Wednesday, 15 September 2021 07:04

ቺንዋ አቼቤን እንደማውቀው

Written by  ንጉጊ ዋቲያንጎ (Ngugi Wa Thiong’o) ትርጉም - ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

ከቺንዋ አቼቤ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘሁበትን አጋጣሚ ፈጽሞ አልረሳውም፡፡ ቦታው ካምፓላ ኡጋንዳ፣ ጊዜው ደግሞ 1961 እ.ኤ.አ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ Things fall apart መጽሐፉ ከወጣ ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡ እኔ ደግሞ በማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እና በዩኒቨርሲቲው በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚዘጋጅ ‹Penpoint› መጽሔት ላይ የታተመ የአንድ አጭር ልብወለድ ደራሲ ነበርኩ፡፡ Mugumo - ይሰኛል ርዕሱ... በእኔ ጎትጓችነት አቼቤ ብቸኛዋን አጭር ልብወለዴን ካነበበ በኋላ ጠቃሚ እርማቶች ሰጠኝ፡፡ በዚያን ጊዜ ለeastern africa literature bureau ለሚዘጋጅ የስነጽሁፍ ውድድር የምጽፈውን ወጥ ልብወለድ አጋምሼ እንደነበር አልነገርኩትም፡፡ መጽሐፉ በኋላ ‹The river between› በሚል ርዕስ ታትሞ ወጥቷል፡፡
ሁለተኛው ከአቼቤ ጋር የነበረኝ የመገናኘት ዕድል የሆነ ድራማዊ ነገር ነበረው፤ ቢያንስ ለእኔ፡፡ ይህ የሆነው አሁን ዝናው በናኘው እ.ኤ.አ የ1962ቱ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚጽፉ ደራሲያን ስብሰባ ጊዜ ነው፡፡ ከአቼቤ በተጨማሪ እንደ ወሌ ሾይንካ፣ ጀፒ ክላርክ፣ ለዊስ ኮሲና ብሎክ ሞዲሴኔ መድረኩን አድምቀውት ብርሃን አላብሰውት ነበር፡፡ ምስራቃዊው የአፍሪካ ክፍል በግሬ ኦጎት፣ ጆናታን ከሪያራ፣ ጆን ናጌንዳና እኔ ተወክሏል፡፡ የእኔ ውክልና የመጣው ‹Penpoint› እና ‹transition› መጽሔቶችና ላይ በጻፍኳቸው አጫጭር ልብወለዶች ጥንካሬ ነበር፡፡ በመርሃ ግብሮቹ ላይ እንደ ኪናዊ የልህቀት ማሳያ ተወስዶ ተደጋግሞ ውይይት የተደረገበት መጽሐፍ Things fall apart ሆኗል፡፡
ሆኖም በእጅጉ ያስደሰተኝ በመድረኩ ላይ እንደ ደራሲ ከመጋበዜ ይልቅ በኋላ ላይ weep not, child በሚል ርዕስ የታተመውን መጽሐፌን ረቂቅ ለአቼቤ የማሳየት ዕድል ማግኘቴ ነበር፡፡ በጊዜው አቼቤ Arrow of God የሚለው ልብወለዱን እየሰራ የነበረበት ወቅት በመሆኑ ረቂቁን ሊያይልኝ መፍቀዱ በራሱ የበጎነቱን ጥግ አስገንዝቦኛል፡፡ Arrow of Godን እየሰራ መሆኑን ያወቅሁት ዘግይቼ ቢሆንም ቅሉ... ልብወለዱን ለመጻፍ በሚያውለው ጊዜና በስብሰባው ተሳትፎው ምክንያት ሙሉውን የመጽሐፌን ትይብ ማየት ባይችልም ጠቃሚ እርማቶች ለመስጠት በሚበቃ ሁኔታ ተመልክቶልኛል። ከሁሉ በላይ ስለ መጽሐፌ የእርሱን መጻሕፍት ለሚያሳትምለት ዊሊያም ሔነመን በስብሰባው ላይ ወኪል ለነበረው ጁን ሚልነ ነግሮልኝ እሱም የማሳተም ፍላጎቱን ገለጸልኝ፡፡ weep not, child በኋላ በቺንዋ አቼቤ አርታኢነት በሄነመን ኢጁኬሽን ፐብሊሸርስ አሳታሚነት ታተመ። ይህ መጽሐፍ አሁን በዚህ አሳታሚ ስር ከታተሙ መጻሕፍት አራተኛው ብዙ የተነበበ መጽሐፍ ሆኗል፡፡
weep not, child ታትሞ ሲወጣ እኔ በኬንያው ኔሽን ጋዜጣ ላይ እሰራ ነበር። ጊዜው እ.ኤ.አ ሚያዚያ 1964... ኬንያም የመጀመሪያውን በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፈ ዘመናዊ ልብወለድ በኬንያዊ አፍሪካዊ ልጇ ስላገኘች ኮራች፡፡ ወይም ጋዜጦች በሚገባ ስላስተዋወቁት በጊዜው እንደዚያ ተሰምቶኛል፡፡ The Sunday nation እንዲያውም ከዋናው ነባር ጸሐፊያቸው ደ ቪለርስ ጋር ያደረኩትን ቃለምልልስ ይዞ ወጥቷል፡፡ ሲመስለኝ ሁሉም የተማረ ኬንያዊ ስለ መጽሐፉ ሰምቷል፡፡ በየመዝናኛው በተዟዟርኩ ቁጥር የማገኘው አዲሱ አፍሪካዊ ልሂቅ ትውልድ እንደ ኬንያዊ የ‹ቲንግስ ፎል አፓርት› መጽሐፍ ደራሲ ይቀበለኝ ነበር፡፡
ከዓመታት በኋላ የአቼቤ ሰባኛ ዓመት ልደት በአሜሪካ ኒው ዮርክ ባርድ ኮሌጅ ሲከበር በቦታው ለነበሩት ቶኒ ሞሪሰን፣ ወሌ ሾይንካ እና ሌሎችም በሕይወቴ ውስጥ በርካታ ጊዜ ሰዎች አቼቤ እየመሰልኳቸው እንደሚተዋወቁኝ ነገርኳቸው፡፡ ወሌ ሾይንካ በተራው ‹‹ከአፌ ነጠቅከኝ›› በማለት እርሱም እንደ እኔ በተደጋጋሚ ሰዎች በስህተት አቼቤ እንደሆነ አስበው እንደሚተዋወቁት አጫወተን፡፡
እውነታው ይሄ ነው፡፡ አቸቤ የHeinemann African writers series እና በአጠቃላይ የአፍሪካ ስነ ጽሁፍ ተለዋጭ ስም ነበር፡፡ ከአቼቤ ጋር ያልተመሳሰለ፣ ሥሙ በስህተት ያልተጠራ አንድም የእኛ ዘመን አፍሪካዊ ደራሲ አለ ብዬ አላምንም። እያንዳንዱ አፍሪካዊ ድርሰት ቲንግስ ‹ፎል አፓርትን› ይመስላል፤ ወይ ሊመሳሰል ይገደዳል፡፡ እያንዳንዱ አፍሪካዊ ደራሲ ደግሞ ቺንዋ አቼቤን... አቼቤ አይደለሁም ማለት፣ መቃወሙ እንኳን ሁልጊዜ የተሳካ አይሆንም፡፡ ይህን የመሰሉ ጥቂት ገጠመኞች ኬንያም ውስጥ፣ ከኬንያም ውጭ አጋጥመውኛል፡፡
የሚከተለው የመጨረሻ ገጠመኜ በ2010 እ.ኤአ. በጆሞ ኬንያታ አየር ማረፊያ ናይሮቢ የሆነ ነው፡፡ እኔ እና የ‹Nairobi Heat› ደራሲው አራተኛ ልጄ ሞኩማ inter-generational dialogue በሚል ጭብጥ በተዘጋጀው ‹Kwani festival› ለመሳተፍ ለጉዞ ኤርፖርት ነበርን፡፡ ሞኩማ እና እኔ የተጠየቅነውን መረጃ በሚገባ ሞልተን ወደ ኢሚግሬሽን [መስኮት] ስንጠጋ የሆነ ሰው ወደ እኔ መጣ፡፡ ዛምቢያዊ የሥነ-ጽሁፍ [ጥናት] ፕሮፌሰር መሆኑን እየነገረኝ እጆቹ ይንቀጠቀጡ ነበር፡፡
‹‹ይቅርታ አድርግልኝ ሚስተር አቼቤ፤ የሆነ ሰው ነው አንተን የጠቆመኝ፡፡ ለረጅም ዓመታት ላገኝህ እፈልግ ነበር፡፡››
‹‹አይ የምትለው ሰው እኔ አይደለሁም።›› አልኩት
‹ይሄውልህ አቼቤ... አቼቤን ተዋወቀው›› ብዬ ወደ ልጄ አመለከትኩት፡፡
በእኔ ቤት የሞኩማን የልጅነት ወዝ አይቶ አባባሌ ፌዝ መሆኑን በቀላሉ ይገነዘባል ብዬ ማሰቤ ነው፡፡ የእኛው ፕሮፌሰር ግን ለልጄ ሞኩማ የመቃወሚያ ፋታ እንኳን ሳይሰጠው እጁን አፈፍ - ጨበጠው። በመጨረሻ የሚያደንቀውን ሰው እጅ መጨበጥ በመቻሉ ፈንድቆ ሄደ፡፡ እስከ 2010 እ.ኤ.አ የዘለቀው ከአቸቤ ጋር የመመሳሰል የመጣረስ ዕጣ፣ አቼቤ ምን ያህል ወደ ረቂቅ የተረት ዓለም ሰውነት (mythical figure) እንደተሻገረ ማሳያ ይሆናል፡፡ አቼቤ እንደ ደራሲ፣ እንደ አርታኢ፣ እንደ ሰው በዘመናዊ የአፍሪካ ሥነጽሁፍ አድማስ ላይ በብቸኝነት የገነነ ምስል ነበር፡፡
አቼቤ በHeinemann African writers series ዋና አርታኢነቱ ለበርካታ አፍሪካዊ ደራሲያን መጎልበትና እውቅና ከፍተኛ እገዛ ያደረገ ሰው ነው፡፡ የአፍሪካዊያኑ ደራሲያን ክህሎት እንዲበለጽግ የጊዜ፣ የኃይል፣ የጽናት፣ እምነት በማሳደር ጭምር የተባበረ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ግን ፈጽሞ ሲኩራራ አይቼው አላውቅም፡፡ እንዲያውም የአፍሪካ ስነጽሁፍ አባትነቱን አጠራር ይቃወማል፡፡ እንደ ሰው ከጽንፎች ይልቅ መካከለኛውን መንገድ በጽናት የሚከተል ከዚህም ጽናቱ እውቀትን የሚሸምን ነበር፡፡ እና ደግሞ መከራን፣ ፈተናን በጽናት መጋፈጥ የሚችል!
Things fall apart ልብወለዱ በአፍሪካ ስነጽሁፍ ውስጥ በስፋት የተነበበና ለሌሎች እንደ መነሳሻ የሚሆን ዘመን አይሽሬ ሥራ ነው፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ለሰባኛ የልደት በዓሉ አከባበር ፊት ለፊት ባገኘሁት ወቅት ከእኔ ጋር ባለቤቴ እጀሪ፣ የአምስት ዓመቱ ልጄ ቲአንጎ እና የስድስት ዓመቷ ልጄ መምቢ አብረውኝ ነበሩ፡፡
ጀምስ ከሬይ የአቸቤን አሳታሚ ሳስተዋውቃቸው የአምስት ዓመቱ ልጄ ቲአንጎ እዛው በዛው የሚታተም ልብወለድ መጻፍ ፈለገ፡፡ በብጣሽ ወረቀት ላይ የሆነ ነገር ከጫጫረ በኋላ ለአሳታሚው ጀምስ ከሬይ አምጥቶ ሰጠው፡፡ ጀምስ በትህትና ተቀበለ፡፡ በቀጠሉት ሰዓታት ልጄ ቲአንጎ በርካታ ባለ አንድ ገጽ ‹ረቂቆችን› ለአሳታሚው ጀምስ አግተለተለ፡፡ ጀምስ አዲሱን ደራሲ ላለማጣት ሲል ፓርቲውን በሙሉ ልብ አልታደመም፡፡ የስድስት ዓመቷ ልጄ መምቢ መንገድ ደግሞ ሌላ ሆነ። አቼቤን መሳልን መረጠች፡፡ ባለቤቴ ከአጎቷ አቼቤ ጋር ፎቶ ትነሳ ዘንድ ባቀረበቻት ጊዜም ስዕሏን አበረከተች፡፡ መምቢ አሁን የሁለተኛ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ ናት፡፡ የአቼቤን ዜና እረፍት ባረዳኋት ጊዜ የልጅነት የመስመር ሙንጭርጭር የአቼቤ ስዕሏን አስታውሳ አወጋችኝ፡፡
አቼቤ ትውልዶችንና ድንበሮችን ይሻገራል፡፡ የአህጉሪቱ እያንዳንዱ ሀገር አቼቤን እንደ ራሱ ዜጋ ደራሲ ይናጠቀዋል። በመጻሕፍቱ ውስጥ የተካተቱ አንዳንድ አባባሎች እንደ ዓለማቀፋዊ ዕውቀት ተወስደው ተደጋግመው ይጠቀሳሉ። የአቼቤ ሕልፈት የአንድ ዘመን ፍጻሜን መጀመሪያ አመላካች ይሆናል፡፡ ሆኖም ኪናዊ መንፈሱ አሁንም በርካታ አፍሪካዊና የሌሎች ዓለማት ደራሲያንን ማነሳሳቱን ይቀጥላል፡፡ እሱ ጊዜያትና ማህበረሰቦችን ሁሉ የሚሻገር፣ የሚጠቀልል፣ የሚያቅፍ የበቃ መንፈስ ነው፡፡
/ንጉጊ ዋቲያንጎ ኬንያዊ ደራሲ ነው። ይሄን ፅሁፍ የከተበው በ2013 እ.ኤ.አ የአቼቤ ህልፈት የተሰማ ሰሞን ነበር/


Read 226 times