Sunday, 12 September 2021 00:00

የዓመቱ አበይት ክንውኖች - ፈተናዎችና ስኬቶች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ዛሬ የሚጠናቀቀው  2013 ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን የመከራም የስኬትም ዘመን ሆኖ ማለፉ ይታወቃል፡፡ ዘመኑ አገሪቱ እንደ አገር መቀጠል እንዳትችል የሚገዳደሯት በርካታ ችግሮችና መሰናክሎችን የተጋፈጠችበትና በሺዎች የሚቆጠሩ  ዜጎችን በጦርነት በግጭትና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ያጣችበት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለስደት የተዳረጉበት ነበር። በሌላ በኩል፤ አገሪቱ ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ የሚደርስባትን ጫና ተቋቁማ ሰላማዊ ምርጫ ያካሄደችበት፣ ሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌት ያከናወነችበትና  በርካታ ፕሮጀክቶችን አጠናቃ ወደ ስራ የገባችበት የስኬት ዘመንም ነበር፡፡
በ2013 ዓ.ም በአገራችን ከተከናወኑ አበይት ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹን ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡
የብር ኖት ቅያሬ
ኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በላይ ስትገለገልበት የቆየችውን የ10፣ የ50 እና የ100 ብር  ኖቶች ቅያሬ ያደረገችውና በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የባለ 200 ብር ኖት ያሳተመችው በዚሁ ባጠናቀቅነው ዓመት ነበር፡፡ ከገንዘብ ጋር የተገኙ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠርና ከባንክ ውጪ ያለውን የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ለመግታት ያስችላል የተባለው ይኸው የገንዘብ  ኖት ቅያሬ ይፋ የተደረገው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር። ከባንኮች ውጪ የሚገኘው ጥሬ ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ገንዘብ ወደ ትክክለኛው የግብይት ስርዓት ለማስገባት ባለመቻሉ ምክንያት እርምጃ መወሰዱን የተናገሩት የብሔራዊ ባንክ ገዢው ዶ/ር ይናገር ደሴ፤ ጥሬ ገንዘብ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት አገራትም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚገኝና ይህም ለህገወጥ ተግባራት እየዋለ መሆኑ እንደተደረሰበት በዚሁ አዲሱን የብር ኖት ይፋ ማድረጊያ ፕሮግራም ላይ ተናግረው ነበር፡፡ የብር ኖት  በ3 ወራት ውስጥ እንዲጠናቀቅ የተደረገ ሲሆን በትግራይ ክልል በነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ እንቅስቃሴ ምክንያት የብር ቅያሬው እስከ መጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲራዘም ተደርጓል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ በተደረገው አዲሱ የብር ኖት 262 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 2.9 ቢሊዮን የብር ኖቶች ለቅያሬው ቀርበዋል፡፡ በዚህ የብር ኖት ለውጥ ሳቢያም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቀድሞ የብር ኖቶች በየመንገዱና በየአደባባዩ ተጥለው የተገኙ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩና በህገወጥ መንገድ የተከማቹ የብር ኖቶች ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡
የህግ ማስከበር ዘመቻ
በፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው የህወኃት ቡድን  መካከል ለወራት የዘለቀው ውዝግብና አለመግባባት ወደ ለየለት ጦርነት ያመራውም በዚሁ ባጠናቀቅነው ዓመት ነበር፡፡ የትግራይ ክልል አመራሮች በ2012 ዓ.ም  ጳጉሜ ወር፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጭ፣ ያካሄዱትን ምርጫ ህገወጥ በመሆኑ አልቀበለውም ባለው የፌደራል መንግስቱና የትግራይ  አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ተባብሶ በመቀጠሉ ሳቢያ ሁለቱም ወገኖች ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ በአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች የተጀመረው የእርቅና ሽምግልና ጉዳይ በትግራይ ክልል አመራሮች በኩል ተቀባይነት በማጣቱ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይህንን ተከትሎም የክልሉ ልዩ ኃይል በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በወሰደው ድንገተኛ የማጥቃት እርምጃ በሰራዊቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በማይካድራ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃንም በትግራይ ክልል ልዩ ሀይልና ሳምሪ በሚል መጠሪያ በተደራጁ ወጣቶች በጅምላ ተጨፈጨፉ። ከዚህ በኋላም መንግስት በአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ላይ የተቃጣውን ጦርነት ለማስቆምና ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ  የህግ ማስከበር  ዘመቻ በይፋ ጀመረ፡፡ በዚህ ዘመቻ  የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ከነበሩት መካከል እነ አቶ ስብሃት ነጋ በቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ እነ አቶ ስዩም መስፍንና፣ አቶ አባይ ፀሐዬን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ የህወኃት አመራሮች በመከላከያ ሰራዊቱ ተደምስሰዋል፡፡ ሰራዊቱ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የህወኃት ከፍተኛ አመራሮች ለህግ ያቀረባቸው ሲሆን ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡
በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል የተጀመረውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ ቀደም ሲል በስውር አሁን በገሃድ ከህወኃት ጋር ጥምረት የፈጠረው ኦነግ ሸኔ፤ በአማራ ክልል አጣዬና አንጾኪያ አካባቢ በንፁሃን ዜጎች ላይ  በወሰደው የግፍ እርምጃ ከመቶ በላይ ንፁሃን ዜጎችን  በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገድል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሏል፡፡ ይህ ግድያና ማፈናቀል በእነዚህ አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ አልቀረም በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች በዚህ ኦነግ ሸኔ በተባለ ቡድን በሺ የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ የፌደራል መንግስት የተናጥል የተኩስ አቁም በማወጅ፣ የትግራይ አርሶ አደር ያለስጋት የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን የትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ በሚል የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ክልሉን ዳግም የተቆጣጠረው የህወኃት ቡድን ባለፉት ወራት ወረራ በፈፀመባቸው የትግራይና አፋር ክልሎች በንጹሀን ዜጎች ላይ የጅምላ ግድያ ፈፅሟል፣ አሁንም እየፈፀመ ነው።
በውጥረት የታጀበ ምርጫ
የዓመቱ ሌላኛው አብይ ክስተት 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ነበር፡፡ በ2012 ዓ.ም ነሀሴ ወር  ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ሳቢያ የተራዘመው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በዚህ ዓመት እንዲካሄድ የተወሰነው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነበር፡፡ ምክር ቤቱ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው የ5ኛ ዓመት  የስራ ዘመን 4ኛ አስቸኳይ ስብሰባ፣ አገራዊ ምርጫው የዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ባስቀመጡት ምክረ ሃሳብ  መሰረት፣ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ምርጫው እንዲከናወን ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ይህ የምክር ቤቱ ውሳኔም በአንድ የተቃውሞ ድምጽና በስምንት ድምጸ ተአቅቦ፣ በአብላጫ ድምጽ  ፀድቋል፡፡  የምክር ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ፣ ምርጫ ቦርድ 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫን ለማድረግ የሚያስችሉትን ዝግጅቶች ማድረግ ሲጀምር፣ የተለያዩ አካላት ምርጫው ተግባራዊ መሆን እንደማይችልና አገሪቷን እጅግ ወደ ከፋ ትርምስና ብጥብጥ እንድትገባ ሊያደርጋት እንደሚችል በመተንበይ ምርጫው እንዳይካሄድ ግፊት አድርገው ነበር፡፡  ግፊቱና ማስፈራራቱ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን በተለያዩ የውጭ አገራት መንግስታትና ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ከምርጫው በኋላ ኢትዮጵያ ሲኦል ትሆናለችም ተባለ፡፡
ከአንዳንድ አገራት ጋር ያበሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም መንግስት ምርጫውን ከማካሄድ ታቅቦ ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሳተፈ ጊዜያዊ መንግስት (የሽግግር መንግስት) እንዲቋቋም ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በተለያዩ ምክንያች ምርጫውን ከመታዘብ ራሳቸውን ያቀቡ ወገኖችም ነበሩ፡፡ መንግስትና ህዝቡ ጫናውንና ውጥረቱን ተቋቁሞ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 በሰላማዊ መንገድ በማካሄድ አገሪቱ ወደ ብጥብጥና ረብሻ ስታመራ ለማየት የጓጉትን ሁሉ አሳፍሯል፡፡ ምርጫው በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች  በሰላማዊ መንገድ ተከናውኖ የምርጫው ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ በመጪው መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ መንግስት ይመሰረታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኮቪድ - 19 ወረርሽኝና ክትባቱ
በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ወደ አገራችን መግባቱ ይፋ የተደረገው የኮቪድ 19- ወረርሽኝ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ለሞት የዳረገበትም ዘመን ነበር - 2013 ዓ.ም፡፡ በሽታው ከቁጥጥር ውጪ ለመሆን የደረሰበት፣ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት ህሙማንን ተቀብሎ ማስተናገድ ከአቅማቸው በላይ የሆነበት፣ በሺዎች  የሚቆጠሩ ዜጎች በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡበት ፈታኝ ዓመት ነበር። ወደ አገራችን ከገባ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ባስቆጠረው በዚህ ወረርሺኝ ሳቢያም እስከ አሁን ድረስ ከ4800 በላይ ወገኖቻችንን ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከ318 ሺ የሚበልጡ ደግሞ በበሽታው ተይዘዋል፡፡ በቅርቡም በስርጭት ፍጥነቱ ቀደም ሲል ከነበረው የኮሮና ቫይረስ በሁለት እጥፍ የሚበልጠውና  በገዳይነቱ የታወቀው “ዴልታ” የተባለው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ወደ አገራችን መግባቱ በጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ይፋ ተደርጓል። ባሳለፍነው አንድ ሳምንት ብቻም 8300 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና 118 የሚሆኑ ደግሞ መሞታቸውን ጤና ሚኒስቴሯ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የኮቪድ 19 ዝርያ - ዴልታ፤ በተለይም ክትባት ባልወሰዱ ሰዎች ላይ እንደሚበረታም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ክትባትም በዚሁ ባጠናቀቅነው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ለዜጎቹ መስጠት የጀመረች ሲሆን፤ እስከ አሁን ድረስ ከ2.6ሚሊዮን በላይ ሰዎች ክትባቱን መውሰዳቸውን ጤና ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
የግድቡ ሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት
የታላቁ ህዳሴ ግደውብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀበትና ግድቡ ሁለት ተርባይኖችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ውሃ መያዙ የተረጋገጠውም በዚሁ ባሳለፍነው ዓመት ነበር፡፡ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም የግድቡ ሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት በይፋ በተጀመረበት ወቅት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ፤ ሙሌቱ በነሀሴ ወር አጋማሽ ላይ እንደሚጠናቀቅ ተናግረው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ በነበረው ከፍተኛ ዝናብ ሳቢያ የግድቡ ሙሌት ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም መጠናቀቁ ይፋ ተደርጓል። የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር መሀመድ አብድል አቲ፣ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን ሙሌት መጀመሯን የሚገልፅ ደብዳቤ እንደተላከላቸው በመጥቀስ፤ ውሳኔው ዓለም አቀፉን ህግ የሚጥስ ነው በሚል ተቃውሞአቸውንም አሰምተው ነበር፡፡ ግብጽ፤ ሱዳንና ሌሎች አጋሮቿን በማሰባሰብም የግድቡ ውሃ ሙሌት እንዳይከናውን በተደጋጋሚ ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካላት  በመቅረቱ ሳቢያ የተለያዩ ዛቻና ማስፈራሪያዎችን ከመላክ ጀምሮ የአገሪቱን ሰላም በሚያደፈርሱ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትን አቋም ለማስቀየርና የግድቡን ስራ ለማስተጓጎል የምታደርገውን ጥረት አሁንም እንደቀጠለች ትገኛለች፡፡
የቀጠለው ጦርነትና መፈናቀል
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ የተቃጣውን ጥቃት ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት የጀመረውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በአጭር ጊዜ በድል ተጠናቆ የፌደራሉ መንግስት የትግራይ ክልልን ማስተዳደር  ከጀመረ  ከ8 ወር በኋላ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም የፌደራል መንግስቱ የተናጥል ተኩስ አቁም በማድረግ ክልሉን ለቆ ወጥቷል፡፡ ይህንን ተከትሎም በተለያዩ ምሽጎች ውስጥ የነበሩት የህወኃት ታጣቂ ኃይሎች ዕድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ህፃናትን በማስታጠቅና ለጦርነት ለማሰማራት ከክልሉ አልፎ በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎችና በአፋር  ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈፀም በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃንን ሲገድል፣ ቤተ እምነቶችን ዘርፏል፤ ትምህርት ቤቶች ሆስፒታሎችና የተለያዩ ተቋማትን  አውድሟል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር 7 ሺ ት/ቤቶች በታጣቂ ቡድኑ መውደማቸውን ባለፈው ሳምንት አስታውቋል፡፡ ከሁለቱ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 500 ሺ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እንስሳትን ሳይቀር በጥይት ደብድቦ ገድሏል፡፡  በሌላ በኩል አማጺው ቡድን ከትግራይ እናቶች ጉያ እየነጠቀ በጦርነቱ የሚያሰማራቸው የትግራይ ወጣቶችና ታዳጊዎች በአስደንጋጭ ሁኔታ እያለቁ ነው፡፡ ሰሞኑን ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ በሰጡት መግለጫ 7ሺ ወጣቶች መገደላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዓለማቀፍ የዲፕሎማሲ ጫና
ኢትዮጵያ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ የተጋፈጠችው መከራና ፈተና ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ አገሪቱ ባሳለፍነው 2013 ቀደም ሲል አይታው ለማታውቀው ዓለማቀፍ የዲፕሎማሲ ጫናና ውጥረትም ተዳርጋለች። እነ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ አየርላንድና ሌሎች የኢትዮጵያን ጉዳይ በየፓርላማቸው እያነሱ ይወያያሉ፡፡ ማዕቀብ ለመጣል ያስፈራራሉ፡፡ የአሜሪካ መንግስት የጉዞ (የቪዛ) ማዕቀብ መጣሉ አይዘነጋም፡፡ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ከኢትዮጵያ የትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ በዓመት ውስጥ ስምንት ጊዜ ተሰብስቧል።
የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልዩ መልዕክተኛ ከጦርነቱ ጋር በተገናኘ ስድስት ወር ሳይሞላ፤ ሁለት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ዓመት ያጋጠማት ችግርና መከራ በተለይም ተገዳ በገባችበት ጦርነት ሳቢያ በዜጎቿ ላይ የደረሰው ሞት፣ መፈናቀልና ስደት በዚህ በአሮጌው ዓመት ተቋጭቶ  አዲሱን ዘመን በተሻለ ተስፋ ብንሻገረው መልካም ነበር። ያ ሊሆን ግን አልቻለም፤ አሁንም አዲሱን ዓመት የምንሻገረው ከነዚህ ችግሮቻችን ጋር መሆኑ ግድ ሆኗል።  አሁን ብቸኛው ምርጫ ጦርነቱን በፍጥነት መቋጨት ብቻ ነው፡፡ መፍትሔው ይሄ ብቻ ይመስላል አዲሱን ዓመት የሰላም-የፍቅር- የደስታ የፍስሀ ያድርግልን!!


Read 747 times