Tuesday, 21 September 2021 00:00

ከተማ፣… የሕግና ሥርዓት መነሃሪያ፣ ወይም የወንጀልና የትርምስ ዓውድማ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

ከፅሁፍ እና ከጋሪ ጋር፣ የዛሬ 5 ሺ ዓመት ገደማ የተከሰተው ትልቅ የሰው ልጅ ታሪክ፣ “ከተማ” የተሰኘው አዲስ የአኗኗር ቴክኖሎጂ ነው። የቴክኖሎጂ ነገር፣ በአዲስነቱ ዘመን፣ ገና የተፈጠረ ጊዜ፣ እንደ ልዩ ተዓምር፣ “ጉድ” ያሰኛል። እንደ ምትሃት ያስደንቃል ወይም በፍርሃት ያስበረግጋል። ሲኒማ ቤትን የሰይጣን ቤት ብለው ሲጠሩት አልነበር? መኪናም የሰይጣን ሰረገላ ተብሎ ነበር። ለጥቂት ጊዜ ከተላመድነው በኋላ ግን፣ እንደ ተፈጥሮ ክስተት፣ “አሁንም ያለ ድሮም የነበረ” ሆኖ ይሰማናል።
ተራራና ሸለቆ ከወዲህና ከወዲያ ማዶ ስንመለከት፣ “መቼ ተሰራ?” የሚል ጥያቄ አይመጣልንም። ከተማም፣ በጣም ስለተላመድነው፣ ከተራራ ጋር አብሮ የተፈጠረ እንጂ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ አይመስለንም። አንዳንዴ ብልጭ ካላለልን በቀር፣ ጋራና ሸንተረሩ ይቅርና፣ ጫካውና በረሃው፣ ወንዙና ሃይቁ ይቅርና፣… ከተማና መንደር ጭምር፣ ነባርና ኗሪ፣ የጥንቱ የዘላለሙ ተፈጥሯዊ ክስተቶች ይመስላሉና። እንደ ወፍ ዘራሽ እፀዋት ይሆንብናል - የከተማ አኗኗር።
ነገር ግን፣ የሰው ልጅን ታሪክ የቀየረ፣ ከማረሻና ከመጥረቢያ፣ ከማጭድና ከቀስት፣ ከምድጃና ከጋሪ ቴክኖሎጂዎች ጎን ለጎን፤ ከፅሁፍና ከመዝገብ፣ ከፊደልና ከቁጥር፣ ከቀመርና ከስሌት፣ ከፊርማና ከማህተም ጋር የመጣ አዲስ ፈጠራ ነው - የከተማ አኗኗር።
ምንም እንኳ የሃሳብና የተግባር መሳሪያዎች (ፅሁፍ እና ጋሪ) የሰውን ኑሮ የሚያሻሽሉ፣ ጉልበትንና ጊዜን የሚቆጥቡ፣ እውቀትንና ምርትን የሚያበረክቱ ቢሆኑም፤ ከከተማ ጋር ነው የሚሳለጡት። የእውቀትና የሙያ መስክ፣ የትምህርትና የምርት ግብይት ከሌለ፣… ሁሉም ሰው በሁሉም መስክ አዋቂና  የተዋጣለት ባለሙያ መሆን አይችልም። አዎ፤ብዙ አይነት እውቀትና ስራ ይኖረዋል። ነገር ግን፣ ጥልቀትና ምጥቀት፤ ሙያና ጥበብ ግን አይኖረውም።
በከተማ አኗኗር ግን፣ እያንዳንዱ ሰው፣ በተወሰነ የእውቀትና የስራ መስክ ላይ ብቻ በማተኮር፣ እጅግ የመጠቀና የጠለቀ እውቀትን የሚያዳብር ልሒቅ እና ጥበበኛ የመሆን እድል ይኖረዋል። እጅግ የተካነ ሙያተኛም መሆን ይችላል። ይሄ፣ የከተማ በረከት ነው። “Division of Labour” በማለት አዳም ስሚዝ መጠሪያ ስም ያወጣለት በከንቱ አይደለም። ከከተማ ጋር አብሮ የተፈጠረው የሙያ ክፍፍልና “አደረጃጀት”፣ የሰዎችን ምርታማነት በእጥፍ ድርብ ብቻ ሳይሆን በአስር እጥፍ የሚያሳድግ ተዓምረኛ ዘዴ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። በየሙያው ብዙ እያመረተ ይገበያያል - “ገበያ” የኑሮ ምሶሶና ማገር ይሆናል። ስልጣኔና ብልፅግናማ ያለ ገበያ አይታሰብም። ይሄም ከከተማ ጋር አብሮ የሚስፋፋ “አደረጃጀት” ነው።
አንዱ የእንጨት ባለሙያ አናጢ፣ ሌላኛውም ጠራቢ፣ ግንበኛ፣ አንጣሪ ወይም ሸክላ ሰሪ፣ መድሃኒት ቀማሚ ወይም እንስሳት አርቢ፣ የስንዴ ገበሬ ወይም ቡና አብቃይ፣ ባለጋሪ ወይም ፊደል አስተማሪ… አዝማሪ ወይም ዳቦ ጋጋሪ፣ ሸማኔ ወይም ሻማ ሰሪ፣ እያንዳንዱ ሰው በየሙያው ላይ ብቻ አተኩሮ የሚሰራው፤ በሁለት ነገሮች ተማምኖ ነው። አንደኛ ነገር፣ በየሙያው ላይ ካተኮረ፣ ብዙ እንደሚያመርት ይጠብቃል-በሙያው ይተማመናል።
ሁለተኛ ነገር፣ ካመረተው ውስጥ ከፊሉን መሸጥና ለኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን መግዛት እንደሚችል ያስባል - በገበያ ይተማመናል።
በእርግጥ፣ “ከተማ” እንዲሁ ለብቻው ተነጥሎ ከምድር አይበቅልም። ከሰማይ አይወርድም። ቦታውና አካባቢው፣ ውሃና አየሩ፣ ተራራውና ሸለቆው፣ ወንዙና ባሕሩ፣ እርሻውና ደኑ፣… የየራሳቸው ድርሻ አላቸው-አንዳንዶቹ ለከተማ እድገት ያመቻሉ፤ አንዳንዶቹ ግን ይፈታተናሉ፤ መፈናፈኛ ያሳጣሉ።
“በበላይ አካል ብዙ ያልታሰበባቸው” ከተሞች፣ የገበያውን እንቅስቃሴና የአውራ መንገዱን አቅጣጫ ተከትለው እያቆጠቆጡ ያድጋሉ። “በበላይ አካል” በዘፈቀደ ውሳኔ “ማስተር ፕላን” የወጣላቸው ከተሞች ደግሞ፣ በባዶ ደንዝዘው ይቀራሉ።  ከምርትና ከንግድ ጋር የተዛመዱ ወይም ተቀራረቡ ከተሞች ያድጋሉ። ሌሎቹ ይቀነጭራሉ። ልዩነታቸው በግልፅ የሚታየው ግን ፣ ከጊዜ በኋላ ነው።
በአንድ ጀንበር መምጠቅና መዝቀጥ የለም። የብዙ ዓመት ስራ ናቸው - ከተሞች።
ይህ ማለት ግን፣ ድንገት የሚበቅሉ፣ ድንገት የሚጠፉ ከተሞች የሉም ማለት አይደለም።
አዎ፣ድንገት የሚበቅል ከተማ ማግኘት ይከብዳል። ግን አይጠፋም። ከነዳጅና ከወርቅ ማዕድን ቁፋሮ ጋር፣ በአሜሪካ ካሊፎርኒያና ቴክሳስ ውስጥ ከባዶ ሜዳ የተፈጠሩ ከተሞች አሉ። አምና ተወልደው ዘንድሮ ለአቅመ ከተማ እንደ መድረስ ቁጠሩት።
 ከሁሉም ከሁሉም ግን፣ ቻይናን የሚስተካከል “ከተማ አብቃይ” አገር ያለ አይመስልም። አንድ ደህና ፎቅ ለመስራት 10 ዓመት ቢፈጅ፣ አይገርምም። ቻይና ውስጥ ግን፣ በ10 ዓመት ውስጥ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ትልልቅ ከተሞች ተሰርተው ያልቃሉ።
ይታያችሁ ከአዲስ አበባ የሚሰፋ፣ ባለመቶ ፎቅ ህንፃ ጭምር የያዘ፣ ከ2 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን በምቾት የሚያኖር፣ የስራ፣ የመንገድ፣ የመዝናኛ፣… ትልቅ ሃብታም ከተማ ተገንብቶ ሲያልቅ አስቡት።
በእርግጥ ግንባታው ቢሳካ እንኳ፤ ነገሩ ተሟላ ማለት አይደለም። አንዳንዶቹ ከተሞች፣ ለበርካታ ዓመታት ያለ ነዋሪ ኦና ሆነው ክረምትና በጋ ይፈራረቅባቸዋል። የከተማ አብቃይ አገር ችግር ነው- ይሄ።
ድንገት የሚደርቁና የሚጠፉ ከተሞችስ?
በጎርፍ፣ በእሳተ ጎሞራ፣ በማዕበል ሳቢያ የወደሙ፣ በዚያም ጠፍተው የቀሩ ከተሞች አሉ። አብዛኞቹ የጠፉት ግን፣ በድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ አይደለም። በሰው እጅ ነው የጠፉት። በወረራና በጦርነት፣ ወይም በስልጣን ሽኩቻና በአመጽ ትርምስ ሳቢያ፣ ብዙ ከተሞች፣ እንዳልነበሩ ሆነዋል።
የዘመናችን የሶሪያና የየመን ከተሞችን ማየት ይቻላል።  አሌፓ እና ሆምስ፣ የሚሊዮኖች መኖሪያ ነበሩ። ይሄውና ዓለም ሁሉ እያየ፣ በጥቂት ዓመታት ጦርነት ከተሞቹ ፈራርሰዋል። በቁፋሮ የተገኙ የጥንት ፍርስራሾችና የከተማ ቅሪቶች ይመስላሉ።
ከአንድ ሺ እስከ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት፣ በግርማ ሞገሳቸው የሚያስደምሙ፣ የሶሪያና የየመን ጥንት ከተሞች፣ ለምን ያኔ ጥንት እንደፈራረሱና “ቅሪተ አካል” ሆነው እንደቀሩ ለመረዳት፣ ታሪካቸውን ከልብ ለማወቅ ይከብዳል።
ዛሬ በዘመናችን ግን፣ በካሜራ እየተቀረፀ፣ በቴሌቪዥንና በኢንተርኔት እለት በእለት እየተተረከ፣ ከተሞች በጦርነት እንዴት እንደሚወድሙ በአይናችን አየን። የጥንት ከተሞች በምን አይነት የጥፋት መዓት አፅማቸው ብቻ እንደቀረ ለመገንዘብ የፈለገ ሰው፣ ዛሬ በዘመናችን ከአይናችን ስር የሚፈራርሱትን ማየት ይችላል።
ባለ ሁለት አፍ ስለት ናቸው- ፅሁፎች፣ ማሽኖችና ከተሞች።
በከተሞች ላይ ለበርካታ ሺ ዓመታት የደረሰው የጥፋት መአት፣ በአጋጣሚ  የተከሰተ ጉዳይ አይደለም። ከከተሞች ተፈጥሮ ጋር የተቆራኘ ነው - አደጋው። ከተማ እና ከተሜነት፣ እንደሌሎቹ ዋና ዋና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች፣ ባለ ሁለት አፍ ስለት ነው።
ፅሁፍ አንዱ ዋና ፈጠራ ነው - የሃሳብ ቴክኖሎጂ። ከጥንታዊ የዋሻና የሃውልት፣ የሸክላና የብራና ፅሁፎች ጀምሮ፣ በአውሮፓ የሃይማኖት ጦርነቶችን ለማቀጣጠል ያገለገሉ የነጠላ ወረቀት (“ በራሪ ወረቀት”) ሕትመቶችን መጥቀስ ይቻላል። ከዚያ በኋላ የሳይንስ እውቀትን ለማስፋፋት የታተሙ መጻሕፍትንም አስታውሱ።
ከአሜሪካ የነፃነት አብዮት ጎን ለጎን የፈረንሳይ የሽብር አብዮትን አዳብሎ ማየትም ይቻላል- የጋዜጣ ሕትመቶች፣ ከፊሎቹ ነፃነትን ገሚሶቹ ሽብርን ለማንገስ ቀስቅሰዋል- በአሜሪካና በፈረንሳይ አብዮት ዘመን።
በአንድ በኩል እውነተኛ መረጃዎችን፣ በሌላ በኩል የአፈና ፕሮፓጋንዳንና የአመፅ ቅስቀሳን፤ በአንድ በኩል እውቀትንና ትምህርትን፣ በሌላ በኩል የኮሙኒዝም ጭፍን የዝርፊያ መፈክሮችን፣ የናዚ ጭፍን የዘረኝነትና የእልቂት ስብከቶችን ለማሰራጨትና ለማዛመት ውሏል - የፅሁፍ ቴክኖሎጂ።
ሌሎቹ የሃሳብ ቴክኖሎጂዎችም፣… እነ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ እነ ሞባይልና ኢንተርኔት፣… ለበጎም ለክፉም ነው አገልግሎታቸው። እንደገና ለማረጋገጥ ከፈለጋሁ፣ ፌስቡክንና ዩቱብን ለአፍታ ያህል ገለጥ ቃኘት  አድርጉ። እንደወትሮው፣ ለእውነተኛ መረጃና ለእውቀት ሊጠቅም የመቻሉ ያህል፤ ለሐሰትና ለጥላቻ፣ ለዛቻና ለጦርነት ቅስቀሳም ይውላል።
ቴክኖሎጂ፣ “መሳሪያ” ወይም  “ዘዴ” ነው። ለመገንባትም ለማፍረስም፣ ለሰላምም ለጦርነትም ይሰራል። ጥፋትንም ልማትንም ያሳልጣል - የሃሳብ ቴክኖሎጂ (የፅሁፍ፣ የድምጽና የምስል ቴክኖሎጂ)። የሁሉም ቴክኖሎጂዎች ተፈጥሮ እንደዚህ ነው- ባለሁለት አፍ ስለት።
እነጋሪ እና ተዛማጅ የተግባር ቴክኖሎጂዎችም፣ መሳሪያዎች ናቸው። ተግባርን አይመርጡም፤ ተግባርን ያሳልጣሉ እንጂ።
ማረሻና ጦር፣ ማጭድና ጎራዴ፣ ድልድይና መድፍ፣ ጋሪና ባሩድ… የተግባር ቴክኖሎጂ እንደመሆናቸው፣ አዝመራን እጥፍ ድርብ ለማበርከት፣ ኑሮን ለማደላደልና ለማለምለም፤ አልያም ዝርፊያ፣ በደልና ግድያን እጥፍ ድርብ ለማባዛት ያገለግላሉ።
እነ ከተማ እና ሌሎች የአኗኗር ቴክሎጂዎች ደግሞ፤ ልማቱን ይበልጥ ማምጠቅ፣ በዚያው ልክ ጥፋቱን ይባስ ማጦዝ ይችላሉ። ለማመን የሚያስቸግር የስልጣኔና የብልጽግና ተዓምረኛ ግስጋሴ፣ ያለከተሞች አይታሰብም።
ለማሰብ የሚዘገንን የእልቂትና የውድመት፣ የጥፋትና የመከራ መዓቶችም፣ ከተሞች በሌሉበት  ቦታና ዘመን አይኖርም።
ከተሞች፣ የቴክኖሎጂና የሃብት ክምችት ናቸው። ለጥፋት ዘመቻ ትልቅ አቅም ይሆናሉ፤ በዚያው ልክ ኢላማ ይሆናሉ። ብዙ ለማውደምና ብዙ ለመዝረፍ ለሚመኙ አጥፊዎች፣ ከከተሞች የሚበልጥ ትልቅ ኢላማ የለም። የልማት መሳሪያና የብልፅግና አቅም የመሆናቸው ያህል፣ የጥፋት መሳሪያና ኢላማ ናቸው።
የሕግና ስርኣት መነሃሪያ፣ አልያም የወንጀልና የትርምስ ዓውድማ መሆን ይችላሉ - ከተሞች።
በአጭሩ፤ ከፅሁፍ እስከ ኢንተርኔት፣ ሁሉም የሃሳብ ቴክኖሎጂዎች፣ “ሃሳብን አይመርጡም”፤ ማንኛውንም ሃሳብ ለማሰራጨትና ለማዛመት የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ናቸውና።
ከጋሪ እስከ መንኮራኩር፣ ከማረሻ እስከ ሚሳየል፣ የተግባር ቴክኖሎጂዎች፣ በራሳቸው ጊዜ “ተግባርን አይመርጡም”። ማንኛውንም ተግባር፣ ልማቱንም ጥፋቱንም ለማፋጠንና ለማባዛት የሚያስችሉ መሳሪዎች ናቸው።
ከመንደርና ሰፈር፣ እስከ ማህበርና ከተማ፣ ሁሉም የአኗኗርና የአደረጃጀት ዘዴዎች (ቴክኖሎጂዎች) ጥሩና መጥፎ አኗኗርን አይመርጡም። ኑሮን በስፋት ለመገንባት፣ አልያም ኑሮን በሰፊው ለማመሳቀልና ለማፈናቀል፤ ለክፉም ለደጉም የሚገለግሉ የተከማቹ መሳሪያዎች ናቸው- ከተሞች።

Read 2671 times