Sunday, 12 September 2021 00:00

የመስከረም ቀለሞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

የኛ አዲስ ዓመት የጳጉሜን ወር ተንተርሶ ሲመጣ፣ በብዙ ተፈጥሯዊ ቀለማትና ውበት ታጅቦ ነው። ከነሐሴው ቡሄ የችቦው ብርሃን ጀምሮ እስከ እንቁጣጣሹ ችቦና ሆያሆዬ የተስፋ ቀለሙ ብሩህ ነው።
ሰማዩ ሲጠራ፣ ምድር በአበቦች ተሸፍና ስትስቅ፣ ተራሮች አረንጓዴ ምንጣፍ ወይም ቢጫ አበባ ሲመስሉ፣ የአየሩ መዓዛ ሳይቀር ሽቶ ይርከፈከፍበታል። ታዲያ ይህን ውበትና ዜማ የሰው ልጆች ዝም ብለው አያጣጥሙትም። ስንኝ ቋጥረው ዜማ አሰናድተው ያቀነቅኑታል። ተባዕት በጐርናና ድምጽ “ኢዮሃ አበባዬ- መስከረም ጠባዬ!” ሲሉ፣ እንስቱ በለሥላሴ ቅላፄ “እቴ አበባሽ እቴ አበባዬ…” ወይ “አበባየሁሽ ለምለም” እያሉ የሕይወትን ለዛ ያጣፍጡታል።
ወንዞች ደፍርሰው አያጓሩም፣ ጠብድለው ድንበር አያልፉም፣ የተደበቁ ድንጋዮች ብቅ ብለው ልክ እንደኛ ሰማዩን ለማየት፣ ተራሮቹን ለማድነቅ አንገታቸውን ቀና ያደርጋሉ። ደብተራቸውን ያስቀመጡ፣ ከጥናት የራቁ ተማሪዎች መንፈሳቸውን ያነቃቃሉ፣ ይፈትሻሉ። እናም፡-
መስከረም መስከረም መስከረም ለምለም
ከወራቱ ሁሉ እንዳንቺ የለም
ደመናውም ሸሸ እያጉረመረመ
በመስከረም ማማር እየተገረመ
እየተባለ ይዘመራል።
መስከረም አንድን ወይም እንቁጣጣሽ የሚውልበትን ቀን አንዳንዶች በተለይም ሃይማኖታዊ  አተያይ ያላቸው እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን የፈጠረበት ቀን እንደሆነ አድርገው ይወስዳሉ፣ ሌሎች ደግሞ ዘመን መርከቢቷ ውስጥ ያሉ ፍጥረታት ተርፈው መርበከቢቴ አራራት ተራራ ላይ ባረፈች ጊዜ ውሃ በምድር መድረቁን ለማረጋገጥ ኖህ የላካት ርግብ ቀንበጥ ይዛ የመጣችበትን ቀን ለማሰብ ነው ብለው ያምናሉ።
ስለ እንቁጣጣሽ የጻፉት ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር “እንቁጣጣሽ ማለት ከመስከረም መጀመሪያ እስከ መስቀል ባለው ጊዜ የምታብብ ውብ አበባ ናት” ይላሉ፣ ይህቺን መጀመሪያ ውብ አበባ በትግራይ “ገልገለ መስቀል” በደቡብ ጎንደሮች ደግሞ “አጎሮ ጎምባሻ” ይሏታል። በመስከረም የምታብብ እንቁጣጣሽ ብቻ ሳትሆን የድመት ዓይን፣ የጅብ ጫማ፣ አደይ አበባ፣ የልጃገረድ ኩል የሚባሉ እንዳሉ ይናገራሉ።
እኛ ብዙዎቻችን ግን ከአደይ አበባ ጋር የሰመረ ቁርኝት አለን። በሰሜን፣ በደቡብ ፣ በምስራቅ፣ በምዕራብ በሁሉም አቅጣጫ ለሁላችን ሩቅ አይደለችም፤ ስለዚህ በየዜማችን መሀል ትገባለች።… “አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ” የሚባልላትም ለዚሁ ይመስለኛል።
በተለይ ምርቃቱ ላይ፡-
ከብረው ይቆዩን፣ ከብረው፣
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው፣
ስላሳ ጥጆች አስረው፣
ከብረው ይቆዩን ከብረው…ይባላል
ቀጥለው
አደይ የብር ሙዳይ
ኮለል በይ
ብለው ምርቃታቸውን ያሳርጋሉ።
መስከረም የአበባና የእሸትም ወር ነው። ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ ዝናብ ጠግቦ፣ ጸሐዩን ቀምሶ እሸት ሲያፈራ ሁሉም ነገር ያምራል፤ የሚበላውም ይጣፍጣል። ከዚህም ሌላ በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች መስከረም ለልጃገረዶች የመታጫ ወር እንደሆነም ይነገራል። “በመስከረም ሴት ያላጨ፣ አበባ ያልነጨ ዋጋ የለውም” እንደሚባል ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ደራሲ ያወሳሉ። ስለዚህም ልጃገረዶች በዚህ ወቀት የሚቋጥሯቸው ስንኞች የሚያጅቡበት ዜማም አላቸው።
የታጩ ጓደኞቻቸውን የሚያጅቡ ልጃገረዶች እንዲህ ይላሉ፡-
እነ ጉብል ሊሄዱ ናቸው
ተጫነላቸው ፈረስ በቅሏቸው
 በኩል ተውቧል ዓይነርግባቸው።
ሳትታጭ የቀረችዋ ደግሞ በብሶትና በቁጭት፣
ጡቴ አጎጠጎጠ አበበ ሊያወጣ፣
ተው አባቴ ዳረኝ ዓመል ሳላወጣ፣
ተይ እምዬ ዳሪኝ ዓመል ሳላወጣ፣
እያለች ታንጎራጉራለች። ሳያጭ ያለፈውም ወንድ የራሱ እንጉርጉሮ አለው።
እገሌም አገባ እገሌም ታጨ
እኔ ብቻ ቀረሁ ቂጤን አገንብጬ!
የገጠሩ በእንዲህ ሲያልፍ የከተማው ወጣት ሆያሆዬ እያለ፣ በግጥምና ዜማ ዱላውን ይዞ መሬት እየደበደበ፣ ሳንቲም ይለቅማል፣ በዓል ያከብራል፣ ጣፋጭ የጓደኞች ቀናት ያሳልፋል። ባገኘው ገንዘብ  ያሻውን ይበላል፤ ይጠጣል።… አንዳንዱም ትምህርት ቤት ሲከፈት እርሳስና ደብተር ሊገዛበት ያስቀምጣል። ታዲያ በዚህ የሆያ ሆዬ ሰሞን ብዙ ጣጣ አለ። ውሻ ያጋጥማል፣ ሰካራም ይረብሻል፣ ቤተሰብ ይቆጣል።.. እንዲያም ሆኖ ይጣፍጣል።
ቄጤማ ይዘው በልጃገረዶቹም በኩል በጠዋቱ ነጭ ልብሳቸውን ለብሰው፣ ፀጉራቸውን ተሰርተው በየቤቱ እየሄዱ፡-
እቴ አበባሽ -እቴ አበባዬ፣
አዬ- እቴ አበባዬ፣
እቴ አበባሽ ስትለኝ ከርማ፣
አዬ- እቴ አበባዬ
ጥላኝ ሄደች በሐምሌ ጨለማ
አዬ- እቴ አበባዬ… ይላሉ።
አሁን የሐምሌ ጨለማ የለም፤ የነሐሴ ዶፍ- አልፏል ማለት ነው። በገጠሩ ኢትዮጵያ ሐምሌና ነሐሴ ጎተራ የሚራቆትበት ጭጋግ አየሩን የሚሸፍንበት ስለሆነ ያኔ ተለይቶ የሚሄድ ሰው በክፉ ቀን እንደ ከዳ ወዳጅ ይቆጠራል።… መስከረም ግን የተስፋ አበባ የጨበጠች፣ በችቦ ወጋገን የደመቀች፣ በዜማ የታጀበች የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ናት፡፡ ስለዚህ የፍጥረት ሁሉ ልብ በደስታ ይፈነጥዛል፤ ወደ ፊት እያየ-ይጎመዣል፡፡
በመስከረም አበባ መሬት ላይ ብቻ ፈክቶ አያበቃም፤ ወንዶች ልጆች ወረቀት ላይ በየዓይነቱ ቀለም  ያጠቀሰ  አበባ ስለው ለሚወዱት ሰው፣ለጎረቤታቸው፣ደስታና ተስፋ ለሚመኙለት ወዳጅ ሁሉ “እንኳን አደረስዎ!” ብለው ይሰጡታል፡፡ አበባ ተቀባዩም እንኳን አብሮ አደረሰን! ብሎ ብሩን መዥረጥ አድርጎ ይሰጥና በዓሉን አብረው ያደምቁታል፡፡
በሌላም በኩል፣በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እርሻ ሲዳክር የከረሙ በሬ አንገቱን ቀና አድርጎ ሳር የሚነጨው  እምቦሳ የሚቦርቀው፣ጭነት ያጎበጠው የጋማ ከብት አዲስ ፀጉር የሚያበቅለው ይሄኔ ነው።
ይህ አዲስ መንፈስ፣ ይህ አዲስ ፅንስና ህይወት ደግሞ የሰው ልብ የጫረውን የውበት ስሜት፣ የምኞት አፀድ ያሰማምረዋል፡፡…. በዚህ የስሜት ምጥቀትና የምናብ ሃይል ከያኒው ከፍ ይላል፡፡ በሰማዩ መንገድ በምድር ሃዲድ ሽር ይልበታል፡-
እናም  ብዕሩን አንስቶ ስንኝ ይቋጥራል፤ ዜማ ያፈሳል፡፡ በእኛ ሀገር ለመስከረም ውበትና መልክ ከተቀኙት መካከል ሠዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ለዛሬው ፅሑፌ በእጅጉ ይገጥማል፡፡ “አንተ ነህ መስከረም” በሚል ርዕስ ፅፎ፣ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” በሚል መፅሀፉ ከታተሙት ጥቂት ስንኞች ለእማኝነት እጠቅሳለሁ፡-
ዕንቁጣጣሽ አንተ ስጦታህ የበዛ፣
ለሰው መታሰቢያ ውበት የምትገዛ፡፡
በሽቱ መዓዛህ ለውጠው ዓመቱን፤
 ይታደስ ያረጀው ፍጥረት ሌላ ይሁን፡፡

ፍየሎች ይዘላሉ ቅጠል  ይበጥሱ፤
ከተሰደዱበት ወፎች ይመለሱ፡፡
ይልቀሙት እህሉን፤ ይስሩ ቤታቸውን፤
 ይስፈሩበት ዛፉን፡፡
የደስ ደስ ያሰሙ ንቦች ይራኮቱ፤
ይንጠራሩ አበቦች ይንቁ ይከፈቱ፡፡
አንበሳና ግልገል በውስጡ ይፈንጩ፤
ከብቶች ሳሩን ይንጩ፡፡
 ሕጻናት ይሩጡ ይሳቁ ይንጫጩ፤
ከብቶች ሳሩን ይንጩ፡፡
ሕፃናት ይሩጡ ይሳቁ  ይንጫጩ፤

ዐደይ አበባ ነህ የመስቀል ደመራ፤
ጠረንህ አልባብ ነው አየርህ የጠራ፡፡
መልካም አዲስ አመት!!

Read 1083 times