Print this page
Wednesday, 15 September 2021 07:14

የሳሚ ዳን የአዲስ ዓመት ስጦታ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

አርቲስት ሳሙኤል ብርሃኑ (ሳሚ ዳን) በሬጌ የሙዚቃ ሥልት አጨዋወቱ ይታወቃል፡፡ ሌላው መታወቂያው በሙዚቃ ሥራዎቹ ትላልቅ ቁምነገሮችንና መልዕክቶችን በማስተላለፍ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም “አስራ አንዱ ገፆች” እና “ከራስ ጋር ንግግር” የተሰኙ አልበሞችን ለአድማጭ አቅርቧል፡፡ ባለፈው ሳምንት ደግሞ  “ስበት” የተሰኘ  ሶስተኛ አልበሙን አውጥቷል፡፡ ለመሆኑ ለሙዚቃ አልበሙ ለምን ስበት የሚል ሥያሜ ሰጠው? አዲሱ አልበሙ በምን ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናሉ? አልበሙን በዚህ ወቅት ማውጣት ለምን መረጠ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአርቲስት ሳሚ ዳን ጋር በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች  ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-


 የአልበምህን መጠሪያ “ስበት” ያልከው ለምንድን ነው?
አልበሙ “ስበት” የተባለበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደምታውቂው ከበጎ ነገር ይልቅ መጥፎ ነገር እየበዛ፣ ሰላም እያጣን ጦርነት ውስጥ እስከ መግባት ደርሰናል፡፡ እናም  አሁን ካለንበት አስቀያሚ ሁኔታ አውጥቶ አንድ ወደሚያደርገን ሰላምና አንድነት ሊያመጣን የሚችል ነገር መፈለግ አለብን የሚል አቋም አለኝ፤ እንደ አርቲስት፡፡  እነዚህ አንድ የሚያደርጉን የስበት ሀይሎች  ሰላም፣ፍቅር አንድነትና መከባበር ናቸው። እነዚህ የስበት ሀይሎች ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሰጠን ፀጋዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የስበት ሀይሎች እንድንቀራረብና አንድ እንድንሆን ያደርጋሉ። ዋናው የ“ስበት” ሀሳብ፤ የሰው ልጅ ራሱን ለበጎና መልካም ነገር ካሰለጠነና ካዘጋጀ፣ መልካም ነገሮችን መሳብ ይችላል፤ ያን ጊዜ ዙሪያው ሁሉ መልካም ይሆናል በሚል  ሀሳብ ተነስተን ነው የአልበሙን መጠሪያ “ስበት” ያልነው፡፡
በአልበሙ ውስጥ “ስበት” የሚል ዘፈን አለ ወይስ አጠቃላይ የእልበሙ መጠሪያ ነው?
“ስበት” የሚል ራሱን የቻለ ዘፈን የለውም፤ ነገር ግን በአልበሙ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ዘፈኖች ከላይ ስለ ስበት የገለፅኩልሽን ሀሳብ ስለያዙ የአልበሙ አጠቃላይ መጠሪያ “ስበት” ሆኗል፡፡
ከአልበምህ ውስጥ “ሀገር ማለት” የሚለውን ዘፈን ግጥም ለማየት ሞክሬ ነበር፡፡ ሌሎቹስ ምን ዓይነት ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያነሱ  ናቸው?
በአልበሙ ውስጥ 13 ዘፈኖች ናቸው የተካተቱት፡፡  በስልተ ምት ደረጃ ያው በአብዛኛው የምታወቅበት የሬጌ ስልት ምቶችን ይዟል፡፡ አሁን ደግሞ ዘመኑ የፈጠረልንን አዳዲስ ድምጾችን ዲጄ ሚላ ከሚባል አቀናባሪ ጋር ሰርተናል። ምክንያቱም ከምታወቅበት ሬጌ ወጣ ብዬ አዲስ ድምፅ፣ አዲስ ጣዕምና ቀለም ለመፍጠር ሞክሬያለሁ፡፡ ያው በዚህም ውስጥ ማለፍ ስለምፈልግ ማለቴ ነው፡፡ አቀናባሪው ኪሩቤል ተስፋዬ ደግሞ አንድ ሀገራዊ ሙዚቃን ወደ ዘመናዊ አምጥቶ ሰርቶልኛል - “ፀዳል” የሚለውን፡፡ ሌሎች ዘጠኝ ዘፈኖችን ከዚህ ቀደም አልበሞቼን አብሮኝ የሰራው ኤንዲ ቤተ ዜማ ነው የሰራው፡፡ በአጠቃላይ ዲጄ ሚላ ሶስት፣ ኤንዲ ቤተ ዜማ ዘጠኝ፣ ኪሩቤል ተስፋዬ ደግሞ አንድ ዘፈን ሰርቶ ከፍ ባለ ሀገራዊ ሀሳብ በአዳዲስ ከለርና ድምፅ ጥሩ አልበም ሆኖ ወጥቷል ብዬ አስባለሁ፡፡ አልበሙ ገና ዛሬ ነው የወጣው፤ ቀሪውን ግብረ መልስ ከአድማጭ ነው የምንጠብቀው ማለት ነው።
ሌላው ቅድም “ሀገር ማለት”ን አንስተሻል፤ ሀገርን ለመግለፅ የሰራነው ነው፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው እንደ “ምንም አይደል” አይነት ሥራዎችም አሉ- በአልበሙ ውስጥ፡፡ “ሙከራችን ባይሳካም ጤናችንና ተስፋችን እስካልሞተ ድረስ ሁሉም መልካም ይሆናል… ምንም አይደል፤ ካጣነው ደግሞ በእጃችን ያለው ይበልጣል፤ ምንም አይደል ተስፋ አንቁረጥ” የሚል ይዘት ነው ያለው፡፡ ሌላው “ፍቅር ሰላም” የሚለው ዘፈን ለምሳሌ በአሁኑ ሰዓት በዋናነት የሚያስፈልገን ፍቅርና ሰላም ነውና፣ ለዚህ ሁላችንም ማድረግ ያለብንን አበርክቶ የሚያስታውስ ነው፡፡ ፍቅርና ሰላም ዝም ብሎ የሚገኝ ነገር አይደለም፤ ሁሉም ለፍቅርና ሰላም ራሱን ማዘጋጀት በዚያም ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በስሜትና በንዴት ከተነዳን እንጠፋለን፤ ረጋ ብለን ማሰብ ማሰላሰል አለብን የሚል መልዕክት ይዟል፡፡ ሌላው “መንገዱ ላይ” የሚለው ዘፈን እስካሁን በመጣንበት መንገድ ስንት ነገር አጣን ዋጋ ከፈልን፣ አሁንስ የያዝነው መንገድ እስከየት ይወስደናል፤ ይህን ዋጋ እየከፈልንበት ያለውን መንገድ በሌላ አዲስና ጤናማ መንገድ ለመቀየር ምን ማድረግ አለብን? የሚል የሚኮረኩር…. ሁላችንም ወደ ውስጣችን እንድናይ የሚያደርግ ነው፡፡ ብዙ የሚያስማሙንን ነገሮች እየተውን፣ የመለየት መንገድ ከመምረጥ አንድ የሚያደርጉን መንገዶች ላይ ማተኮር የለብንም ወይ እያለ የሚጠይቅ ነው፡፡
13ኛው ዘፈን ደግሞ “የመውጫ ሀሳብ” የሚል ርዕስ ያለው ነው ….
ትክክል ነሽ፤ “የመውጫ ሀሳብ”ን ብታይው ሶስት ዘመናትን የሚፈትሽ ነው፡፡ አባቶቻችን እንዴት ሆነው እንዴት አድርገው ሀገር እንዳስረከቡን፣አሁን ያለነው ትውልድ በክብር የተረከብነውን ሀገር ለመጪው ትውልድ በክብር ማስረከብ ሲገባን ጭራሽ የመጪውን ትውልድ አገር እንዴት እየቀማነው እንደሆነ፣ መጪው ትውልድ ምን ፍርድ እንደሚጥልብን ተጠያቂነታችንን ሁሉ የሚያሳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ያለፈውን አሁን ያለውንና መጪውን ዘመን የሚፈትሽ ነው፡፡ በፊት አንድ ሆነው የውጪ ወራሪን መክተው ሀገር አስረከቡን፤ እኛ ያንን ታሪክ ከመድገም ይልቅ እርስ በእርስ የማንስማማ በጦርነት ጎራ የምንፋለም ሆነን ተገኘን፡፡ በዚህ አያያዛችን ለመጪው ትውልድ ሙሉ ሀገር እናስረክባለን ወይ የሚለው ነገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል፡፡ ይሄ ጉዳይ ትኩረት ይሻልና ይህን በደንብ አድርጎ የሚያሳይና የሚያሳስብ ነው- “የመውጫ ሀሳብ” ዘፈን፡፡ የዘፈኑ ስታይል አሁን ያለው የዘመኑ ስታይል ቢሆንም፣   የገለፅኩልሽን ሀሳብ በጥልቀት የሚፈትሽ ነው፡፡ በአጠቃላይ “ስበት” አልበም እንዲህ አይነት ወቅታዊ ጉዳዮችን እያነሳ ልብ ያላልናቸውን ነገሮች በጥልቀት እንድናስብ የሚያደርግ ነው፡፡
በአብዛኛው ሳሚ ዳን የሚታወቀው የራሱን ግጥምና ዜማ በመስራት ነው፡፡ አሁንስ እንደ ቀድሞው የአዲሱ አልበሙን ግጥምና ዜማ ራሱ ሰራ ወይስ ሌሎች ባለሙያዎችን አሳተፈ?
በእርግጥ የአሁኑም አልበም ላይ 13ቱንም ግጥምና ዜማዎች የፃፍኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ቅድም እንደገለፅኩልሽ በዚህ አልበም አዲስ ነገር የምለው የሀሳቦቹ ጠንካራነት እንዳለ ሆኖ አዳዲስ ድምጽና ከለሮች ከአዳዲስ አቀናባሪዎች ጋር መስራቴ ነው፡፡ በፊት እኔና ኤንዲ ቤተ ዜማ ብቻ ነበርን የምንሰራው፤ አሁን ላይ ኪሩቤል ተስፋዬና ዲጄ ሚላን አሳትፈናል፤ አዳዲስ ድምጾችን ጨምረናል፡፡ ግጥምና ዜማ ግን አሁንም ሁሉንም ራሴ ነኝ የሰራሁት፡፡ አልበሙ ከ“ከራስ ጋር ንግግር” እና ከ”11ዱ ገጾች” በተለየ ሞቅ ይላል፡፡ አዳዲስ ጣዕሞችም ተጨምረውበታል፡፡
በአምስት ዓመት ውስጥ ሶስት አልበሞችን ሰርተሃል፤ በሰባት ዓመት ውስጥ የአልበምህን ቀጥር አራት ለማድረስ እቅድ እንዳለህም ነግረኸኛል፡፡ እንዲህ ቶሎ ቶሎ አልበም ማውጣት አይከብድም? ምክንያቱም አንዳንድ አርቲስቶች ሰባት ዓመት ስምንት ዓመት ቆይተው ነው አንድ አልበም የሚሰሩት፡፡ ቆይተው የሚያወጡት ደግሞ ጥራቱን ለመጠበቅ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ?
በእኔ እምነት አንድ የጥበብ ስራ እንዴ ከተፈጠረ በኋላ ሰው ጆሮ ሳይደርስ መቆየት የለበትም፡፡ አንዳንድ ግጥምና ዜማ አንዴ ከፈጠርሽው በኋላ የፈለገውን ያህል ጊዜ አንቺ ጋር ብታቆይውና ብታሽው የምታስተካክይው ነገር አምስት በመቶ አይሆንም፡፡ 95 በመቶው እዛው ላይ ነው የሚሆነው፡፡ በአብዛኛው እንዲያውም መቶ በመቶ ከነበረበት አትቀይሪውም፤ አንዴ ፈጥረሽዋል፡፡ ከዚህ አልፈሽ አንዴ የፃፍሻቸውን ነገር አንቺ ጋር አክርመሽ ማሽሞንሞንና ማሸት ወይ ለማበላሸት ነው አሊያም በቃ ለማስቀረት ነው፡፡ አየሽ ፈጠራ አንዴ ሲመጣልሽ አውርደሽ ነው የምትጨርሺው፡፡ እና ያንን የፈጠርሽውን ነገር አግተሽ ይዘሽ ማቆየቱን እኔ በበኩሌ አልስማማበትም፡፡
የአልበሙ ሽያጭ በሲዲ ብቻ  ነው ወይስ  በኦንላይንም ይሸጣል?
ሁሉንም አይነት ፕላትፎርሞች ተጠቅመናል። በሲዲም ይሸጣል፤ በኦንላይንም እንደነ ሲዲ ቤቢ፣ አፕሚዩዚክና ሌሎችም ላይ ለሽያጭ ቀርቧል። አማዞንም ላይ ይገኛል።
እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣትም ሆነ እንደ ኪነ-ጥበብ ሰው የአገርህን ሁኔታ በንቃት ትከታተላለህ ብዬ አስባለሁ። የሰራኸውም አልበም ይህን የሚያሳይ ነው፡፡ ግን አሁን አገር በውጥረት ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ሰው ጊዜ ወስዶ ሙዚቃ የማዳመጥ ፍላጎት የለውም የሚል አስተያየት  እሰማለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር፣ አልበሙን በዚህ ጊዜ ማውጣትህ አላስፈራህም?
እንደኔ እንደኔ እንዲያውም በዚህ ሰዓት ነው ሙዚቃ ይደመጣል ብዬ የማስበው። አሁን እኛ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ነን። የኔን “ሀገር ማለት” የተሰኘውን ዘፈኔን ግጥም አይተሽዋል። ይህ ግጥም ዘፈን  ሆኖ ሲደመጥ ሀገርን በትልቅ ደረጃ ስሎ የማሳየት ነገር አለው። ይህንን ዘፈን በምንሰማበት ጊዜ ወደ ውስጣችን እንድናይና በጥልቀት እንድናስብ ያደርገናል። ለምሳሌ “ፍቅር ሰላም” ስለ ፍቅርና ስለ ሰላም ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው። ሰው ሰላምና ፍቅር በመፈለግ ላይ ነው። ይሄ በሙዚቃ መልክ ሲመጣ የውስጡን ሀሳብና ፍላጎት ስለሚገልፅለት ያዳምጠዋል። ያኔ እኛ ስንራብ የውጪዎቹ አርቲስቶች “We are the world” ብለው አቀንቅነው እኮ ነው ብዙ ሚሊዮን ዶላር ሰብስበው ያመጡልን። አሁንም ችግር ውስጥ ነን። አገር ውጥረት ላይ ናት። ችግራችንን በሙያችን ለመግለጽ የመፍትሄ መንገዶችን ለመጠቆም እኛም ጋር አቅም አለ፣ ሀሳብ አለ፣ ብለን ነው የሰራነው። ስለዚህ እንደውም የኪነ-ጥበብ አስፈላጊውና ትክክለኛው ሰዓት አሁን በመሆኑ አድማጭ እናጣለን የሚል ቅንጣት ጥርጣሬ የለንም። ዘፈን ለፌሽታ ጊዜ ብቻ እኮ አይደለም የሚሆነው። እኔ እንዲያውም “ፍቅር ሰላም”ን፣ “ሀገር ማለት”ን፣ “ምንም አይደል”ን፣ “የመውጫ ሀሳብ” የሚለውንና ሌሎቹንም ትልልቅ ሀሳቦች ያለቸውን ሙዚቃዎች ሰው እንዲያደምጥልኝና አጽንኦት እንዲሰጥልኝ እፈልጋለሁ።
ለአዲሱ ዓመት ምን ትመኛለህ?
አሁን ሁሉንም  ሰቅዞ የያዘው ወቅታዊው የሀገራችን ሁኔታ አለ። ህዝብም ወዴት እያመራን ነው እያለ ነው። እኛ ደግሞ በአዲሱ ዓመት ወደ ራሳችን መሳብ የምንፈልገው ምንድን ነው እያልኩ አስባለሁ። በአንደኛው ቋት ውስጥ ሰላም፣ ፍቅር መተሳሰብና መከባበር አለ። በሌላኛው ቋት ውስጥ ደግሞ ጦርነት፣ መናናቅ አለ። እኛ ወደ ራሳችን መሳብ ያለብን የትኛውን ነው። መጀመሪያ ላይ እንደገለጽኩት፤ አንድ ሰው ለበጎ ነገር ራሱን ካሰለጠነ መልካም ሀሳቦችን፣ መልካም ሰዎችንና መልካም ነገሮችን ይስባል። በዙሪያው በሙሉ መልካም ነገር ይስባል። እናም በአዲሱ ዓመት የምመኘው፣ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ወደ ራሳችን በመሳብ ዙሪያችንን መልካም እንድናደርግ ነው።
ዙሪያችንን በጥሩ ነገር ስንከብ እረፍት እናገኛለን፤ ወደ ቀደመ ሰላማችን እንመለሳለን። መተሳሰብ እንጀምራለን፤ አገራችንንም አናጣትም። ይህ እንዲሆን ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለመተሳሰብ፣ ለመደማመጥና ለመከባበር ሁላችንም መቆም አለብን ነው የምለው፡፡ በ2014 ዓ.ም ይህን ፈጣሪ እንዲያድለን ነው የምመኘው።

Read 1001 times