው - አኗኗሩ።
እንዲያም ሆኖ፣… ትምህርቱ፣ እርሻው፣ ኢንቨስትመንቱ፣… ለኑሮ የሚበጅ ትርፍ ይኖረዋል።ነገር ግን፣ ምንም ትርፍ የሌላቸው ነገሮች አሉ።
“ሞባይል ጌም” አስገራሚ ነገር ነው። የብዙ ሰዎች “የሞባይል ጌም” ትጋት ሲታይ፣ ዋና የኑሮ መተዳደሪያ ይመስላል። “ሌቭል 23” ደርሻለሁ እያሉ ይደሰታሉ፤ ጨዋታውን በአዲስ ስሜት ይቀጥላሉ። “ሲፎርሹም”፣ እጃቸውን አይሰጡም። በእልህ ስሜት ተጠምደው፣ ጨዋታውን ወጥረው ይይዛሉ። ለምን? ጥያቄው ከባድ ነው፡፡ በቀላሉ መልስ ለመስጠት ያስቸግራል።
ለነገሩ፣ የስፖርት ውድድሮችን እንደሱስ መከታተልስ ለምን? እህል ውሃ እንደማይሆንለት እያወቀ፣ ለአትሌቲክስና ለኦሎምፒክ፣ ለፕሪሜር ሊግና ለሻምፒዮንስ ሊግ፣ ልቡን ይሰጣል። ምኔ ናቸው ሊል ነው?
ለአገር ውስጥ እግርኳስ ሳይቀር፣ ዋጋ ከፍሎ፣ ለፀሐይና ለዝናብ ሳይሸነፍ፣ ስታዲዬም ለመግባት ወረፋ ይሰለፋል። ምን አትርፎ ሊወጣ? ከወጪ ቀሪ የለውም። ወጪ ብቻ ነው። “እንዴ! እስከዛሬ ድረስ ተሸውጃለሁ” ብለው፣ ከእግር ኳስ ጋር የሚሰነባበቱ ሰዎች ይኖራሉ?  አይኖሩም። ስታዲዮሞች ኦና እንዳይቀሩ አትስጉ።
“ትርፍ “ ባይኖረውም ወደ እግር ኳስ የሚጎርፍ ሰው አይቀንስም።  ለዚያውም፣ ጊዜ ሰጥቶ ዋጋ ከፍሎ።
መፅሐፍ ማንበብ የሚሉት አስገራሚ ነገር ደግሞ አለ።
ለእለት ስራና ለመተዳደሪያ ሙያ የሚጠቅሙ መፃህፍትን ብቻ እየመረጡ ማንበብ አንድ ነገር ነው። አብዛኞቹ መፃህፍት ግን፣ የስራና የሙያ አይደሉም። አዳሜ፣ ያንንም ያንንም እየጻፈ ያሳትማል። ገምነብ ከፍሎ የሚገዛም አለ፡፡ ምን ይሄ ብቻ?
ልፋ ቢለው፤
ከሺህ ዓመታት በፊት የተጻፉ፣ የሩቅ ዘመንና የሩቅ አገር ትረካዎችን፣ ገለፃዎችን፣ ሐተታዎችንና ስብከቶችን፣ ስራዬ ብሎ ያነብባል፤ በቁም ነገር፣ የራሴ ጉዳይ ብሎ ያዳምጣል።
ከእልፍ አመታት በፊት፣ አይቶት በማያውቀው የባሕር ማዶ አገር፣ ሰምቶት በማያውቀው ሌላ ቋንቋ የተፃፈ ጉዳይ፣ …. በብዙ ፍለጋ፣ በውሰት ውሰት፣ በብዙ ድካም ተተርጉሞ፣ በብዙ ወጪ ታትሞ፣ ሰዎች ሲያነብቡትና ሲያጠኑት፣ አይገርምም? ለዛሬው ሕይወቱና ለግል ኑሮው፣ ምን ጠብ ይልለታል?
ሰው እና ተግባሩ፣ ሰውና አኳሃኑ ያስገርማል።  የወጪ ቀሪ የሌላቸው፣ ምክንያት የማይገኝላቸው፣ ግን ደግሞ በጣም የተለመዱና “ኖርማል” የሚመስሉ ነገሮች ብዙ ናቸው። ሰዎች፣ ከሌላው ቀን አስበልጠው፣ የበዓል ቀን ያከብራሉ - በብዙ ወጪ።
“የፀረ ወባ ቀን”፣ “የእጅ መታጠብ ቀን” የተሰኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚፈለፍላቸው የበዓል ዓይነቶችን መቁጠር ያስቸግራል። በእርግጥ፣ እጅ መታጠብና ፀረ ወባ ተግባራት፣ “ትርፍ” ያመጣሉ ማለት ይቻላል። ለጤንነት ይጠቅማሉ። ችግሩ ምንድን ነው? ትርፍ ካላቸው፣ የእለት ተግባር ይሆኑና፣ በዓል መሆናቸው ይቀራል።
እውነተኛ በዓላት ግን፣”ትርፍ” የላቸውም። እንዲያውም፤ እጥፍ ድርብ ወጪ፤ የበዓላት ልዩ ባሕርይ ነው።  የአዲስ ዓመት በዓል፣የልደት ቀን፣ የጋብቻ ቀን፣ የምረቃ ቀን፣ የመታሰቢያ ቀን፣ የእረፍት ቀን እያሉ በልዩ ስሜት ያከብራሉ። ሌላው ቀርቶ፣ ከበርካታ ዓመታት በፊት ለሞተ ሰውም፣ በአክብሮት፣ በአድናቆትና በፍቅር፣ መታሰቢያ በዓል ይደግሳሉ። የሰው መንፈስ አይሞትም ለማለት ይሆን?
ኧረ፤ የሰዎች ነገር፤ ግራ ያጋባል። ብዙ ሰዎች፣ ውለታ ሳይቆጥሩ፣ ክፍያ ሳይጠይቁ፣ ስጦታ ያበረክታሉ። ለጎበዝ ተማሪ ድጋፍ ይሰጣሉ። የሚተጋ ወጣት ሲያዩ ያግዛሉ። የተቸገረ ሰው ሲገጥማቸው ይረዳሉ - የማያውቁት ሰው ቢሆንም። የሰው ጉዳት ሲያዩ ያዝናሉ- ከዚያ በፊት ያላዩት እንግዳ  ሰው ቢሆንም።
ይሄ ሁሉ ለምን ተብለው ቢጠየቁ ምን ብለው እንደሚመልሱ እንጃ። ሌላ ነገር ላይ ኮ፤ ከወጪ ቀሪ ሂሳብ ሰርተው አወራርደው፤ አወዳድረው ምክንያታቸውን ይናገራሉ። መልስ ይሰጣሉ።
ከስሌትና ከሂሳብ፣ ወደ መርህና ወደ ሃሳብ፣ ከዚያ ወደ መንፈስና ስብዕና።
እቃ ሲገዙ፣ ዋጋውንና ጥቅሙን ያሰላሉ። ለምን ሁልጊዜ እንደዚያ አያሰላስሉም? ባታልለው፣ ባጭበረብረው፣ ብሰርቀው፣ ብነጥቀው፣ ብመነትፈው፣ ብዘርፈው፣ ብደበድበው፣ ብገድለው፣ …. ያንን ገቢ አገኛለሁ፣ ያንን ወጪ አስቀራለሁ፣ ያንንና ያንን እጠቀማለሁ እያሉ፣ ለምን ኦዲት አይሰሩም?
ከነቃብኝ፣ ከደረሰብኝ፣ ካስጣለኝ፣ ከመከተኝ፣ ካሸነፈኝ፣ ከጣለኝ፣ በፖሊስ ካስያዘኝ፣ ለፍርድ ቤት ከከሰሰኝ፣ በማስረጃ ካስቀጣኝ…. ጉዳትና ኪሳራውን፣ ይሄኛውና ያኛውን እያነፃፀሩ፣ እየደመሩና እየቀነሱ ለምን ስሌት አይሰሩም?
እንደዚህ አይነት ስሌት ውስጥ የማይገቡ ሰዎች አሉ። እናስ ምን ያደርጋሉ? እውነትና ሐሰት፣ መልካምና ክፉ፣ ኃጥያትና ፅድቅ፣ ሕጋዊና ሕገወጥ፣ ጨዋና ስርዓት አልበኛ፣ ሰላማዊና ሞገደኛ፣ ንፁሕና ወንጀለኛ…. በማለት ይዳኛሉ።
መዋሸት፣ ለዛሬ ጠቃሚ ቢሆንስ? ሰዎች ቢያምኑኝና ጥቅም ባገኝበትስ? መሸፈጥ፣ ለዚህ ጉዳይ ጉዳይ ብቻ የሚያዋጣ ቢሆንልኝስ? በማለት አይቆምሩም። ሸፍጥና ዝርፊያ፣ ድብደባና ግድያ፣ …. ጨርሶ መታሰብ የማይገባቸው ወራዳ የክፋት መንገዶች ናቸው ብለው ዘግተውባቸዋል።  እያንዳንዱ የውሸትና የሸፍጥ አጋጣሚ እየተመዘዘ፣ በነጠላ በነጠላ፣ ጥቅሙና ጉዳቱ እዚያው በዚያው ይመዘን፣ እጅ በእጅ ይቆጠር፣ ብለው ስሌት አይሰሩም።
ለምን?
በጊዜና በቦታ፣ በጉዳይና በባለ ጉዳይ፤ በእድሜና በስም፣ በፆታና በትውልድ ሐረግ ያልታጠሩ፣ …. ዘላለማዊና ሁለገብ፣ ሁለንተናዊና ሁሉንም ሰው የሚያካትቱ፣ ትክክለኛ መርሆችን መያዝ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው።  በእርግጥ የሃሳብና የተግባር መርህን፣ አንዳንዴ ከእምነትና ከትዕዛዛት ጋር፣ ወይም ከባሕልና ከልማድ ጋርም ያዛምዱታል፤ አንዳንዶቹም ያምታቱታል።
ቢሆንም፤ ቢምታታም ቢስማማም፤ ያለ መርህ አይሆንላቸውም። መሰረታቸውን እውነት ላይ አፅንተው፤ የቅርብና የሩቅ መልካም  አላማን አጥርተውና  አጉልተው፤ መንገዱንም አቃንተውና በብርሃን አድምቀው የሚያሳዩ ትክክለኛ መርሆችን ይሻሉ፣ የጥበብና የብቃት፣ የብርታትና የፅናት ማንነትን የሚገነቡ፣ ነፃነትን ከግል ሃላፊነት ጋር፤ ፍቅርን ከፍትህ ጋር ያጣመሩ  ትክክለኛ መርሆችን በእጅጉ ይፈልጋሉ፡፡
እነዚህን የሥነ-ምግባርና የሕግ መርሆችን ካልያዙ በቀር፣ የሕልውና ትርጉም አይታያቸውም፤ ወይም ይፈርስባቸዋል። የሕይወት ጣዕም አይሰማቸው፤ ወይም ይጎመዝዛቸዋል። የግል ማንነትና ሰብዕና አይያዝላቸውም፤ ወይም እንደ ቅዠት ይጠፋባቸዋል፤ ወይም ቆሻሻ ውስጥ እየተንከባለሉ ለመኖር የመረጡ ያህል አስቀያሚ ውርደት ይሆንባቸዋል።
በሌላ አነጋገር፣ ሰው በስሌት ብቻ አይኖርም- በመርህ (በቀመር) ጭምር እንጂ። መርህና ስሌት ሲዋሃዱ ነው መንገዱ የሚቃናው።
እንዲህም ሆኖ፣ ሰው በመርህና በስሌት ብቻ አይኖርም። ለእያንዳንዱ ነገር፣ ተጨማሪ ትርጉም  የመስጠት ተፈጥሮ (መንፈስ) አለው ሰው ሲባል። አስቡት።
ልብስ ስንሰራ ወይም ስንገዛ፣ ብርድና ሐሩርን የሚከላከል፣ ለእንቅስቃሴ የሚመችና ለሰውነት የሚስማማ፣ ለስፌትና ለእጥበት የማያስቸግር መሆኑን ብናሰላ፣ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ዋጋውንና የአገልግሎት ጊዜውን ብንለካ፣ ትክክል አስበናል። የጨርቁን ቀለም ከነማላበሻው ለማስማማት፣ የስፌቱን ጥንካሬና ልክ ብቻ ሳይሆን ቅርፁን ከነማስጌጫው ለማቆንጀት መፈለጋችን ለምን?
የምግብ አይነትና ብዛትን ማመዛዘን ብቻ ሳይሆን የአቀራረብና የአመጋገብ ስርዓቱን ለማስዋብ፣ የምግብ ንጥረነገሩን ብቻ ሳይሆን ጣዕሙንና መልኩን ለማሳመር ሁሉ ማሰብስ ለምን አስፈለገ?
ትርጉም አለው- መንፈሳዊ ትርጉም፡፡
በቤት ያዘጋጁትና አሳምረው ያሰናዱት ምሳ፣ ወይም ከሐይቅ ዳርቻ ጨረቃዋን ከማዶ ሸማውም ከዳር በርቶ ለጥንዶች ቀረበ እራት… እኩል ትርጉም የላቸውም። ያለቀውን ዱቄት አራግፈው፣ የተሟጠጠውን ቅባት ነቅንቀው፣ የጎደለውን ከጎረቤት ተበድረው የሰሩት ምግብ ሲጎርሱስ ትርጉሙ አንድ ነው? ለክብር ያህል ብሉ ሌበል ከፍተው ሲቀዱና፣ አዩኝ አላዩኝ ብለው ጭላጭ ሲቸለልሱ አንድ ነው? አይደለም? የምግብ የመጠጡ አይነትና መጠን እኩል ቢሆን እንኳ፣ ትርጉሙ ይለያያል፡፡ የፕሮቲን እና የአልኮል መጠኑን በመቶኛ ማስላት ይቻላል፡፡ ከጤንነት እና ከስካር ጋር በመርህ ማዛመድ፣ ጥሩና መጥፎ ብሎ መፈረጅም ይቻላል፡፡ ነገር ግን፣ ከስሌትም ከመርህም በተጨማሪ፣ የትርጉምና የመንፈስ፣ የክብርና የማንነት ጉዳይም አለው።
ሰው በአካልና በእንጀራ ብቻ አይኖርማ። መንፈሳዊም ነው - ሰው ማለት። የስፖርት ውድድር፣ ልብወለድ ድርሰት፣ የዓመት በዓል ድግስ፣ … ከዚህ የሰው መንፈሳዊ ተፈጥሮ የሚመነጩ ናቸው።
የምናብ ፈጠራ ቢሆኑም።
የስፖርት ውድድሮች፣ የዓለም መግባቢያ መሆናቸው አይገርምም። ይሁኑ ግድ የለም። ቅንጣት ትርፍ አለመስጠታቸው፤ ከእለት ኑሮ ጋር አለመዛመዳቸው ግን ይገርማል። በአትሌቲክስና በኦሎምፒክ፣ በእግር ኳስና በሻምፒዮንስ ሊግ፣ … የሰው ብቃትን በእውን በገሃድ እያየ ይዝናናል - አዳሜ። እስካልበዛና ልክ እስካላጣ ድረስ፣ ጥሩ ነው። የሰው ልጅን የሚያከብርና ብቃቱን አድምቆ የሚያሳይ ጨዋታ፣ የመልካም መንፈስ ገፅታ ነው። የሞባይል ጌምም መጥፎ አይደለም- ከተመጠነ።
ገበያ መሃል፣ በሰዎች መሃል፣” የመሰናክል ብቃት” ለማሳየት የሚሞክር ሾፌርን ደግሞ አስቡበት፡፡ ጦርነትን እንደ ጌም የሚያሳይም አለ፡፡ ከዚያስ የሞባይል ጌም ይሻላል፡፡ የስፖርት ውድድሮች ደግሞ በጣም ይሻላሉ።
ድርሰቶች፣ ድራማዎች፣ ፊልሞች ደግሞ የባሰባቸው ናቸው። ቁርስና እራት አይሆኑም። አንዱንም መሆን አይችሉም እንጂ። ወቅታዊ የገበያ፣ የጨረታ፣ ክፍት የስራ ቦታ መረጃዎችን አናገኝባቸውም። ከተማው አገሩ አማን ነው? ሽፍታና ወሮበላ ያሰጋል? ፖሊስና ፍ/ቤት ያስተማምናል? እንዲህ አይነት ለእለት እንቅስቃሴ የሚጠቅሙ መረጃዎችንም አይሰጡንም-ልብወለዶች፡፡ ለሙያ እውቀትና ለስልጠናም አያገለግሉም።
እህስ? መልካምና ክፉ ሰዎችን፣ አላማና ፈተናቸውን፣ ጥቃትና መከራቸውን፣ ውድቀትና ስኬታቸውን በምናብ እየፈጠሩ፣ በእውን ያልተከሰተውን እየተረኩ፣ በሃዘንና በደስታ ስሜት እያስዋኙ፣… ልብ አንጠልጥለው፣ በገሃድ የሌለ አለም ውስጥ ያሰምጣሉ። በክፉ ሰው እንናደዳለን - ክፋቱ እንዲታወቅበት እንዲነቁበት እንመኛለን። የእጁን እንዲያገኝ ዳኝነት እንሰጣለን።
ለአሪፍና ለጀግና ሰዎች ደግሞ ጥሩ ጥሩ እንዲሳካላቸው፣ እንዲበረቱ፣ከአደጋ እንዲያመልጡና እንዲያሸንፉ እንመኛለን። ትንፋሽ እስኪያጥረን ድረስ እንጨነቅላቸዋለን። ተቆርቋሪና አድናቂ እንሆናለን።
በእውን የሌሉ፣ የምናብ ፈጠራ እንደሆኑ ጠፍቶን ነው? አሳምረን እናውቃለን። እንዲያውም፤ ልብወለድ ፈጠራ መሆናቸውን አረጋግጠን ነው የምንመሰጥባቸው። የሰው ተፈጥሮ ነው። የመልካም መንፈስ ገፅታ ነው።  ትርፍ የሌለው፣ጭፍን ጥላቻ፣ የሐሰት ውንጀላ፣ ሐሜት፣ ፋታ የለሽ ብሽሽቅ ደግሞ አለ። ይህ የክፉ መንፈስ ገፅታ ነው።
ይሄም፣ የሰዎች ልዩ ባህርይ ነው። ለክፉ መንፈስ ይልቅ መልካም መንፈስ መምረጥ የእያንዳንዱ ሰው ፈንታ ነው፡፡ ወይ በጭፍን ጥላቻ የጎረቤትና የቢሮ ሃሜት የብሽሽቅና የሐሰት ውንጀላ ዓለም እየፈጠረ ይንጨረጨራል በክፉ መንፈስ፡፡
ይህን ያልፈለጉ ሰዎችስ? መልካም ልብወለድ ድርሰትን ማንበብ ይችላሉ። በቀጥታ ለእለት ኑሮ ቅንጣት ጥቅም እንደሌለው እያወቁ፣ በእውን የሌሉ ሰዎችንና ታሪኮችን በምናብ እየፈጠሩ፣ ክፉና ደጉን፣ ውጣ ውረዱን፣ መሰሪነትንና ጀግንነትን ያያሉ። ይመሰጣሉ። በራሳቸው የግል ጉዳይ ላይ ከምር የተጠመዱ ይመስል፤ ክፉና ደጉን ይዳኛሉ - ከልብ።
ይህም ብቻ አይደለም። ሁልጊዜ ዓመት በዓል እንዳልሆነ፤ እለት በእለት ፋሲካ እንደማይመጣ ቢያውቁም፤ ይደግሳሉ። ለኑሮ የሚመኙት ድሎትና ሰላም፣ ሁሌ የሚጓጉለት ደስታና የሕይወት ጣዕም ገና እንዳልተሟላ ባይጠፋቸውም፤ የልባቸው የደረሰ፣ ምኞታቸው ሁሉ የተሟላ ይመስላል - የዓመት በዓል ዝግጅታቸውና ድግሳቸው ሲታይ።
 ኑሮው በነባር ችግርና በዋጋ ንረት መናጋቱን፤ አገር በነባር ኋላቀርነትና በጦርነት መመሳቀሉን አላጣውም። ችግርና ሃዘን በዝቷል። የእለት ተእለት ክስተት ነው። ቢሆንም፤ ቢሆንም ዓመት በዓሉ አለ። ሰዎች፤ሁል ጊዜም ባይሆን፣ አልፎ አልፎ፣ በዓመት አንዴ ወይም ሁለት ሶስቴ፣ ይደግሳሉ፡፡ - በእውን ገና ያልተሟላውን ምኞትና የሕይወት ጣዕም፤ ምንኛ ያማረባት እጅግም የከበረ ምኞት እንደሆነ ለማየትና ለማጣጣም፣ ዓመት በዓልን የመሰለም ፀጋ የለም። የመልካም መንፈስ ገፅታ ነው። ሰው ሲባል፤ ኑሮው ቢጨላልምም፤ የተስፋ ጭላንጭልን ማየትና ሕይወት ፈካ ማድረግ እንደሚችል፤ በእውን ለአፍታው የምናይበት መልካም ጊዜ ነው- ዓመት በዓል፡፡

Read 12489 times