Saturday, 18 September 2021 16:46

ጦርነት ስደትና ረሃብ በሰሜን ወሎ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(10 votes)

- ከሰሜን ወሎ ተፈናቅለው ደሴ ከተማ የገቡ ከ3000 ሺ በላይ ወገኖች አሉ
     - በመጠለያ ካምፖቹ ውስጥ ባለፈው ነሐሴ ወር ብቻ 118 ተፈናቃይ ሴቶች ወልደዋል
     - ለተፈናቃዮቹ አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በደሴ ተካሂዷል
     - ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ እርዳታ አጥተው ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎች የሉም ብሏል
                        
          የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በተቆጣጠሯቸው የሠሜን ወሎና የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች እጅግ ለከፋ ስደትና ረሃብ መጋለጣቸውን የአካባቢው የዓይን  እማኞች ይገልፃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ግን እርዳታ አጥተው ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎች የሉም ብሏል፡፡
ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም በማወጅ የትግራይ ክልልን ለቆ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በሚሰነዘሩ ጥቃቶች፣ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችና በአፋር ክልል ህዝቦች ላይ መጠነ-ሰፊ ጉዳት ደርሷል፡፡ በተለይም በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎና ዋግ ኸምራ አካባቢዎች በህወኃት ታጣቂ ኃይሎች በተፈፀመው ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ሲገደሉ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ደሴ ከተማ ውስጥ ከሚገኙት 14 የተፈናቃዮች መጠለያ  ካምፖችና ት/ቤቶች አንዱ በሆነው ዳውዶ ት/ቤት ውስጥ  የምትገኘው ወ/ሮ ወጋየሁ ይማም፣ ተወልዳ ካደገችበትና ወልዳ ልጆቿን ከምታሳድግበት ሰሜን ወሎ ዞን ሃራ ከተማ፣ ከሞቀ ጎጆዋ ተፈናቅላ ወደ ደሴ ከተማ በመምጣት፣ በመጠለያ ጣቢያው መኖር ከጀመረች 5 ሳምንታት አልፈዋታል፡፡ ወ/ሮ ወጋየሁ የህወኃት ታጣቂ ኃይሎች ወደ አካባቢያቸው ከመድረሳቸው ሶስት ቀናት በፊት ነበር 3 ልጆቿን ይዛ ለስደት የወጣችው።
በንግድ ስራ የሚተዳደረው ባለቤቷ የሱፍ ዘሩ፤ በአካባቢው የሚታየው  ስላስፈራው ነበር ሚስቱንና ልጆቹን  ወደ ደሴ ከተማ እንዲሸሹ አድርጎ እሱ ንብረቱን ሊጠብቅ እዛው ሃራ ከተማ ውስጥ የቀረው፡፡ ወ/ሮ ወጋየሁ ደሴ በገባችበት ጥቂት ቀናት ውስጥ ባለቤቷ ስላለበት ሁኔታ እንደሷ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ወዳለችበት በሚመጡ የአካባቢዋ ሰዎች አማካኝነት ትሰማ ነበር፡፡ ላለፉት 3 ሳምንታት ግን ባለቤቷ ስላለበት ሁኔታ የሚነግራት በማጣቷ ይሙት ይኑር እንኳን ሳታውቅ እጅግ በበዛ ሃዘንና ሰቆቃ ውስጥ ትገኛለች፡፡
እነ ወጋየሁ ባረፉበት  የዳውዶ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በአንድ ክፍል ውስጥ 30 እና 40 እየሆኑ ያድራሉ፤ ምግብ፣ልብስና ህክምና በበቂ ሁኔታ ባለማግኘታቸውም ብዙዎች ለከፋ የጤና ችግርና ለከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡  የደሴ ከተማ ህዝብና መንግስት ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን የምትገልጸው ወጋየሁ፤ ይህ ግን በቂ አይደለም፤ 3 ልጆችን ይዤ እስካሁን ለመቆየት የቻልኩት ባለቤቴ በቋጠረልኝና ከጉዞ በተረፈችኝ ጥቂት ገንዘብ ምግብ እየገዛሁ ነበር፡፡ እዚህ ደሴ ውስጥ አንድ ደረቅ ዳቦ 12 ብር እየገዛሁ ልጆቼ ሕይወታቸው እንዲቆይልኝ ሳደርግ ነው የቆየሁት፡፡ አሁን ግን ያንን ማድረግም አልችልም ምንም የቀረኝ ገንዘብ የለም በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የሚሰጠን እርዳታ ህይወታችንን እንኳን ለማቆየት የሚያስችለን አይደለም-በዚያ ላይ ባለቤቴ ያለበትን ሁኔታ አለማወቄ እጅግ ያስጨንቀኛል፤ መንግስት እንዲደርስልንና ከዚህ መከራ እንዲታደገን ነው የምለምነው ትላለች፡፡
በአሁኑ ወቅት በደሴ ከተማ ውስጥ የተቋቋሙት 14 የመጠለያ ካምፖችና ት/ቤቶች እነዚህኑ ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው የሚመጡ ዜጎችን ተቀብለው ለማስተናገድ አቅም እያጠራቸው መሆኑን የዓይን እማኞች ይናገራሉ፡፡ በመጠለያ ካምፖቹ ውስጥ ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል ህጻናትና ነፍሰ ጡር እናቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡
በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ሴቶችና አቅመ ደካሞች በቁጥር በርከት ይላሉ፡፡ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከገቡ ነፍሰ ጡር እናቶች መካከል በነሀሴ ወር ውስጥ ብቻ 118 የሚሆኑት እዛው መጠለያ ጣቢያው ውስጥ መውለዳቸውን ከስፍራው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
ደሴ ቅዳሜ ገበያ ት/ቤት ውስጥ ባለው መጠለያ ውስጥ ከ3 ልጆቿ ጋር የምትገኘው ወ/ሮ አያል፤ በዚሁ መጠለያ ካምፕ ውስጥ አራተኛ ልጇን ለመገላገል ተገዳለች፡፡ አያል  መጠለያ ጣቢያው አቅራቢያ በሚገኘው ጤና ጣቢያ ውስጥ ልጇን እንድትገላገል ከተደረገ በኋላ ወደ ነበረችበት መመለሷንና አሁን በአንድ ክፍል ውስጥ ከሚገኙ 30 ተፈናቃዮች ጋር በጋራ በምትኖርበት መጠለያ ውስጥ ከነ አራስ ልጇ  እየኖረች እንደሆነ ገልፃለች፡፡ አያል ምግብ በበቂ ሁኔታ ባለማግኘቷ ለልጇ አስፈላጊውን የእናት ጡት ወተት ለመስጠት እንደተሳናትና  የአኗኗር ሁኔታዋም ለበሽታ ሊያጋልጠን ይችላል የሚል ስጋት እንዳለባትም ትናገራለች፡፡
በህወኃት ታጣቂ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኙት የሰሜን ወሎ ዞን ወረዳዎችና የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ ወገኖች እጅግ ለከፋ ስቃይና ረሃብ መዳረጋቸውንም  በደሴ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮቹ፤ ይናገራሉ፡፡ አካባቢዎቹን የህወኃት ታጣቂ ኃይሎች የተቆጣጠሯቸው በመሆኑ በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ለማወቅ እንደተቸገሩ የሚናገሩት እነዚህ ተፈናቃዮች እንደ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያ  ያሉ  መሰረተ ልማቶች በመውደማቸው ምክንያት ከጥይት የሚተርፉት  ቤተሰቦቻቸው በረሃብና  በህክምና እጦት ሳቢያ ለሞት የሚዳረጉ መሆናቸው አይቀሬ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን የነበሩ 6 ሆስፒታሎችና በርካታ የግል የጤና ተቋማት ለነዋሪው ህዝብ የህክምናና የማዋለድ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር የገለፁት እነዚህ ተፈናቃዮች፤ የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች አካባቢዎቹን እንደተቆጣጠሩ በመጀመሪያ የወሰዱት እርምጃ እነዚህን ተቋማት ማውደም መሆኑንና ተቋማቱ ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጪ  እንዲሆኑ መደረጋቸውን ይናገራሉ፡፡
በእነዚህ አማጺያኑ ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖች እጅግ ለከፋ ረሃብ ለበሽታና ለሞት የተጋለጡ መሆናቸውንም ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ፡፡ መንግስት ይድረስልን ሲሉም ይማፀናሉ፡፡
ይህን የተፈናቃዮቹን ተማፅዕኖ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አይቀበለውም። እንዲያውም በኢትዮጵያ እርዳታ አጥተው ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎች የሉም ይላል፡፡ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አያድሩስ ሃሰን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች መንግስት ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ አንድ ቦታ በማሰባሰብና ሁሉም አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ በማመቻቸት ላይ በመሆኑ እስካሁን እርዳታ አጥተው ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎች የሉም። የኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ፈጣን ምላሽ ማስተባበሪያ ዳይሬክተሩ አቶ ጀምበሩ ደሴ በበኩላቸው፤ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በአጎራባች አካባቢዎች ላሉ ወገኖች የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በህወኃት ቁጥጥር ስር ወደሚገኙ ቦታዎች ግን መግባት ባለመቻሉና የመገናኛ አገልግሎት ባለመኖሩ ነዋሪዎቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ አለመቻሉን ተናግረዋል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ወደ ሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታ ማጓጓዝ ተጀምሯልም ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው ደሴ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች  በምግብና መድሃት እጥረት ሳቢያ ለሚሰቃዩ ዜጎች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ከትናንት በስቲያ በደሴ ከተማ ውስጥ አድርገዋል፡፡
“ትኩረት በሰሜን ወሎ ለሚገኙ ወገኖቻችን” እና “ወሎ እየተራበ ነው” የሚሉ መልዕክቶችን ያነገቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድግ በረሃብ እየሞቱ ነው ላሏቸው የሰሜን ወሎ ነዋሪዎች አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ ጠይቀዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ቤለኒ ስዩም ሰሞኑን በሰጡት መግለጫም፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለትግራይ ክልል የሰጡትን ትኩረት ለአማራና ለአፋር ክልል ተጎጂዎች እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በተቆጣጠሯቸው የሰሜን ወሎ ዞንና የዋግ ኸምራ አካባቢዎች ይኖሩ ከነበሩ ወገኖች ጥቂቶቹ ዕድል ቀንቷቸው ደሴ በመድረስ በመጠለያ ካምፖች ውስጥ የገቡ ቢሆንም አብዛኛዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን አሁንም በህወኃት ቁጥጥር ስር በሆኑት አካባቢዎች ውስጥ እንዳሉና እነዚህ ወገኖች ስላሉባቸው ሁኔታዎች ለማወቅ የሚያስችል ምንም አይነት መንገድ እንደሌለ ተገልጿል፡፡


Read 22781 times