Monday, 20 September 2021 00:00

የ2021 ታላላቅ ማራቶኖች በሚቀጥሉት 7 ሳምንታት ይካሄዳሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 በ2020 እኤአ ላይ በኮቪድ 19 ሳቢያ ሳይካሄዱ የቀሩት የዓለማችን ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች በሚቀጥሉት ሰባት ሳምንታት በመላው ዓለም በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች ተከታትለው ይካሄዳሉ፡፡ መስከረም 16 ላይ  የበርሊን፤ መስከረም 23 ላይ የለንደን፤ መስከረም 30 ላይ የቺካጎ፤ ጥቅምት 1 ላይ የቦስተንና ጥቅምት 8 ላይ የኒውዮርክ ማራቶኖች  እንደቅደም ተከተላቸው ይከናወናሉ፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው በታላላቆቹ ማራቶኖች ላይ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቶች፤ ለሽልማት የቀረቡት ገንዘቦች እና ተያያዥ ሁኔታዎች ናቸው፡፡  
በ47ኛው የበርሊን ማራቶን
ከ39ሺ በላይ ተሳታፊዎችን የሚያስተናግደው የበርሊን ማራቶን ለ47ኛ ጊዜ ሲካሄድ ለሽልማት የቀረበው ከ270ሺ ዶላር በላይ ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች 47ሺ ዶላር በነፍስ ወከፍ ሽልማት እንደሚያገኙ እና የዓለም ሪከርድ ለሚያስመዘግቡ ከ58ሺ ዶላር በላይ ቦነስ ቀርቧል፡፡ በበርሊን ማራቶን ላይ ከፍተኛውን ትኩረት የሳበው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ለ4ኛ ጊዜ በሚያደርገው ተሳትፎ  ሲሆን የዓለም የማራቶን ሪከርድን ለማሻሻል የመጨረሻውን ሙከራ እንደሚያደርግ ተወስቷል፡፡ ቀነኒሳ በሮጠባቸው 3 የበርሊን ማራቶኖች ላይ  በ2016 እና በ2019 ላይ ሲያሸንፍ የዓለምን የማራቶን ሪከርድ እንደ ቅደም ተከተላቸው በ6  ሰከንዶች እና በ2 ሰከንዶች ልዩነት ከመስበር ስቷቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በ2017 ደግሞ ውድድሩን ሳይጨርስ አቋርጦ ወጥቷል፡፡ በ39 ዓመቱ የበርሊን ማራቶንን የሚሮጠው ቀነኒሳ በ2 ሰዓት ከ01 ደቂቃ ከ41 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ የዓለማችንን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት እንደያዘ ይታወቃል፡፡
ከቀነኒሳ ባሻገር በበርሊን ማራቶን ላይ በወንዶች ምድብ የሚሮጡት ጉዮ አዶላ (2፡03፡46) እና አሊካ አዱኛ (2፡06፡15) ሲሆኑ በሴቶች ምድብ ደግሞ ህይወት ገብረኪዳን (2፡19፡35)  ፤ ሹራ ደምሴ (2፡20፡59) እና አማኔ በሪሶ ይሳተፋሉ፡፡ ህይወት ገብረኪዳን ከ6 ወራት በፊት በሚላን ማራቶን የግሏን ምርጥ ሰዓት እና የዓመቱን ፈጣን ሰዓት  2፡19፡35 በሆነ ጊዜ ማስመዝገቧ ተጠባቂ አድርጓታል፡፡
በ41ኛው የለንደን ማራቶን
41ኛው የለንደን ማራቶን መስከረም 23 ላይ  ሲካሄድ ከመደበኛው  ወቅት በ6 ወራት ተሸጋሽጎ ሲሆን ከ40ሺ ላይ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩት የሚጠበቅ ነው፡፡ የውድድሩ አዘጋጆች ለሽልማት የሚያቀርቡትን ገንዘብ በኮቪድ 19 ተፅእኖ በግማሽ በመቀነስ በድምሩ 158ሺ ዶላር እንዳዘጋጁ፤  በሁለቱም ፆታዎች  ለሚያሸንፉት 30 ሺ ዶላር እንደሚበረከትና የቦታውን ክብረወሰን በማስመዝገብ 20ሺ ዶላር ቦነስ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ ከፍተኛ ፉክክር በሁለቱም ፆታዎች እንደሚያጋጥምበት በሚጠበቀው የለንደን ማራቶን 11 የኢትዮጵያ አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ በወንዶች ምድብ  ሹራ ኪታታ (2፡04፡49)፤ ብርሃኑ ለገሰ (2፡02፡48)፤ ሞስነት ገረመው (2፡02፡55)፤ ሙሌ ዋሲሁን (2፡03፡16)፤ ሲሳይ ለማ (2፡03፡36)   እና እንዴ አትላው (2፡03፡51)  ሲሆኑ በሴቶች ምድብ ደግሞ ሮዛ ደረጀ (2፡18፡38)፤ ብርሃኔ ዲባባ(2፡18፡35)፤ ደጊቱ አዝመራው (2፡19፡26)፤ ዘይነባ ይመር (2፡19፡28)  እና ትግስት ግርማ (2፡19፡52)  ናቸው፡፡
በለንደን ማራቶን ላይ የአሸናፊነት ክብሩን ለመመለስ የሚፈልገው ሹራ ኪታታ በተሳትፎው ዙርያ የመጀመርያ አስተያየቱ ቶኪዮ ኦሎምፒክን በተመለከተ ሲሆን ‹‹በኦሎምፒክ መድረክ ውድድር አቋርጬ መውጣቴ አበሳጭቶኛል፡፡ ከአየር ሁኔታው ጋር ለመላመድ ከብዶኝ ነበር። በኦሎምፒኩ ወቅት ከአዲስ አበባ ከቀዝቃዛ አየር ተነስተን ነበር የሄድነው፤ የቶኪዮን ሞቃታማ አየር ለመቋቋም አልቻልኩም፤ መተንፈስ ሁሉ አስቸግሮኝ ነበር፡፡›› ብሏል፡፡ ሹራ በለንደን ማራቶን ተሳትፎ የሚያደርገው ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን በ2018 ላይ ኪፕቾጌን ተከትሎ በመግባት ሁለተኛ ደረጃ እንዳገኘ እና በ2020 እኤአ ላይ ኪፕቾጌን አስከትሎ በመግባት ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ በ2021 የለንደን ማራቶን  ተሳትፎው ላይ በሰጠው አስተያየት  ‹‹ለንደን ላይ በሙሉ ጤንነት ለመሮጥ  ከአሰልጣኜ ጋር በመሆን ብቁ ዝግጅት አድርጊያለሁ፡፡ በድጋሚ ለማሸነፍም እፈልጋለሁ›› ሲልም ተናግሯል፡፡
በ43ኛው የቺካጎ ማራቶን
በ2019 እኤአ ላይ በኮቪድ ሳቢያ የተሰረዘው የቺካጎ ማራቶን መስከረም 30 ላይ ከ44ሺ በላይ ተሳታፊዎችን በማግኘት ለ43ኛ ጊዜ ሲካሄድ በድምሩ 708ሺ ዶላር የሽልማት ገንዘብ የቀረበበት ሲሆን፤ በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉት 100ሺ ዶላር እንደሚበረከት ታውቋል፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቶች በዚህ ማራቶን ላይ ዘንድሮ ከፍተኛውን ትኩረት የወሰደው 2፡03፡34 በሆነ ጊዜ የግሉን ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበው  ጌታነህ ሞላ ሲሆን ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን  ሰይፉ ቱራ (2፡04፡33)፤ ሽፈራ ታምሩ  (2፡05፡18)  እና ፍቅሬ በቀለ (2፡06፡27)  ናቸው፡፡ በሴቶች ምድብ ከኢትዮጵያ አትሌቶች ማን እንደሚሳተፍ አልተገለፀም፡፡ ዘንድሮ በቺካጎ ማራቶን ላይ ውጤታማ እንደሚሆን ከፍተኛ ግምት የተሰጠው በ2017 እኤአ ላይ ለማሸነፍ የበቃው እና በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ8ኛ ደረጃ ጥሩ ውጤት ያስመዘገበው አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ (2፡11፡41)  ነው፡፡
በ125ኛው የቦስተን ማራቶን
በአንጋፋነቱ የሚታወቀው የቦስተን ማራቶን ዘንድሮ ለ125ኛ ጊዜ  ሲካሄድ ከ32ሺ በላይ ተሳታፊዎችን በመግኘት ለሽልማት የቀረበው ገንዘብ ከ876ሺ ዶላር በላይ ነው።   በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉት አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 150ሺ ዶላር እንደሚበረከትም ታውቋል፡፡ 10 የኢትዮጵያ አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ በወንዶች ምድብ አሰፋ መንግስቴ (2፡04፡06)፤ ለሚ ብርሃኑ (2፡04፡33)፤ ሌሊሳ ዴሲሳ (2፡04፡45)፤ ደጀኔ ደበላ (2፡05፡46)  እና ፅናት አያና (2፡06፡18)፤  እንዲሁም በሴቶች ደግሞ ያበሩኛል መለሰ (2፡19፡36)፤ ማሬ ዲባባ(2፡19፡52)፤ ወርቅነሽ አዴሳ (2፡20፡24)፤ ሱቱሜ ከበደ (2፡20፡30)  እና አፀደ ባይሳ (2፡22፡03)  ናቸው። በቦስተን ማራቶን ታሪክ የኢትዮጵያ አትሌቶች 14 ድሎችን 8 ጊዜ በሴቶች 6 ጊዜ በወንዶች ያስመዘገቡ ሲሆን በወንዶች በ2013 እና በ2015 ያሸነፈው ሌሊሳ ዴሲሳ እና በ2016 ያሸነፈው ለሚ ብርሃኑ ዘንድሮም ውጤታማ እንደሚሆኑ ተጠብቀዋል፡፡ በሴቶች ምድብ ከ2 ሰዓት ከ22 ደቂቃዎች በታች የገቡ 9 ምርጥ አትሌቶች መወዳደራቸው ከፍተኛ ፉክክር እንደሚፈጥር የተነገረ ሲሆን በሪዮ 2016 ኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችው ማሬ ዲባባ ልዩ ግምት ተሰጥቷታል፡፡
በ50ኛው የኒውዮርክ ማራቶን
ጥቅምት 28 ላይ በሚካሄደው 50ኛው የኒውዮርክ ማራቶን ላይ 33ሺ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩት የተገለፀ ሲሆን ለሽልማት የተዘጋጀው ገንዘብ ባይገለፅም ከ2 ዓመት በፊት በድምሩ የቀረበው ከ682ሺ ዶላር በላይ እንደሆነና በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉት 100ሺ ዶላር የሚበረከትበት ነው፡፡  ቀነኒሳ በቀለ የበርሊን ማራቶንን ከሮጠ ከ42 ቀናት በኋላ ሁለተኛ የማራቶን ውድድሩን ኒውዮርክ ላይ ማድረጉ ከፍተኛ ትኩረት አስገኝቷል፡፡ ቀነኒሳ በኒውዮርክ ማራቶን ላይ የሚሳተፈው በሩጫ ታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን፤ በ2019 ላይ ሶስተኛ ደረጃ ያገኘው እና በኒውዮርክ ማራቶን አዘጋጆች በ2020 ምርጥ የማራቶን ሯጭ ሆኖ የተመረጠው ግርማ በቀለ ገብሬ (2፡03፡38)   እና በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ የብር ሜዳልያ ያገኘው እና ለሆላንድ የሚሮጠው አብዲ ነገየ (2፡09፡58)  ዋንኛ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ የተጠበቁት ናቸው፡፡ በቀነኒሳ በቀለ የኒውዮርክ ማራቶን ተሳትፎ ላይ ማናጀሩ ጆስ ሄርማንስ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት  የተሳትፎ ክፍያ እና ሽልማቶችን ስላጓጉት አለመሰለፉን ጠቁመው የኒውዮርክ ማራቶን የመሮጫ ጎዳና በአገር አቋራጭ ከፍተኛ ስኬት ላለው አትሌት የሚመች በመሆኑ ከበርሊን በኋላ ሁለተኛ ማራቶን በመሮጥ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግበትን ሊፈጥርለት እንደሚችል አብራርተዋል፡፡ ሄርመንስ  ተጨማሪ አስተያየት ሲሰጡ ‹‹እንደሱ ብቃት ባለው ሰው  ማንኛውም ነገር ሊከናወን ይችላል... ሞተሩ አሁንም በጣም አስደናቂ ነው። ሳንባና ልቡም እንደ ፌራሪ ናቸው።›› ብለዋል። በሴቶች ምድብ ኢትዮጵያን በመወከል የኒውዮርክ ማራቶንን የሚሳተፉት ሩቲ አጋ (2፡18፡34)  እና አባቤል የሻነህ (2፡20፡51)  ናቸው፡፡
የመሮጫ ጫማዎች ጉዳይ
ባለፉት 5 የውድድር ዘመናት በዓለም አትሌቲክስ ከመሮጫ ጫማዎች በቴክኖሎጂ መዳበር ጋር በተገናኘ አወዛጋቢ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ቆይተዋል፡፡ ከሰሞኑ  ደግሞ በቪዬና ማራቶን ላይ ኢትዮጵያዊው አትሌት ደራራ ደሳለኝ ሁሪሳ ካሸነፈ በኋላ ውጤቱ በውድድሩ አዘጋጆች የተሰረዘበት ሁኔታ የመሮጫ ጫማዎችን አከራካሪነት እንዲያገረሽ አድርጎታል፡፡  አትሌት ደራራ  በቪዬና ማራቶን ላይ አድርጎት የሮጠበት የአዲዳስ የመሮጫ ጫማ የነበረው የሶል ውፍረት 5 ሴሜ ሲሆን ይህም በዓለም አትሌቲክስ ፈቃድ ካገኘው ውፍረት በ1 ሴሜ የጨመረ ሆኖ መገኘቱ ያገኘውን ውጤት አስነጥቆታል፡፡ በውድድሩ አዘጋጆች አሸናፊነቱ እንዲሰረዝ እና ለአሸናፊነት የሚሰጠውን 10ሺ ዩሮ እንዲያጣም ምክንያት ሆኖበታል፡፡
የመሮጫ ጫማዎችን ህጋዊነት በማጽደቅ አይነታቸውና ዝርዝራቸውን ከዓመት በፊት ይፋ ያደረገው የዓለም አትሌቲክስ ማህበር፤ አትሌቶች እና ተወካዮቻቸው በዓለም  አቀፍ ውድድሮች  ስለሚጠቀሙት ጫማ ዝርዝር መረጃዎችና ሁኔታዎችን ማሳወቅ እና ፍቃድ ማግኘት እንደሚኖርባቸው አሳስቧል፡፡ በዎርልድ አትሌቲክስ የውድድር ደንብ RULE 5 መሰረት የውድድር አዘጋጆች እና ዳኞቻቸው አትሌቶች በተወዳደሩበት ጫማ ላይ ጥርጣሬ ካላቸው የመሮጫ ጫማዎችን ከአትሌቱ እግር ላይ አስወልቀው በመመርመር ውጤት የማፅደቅ ወይም የመሰረዝ መብት እንዳላቸውም ተገልጿል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ በስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች ላይ አስፈላጊውን ደንብ እና ቁጥጥር ለማድረግ የተገደደው በ2016 እኤአ ላይ የአሜሪካው ናይኪ ኩባንያ የአትሌቶቹን የመሮጥ ብቃት በ4 በመቶ ያሳድጋል ያለውን የጫማ ምርት ካስተዋወቀ በኋላ ነው፡፡ ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሌሎችም ታላላቅ ኩባንያዎች የየራሳቸውን ምርት በማቅረብ ወደ ገበያ በመግባታቸው ‹‹ቴክኖሎጂ ዶፒንግ ›› በሚል ስያሜ የተፈጠረውን ክርክር ፈጥሯል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር የመሮጫ ጫማዎች በቴክኖሎጂ መራቀቅ በዓለም አትሌቲክስ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለማብረድ ህጎችን ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡
በ1960ዎቹ ባሕላዊው መንገድ በመከተል የሚነጠፉ የመሮጫ ትራኮች እንደስፖንጅ በሚያነጥሩ ሰው ሠራሽ ወለሎች መተካታቸው  ፅናትን በሚጠይቁ የረጅም ርቀት ሩጫ ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ለውጦችን አስከትለዋል። የረጅም ርቀት ላይ  ሯጮች በቴክኖሎጂ ድጋፍ በተሰናዱት  የመሮጫ ትራኮች ላይ  በርካታ የዓለም ሪከርዶችን በየውድድር መደቡ ሊያስመዘግቡም በቅተዋል።  ባለፉት 5 የውድድር ዘመናት ደግሞ በትራክ እና በጎዳና ላይ የረጅም ርቀት ሩጫ ውድድሮች ከፍተኛ ለውጥ እየፈጠሩ የሚገኙት በቴክኖሎጂ የተራቁት የመሮጫ ጫማዎች ሆነዋል፡፡
ከ2016 እስከ 2020 በነበሩት 4 የውድድር ዘመናት በትራክና በጎዳና ላይ በዓለም አትሌቲክስ ከ5ኪሜትር እስከ ማራቶን በተካሄዱ ውድድሮች ከ17 በላይ የዓለም ክብረወሰኖች የተሻሻሉ ሲሆን ከእነሱም መካከል 14 ድሎች super shoes የተባሉትን የመሮጫ ጫማዎች ባደረጉ አትሌቶች መመዝገባቸው ይታወቃል፡፡Read 11523 times