Saturday, 18 September 2021 16:45

የአማራ የአደጋ ጊዜ ገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴ” ለተፈናቃዮች ከ1ሚ. ዶላር በላይ አሰባሰበ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 12 ሚ. ብር የሚያወጣ የሰብአዊ እርዳታ ሰኞ ወደ ደሴ ይጓጓዛል
                               
                  በመላው ዓለም የሚኖሩ የአማራ ሲቪክ ማህበራት የሚሳተፉበት “የአማራ የአደጋ ጊዜ ገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴ”፣  በትህነግ ወረራ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ የሚውል 1. ሚ ዶላር ማሰባሰብ መቻሉን የኮሚቴው ተወካዮች አስታወቁ።
የኮሚቴው ተወካዮች ትላንት ረፋድ ላይ በጣይቱ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ1. ሚ. በላይ ዶላር መሰብሰብ መቻላቸውን ጠቁመው፣ በዚህ መፈናቀል ወቅት ለተወለዱ ጨቅላ ህፃናት፣ ለአራስ እናቶችና በረሃቡ በጣም ለተጎዱ ወገኖች በአስቸኳይ የሚደርስ  የ12 ሚ. ብር የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እርዳታ የፊታችን ሰኞ ወደ ደሴ እንደሚጓጓዝ የኮሚቴው ተወካይ አቶ ጌታቸው በየነ ተናግረዋል። ከሚጓጓዙት መካከል 1 ሺህ 500 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ ለአራስ ህፃናት መንከባከቢያ አልባሳት፣ ብርድ ልብስና ፍራሽ፣ አልሚ ምግብ እንዲሁም ለአራስ እናቶች የሚሆን አልሚ ምግብ እንደሚገኙበት አቶ ጌታቸው ገልፀዋል።
አማራው በዜግነቱ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሚኖርባቸው የሀገሪቱ ማዕዘናት በፖለቲካዊ እቅድ ተለይቶ ሲገደል፣ ሲፈናቀልና ሲሰደድ፣ ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጦ በችግር ሲማቅቅ በርካታ አስርት ዓመታትን ማሳለፉን  የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ የለውጥ ጊዜያት በተባሉት ባለፉት 3 ዓመታትም ቢሆን ከቀደመው በባሰ መልኩ አማራው ዘር ማንዘሩ እየተጨፈጨፈ ቀዬውና ከተሞቹ እየወደሙ፣ ከሞት የተረፈው በሚሊዮን የሚቆጠር አማራ ደግሞ በገዛ አገሩ ስደተኛ ሆኖ ያለ በቂ መጠለያ፣ የእለት ጉርስ ተመፅዋች ሆኖ መቀጠሉን በምሬት ተናግረዋል።
ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ አሸባሪው የትህነግ ሃይል ከስምንት ወር ሽሽት በኋላ  ዳግም በማንሰራራት፤ አማራን ኢላማ አድርጎ በከፈተው ጦርነት በአማራ ክልል ሰሜናዊ ክፍል በኮረም፣ አላማጣ፣ ቆቦ፣ላሊበላ፣ አደርቃይ፣ ማይካድራ፣ ጠለምት፣ ዋግህምራ፣ ንፋስ መውጫ፣ ጋይንትና በአጎራባች ወረዳዎች ከ1ሚ በላይ ሰላማዊ ዜጎች መፈናቀላቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው ፣ ባለፉት 3 ዓመታት በወለጋ፣ በቤንሻንጉል፣ በሻሸመኔና አካባቢው፣ አጣዬና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች አማራው በማንነቱ ብቻ በደረሰበት ጥቃት ከ1.5 ሚ በላይ የአማራ ህዝብ በአማራ ክልል ያለበቂ እርዳታና ድጋፍ እየተንገላታ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
አሁንም በትህነግ ወረራና፣ ጭፍጨፋ አማራው ከቀዬው ከመፈናቀሉም በተጨማሪ እጅግ አሰቃቂ  የሰብአዊ መብት ጥሰት እየደረሰበት እንደሆነ የገለፁት የኮሚቴው ተወካይ፤ የማይካድራ፣ የጋሊኩማ፣ የአጋምሳ እና የጭና ተክለሃይማኖት የጅምላ ጭፍጨፋዎች የወራሪውን የትህነግ ሃይል ጭካኔ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
ሞት፣ መቁሰል፣ የአካል ጉዳት፣ ተገድዶ መደፈር፣ መፈናቀልና መሰደድ፣ የምግብ እጥረትና ወረርሽኝ፣ የምጣኔ ሀብት ውድመትና የድህረ ስቃያት ጭንቀት (Post Traumatic stress disorder) የወረራና የጦርነት ፍሬዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ተወካዩ በነዚህ ክፉ ተግባራት ሳቢያ በርካታ የአማራ ወገኖች ቆስለው በደሴ፣ በቦሩ፣ በኮምቦልቻ፣ በሀይቅ፣ በጎንደር፣ በደባርቅና በሌሎች ከተሞች ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው ቢሆኑም፣ ከተጎጂው ብዛትና ከሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ማነስ አንፃር፣ በተለይ በጎንደርና በወሎ ሆስፒታሎች ህክምና ለማግኘት ወረፋ የሚጠብቀው ወገን በርካታ መሆኑ ተጠቁሟል።
ለዚህ አስከፊ ሁኔታ ለተዳረገው የአማራ ህዝብ ሰብአዊና መሰረታዊ እርዳታ ለማቅረብ ቀድሞ መገኘት ያለበት ከአብራኩ የወጣው ልጁ መሆኑን የተናገሩት ተወካዩ፤ ይህንን ፈተና ለመጋፈጥ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ የአማራ ሲቪክ ድርጅች በጋራ “በቃን” በሚል መሪ ቃል፣ የአማራ የአደጋ ጊዜ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻ በማካሄድ ከ1.ሚ በላይ ዶላር መሰብሰብ መቻሉንና የሀብት ማሰባሰቡ ዘመቻ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።
ይህ ስብስብ ከዚህ ቀደምም በአማራ መልሶ ማቋቋሚያ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻን በመምራት፣ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር በማሰባሰብ ከወለጋ፣ ጉራፈርዳ፣ ከመተከል ከአጣየና ከሌሎችም አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ፣ የአልባሳትና የህክምና እርዳታ ማድረጉን አቶ ጌታቸው አስታውሰዋል። ከሀምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮም በመካሄድ ላይ ላለው የአማራ የአደጋ ጊዜ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻ፣ ከ1 ሚ በላይ ዶላር ማሰባሰብ መቻሉንና በጁላይ 31 በተደረገው ቴሌቶን ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ዶላር እንዲሁም ነሀሴ 15 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው ሁለተኛ ዙር ቴሌቶን ከ300 ሺህ በላይ ዶላር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።  በአሁኑ ሰዓት ለወገን ደራሽ ከሆነው የዲያስፖራ ማህበረሰብ የተሰበሰበውን እርዳታ በረሃብ እየተሰቃየ ላለው ወገን ለማድረስ ዝግጅት ጨርሰናል ያሉት ተወካዩ በተጨማሪም አስቸኳይ ህክምና እርዳታ ለመስጠት በጎ ፈቃደኛ ሃኪሞችን በየአካባቢዎቹ ለማሰማራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የፊታችን ሰኞ 12 ሚ ብር የሚያወጣ የምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እርዳታ ወደ ደሴ እንደሚጓጓዝ ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው በመጨረሻም፣ ለኢትዮጵያ መንግስት ባስተላለፉት ጥሪ፤ በአማራው ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ መላው ኢትዮጵያዊያን በረሃብ እያለቀ ላለው አማራ ወገኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ፣ መገናኛ ብዙኃን በአማራው ላይ እየደረሰ ያለውን እልቂት በግልጽ በመዘገብ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ዓለማቀፍ ማህበረሰብም ለትግራይ ክልል እየተደረገ ያለውን አስደናቂ የሰብአዊ ድጋፍና ትኩረት በሌላውም የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለይም በአማራና በአፋር ክልሎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሰብአዊነቱን እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል።
“በቃን” በተሰኘው የአማራ የአደጋ ጊዜ ገንዘብ ማሰባሰቢያ የሚሳተፉትም፡-  የአማራ ማህበራት ህብረት በሰሜን አሜሪካ (ፋና)፣ የአሜሪካ ማህበር በአሜሪካ፣ የአማራ ባለሙያዎች ማህበር፣ የአማራ ማህበር በኮሎራዶ፣ የአማራ ህዝብ ሲቪክ ድርጅት፣ የአማራ ማህበር በጆርጂያ፣ የአማራ ማህበር በሲያትል፣ የአማራ ማህበር በካሊፎርኒያ፣ የአማራ ማህበር በሎስ አንደለስ፣ የአማራ ማህበር በኔቫዳ፣ የአማራ ህብረተሰብ ቅርስ በሚኒሶታ፣ በካናዳ የአማራ ማህበረሰብ ህብረት (Casa)፣ ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረትና ሌሎችም ሲቪክ ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል።
ጳጉሜ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰሜንና ከደቡብ ወሎ አስተዳደሮች በወጣ መረጃ፤ 234 ሺህ 249 ተፈናቃዮች በደሴና በኮምቦልቻ ከተሞች እንደሚገኙ  ተገልፆ የነበረ ሲሆን ከትላንት በስቲያ ሀሙስ የተፈናቃዮቹ ቁጥር 290 ሺህ መድረሱ ታውቋል። ኮሚቴው ከወሎ በመቀጠል ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ወደ ጎንደር ለማጓጓዝ ማቀዱን የተገለጸ ሲሆን  በተለይ በትህነግ ቁጥጥር ስር ያሉ የሰሜን ወሎ ከተሞች ነዋሪዎች ስቃይና እንግልት እጅግ እንደሚያሳስበው ጠቁሞ፤ አለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች  ለእነዚህ አካባቢዎች ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።

Read 14286 times