Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 13:32

አቶ ሃይለማርያም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ይሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የስልጣን ክፍተትና አለመረጋጋት እንዳይፈጠር የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሹመት ከሁለት ሳምንት በፊት በፓርላማ እንዲፀድቅ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፤ የአገሪቱን መረጋጋትና የህዝቡን ስሜት በማየት እንዲሁም የፕሮቶኮልና የአሰራር ደንቦችን ለማሟላት ሲባል ወደ መጪዎቹ ሳምንታት እንደተሸጋገረ ምንጮች ገለፁ።የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወትን በተመለከተ የመጀመሪያ መግለጫ በተሰጠበት ማክሰኞ እለት፤ በህገመንግስቱ መሰረት ምክትል ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ መንግስትን የመምራት ሃላፊነቶችን በሙሉ እንደተረከቡ መገለፁ ይታወሳል። የሚቀር ነገር ቢኖር፤ የክረምት እረፍት ላይ የሚገኘው ፓርላማ ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሹመት ማፅደቅ እንደሆነም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር በረከት ስምኦን በእለቱ ተናግረዋል። የአቶ በረከት መግለጫ ሁለት አላማዎች እንደነበሩት የሚገልፁ ምንጮች፤ ሁሉም ነገር በህገመንግስቱ መሰረት እንደሚቀጥል መተማመኛ መስጠት አንዱ አላማ ሲሆን፤ የስልጣን ክፍተትና ሽኩቻ እንደማይኖር ማረጋገጫ በመስጠት አለመረጋጋት እንዳይፈጠር በር መዝጋት ሁለተኛው አላማ ነበር ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት በፍጥነት እንዲፀድቅ ታስቦ እንደነበር የሚገልፁት ምንጮች፤ ሃሙስ ነሐሴ 17 ቀን የፓርላማ አባላት ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርተው እንደነበር ይጠቅሳሉ።

በእለቱ የአቡነ ጳውሎስ የቀብር ስነስርዓት በሚፈፀምበት የቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን አጠገብ በሚገኘው ፓርላማ ውስጥ ስብሰባውን ማካሄድ አመቺ ስላልነበረ ለአርብ ቀን መተላለፉንም ያስታውሳሉ ምንጮቹ። ይሁንና አርብ ነሐሴ 18 ቀን በተካሄደው የፓርላማ ስብሰባ የጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት ጉዳይ አልተነሳም፤ የህሊና ፀሎት በማካሄድና የሃዘን መግለጫ በማውጣት ስብሰባው ተጠናቋል። እንደምንጮቹ አባባል፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት በፍጥነት ለማፅደቅ የሚገፋፋ ነገር አለመኖሩ በመረጋገጡና የአሰራር ደንቦችን ለማሟላት በመመረጡ ነው። ከማክሰኞ ነሐሴ 15 ጀምሮ በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረው የሃዘን ስሜት ከፍተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ የአለመረጋጋት ፍንጭ አለመታየቱ፤ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር በፍጥነት የመሾም ጉዳይ ቸል እንዲባል አስተዋፅኦ አድርጓል ይላሉ ምንጮቹ። የተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት አጣዳፊ ጉዳይ እንዳልሆነ በመንግስት ቃል አቀባይ በኩል የተገለፀው በዚሁ ወቅት እንደነበር ምንጮቹ ጠቅሰው፤ ይሁንና ምንም አይነት ሽኩቻና የስልጣን ክፍተት እንደማይፈጠር የመንግስት ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ በድጋሚ መናገራቸውን ያስታውሳሉ። የስልጣን ሽግግርና የመተካካት ጉዳይ፤ ከአንድ አመት በፊት ያለቀለትና የተወሰነ ጉዳይ ስለሆነ አንዳችም ክፍተት አይፈጠርም በማለት ነበር የመንግስት ቃል አቀባይ የተናገሩት። ከዚህም በተጨማሪ፤ ከቀብር በፊት የተተኪ ሹመት ማፅደቅ ኦፊሴላዊ አሰራርን (ፕሮቶኮልን) ሊያጓድል ይችላል የሚል ጥያቄ ተነስቶ እንደነበር የገለፁት ምንጮች፤ ሹመቱን ማዘግየት የፓርቲ የአሰራር ደንብንም ለማሟላት ጠቅሟል ብለዋል። በፓርላማው አሰራር ደንብ መሰረት፤ ብዙ ወንበር የያዘው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ነው ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩ የሚያቀርበው። በኢህአዴግ አሰራር ደግሞ፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ነው ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በእጩነት የሚቀርበው። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመጪው ምርጫ እንደማይሳተፉና ከስልጣን እንደሚወርዱ በተናገሩበት ወቅት፤ በፓርቲ ሊቀመንበርነታቸውስ ይቀጥሉ እንደሆነ መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን፤ እንደማይቀጥሉ የገለፁትም በዚህ ምክንያት እንደነበር ምንጮቹ ገልፀዋል። ኢህአዴግ በፓርላማ ብዙ መቀመጫዎችን እስከያዘ ድረስ፤ የፓርቲው ሊቀመንበር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል በማለት አቶ መለስ በሰጡት ምላሽ፤ ፓርላሜንታዊ ስርዓት በሚከተሉ አገራት ውስጥ የሚታየው አሰራርም ተመሳሳይ መሆኑን ጠቅሰው ነበር። በእነዚህ የፓርላማና የፓርቲው አሰራሮች መሰረት፤ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትርን ለሹመት ከማቅረብ በፊት የፓርቲው ተተኪ ሊቀመንበርን መሰየም ይቀድማል ብለዋል ምንጮቹ።36 መሪዎችን የያዘው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ እለት ከተሰበሰበ በኋላ በማግስቱ ባሰራጨው መግለጫ፤ በመስከረም የመጀመሪያው ሳምንት 60 አባላትን የያዘው የኢህአዴግ ምክር ቤት እንደሚሰበሰብ ጠቅሶ፤ ሊቀመንበርና ሌሎች የሚጓደሉ አመራሮችን ይመርጣል ብሏል። ካሁን ቀደም እንደተሰጡት መግለጫዎች ሁሉ፤ የስራ አስፈፃሚ መግለጫም አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የፓርቲው ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ምንጮቹ ያስረዳሉ። ሌላ ሰው በሊቀመንበርነት ለመሰየም ቢታሰብ ኖሮ፤ ሌላ የሚጓደል አመራር አይኖርም ነበር የሚሉት እነዚሁ ምንጮች፤ አቶ ሃይለማርያም የሊቀመንበርነቱን ቦታ እንዲይዙ ሲደረግ ግን፤ በእሳቸው ተይዞ የነበረው የምክትል ሊቀመንበርነት ቦታ ስለሚጓደል ተተኪ ያስፈልገዋል ብለዋል።አቶ ሃይለማርያም፤ ከ1993 ዓ.ም በኋላ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፤ ከ1998 ዓ.ም በኋላ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አማካሪና በፓርላማ የመንግስት ዋና ተጠሪ በመሆን ሰርተዋል። ከ2003 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ፤ ይዘውት ለነበረው የምክትልነትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ ሌላ ተተኪ ይሾምለታል።

 

 

 

Read 46248 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 13:45