Wednesday, 15 September 2021 06:23

አስገራሚ የዘመን መለወጫ አከባበሮች፤ ከመላው ዓለም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አመቱን ሙሉ አብሮን በዘለቀውና ገና አብሮን መክረሙ የማይቀር በሚመስለው የኮሮና ወሬ፣ አልያም የስልጣን ሽኩቻ መገለጫዋ የሆነው አፍሪካ በ5 ወራት ውስጥ ሶስተኛውን መፈንቅለ መንግስት ማስተናገዷ ስለተሰማበት የሰሞኑ የጊኒ ክስተት፣ ወይም ስለአፍጋኒስታን መሰንበቻ ወዘተ በማስነበብ የዓውደ አመት ፈካ ያለ መንፈሳችሁን ከማጨፍገግ ይልቅ በዓል በዓል የሚሸቱ አለማቀፋዊ ጽሁፎችን መራርጠን ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡
ወቅቱ የዘመን መለወጫ እንደመሆኑ፣ በተለያዩ የአለማችን አገራት የዘመን መለወጫ በዓላት በምን አይነት መልኩ እንደሚከበሩ ቃኝተን ለአንባቢዎቻችን ለማጋራት የተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ምንጮችን ስንበረብር ያገኘናቸውን ለሰሚ የሚገርሙ አስገራሚ ልማዶችና ባህሎች በአጭሩ አሰናድተን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል!
ሮማንያውያን ከእንስሳቶቻቸው ጋር በማውራት አዲሱን አመት በተስፋ ባርከው በሚጀምሩበት የዘመን መለወጫ ዋዜማ ዕለት፣ ፊንላንዳውያን ደግሞ አንጥረኛ ይመስል ብረት ሲያቀልጡ ማምሸት የተለመደ ጠባያቸው ነው፡፡ መሸትሸት ሲል፣ ያቀለጡትን ብረት በጥንቃቄ ይዘው ወደ ቀዝቃዛ ውሃ ይረጩታል። የቀለጠው ብረት ውሃው ላይ አርፎ የሚሰራውን ቅርጽ በመመልከትም፣ አዲሱ አመት ለእነሱ ምን ይዞ እንደሚመጣ ለመተንበይ ይሞክራሉ፡፡
ቅርጹ የልብ ወይንም የቀለበት ከመሰለ፣ በአዲሱ አመት ትዳር እንመሰርታለን ብለው ያስባሉ፡፡ የመርከብ ከመሰለ፣ ከአገራችን ርቀን እንጓዛለን ብለው ይተነብያሉ፡፡
“የጎመን ምንቸት ውጣ፤ የገንፎ ምንቸት ግባ” እንዲል ሐበሻ መስከረም ሲጠባ፣ የዌልስ አባወራዎችም በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አመት ዋዜማ እኩለ ሌሊት ላይ የቤታቸውን የጓሮ በር ከፍተው መልሰው በፍጥነት ይዘጋሉ። ያለፈው አመት ወደ ቤታቸው ይዞት የገባው መጥፎ ዕድል ሹልክ ብሎ ይወጣ ዘንድ ነው በውድቅት ሌሊት በራቸውን መክፈታቸው፡፡
በዚህም አያበቁም፤ ልክ ሲነጋ ደግሞ ያንኑ በር መልሰው ይከፍቱታል። አባወራዎቹ ሲነጋ በሩን የሚከፍቱት አዲሱ አመት መልካም ዕድልን፣ ብልጽግናንና ሰላምን ይዞ ወደ ቤታቸው እንዲገባ ነው፡፡
ጃፓናውያን በበኩላቸው፤ ኦሾጋትሱ ብለው የሚጠሩትን የአዲስ አመት በዓል የሚያከብሩት ቤታቸውን ከወትሮው በተለየ በማጽዳትና በማሸብረቅ ነው፡፡ የጃፓናውያኑን የአውዳመት ጽዳት ለየት የሚያደርገው ግን፣ ቤታቸውን ከቆሻሻ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ከዕዳ ማጽዳታቸው ነው፡፡
ሁሉም የቤተሰብ አባል ያለበትን የገንዘብ ዕዳ በሙሉ ከፍሎ፣ ከተቀያየመውና ከተጣላው ሰው ጋር እርቅ አውርዶ፣ ከቂምና ከዕዳ ከነጻ በኋላ ነው አዲስ አመትን በደስታ ማክበር የሚጀምረው። ሌላኛው የጃፓናውያን የአዲስ አመት ለየት ያለ አከባበር ደግሞ፣ በዋዜማው ምሽት ሁሉም ሰው ለ108 ጊዜያት ያህል ደወል መደወሉ ሲሆን፣ ድምጹ መጥፎ መንፈስን በማባረር በጎ መንፈስን ይጠራል ብለው ያስባሉ፡፡
በኢስቶኒያ የቤተሰብ አባላት በአዲስ አመት ዋዜማ 7 ወይም 9 ወይም 11 ጊዜ ያህል ምግብ የሚመገቡ ሲሆን፣ ይሄም እነዚህ ቁጥሮች መልካም ዕድልን ያመጣሉ ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው፡፡ ስፔናውያን ደግሞ በአዲስ አመት የመጀመሪያዋ ቀን ሰዓታቸውን እያዩ ልክ አንድ ሙሉ ሰዓት ሲሆን አንድ ወይን የሚበሉ ሲሆን፣ ቀኑን ሙሉ የሚበሏቸው 12 የወይን ፍሬዎች፣ በአዲሱ አመት 12 ወራት፣ መልካም ዕድልንና ደስታን ያመጡልናል ብለው ያምናሉ፡፡
አየርላንዳውያን የአዲስ አመትን አከባበር የሚጀምሩት፣ በዋዜማው ምሽት፣ በየቤታቸው ግድግዳና በር ላይ ዳቦ በማንጠልጠል ነው። ዳቦው የተትረፈረፈ ጸጋን እንደሚስብና መጥፎ መንፈስንና ክፉ እድልን ከቤታቸው እንደሚያስወጣ ያምናሉ፡፡ በዚህም አያበቁም። ከቤታቸው በዳቦ ያባረሩት መጥፎ መንፈስና ክፉ እድል ከደጃፍ እንዳይጠብቃቸው በመስጋት በእኩለ ሌሊት ከቤታቸው በመውጣት፣ ጆሮ የሚበጥስ ሃይለኛ ጩኸት ያሰማሉ፡፡
ሁሉም በየደጃፉ ቆሞ አቅሙ በፈቀደው መጠን እሪታውን ያቀልጠዋል። ህጻን አዋቂው ጉሮሮው እስኪደርቅ በመጮህ፣ ከደጃፉ ያደፈጠውን መጥፎ መንፈስና ክፉ እድል፣ ከአገር ምድሩ ጠራርጎ ያስወጣና፣ አዲስ አመትን “በል እንግዲህ ሰተት ብለህ ግባ!!” ብሎ ይቀበላል፡፡
አንዲት መልከ መልካም ብራዚላዊት በአውደ አመት ምድር፣ የወርቅና የአልማዝ ጌጣጌጦቿን አወላልቃ፣ ወደ ባህር ስትወረውር ቢያዩ፣ ጤንነቷን ሊጠራጠሩ ይችላሉ፡፡ አይጠራጠሩ! ጤነኛ ናት፡፡ ጌጣጌጦቿን ወደ ባህር የምትወረውረውም፣ ያለፈውን አመት በሰላም በጤና እንዳሳለፈችው ሁሉ፣ አዲሱ አመትም የሰላምና የጤና እንዲሆንላት አምላኳን ለመለመን ነው፡፡
በቱርክ በአዲስ አመት ዋዜማ ከሌሊቱ 6  ሰዓት ሲሆን፣ በቤታቸው ዋና በር ስር ጨው መነስነስ በአዲስ አመት ሰላምና ብልጽግና ያመጣል ተብሎ የሚታሰብ የተለመደ የአውዳመት ልማዳዊ ተግባር እንደሆነ ይነገራል፡፡
ኮፓካባና ተብሎ የሚጠራው የብራዚል ባህር ዳርቻ፣ አመቱን ሙሉ በቱሪስቶች የሚጥለቀለቅ ታዋቂ የመዝናኛ ስፍራ ነው፡፡ ኮፓካባና ከአመት አመት የመዝናኛ፣ ከአመት አንድ ቀን ደግሞ የአውዳመት ማክበሪያና የመማጸኛ ባህር ነው፡፡
ብራዚላውያን በዘመን መለወጫ ዋዜማ በሚያከናውኑት ‘ፌስታ ዲ ኢማንጃ’ የተባለ ባህላዊ ክብረበዓል፣ ወደ ባህሩ አቅንተው ‘ኢማንጃ’ የተባለችዋን የባህር አምላክ ይለማመናሉ። አዲሱን አመት መልካም እንድታደርግላቸው ይጸልያሉ። በስተመጨረሻም ወደ ባህሩ እጅ መንሻ ይወረውራሉ፡፡ በአዲስ አመት ዋዜማ ወደ ባህሩ የሚወረውሩት ጌጣጌጦች ብቻም አይደሉም፡፡ ውድ ዋጋ የሚያወጡ ሽቶዎች፣ አበቦችና ፍራፍሬዎች ጭምር እንጂ፡፡
ድሮ ድሮ ወደ አገራችን መጥቶ በጥምቀት በዓል የታደመ እንግዳ ደራሽ ዴንማርካዊ፣ ኮበሌው ወደ ልጃገረዷ ደረት ሎሚ ሲወረውርና ጡቷን ሲመታ ቢያይ ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ ውርወራው ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አያውቅምና፡፡ ወደ ዴንማርክ አቅንቶ የዘመን መለወጫ በዓላቸውን የታደመ የኛ አገር ሰው በተራው፣ ስኒ እንደ ድንጋይ ወደየቤቱ ደጃፍ ሲወረወር ቢያይ፣ በተመሳሳይ ግራ መጋባቱ አይቀርም፡፡ ውርወራው ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አያውቅምና፡፡
ዴንማርካውያን በአዲስ አመት ዋዜማ እኩለ ሌሊት ላይ፣ የማጀት እቃዎቻቸውን ለቃቅመው ወደ ጎዳና ይወጣሉ፡፡ በጨለማ ውስጥ ተደብቀው ማንም ሳያያቸው፣ ወደመረጡት ጎረቤት ወይም ወዳጅ ዘመድ ቤት ያመራሉ፡፡ ከዚያስ?... በደረቅ ሌሊት በወዳጅ ዘመዳቸው ቤት ጣራ ላይ የማጀት እቃዎቻቸውን እንደ ድንጋይ ይወረውራሉ፡፡
በዚህች የዴንማርክ ምሽት ብርጭቆ፣ ትሪ፣ ሰሃን፣ ጭልፋ፣ ማንኪያ፣ ድስትና ሌላ ሌላው የቤት እቃ በሙሉ ከየመደርደሪያው ወርዶ ወደየቤቱ ደጃፍ ይወረወራል። ከግድግዳ እየተጋጨ፣ ከመስኮት እየተፋጨ፣ በየበሩ ሲሰባበር፣ በየደጃፉ ሲነካክት ያመሻል፡፡
ሲነጋጋ ሁሉም ከቤቱ በመውጣት በየራሱ ደጃፍ የተጠራቀመውን ስብርባሪ የማጀት እቃ በማየት ደስታን ይጎናጸፋል፡፡ የተሰባበረው እቃ የመልካም ነገሮች ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል። ምሽቱን ወደ ቤቱ ብዙ እቃ ሲወረወርበት ያደረ፣ ሲነጋ ከደጃፉ ብዙ ስብርባሪ ተጠራቅሞ ያገኘ ቤተሰብ፣ በሌሎች ዘንድ የበለጠ ተወዳጅ እንደሆነና መጪው አመትም በተለየ ሁኔታ የደስታ፣ የብልጽግናና የጤና እንደሚሆንለት ይታሰባል፡፡
ዴንማርካውያን ከዚህ በተጨማሪም በአዲሱ አመት ዋዜማ እኩለ ሌሊት ላይ፣ ወንበር የመዝለል ባህል አላቸው። ይህም ከአሮጌው አመት ወደ አዲሱ አመት፣ ከችግር ወደ ስኬት በሰላማዊ ሁኔታ የመሸጋገር ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
“ቺሊያውያን የዘመን መለወጫን በዓል ከዘመድ አዝማድ ጋር ነው የሚያከብሩት” ብዬ ስነግርዎት፣ “ታዲያ ይሄ ምን ይገርማል?… እኛስ ከዘመድ አዝማድ ጋር አይደል እንዴ የምናከብረው?!” እንደሚሉኝ አላጣሁትም፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው…
የቺሊያውያንን የዘመን መለወጫን በዓል ከዘመድ አዝማድ ጋር የማክበር ባህል ከእኛ የሚለየው ዋናው ጉዳይ፣ ወደ ዘመዶቻቸው የሚሄዱት በዋዜማው ምሽት መሆኑም አይደለም - በህይወት ወደሌሉ ዘመዶቻቸው መሄዳቸው እንጂ!! ቺሊያውያኑ በሞት የተለዩዋቸው ዘመዶቻቸው ወዳረፉበት መካነ መቃብር በአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት ያመራሉ፡፡ በድቅድቅ ጨለማ በተዋጠው የወዳጅ ዘመዳቸው መቃብር ውስጥ አረፍ ብለውም፣ ከወዳጅ ዘመዳቸው ጋር በዓሉን በዝምታ ጨዋታ ሞቅ ደመቅ አድርገው ያከብራሉ።
ኢኳዶራውያን በአዲስ አመት ዋዜማ ከሚያደርጓቸው የተለዩ ገራሚ ድርጊቶች መካከል አንዱ ደግሞ፣ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በአገራቸው በተለያዩ ነገሮች አነጋጋሪ የነበሩ ታዋቂ ሰዎችንና ዝነኞችን ፎቶግራፎች በእኩለ ሌሊት ማቃጠል ነው፡፡ ድርጊቱ ያለፈውን አመት መጥፎ ትዝታ ይፍቃል ተብሎ ይታመናል፡፡
አዲሱ አመት የሰላም፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሆንላቸው የሚመኙ ሜክሲኳውያን፤ በዋዜማው ምሽት ቀይ ወይም ቢጫ የውስጥ ሱሪ የማድረግ ልማድ አላቸው፡፡ ቀዩ ለብልጽግና፣ ቢጫው ደግሞ ለፍቅርና ለሰመረ ትዳር ይመረጣል።
በአዲስ አመት ጥሩ ፍቅርና የሰመረ ትዳርን ስለ መሻት ካነሳን አይቀር፣ የአየርላንዳውያን ሴቶችን ልማድ እንመልከት፡፡ በአዲሱ አመት ጥሩ ፍቅርና የሰመረ ትዳር ይገጥማት ዘንድ የምትመኝ አየርላንዳዊት ሴት፣ በበዓሉ ዋዜማ ሚስትሌቶ የሚባል የተክል አይነት በትራሷ ስር ሸጉጣ ታድራለች፡፡
በአገራችን ስራ ተፈትቶና ዘና ተብሎ የሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓል፣ በኮሎምቢያና በሜክሲኮ ከዋዜማው እኩለ ሌሊት አንስቶ ከባድ ሸክም በመሸከም እንደሚከበር ሲሰሙ ምን ይሉ ይሆን?
የኢኳዶር ዜጎች በበኩላቸው፤ በአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት ከየቤታቸው ተጠራርተው ደጃፍ ላይ ይሰባሰባሉ - ለደመራ። ታዲያ ይሄ ምን ይገርማል ሊሉ ይችላሉ፡፡ የሚገርምዎት ኢኳዶራውያኑ በደመራ መልክ የሚያነድዱት እንጨት ሳይሆን ፎቶግራፍ መሆኑ ነው፡፡ እናት፣ አባት፣ እህትና ወንድም ሁሉም ባለፈው አመት ያጋጠማቸውን ማንኛውንም መጥፎ ነገርና ገጠመኝ የሚያሳዩ ፎቶግራፎቻቸውን ከአልበሞቻቸው ውስጥ በርብረው በማውጣት፣ እንደ ችቦ ደመራ አድርገው በእሳት ያጋዩዋቸዋል፡፡ ፎቶው ሲቃጠል፤ ያ መጥፎ አጋጣሚም ከአሮጌው አመት ጋር ከውስጣቸው ወጥቶ ያልፋል - እነሱ እንደሚያምኑት፡፡
ከኢኳዶር ሳንወጣ ሌላ የአዲስ አመት አከባበራቸው አካል የሆነ ልማዳቸውን እናክል፡፡ በአዲሱ አመት የመጀመሪያ ቀን፣ ምንም የሌለበት ባዶ ሻንጣ ይዘው ረጅም ርቀት የሚጓዙ በርካታ ኢኳዶራውያንን ጎዳና ላይ መመልከት የተለመደ ነገር ነው። ባዶ ሻንጣ ይዘው ርቀው የሚጓዙት፣ እንደዚያ ካደረጉ በአዲሱ አመት በብዛት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ወይም ወደ ሌሎች ቦታዎች እንደሚጓዙ ስለሚያምኑ ነው፡፡
ሩስያውያን በበኩላቸው፤ በዋዜማው ምሽት በአንድ ላይ ይሰባሰቡና በአዲሱ አመት ሊያሳኩት የሚፈልጉትን ነገር በሙሉ በዝርዝር በየራሳቸው ወረቀት ላይ ይጽፋሉ። ጽፈው ከጨረሱ በኋላ፣ ወረቀቱን በእሳት ያቃጥሉትና አመዱን ከሻምፓኝ ጋር ቀላቅለው እኩለ ሌሊት ከማለፉ በፊት ጭልጥ አድርገው ይጠጡታል - በዚህም አዲሱ አመት ያሰቡት የሚሳካበት ይሆናል ብለው ያስባሉ፡፡
እንደ ሩስያውያን ሁሉ ደቡብ ኮርያውያንም የአዲስ አመት ህልምና ምኞትን በወረቀት ላይ የማስፈር ልማድ አላቸው፡፡ የእነሱን ለየት የሚያደርገው ግን፣ በአዲሱ አመት የመጀመሪያዋ ቀን ንጋት ላይ ከደጃፍ ቆመው፣ ጎህ ሲቀድ እያዩ፣ ህልምና ምኞታቸውን በወረቀት ላይ ጽፈው፣ በፊኛ ውስጥ አድርገው ወደ ሰማይ መላካቸው ነው፡፡
ከሩስያ ፊታችንን ወደ ስኮትላንድ እናዙር። ስኮትላንዳውያን ቤተሰቦች፣ የአሮጌው አመት የመጨረሻ ዕለት ተጠናቅቃ፣ የአዲሱ አመት የመጀመሪያ ቀን ስትጠባ፣ ማልደው በር በሩን ማየት ይጀምራሉ፡፡ ቀጣዩ የበዓል አከባበር የሚደምቀውና የሚሞቀውም ሆነ የቤተሰቡ የአዲስ አመት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በዚያች ማለዳ ቀድሞ ወደ ቤታቸው በሚመጣው ሰው ነው፡፡
በዚያች ማለዳ ደጃፋቸውን ቀድሞ የረገጠው ሰው፣ ቁመተ ሎጋና መልከመልካም ወንድ ከሆነ፣ አዲሱ አመት የደስታ ይሆናል ብለው ስለሚያምኑ አብዝተው ይፈነጥዛሉ። በአንጻሩ በዚያች ማለዳ ቀይ ጸጉር ያላት ሴት አልያም ህጻን ልጅ ቀድመው ወደ ቤታቸው ከመጡ ደግሞ አመቱ ለቤተሰቡ ይዞት የሚመጣው አንዳች መከራ አለ ተብሎ ይታመናል፡፡
የሚመጣውን አዲስ አመት ወደ ቤታቸው በሚመጣው ሰው የሚተነብዩት ስኮትላንዳውያን ወንዶች፣ የዘመን መለወጫ በአልን በአጉል ጨዋታ ነው የሚያከብሩት - ነበልባል እሳት እንደ ኳስ እያንጠባጠቡና በሰራ አካላቸው ላይ እያሽከረከሩ በመንገድ ላይ እየተደሰቱ በመጓዝ፡፡ መጪውን አመት እንደነሱ ከእሳት ሳይሆን ከሳቅ ጋር የምንጓዝበት ያድርግልን!
      

Read 6569 times